የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ይፋ እንዳደረጉት እሳቸው የሚመሩት ተቋም ካሁን በሁዋላ ንብረትነቱ የህወሃት ከሆነው አልሜዳ ጨርቃጨርቅ የሚቀርብለትን የድንብ ልብስ መጠቀሙን አቁሟል። ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ አዲስ የደንብ ልብስ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል። ይህንን ተከትሎ አልሜዳ ወደፊት ምን ሊገጥመው ይችል ይሆን? የሚለው ጉዳይ እያነጋገረ ነው።
አልሜዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አድዋ የሚገኝ የህዋሃት ኩባንያ ሲሆን በኢትዮጵያ በግዙፍነቱ ግንባርቀደም የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ንብረት ነው። ፋብሪካው ለጊዜው በውል ላልታወቁ ዓመታት ግምታቸው 1.4 ሚሊዮን ለሚሆኑ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሲቪል ሰራተኞች፣ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ሰራተኞች፣በየክልሉ ላሉ የፈጥኖ ደራሽ፣ ልዩ ሀይልና መደበኛ ፖሊስ፣ እንዲሁም ለፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ፖሊሶችና ሠራተኞች የደንብ ልብስ በብቸኛነት ያመርታል።
ከላይ የተዘረዘሩት ተቋማት በሙሉ በአገርና በክልል ደረጃ ውል ገብተው ግዢ የሚፈጽሙት ያለ አንዳች ጨረታ ከአልሜዳ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል። ዜናው ከተሰማ ወዲህ በገበያ እጦት ሰራተኛ እየቀነሱና ለኪሳራ ተዳረጉ የሚባሉት አንጋፋ የመንግስት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እድሉን ለምን ተነፈጉ የሚለው ጥያቄ የበርካቶች ነበር።
ቀድሞ የአቶ በረከት ምክትል በመሆን በመንግስት የኮሙኒኬሽን ሚንስትር ዳኤታ የነበረው ኤርሚያስ ለገሰ ” የመለስ ልቃቂት” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሃፉ፣ “አቃቂ ጨርቃጨቅ ፣ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ በርካታ ሰራተኞችን ሲቀንሱ የአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እየተስፋፋ ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የወታደሮችና ፖሊሶች አልባሳት ኮንትራት ከአቃቂና አርባ ምንጭ ተቀምቶ ለአልመዳ በብቸኝነት ስለተሰጠ ነው” በማለት አሜሪካ እንደገባ የሚያውቀውን መስክሮ ነበር።
አፍሪካ ቢዝነስ የሚባለው የንግድ ማስተዋወቂያ ድረገጽ እንዳለው አልሜዳ የኤፈርት አንድ እህት ኩባንያ፣ ከኢትዮጵያ ግዙፍ፣ 100 ሚሊዮን የሽያጭ አውድ ያለው፣ በ94 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የተገነባ፣ በወቅቱ ድረገጹ ከካምፓኒው ባገኘው መረጃ መሰረት 2500 ሰራተኞች ያሉት፣ የድርጅቱን ሃብት ማላቅ ዋና ተልዕኮ ያነገበ ነው።
ይህ ግዙፍ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አፈጣጠሩ ከሃሜት የጸዳ ባያደርገውም፣ ዘመናዊ መሆኑ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ማቀዱ፣ ለክልሉ ተወላጆች የስራ እድል መፍጠሩና ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ለአገር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ይሆናል በሚል ታሳቢ በይሁንታ የሚታይ እንደሆነ የሰከኑ አስተያየት ሰጪዎች በተለያየ ውቅት ከቅሬታቸው ጎን ለጎን የሚያነሱት ጉዳይ ነው።
