ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለመምረጥ ይቸገር የነበረው ሕዝብ ላለመምረጥም ተቸግሯል

አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ምርጫቸውን ሳይሆን ምርጫ ሲመርጡ መኖራቸው ይነገራል፡፡ መከራከሪያው ደግሞ የሚፈልጉትን ሳይሆን የሚፈለግላቸውን መርጠዋል የሚል ነው፡፡በአምባገነን ስርዓት ስትገዛ ለምርጫ የምታስፈልገው ካርድ እንደትወስድና ካርድ እንደትመልስ ብቻ ነው፡፡ ቆጥረው ይሰጡሀል፤ ቆጥረው ይቀበሉሀል።በደደቢት በረሃ ጉዞውን ዳዴ ያለው የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) ቡድን ሀገሪቱን ስልታዊ በሆነ መንገድ ከተቆጣጠረ በኋላ የቀደመውን የኢትዮጵያን የክብር ካባ እያወለቀ እራሱ የሰፋውን አለበሳት፡፡

ከአንድነት ይልቅ ብቸኝነትን፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በብሔር መደራጀትን ምርጫው አደርጎ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ኢትዮጵያን አስተዳደረ፡፡ በዚህ ዘመን ሰብዓዊነትና ሰውነት እየተናቀ ሔደ፡፡ ወንድም ወንድሙን ተጠራጠረ፡፡ ነጻ አውጭ ለነጻነት ብለው የመጣው ሥርዓት ታይቶ ወደማይታወቅ አፈና አመራ፡፡ አራት ነጻ አውጭ ድርጅቶችን ይዞ ግንባር በመፍጠር በራሱ ፊት ግንባሩን እየመራ ሌሎች ግንባርና ፊት እንዳይኖራቸው አድርጎ ዘለቀ፡፡ በእውኑ ነጻ ማውጣት ከአፋኝ ስርዓት ወይስ ከኢትጵያዊነት ማማ ላይ ማውረድ ? በእንቢተኝነት የመጣው ሕወሃት በእንቢተኝነት ተፈንግሎ ወደ ጎን አፈገፈገ፡፡

አብዛኛውን የኢትዮጵያን ክፍል ቢለቅም ቀድሞውንም በተነሳበት አካባቢ ግን አሁንም በአፋኝነቱ ቀጥሏል ነው የሚባለው፡፡ ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዛ ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡ ይህን እንዲያደርግ በሕገ መንግሥቱ ስልጣን የተሰጠውም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው፡፡ የምርጫው እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት ታዲያ ዓለምን እያስጨነቀ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያንም ስላስጨነቃት ምርጫው እንዲራዘም ተጠዬቀ፡፡ የምርጫ ቦርድ በጠዬቀው መሠረትም በውይይት እንዲራዘም ተወሰነ፡፡በዚህ ውሳኔ የትግራይን ክልል የሚመራውና ግንባሩ የተናደበት ሕወሃት ‘አልስማም አለ’፡፡

ምርጫ ከማድረግ የሚያግደኝ አንድም አካል የለም አለ፡፡ የራሱን ምርጫ ቦርድ በማቋቋም ምርጫውን ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ምርጫው ምን አይነት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል መገመት ባይቻልም፡፡ በሕወሃት ምርጫ እንቅስቃሴ ላይ ታዲያ የሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ወትሮውንም የማንነትና የወሰን ጥያቄ ሲያነሱ በቆዩ የራያ፣ ወልቃይትና ጠለምት አካባቢዎች ተቃውሞው ላቅ ያለ ነው፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ነዋሪዎች በግዴታ የምርጫ ካርድ ውሰዱ፣ ካልወሰዳችሁ ደግሞ የብርና የእስራት ቅጣት ይጠብቃችኋል እየተባልን ነው እያሉ ነው፡፡

ቅጣቱ ካርድ ወስደው የምርጫ ጣብያ ላይ ካልተገኙ የከፋ እንደሚሆንም ነው የሚናገሩት፡፡አብመድ ይህንን በተመለከተ የትግራይ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን ጠይቆ “ድርጊቱን አልፈጸምንም” የሚል ምላሽ መሰጠቱን ማስነበባችን ይታወሳል።ይህ ሃሳብ ምን ያክል አዋጭ ነው? እነዚህ ዜጎችስ መች ነው ሰሚ ጀሮ የሚያገኙት? በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ቤት የሕግ መምህሩ ደመወዝ ካሴ በዚሕ ሰዓት ምርጫ ማድረግ ወይንም አለማድረግ ለክርክር ክፍት ማድረግ ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ምርጫ ማድረግ አይቻልም ተብሎ ተወስኖ አድሯል፤ ሕወሃት አደርገዋለሁ የሚለው ምርጫ ልክ አይደለም ነው የሚሉት፡፡

ሀገራዊውም ሆነ ክልላዊ ምርጫ የማድረግ መብቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው ያሉት መምህሩ ሕወሃት ግን የራሱን ሕገመንግሥት ራሱ ሽሮታል ነው ያሉት፡፡ በራያ፣ ወልቃይትና ጠለምት የሚነሱት ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ምርጫው እየጋለ ስለመጣ ተነሱ እንጂ በቅርብ የተጀመሩ አይደለም ያሉት መምህሩ በአካባቢው የሕወሃት ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለዓመታት የዘለቀ ነው ብለዋል፡፡

