“Our true nationality is mankind.”H.G.

ወያኔ የኢራቅ ኩርዶች እጣ ፋንታ ይገጥማታል

 
This image has an empty alt attribute; its file name is haile-mulu.jpg
…የኢራቅ ኩርዶች መገንጠል በየግዛቶቻቸው ለሚኖሩ ኩርዶች መጥፎ ተምሳሌት ይሆናል ብለው ስላመኑ ግንኙነታቸውን ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን ከኩርድ ክልል ጋር የሚያገናኛቸውን ድንበር ዘግተው ሚሳኤሎቻቸውን ደገኑ። ይህ ያልጠበቁት ዱብ እዳ የደረሰባቸው የኩርድ ፖለቲካ ኃይሎች እርስ በእርሳቸው ሲወነጃጀሉ የኢራቅ ጦር ሀይል ያለማንም ከልካይ ወደ ኩርዶች ክልላዊ ግዛት ሰተት ብሎ በመግባት በነዳጅ ምርት የበለፀገችውንና አወዛጋቢዋን ኪርከክ ግዛት በቁጥጥር ስር አዋለ።
 
ነጻ አስተያየት (በኃይሌ ሙሉ)
 
 
የኢራቅ ኩርዶች ከኢራቅ ማዕከላዊ መንግስት ተነጥለው ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት ይሰጣቸው ዘንድ ለበርካታ አመታት ታግለዋል። ይህንን መብት ለማስከበር በተለያዩ ጊዜያት በተካሄደው አመፅም በሺህዎች የሚቆጠሩ ኩርዶች ተገድለዋል። መቶ ሺህዎች ለስደት ተዳርገዋል።
ህዝባዊ አመፁ አንዴ ሲሞቅና አንዴ ሲቀዘቅዝ ቆይቶ እ.አ.አ በ2003 ዓ.ም በኩርዶችና በማዕከላዊው የኢራቅ መንግስት መካከል የነበረውን ግንኙነት የሚቀይር ክስተት ተፈጠረ። አሜሪካ ኢራቅን በወረረችበት በዚህ ወቅት ከጎኗ የተሰለፉት ኩርዶች የሳዳም ሁሴን መንግስት ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ተፈቀደላቸው።
እ.አ.አ በ 2005 የረቀቀው የኢራቅ ህገ መንግስት ደግሞ ኩርዶች የራሳቸውን መንግስት እንዲያቋቁሙ፣ ያለምንም ገደብ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት እንዲመሰርቱ፣የራሳቸው ፓርላማ እንዲኖራቸውና የጦር ሀይል እንዲያቋቁሙ የሚያስችል መብት አጎናፀፋቸው።
ይህንን ተከትሎም የተለያዩ ሀገራት ከኩርዶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ጀመሩ ። ዲፕሎማቶቻቸውንም ወደ ዋና ከተማዋ ኢብሪል ላኩ፤ኢንቨስትመንትና ንግድ ተስፋፋ። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ አይሲስ የተባለው እስላማዊው አሸባሪ ቡድን በኢራቅ ያካሄደው ወረራ ለኩርዶች ያልታሰበ በረከት ይዞላቸው መጣ።
እንደ አውሮፓ አቆጠር በ 2014 አሸባሪው አይሲስ በፈፀመው ወረራ የኢራቅ ሰራዊት ተንኮታኩቶ ሊወድቅ ጫፍ በደረሰበት ወቅት ኩርዶች ከአይሲስ ጋር ተዋግተው በማዕከላዊው የኢራቅ መንግስት ክልል ውስጥ የነበረችውንና ኋላ ላይ በአይሲስ ቁጥጥር ስር የወደቀችውን ኪርከክ የተባለችውን በነዳጅ ምርት የበለፀገችውን አወዛጋቢ ግዛት ተቆጣጥረው በየቀኑ አንድ ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ እያመረቱ ገቢውን ለራሳቸው ማዋል ጀመሩ።
