ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ግልፅ ደብዳቤ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ ቢደርስም ባይደርስም!!

ሰላምታዬንና አክብሮቴን በማስቀደም የተከበሩ ሚኒስትር፣ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ኢዜማ በጥናት ደረስኩበት ብሎ ይፋ ላደረገው ሰነድ በሰጡት መልስ የተገነዘብኩት እንደ አንድ ተራ ዜጋ ላቀርብልዎት እወዳለሁ ።
ሲጀመር የሰጡት አርስት ራሱ ችግር እንዳለበት ይሰማኛል። ማስረጃ አጠናቅሬያለሁ ያለ ድርጅት መግለጫ ከማውጣቱ ሰነዱን ለሚመለከታቸው አቅርቦ ይመሩት የነበረው ፅ/ቤት መልስ ስላልሰጠ። ኢዜማ ከዚህ ቢሮ መልስ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ አንደኛ መልሱን ሪፖርቱ ላይ ያካትት ነበር፣ አሳማኝ የሆኑ ጉዳዮች ከቀረቡም ፓርቲው ከሪፖርቱ ላይ የተወሰኑትን እንዲያርም ወይም እንዲያሻሽል እድሉ ክፍት ይሆን ነበር ብየ አምናለሁ።
በመቀጠልም ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ባልገኝም ሲሉ ተገቢው ቦታ ለመሆኑ የቱ ነው። ሰነዱ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ግለሰቦች አካላት እስዎና እስዎ ይመሩት የነበረው ተቋም በመሆናቸው መልስ እንዳይሰጡ ቦታ ምክንያት ይሆናል ብዬ አላስብም ።
በመቀጠልም የመሬት ወረራን በተመለከተ ስልጣን ላይ ከወጣንበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ ጠንካራ እርምጃዎች ስንወስድበት የነበረ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለስዎ አድልተን ያሉትን ብንቀበል እንኳን “የመሬት ወረራውን አስቆሙት ወይ ? የኮንዶሚኒየሙን አድሎአዊ እደላ አስወገዱት ወይ ነው?” ጥያቄው በራስዎ አንደበት የሀይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ በኢ_መደበኛ አደረጃጀቶች ሲወረሩና በመንግስት አካላት ሲፈርሱ በተነሳብዎት ተቃውሞ ምክንያት እስዎ ራስዎ ይቅርታ አልጠየቁም ወይ? ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ እንዳለ በይፋ አልተናገሩም ወይ? ባለፉበት ባገደሙበት ሁሉ የከተማዋን መሬት ለግለሰቦችና ለተቋማት ሲያድሉ አልነበር ወይ?
ሌላው ክቡር ኢንጂነር የተፈናቀሉትን አርሶ አደሮች በመታከክ እንደ ህወሀቶቹ የቀን ጅቦች ብሄርዎን ዋሻ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ በጣም ከስዎ በጭራሽ ያልጠኩት ነበር። ለመሆኑ የትኛው የኢዜማ የመግለጫው ክፍል ላይ ነው “የተፈናቀሉት ገበሬዎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ አይሆኑ” የሚለው። ማነው በቃለ መጠይቁስ ላይ “ለተፈናቀሉት ቤት አይሰጥ” ያለው? በስዎ የስልጣን ዘመን በገፍ ቤት የታደላቸው በሺዎች የሚቆጠሩት የኦሮሚያ ባለስልጣናት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ነበሩ ወይ? እስከ ልጅ ልጅ የሚሰጠው መሬት ፍትሀዊ ነበር ወይ? ለክለቦች የታደለውስ? ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው እኮ “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ድሆች ከዛሬ ነገ አንገታችንን ማስገቢያ፣ ልጆቻችንን ማሳረፊያ ቤት ልናገኝ ነው” በማለት ቤትን የህልውናቸውና የተስፋቸው ጥግ አርገው እየጠበቁ ሳለ ነው።
“እኛ ህጋዊ እርምጃ ስንወስድ የዛሬ ተችዎቻችን የሰብአዊ መብት ተነካ፣ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ የከፈቱብን አካላት ናቸው”ብለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ሲወሰድ የሰብአዊ መብት መከበር አለበት የሚለው አለማቀፋዊ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ “ዘመቻ” ላሉት ቃል ግን ይቅርታ ያድርጉልኝና ማፈር ይኖርብዎታል። ለእስዎም ሆነ ለመንግስትዎ የኢዜማን ያክል እድል የሰጠ አንድም ድርጅት የለም። መወቀስ ካለበትም በሰጣችሁ ሰፊ እድልና በታገሳችሁ ልክ መሆን አለበት ምንም እንኳን ሁለቱም ምክንያታዊ ናቸው ብዬ ባምን።
ሌላው እጅግ አስገራሚ የሆነው ደሞ “አንድም ቀን ለተናቀሉት የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ድርጅት” ሲሉ የጠቀሱት ለመሆኑ ኢዜማ የጠቀሷቸው ዜጎች ሲፈናቀሉ ህልው ፓርቲ ነበር ወይ? ያፈናቀላቸው እኮ የራስዎ ድርጅት የዛሬው የኦሮሚያ ብልፅግና የትናንቱ ኦህዴድ ነበር! ተረሳ ክቡር ሚኒስትር? አግ7 እንዲሁም ከስመው ኢዜማን የመሰረቱት እኔ የማቃቸው ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ሁሉ እናንተ ስታፈናቅሉ እነሱ ከተፈናቃዮች ጎን ሆነው ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበሩ መሆናቸውን አስረግጬ መናገር እችላለሁ። እንደ አንድ ለወገኑ እንደሚቆረቆር ኢትዮጲያዊ እኔም ከነሱ ባለሁበት ያቅሜን ስጮህ ነበር። ለምን ይዋሻል ኢንጂነር!
“የአርሶ አደሮችን ጉዳይ ለተቀባይነት ማግኛ” በማለት የፃፉት እና “መጀመሪያ ላይ በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ እንጂ አይገነባም” ላሉት ደሞ ትንሽ ማለት አለብኝ። ለመሆኑ ኢዜማ እስዎ ባሉት መልኩ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚቻል ጠፍቶት ነው በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹን ያጣው? ሌላው ቢቀር በእናት ድርጅትዎ መዋቅር በአብዛኛው ኦሮሚያና እስዎ ሲያስተዳድሯት በነበረችው በአዲስ አበባ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማስጮህ ብቻ ተከታይን ማፍራት አይቻልም ብለው ያስባሉ? ይልቅስ ከላይ እንደጠቀስኩት የተፈናቃዮችን ልብ በፀረ ኢዜማ ትርክት ለማነፅና ጭፍን ተከታይ ለማፍራት የኳተኑት እስዎ ራስዎ ነዎት። በነገራችን ላይ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት እድል መስጠት ከመንግስታዊ ኢ_ህገመንግስታዊ ተግባራት ጋ ማበር አይደለም።
ክቡር ኢንጂነር አሁን ላይ በደንብ የገባኝ ከስልጣን ሲወርዱ፣ በሀሳብ መሟገት ሲያቅታቸውና ፖለቲካ ፊት ስትነሳቸው “ብሄርን መደበቂያ ዋሻ” ማድረግ በስፋት እየተዛመተ ያለ አስፈሪ ፖለቲካዊ ባህል መሆኑን ነው። ። እስዎም ይሄን መንገድ በመከተል የነ ሀይለመስቀል ሸኚን ፣ የነ አቦይ ስብሀትን የነልደቱ አያሌውን ዱካ እንደተከተሉ ተረድቻለሁ።
የአሿሿምዎ ሂደት አጠያያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ ክቡር ሚኒስትር እስዎ የታላቋ አዲስ አበባ ከንቲባ ነበሩ። ሲያስተዳድሯት የነበረችው አዲስ አበባ ማለት የ AU፣ የ ECA እና የመሳሰሉት ታላላቅ አለማቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫና በአለም ላይ 3ኛዋ ወይም 4ኛዋ የዲሎማሲና የፖለቲካ ከተማ እንደሆነች አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው። አሁንም ቢሆን ሚኒስትር እንጂ እንደኔ አክቲቪስት አይደሉም። ቢሆን ደስ የሚለኝ “ቀረበ” የተባለውን ሰነድ በሚገባ ፈትሸው ተመጣጣኝ በሆነ አግባብ መልስ ቢሰጡ ነበር። ሰነዱን በሙሉም ሆነ በከፊል ወይም በተወሰነ ደረጃ ተቀብለው ያም ካልሆነ ተቃውመው የነበሩበትንና ያሉበትን ወንበር የሚመጥን አፀፋ ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። በኔ በኩል ያደረጓቸውን በጎ ተግባራት በዜሮ የማጣፋ ሰው አይደለሁም። የዛሬው መልስዎ ስሜቴን በእጅጉ ቢበርዘውም ለበጎ ለበጎዎቹ ስራዎችዎ ዛሬም ክብር እሰጣለሁ። ይሁን እንጂ በቀረበብዎ ክስ እና በሰጡት መልስ ምክንያት የተደበቀውን “ኢንጂነር ታከለ ኡማን” ማየቴን ደሞ አልሸሽግዎትም። አሁን ለደረስኩበት ግንዛቤ ትልቁ ግብአቴ ደሞ እስዎ ራስዎ የነገሩንን ጭምር በመካድዎ ነው። ይሄ ሁሉ ሆኖም የነበሩበትንና ያሉበትን ደረጃ የሚመጥን መልስ ካለ ለመስማት አሁንም ፍቃደኛ ነኝ።
ክቡር ሚኒስትር ስንብቴን አስቀድሜ እያቀረብኩ ደብዳቤየን ከማጠናቀቄ በፊት እስዎ ወይም ይመሩት የነበረው አስተዳደር ስለተሞገታችሁ ብቻ ሀገር እንደማትፈርስ በርግጠኝነት ልነግርዎ እወዳለሁ። ይልቅስ ሀገር የሚያፈርሰው የዜጎችን ድምፅ ለማፈን ይመሩት የነበረው ተቋም እየወሰደ ያለው ኢ_ህገመንግሳታዊና ኢ_ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ነው። የኢዜማ መግለጫዎች መታገድ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ሳይሆን የእስዎ የሁለት አመታት የከንቲባነት ዘመን ውጤት ነው። የክብርት ከንቲባዋን ውጤት ደሞ ሰነባብተን እናየዋለን።
አክባሪዎ Wondemagegnehu Addis