ምርጫ ሕገወጥ ከሆነ ቀጥለው ሊመጡ የሚችሉት ነገሮችም ሕገወጥ ናቸውም ብለዋል፡፡ ራያ፣ ወልቃይትና ጠለምት በፖለቲካዊ ውሳኔ በጉልበት የሄዱ እንደሆነ ያመላከቱት መምህር ደመወዝ አሁን ያለው ጭቆና ከቀድሞው የቀጠለ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የማንነት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ምርጫን ተገን አድርገው የሚነሱት የሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ከሕወሃት ባህርይ አንጻር ከፍ ሊሉ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ምርጫ በግዴታ ሳይሆን በፍላጎትና በፈቃደኝነት መሆን መቻል አለበትም ነው ያለት፡፡

ሕወሃት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከዲሞክራሲያዊም ሆነ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ልክ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በምርጫ ሂደት ውስጥ እኔን የሚወክለኝ ስለሌለ የተከበረውን ድምጼን ያልተገባ ሥፍራ ላይ አልጥልም ማለት መብት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ እንኳን አማራጭ በሌለበት የምርጫ ሂደት ውስጥ አማራጭ ኖሮ እንኳን ከተቀመጡት አማራጮች መካከል እኔን የሚወክል አማራጭ አልተቀመጠም የሚል ካለ ያለ መምረጥ መብቱ የተጠበቀ ነውም ብለዋል፡፡ ምርጫ ላይ መሳተፍ መብት ከሆነ አለመሳተፍ ግዴታ የሚሆንበት አግባብ የሌለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ የፌደራል መንግሥት ዝም ብሎ ማዬት የለበትም ያሉት መምህሩ የዜጎችን መብት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ መብት ጥሰት ተፈጽሟል፣ የፌደራል ስርዓቱም አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያስብ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በራያ፣ወልቃትና ጠለምት እየተደረገ ያለው የመብት ጥሰት አሁን ያለውን መንግሥት በዓለማቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቅ ነውም ብለዋል፡፡ መንግሥት ያለውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ጣልቃ ገብቶ ማስተካከል ካልቻለ ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለራሱም አደጋ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ የራያ፣ ወልቃይትና ጠለምት ነዋሪዎች የተረሱ ናቸው ያሉት የሕግ መምህሩ በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስተካከል ሥራ እየተሰራ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሕወሃት አሁን እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ የሚገርም አለመሆኑንም ነው ያስረዱት። ሰነድ ተሰንዶ ሲሰራበት የነበረ፣ ሲመሰረት የነበረውን አላማ ያስቀጠለ ነውም ብለዋል፡፡የሕወሃት አቋም ኢትዮጵያን እኔ ከመራኋት በጄ፤ እኔ ካልመራኋት ግን አያሻንም አይነት ነውም ብለዋል፡፡ ሕወሃት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተገማች እንዳይሆንና አካባቢው የስጋት ቀጣና እንዲሆን የማድረግ ሥራ ሊሰራ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከተቀጠለ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚኖራት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነትም አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡ ከቻለ ኢትዮጵያ ያልተረጋጋች ሀገር እንድትሆን ካልቻለ ግን በተስፋ ቢስነት የሽብር ሥራዎችን መሥራቱ አይቀሬ ነውም ብለዋል፡፡

በተለይም የአማራ ክልል መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ይህንን ለማስተካከል የማይሠሩ ከሆነ አስቸጋሪ የሆነ ተግባር ሊፈፀም እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡ ሕወሃት ከሰሞኑ እያሳዬችው ያለው እንቅስቃሴ ‹‹ አቅም ያለው ይግጠመኝ›› አይነት መሆኑን ያመላከቱት የሕግ መምህሩ አደጋው የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ ለሌሎች ኢትጵያዊያንም ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡ ዳፋው ከኢትዮጵያውያንም አልፎ ለጎረቤት ሀገራትም እንደሚተርፍ ነው የተናገሩት፡፡ ጥያቄዎቹን ለመፍታትና ለመመለስ ግጭት መፍትሔ አለመሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ከራያ፣ ወልቃይትና ጠለምት ፍትኃዊ ጥያቄ ጎን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከጎናቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ የአማራን ሕዝብ ከሚመራው የፖለቲካ ፓርቲ ተገቢ የፖለቲካ ጫና ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ወልቃይት ለኢትዮጵ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም መሠረታዊ የሆነ ሥፍራ ነው ያሉት መምህሩ ወደ ታላቅ ጥቅም ከመቀዬር ይልቅ ለተራዘመ የግጭት አካባቢ እንዳይሆን ስጋት አለኝም ብለዋል፡፡ ሥፍራው በፖለቲካው እንቅስቃሴ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነውም ብለዋል፡፡ የዜጎቹ የማንነትና የወሰን ጥያቄ ለአማራ ሕዝብና መንግሥት ብቻ የተሰጠ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄዎቹ እንደሚለሱ የራሱን አስተዋፅዖ ማድረግ መቻል አለበት ነው ያሉት፡፡ ከተስፋ መቁረጥና ከዕብሪት የመጣውን የትህነግን እንቅስቃሴ የፌደራል መንግሥት ማስታገስ እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡ በየትኛውም አካል በሚደረግ ግፊት የትግራይና የአማራ ሕዝቦች ወደ ግጭት መግባት እንደሌለባቸውም አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ኃላፊነት የመወስድና የመወጣት የፌደራል መንግሥት መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ

አማራ ማስ ሚዲያ