ከዚህ በተጨማሪ ማዕከላዊው የኢራቅ መንግስት ከሚያገኘው የነዳጅ ሽያጭ ገቢ 17 በመቶ የሚሆነውን ለኩርድ ክልላዊ መንግስት በድጎማ መልክ ይሰጣል። ይሄ ሁሉ ተደማምሮ የኩርድ ክልላዊ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ብልፅግና ማምራት ጀምረ። ይህንን የተመለከቱ ታዛቢዎችም የኩርድ ክልላዊ መንግስት የሚያስተዳድረውን ቀጠና “ቀጣዩ ዱባይ” የሚል ስያሜ ሰጥተውት ነበር።
ይህ ፈጣን የአገሪቱ እድገት ግን በሂደት እንቅፋት እየገጠመው መጣ።አገሪቱን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ጠፍንጎ አላንቀሳቅሳት አለ። ሙስና ተስፋፋ። መንግስት በገጠመው የፋይናንስ እጥረት ለሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈል ተቸገረ። ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች PUK(Patriotic Union Of Kurdistan) እና KDP(Kurdistan Democratic Party) ተግባብተው አገር ማስተዳደር አልችል አሉ።ለህዝብ የሚጠቅም ስራ በመስራት ፋንታ ስልጣን ይዞ ለመቆየት የእርስ በእርስ ፍትጊያ ጀመሩ። ይህንን ተከትሎም ህዝቡ ተቃውሞ ማሰማት ጀመረ።  ከዚህ በሗላ ነው እንግዲህ የህወሀትና የኩርዶች አካሄድ መመሳሰል የሚጀመረው።
ስልጣናቸው አደጋ ላይ መውደቁን የተገነዘቡት የኩርድ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት የነበሩት መሱድ ባርዛኒ ለችግሩ መፍትሄ በመፈለግ ፋንታ ለጊዜው የህዝቡን ትኩረት የሚለውጥ አጀንዳ ይዘው ብቅ አሉ። “የኩርድ ክልላዊ መንግስት ከኢራቅ ተገንጥሎ የራሱን መንግስት ይመሰርት ዘንድ ሪፈረንደም ይካሄዳል” የሚል ውሳኔ መተላለፉን ለህዝብ አሳወቁ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ውሳኔ ካስተለፉ ከአስር ቀናት በሗላ ለሁለት አመት ያህል ተጠርቶ የማያውቀው ፓርላማ ተሰብስቦ የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ አፀደቀ።
ከዚያም የህዝቡን ትኩረት የሚስብ ፕሮፖጋንዳ መስተጋባት ተጀመረ።
“ማዕከላዊው የኢራቅ መንግስት የከሸፈ መንግስት ነው፤ ደካማ ነው፤ከኢራቅ ጋር አብረን ስንኖር ባህልና ቋንቋችን ትተን አረብ እንድንሆን ተገደናል ፤ በአረቦች ተውጠናል፤ በአሀዳዊ መንግስት ተፅዕኖ ውስጥ ወድቀናል” የሚሉ ስሜት ቀስቃሽ ፕሮፖጋንዳዎችን በማስተጋባት የህዝቡን ስሜት መግዛት ቻሉ።
በስልጣን ላይ ያለው ዋነኛ ተቀናቃኝ ፓርቲን ጨምሮ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መጀመሪያ ላይ የመገንጠል ሀሳቡን የተቃወሙ ቢሆንም ኋላ ላይ ግን ህዝቡ የሀገር ፍቅር የላቸውም (unpatriotic) ናቸው ብሎ ያገለናል በሚል ፍርሀት ሳይወዱ በግዳቸው ሪፈረንደም እንዲካሄድ የሚደግፉ መሆናቸውን አሳወቁ።
በፕሬዚዳንት አባዲ የሚመራው የኢራቅ መንግስት በበኩሉ የኩርዶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንደሚያከብር ገልፆ ነገር ግን በሁለቱ ወግኖች መካከል ውይይት ሳይካሄድ ሪፈረንደም ማካሄድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን አሳወቀ። የኩርድ ክልላዊ መንግስት ግን ይህንን የኢራቅ መንግስት ጥያቄ ወደጎን ትቶ ሪፈረንደሙን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጧጧፍ ጀመረ። ሽማግሌዎች ተልከው ቢለምኑት ሁሉ አልሰማም አለ።
ባሳለፍንው የፈረንጆች አመት በአሜሪካ ድሮን በተተኮሰ ሚሳኤል የተገደሉት የኢራኑ ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒ ሳይቀር ወደ ኢብሪል ተጉዘው የኩርዶች ዲፋክቶ ፕሬዚዳንት መሱድ ባርዛኒ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ለማግባባት ሞክረዋል። ጥረቱ ከሙከራ አላለፈም እንጂ።
ሪፈረንደሙ ቢካሄድ በክልሉ ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ያሰጋት አሜሪካ ሳትቀር ለኩርድ ክልላዊ መንግስት የማርያም መንገድ ሰጥታ ነበር። ኩርዶች ሪፈረንደሙን ለሁለት አመት እንዲያራዝሙና ከመአከላዊው የኢራቅ መንግስት ጋር ውይይት እንዲጀምሩ፣ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ ካልደረሱ ግን ኩርዶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሪፈረንደም እንዲያካሂዱ ድጋፍ የምትሰጥ መሆኗን አሜሪካ አስታወቀች። ፕሬዝዳንት መሱድ ባርዛኒ ግን “አንዴ ወስነናል ወደኋላ አንመለስም” በማለት ወይ ፍንክች አሉ። እናም ሪፈረንደሙ በታቀደለት ጊዜ ማለትም እ.አ.አ ሰኔ 2017 ተከናወነና 93 በመቶ የሚሆነው መራጭ መገንጠልን መረጠ።
ሪፈረንደሙን ተከትሎ ግን የተከሰተው ነገር ያልተጠበቀ ነበር ። የኩርድ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት መሱድ ባርዛኒ የሚያስተዳድሩትን ክልል ከከኢራቅ ለመገንጠል ሲወስኑ ማዕከላዊው መንግስት የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ ከማቆም ውጭ የከፋ እርምጃ አይወስድም የሚል ግምት ነበራቸው። ነገር ግን እንደጠበቁት አልሆነም።
የኢራቅ ፖርላማ ተሰብስቦ እገነጠላለሁ ባለው የኩርድ ክልላዊ መንግስት ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ ውሳኔ አስተላለፈ።
ለወትሮው የኩርድ ክልላዊ መንግስት ወዳጅ የነበሩት የኢራንና የቱርክ መንግስታትም የኢራቅ ኩርዶች መገንጠል በየግዛቶቻቸው ለሚኖሩ ኩርዶች መጥፎ ተምሳሌት ይሆናል ብለው ስላመኑ ግንኙነታቸውን ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን ከኩርድ ክልል ጋር የሚያገናኛቸውን ድንበር ዘግተው ሚሳኤሎቻቸውን ደገኑ። ይህ ያልጠበቁት ዱብ እዳ የደረሰባቸው የኩርድ ፖለቲካ ኃይሎች እርስ በእርሳቸው ሲወነጃጀሉ የኢራቅ ጦር ሀይል ያለማንም ከልካይ ወደ ኩርዶች ክልላዊ ግዛት ሰተት ብሎ በመግባት በነዳጅ ምርት የበለፀገችውንና አወዛጋቢዋን ኪርከክ ግዛት በቁጥጥር ስር አዋለ።
ነፃነታችን ማንም አይከለክለንም እያሉ ሲደነፉ የነበሩት የዲፋክቶው ክልል ፕሬዝዳንት መሱድ ባርዛኒም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ። የኢራቅ ኩርዶች የመገንጠል ምኞትም ቅዥት ሆኖ ቀረ። ትዕቢት እንዲህ ነው! ውድቀትህን ያፋጥነዋል!
ወደ አገራችን ስንመለስ በተመሳሳይ መልኩ ወያኔ ከአራት ኪሎ ከለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ በትግራይ ክልል ከሚያስተዳድረው ህዝብ ለሚነሱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የመብት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ፋንታ ልክ እንደ ኩርድ ክልላዊ መንግስት መሪዎች ሁሉ የአብይን አስተዳደር አንዴ “ደካማ” ሌላ ጊዜ “አሀዳዊ” እያለ በመወንጀል የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ሲያስቀይር ከርሟል።
ወያኔ ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ቡራ ከረዮ ሲል፣ አሜሪካና ኢራን ለኢራቅ ኩርዶች እንዳደረጉት ሁሉ የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ተጉዘው ህወኃት ከመአከላዊው መንግስት ጋር እንዲደራደር በመጠየቅ ከገባበት አጣብቂኝ እንዲወጣ የማርያም መንገድ ሰጥተውት ነበር። “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም” እንዲሉ ህወሓት ግን የሽማግሌዎቹን ምክር አሻፈረኝ ብሎ ምርጫውን ለማካሄድ ወስኗል።
የኢራቅ ማዕከላዊ መንግሥት ከበጀት ድጎማ ማቋረጥ የዘለለ እርምጃ አይወስድም የሚል የተሳሳተ ግምት የኢራቅ ኩርዶች ይዘው እንደነበሩት ሁሉ ወያኔም የአብይ አስተዳደር የከፋ እርምጃ ወሰደ ከተባለ የበጀት ድጎማ መስጠቱን ከማቆም አያልፍም ብሎ ራሱን አሳምኗል። እንግዲህ በዚህ መልኩ ነው ወያኔ በስህተት ላይ ስህተት እየፈፀመች የራሷን መቃብር በመቆፈር ላይ የምትገኘው።
ወያኔ ለወራት ስታካሂደው ከነበረው ፉከራና ቀረርቶ አልፋ ትናንት ባወጣችው መግለጫ “የትግራይን ክልል ምርጫ ለማስቆም ወይም ለማደናቀፍ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወስደው ማናቸውም ውሳኔ እንደ ጦርነት አዋጅ ይቆጠራል” የሚል ዛቻ ማውጣቷን ለተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ቢያንስ ቢያንስ ለራሱ ህልውና ሲል እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ መረዳት አያዳግተውም።
በዚህ ላይ የራያና የወልቃይት ህዝቦች በህወሓት አገዛዝ እየደረሰባቸው ካለው ግፍና በደል የአብይ አስተዳደር እንዲታደጋቸው በየጊዜው የሚያቀርቡት ጥሪ እረፍት የሚነሳ በመሆኑ መንግስት ሀላፊነቱን ለመወጣት መንቀሳቀሱ አይቀርም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ለመውሰድ አንዴ ከተንቀሳቀሰ ደግሞ የዘረኛዋ ህወሓት ስርአት ቀብር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይከናወናል። እነ ደብረ ፅዮንና ጌታቸው ረዳም ከስልጣን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን እጃቸው ላይ ሰንሰለት ታስሮ ክንፈ ዳኘውን ይቀላቀላሉ። የኢራቅ ኩርድ መሪዎች ተንቀዥቅዥው በወሰዱት እርምጃ በነዳጅ የበለፀገችውን የኪርከክ ግዛት በኢራቅ ጦር ኃይል እንደተነጠቁት ሁሉ፣ ለም መሬታቸውን ብቻ በሚፈልገው የህወሓት ግፈኛ አገዛዝ “የማንነት ጥያቄ ለምን አነሳችሁ?” በሚል ለአመታት ሰቆቃ ሲፈፀምባቸው የኖሩት የራያና የወልቃይት ህዝቦችም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ነፃነታቸውን ያውጃሉ።
ይሄው ነው!
 
 
0Shares
0