ሰሞኑን ይፋ ይሁን እንጂ ዛጎል ከወራት በፊት መንግስት የጸጥታ ሃይሉን የደንብ ልብስ የመቀየር ዓላማ እንዳለው ጥቆማ ሰጥታ ነበር። መንግስት ወደዚህ ውሳኔ ሲሄድ የደንብ ልብሱን ከአገር ውስጥ ያስመርት ወይም ከውጭ ያስመጣው ይፋ ባይሆንም ከአልሜዳ ጋር የገቡት ውል ያከተመ ይመስላል።
ለዚህ ውሳኔ መነሻው መንግስትን በትጥቅ ትግል እናስወግዳለን የሚሉ ሃይሎች ከመከላከያና ከፌደራል ፖሊስ ጋር የሚመሳሰል የደንብ ልብስ መልበሳቸው፣ ይህንኑ የደንብ ልብስ በመልበስ ከአንድ አገር የመከላከያ ሰራዊት በማይጠበቅ መልኩ ለእይታ የማይመች ተግባር በፊልም እየተቀረጸ በሚዲያና በማህበራዊ ገጾች መሰራጨቱ፣ ከሁሉም በላይ በየጊዜው አዳዲስ ትጥቅ የሚኩላቸው ወገኖች / የህወሃትን አመራር/ ማለት ነው ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ንግግር ቢደረገም ሰሚ በማታቱ የተነሳ ስለመሆኑ የኮሚሽነር ጀነራሉ ንግግር ያሳብቃል።
አሁን ጥያቄው በሚሊዮን ለሚቆተሩት የአገር የጸጥታ አካላትና የክልል ሃይሎች የደንብ ልብስ የሚያቀርበው የአልሜዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ይህንን ያክል ገበያ ሲያጣ የሚገጥመው የገበያ መናጋት ነው። የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎ ፋብሪካውም ይሁን ህወሃት በግልጽ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ውሳኔው ብስጭት እንደፈጠረ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ለዛጎል ተናግረዋል።
በድርጅቱና በፖለቲካ አመራሩ የንግድ ጨዋነትን ማጓደል የተነሳ ይህ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሰራተኞችን የያዘው ፋብሪካ የገበያ መናጋቱ ሌላ ችግር እንዳያስከትል ስጋት እንዳላቸው ነው እነዚሁ ወገኖች የገለጹት። ለአንድ ሰው በዓመት ሁለት ጊዜ ሙሉ ወታደራዊ ትጥቅ የሚያዘጋጀው አልሜዳ ዘወትር የደንብ ልብስ በማምረት ስራ ላይ እንደነበር የገለጹት ወገኖች፣ የደንብ ልብስ ማምረቱ ከቆመ ስራው በስፋት እንደሚቀንስ ጠቁመዋል። የስፌት ሰራተኞችና ማሽኖች ቅድሚያ ስራ እንደሚቀንስባቸው አመልክተዋል።
ከለውጡ በሁዋላ በህወሃትና በገዢው ፓርቲ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት፣ ህወሃት ከኦነግ ሸኔና ራሳቸውን ክልል ለማድረግ በስፋት ከሚሰሩ ቡድኖች ጋር የፈጠረው ግንኙነት፣ ለፌደራል መንግስቱ አልታዘዝም ማለቱ፣ በአገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየውን ቀውስ ስፖንሰር በማድረግ የሚከሰሰው ህወሃት በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱት በርካታ የንግድ ተቋማቱም መቀዛቀዛቸው እየተሰማ ነው። አንዳንዶቹ ጭራሹኑ ከገበያ ወጥተዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በስፋት የዘረጉት የንግድ ሰንሰለት አሁን ላይ ወደመቆራረጥ ደረጃ ላይ መድረሱ ህወሃት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት አጥብቆ ለመዋጋትና ለመጣል ካነሳሱት ምክንያቶች ግንባር ቀደሙ እንደሆነ ስለጉዳዩ የሚያውቁ ይናገራሉ። እነዚህ ወግኖች እንደሚሉት የኤፈርት ድርጅቶች ነገሮች ካልተቀየሩ በስተቀር መመናመናቸውና ትግራይ ላይ ብቻ ለማተኮር እንደሚገደዱ ግምታቸውን ያኖራሉ። በተመሳሳይ ይህ አካሄድ በንግድ አሻጥር ጉሮሯቸው ታንቆ ለነበሩ የግል ባለሃብቶች እፎይታን መፍጥሩም እየተሰማ ነው።
አቶ ስብሃት ነጋ እንዳሉት ኤፈርት ከአፍሪካ ትልቁ የንግድ ኢምፓየር ነው።
አልሜዳ ለሲውዲን ታዋቂ የልብስ አምራችና ነጋዴ ድርጅት ምርቱን የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *