“Our true nationality is mankind.”H.G.

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ! – የወልቃይት እና ራያ ወቅታዊ ሁኔታ

የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሥርአት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሰረት የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጣልቃ ሊገባ ከሚችልባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ሰብአዊ ቀውስ (Humanitarian Crisis) መሆኑ በግልጽ ተመልክቷል። ትህነግ በወልቃይት እና ራያ ላይ እየፈጸመ ያለው ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን እና ሰብአዊ ቀውሱን የማስቆም ግዴታ በፌደራል መንግሥቱ ላይ የሚጥል ሲሆን፣ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ ገብቶ አካባቢዎቹን ከትህነግ የጸጥታ ሃይሎች ነጻ የማድረግ ሃላፊነት የሚጥል ነው።

ነጻ አስተያየት – መልካሙ ሹምዬ ኮከብ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ 30/12/2012ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ለአባላቱ ጥሪ ማስተላለፉን በፌስ ቡክ ገፁ ገልጧል። ምክርቤቱ ባስተላለፈው ጥሪ የስብሰባውን አጀንዳ ይፋ ባያደርግም፣ ትህነግ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ክልላዊ ምርጫ (በአንዳንዶች አተያይ የሃገረ ትግራይ ምስረታ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ይወሰዳል) ለማድረግ ዝግጅቱን ጨርሶ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የስብሰባው አጀንዳ ከዚያ አያልፍም ተብሎ ይጠበቃል።

ትህነግ ምርጫውን በዚህ ወቅት የሚያከናውነው የስልጣን እድሜው በገበያ ግርግር ለማራዘም ብቻ ሳይሆን፣ ምርጫውን እንደ ህዝበ ውሳኔ በመጠቀም በወልቃይትና ራያ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ ትግል ሲደረግባቸው የቆዩትን የማንነት ጥያቄዎች በማያዳግም ሁኔታ ለመድፈቅ መሆኑ ይታወቃል። እዚህ ላይ ወልቃይት ስንል ከተከዜ ምላሽ ያሉትን ጠለምት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ እና ራሱ ወልቃይት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

ትህነግ አላማውን ለማሳካት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በወልቃይት እና ራያ ሰፊ የአፈና፣ ግድያ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እያከናወነ ይገኛል። እንደሚታወቀው የወልቃይት እና የራያ ማንነት ጥያቄዎች በአካባቢው ተወላጆች እና በአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ትግል ሲደረግባቸው የቆዩ እና አሁን ለመጣው አንጻራዊ ለውጥ ዋነኛ ማስፈንጠሪያ ሁነው ያገለገሉ ቢሆንም ለውጡን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር አሁን ድረስ ለጥያቄዎቹ መፍትሄ ሳይሰጥ ቆይቷል።

Related stories   የተላላኪው ጠበቃዎች

በተለይም የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት በሚፈቅደው አሰራር መሰረት ሁሉንም ሂደቶች አልፎ አቤቱታው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የደረሰ ቢሆንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እልባት ሳይሰጥበት አሁን ድረስ በእንጥልጥል ቆይቷል።

በወልቃይት እና በራያ አካባቢዎች እየተፈጠረ ካለው ሰብአዊ ቀውስ (Humanitarian Crisis) እና በሕግ አግባብ የማንነት ጥያቄው ቀርቦ ለበርካታ ዓመታት በይደር ከመያዙ አንጻር፣ የወልቃይትና ራያ አካባቢ ሕዝብ እና በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ ከቅዳሜው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቸኳይ ስብስባ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ እንደሚመከረበት እና ውሳኔ እንደሚተላለፍ ይጠብቃል።

የመጀመሪያው ጉዳይ በወልቃይት እና ራያ ምርጫውን ተገን አድርጎ ትህነግ ማንነትን መሰረት ያደረገ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየፈፀመ መሆኑን በጥልቀት እንደሚወያይበት ይጠበቃል። ትህነግ በሁለቱ የአማራ አካባቢዎች የሚኖረውን የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ አማሮችን የመግደል፣ አፍኖ ወደ አልታወቀ ስፍራ የመውሰድና የማፈናቀል ስራ እየፈፀመ ነው። “አማራ ነኝ” የሚል አካባቢውን ለቆ ይውጣ፣ ይህ “ትግሬ ብቻ” የሚኖርበት ነው በማለት ከፍተኛ ወከባና አፈና እየፈፀመ ነው።

በተጨማሪም የአማራውን ማህበረሰብ ለጦርነት ብር አምጡና ሥንቅ ቋጥሩ በማለት ከፍተኛ ማዋከብ እየፈፀመ ነው። ትህነግ በአካባቢዎቹ እየፈጠረ ያለው ሰብአዊ ቀውስ፣ በስራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት እና እሱን መሰረት አድርገው በወጡ ሕጎች መሰረት የፌዴራል መንግስሥቱ በአካባቢዎቹ ጣልቃ እንዲገባ እና እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት የማስቆም ግዴታ ይጥላል።

የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሥርአት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሰረት የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጣልቃ ሊገባ ከሚችልባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ሰብአዊ ቀውስ (Humanitarian Crisis) መሆኑ በግልጽ ተመልክቷል። ትህነግ በወልቃይት እና ራያ ላይ እየፈጸመ ያለው ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን እና ሰብአዊ ቀውሱን የማስቆም ግዴታ በፌደራል መንግሥቱ ላይ የሚጥል ሲሆን፣ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ ገብቶ አካባቢዎቹን ከትህነግ የጸጥታ ሃይሎች ነጻ የማድረግ ሃላፊነት የሚጥል ነው።

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

በወልቃይት እና በራያ አካባቢ እየተፈጠረ ካለው ሰብአዊ ቀውስ በተጨማሪ የወልቃይትና የራያ አማራ ማሕበረሰብ ከላዩ ላይ የተጫነውን አዲስ ማንነት በመቃወም ትግል ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል:: የአማራ ማንነቱ እውቅና ተሰጦት በኃይል እንዲቀላቀል ከተደረገበት የትግራይ ክልል ወጥቶ ከሰፊው የአማራ ማሕበረሰብ ወገኑ ጋር ለመቀላቀል ግልፅ ጥያቄ አቅርቦ ትግል እያደረገ ይገኛል:: የወልቃይትና ጠገዴ ሕዝብ ደግሞ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አቋቁሞ በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ያስቀመጠውን ሂደት ሁሉ አሟጦ ጥያቄው ምላሽ እንዲሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ፅ/ቤት ከአስገባ 3 ዓመት አልፎታል::

በአለፉት ዓመታት ምክር ቤቱ በትህነግ ተጠፍንጎ የተያዘ ስለነበር ጥያቄውን ለማስተናገድ ፈቃደኝነት አልነበረም:: የአፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ወደ ኃላፊነት መምጣት ምክር ቤቱ ከትህነግ ፍላጎት ማስፈፀሚያነት እንዲላቀቀ በር ከፍቷል ተብሎ ይገመታል። በመሆኑም ምክር ቤቱ ከፊል የዳኝነት ሥልጣን (quasi judicial power) ያለው በመሆኑ ይህን ሥልጣኑን በመጠቀም የወልቃይትና ራያ ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ትህነግ እያደረገ ያለውን ጥያቄውን የማፈንና የመቅበር እንቅስቃሴ እንዲያቆም እግድ (injunction) እንዲሰጥ፣ እግዱንም የፌደራል መንግሥቱ በፀጥታ ኃይሉ አማካኝነት እንዲያስፈፅም ለማዘዝ ስልጣን ያለው በመሆኑ፣ በሕግ አግባብ የቀረበው የማንነት ጥያቄ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ አካባቢዎቹ ከትህነግ ቁጥጥር ስር ውጭ ሁነው በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ውሳኔ እንደሚሰጥ የአማራ ህዝብ ከምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ የሚጠብቀው ውሳኔ ነው።

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

የፌዴራል መንግስት በወልቃይት እና ራያ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት፣ ትህነግ በአካባቢዎቹ ሲፈጽም የኖረውን እና እየፈጸመ ያለውን ግፍ የማስቆም ውጤት ብቻ ሳይሆን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ተደራራቢ ፖለቲካዊ ድል የሚያስገኝለት ውሳኔ ነው። አስተዳደሩ የሁሉንም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ያገኛል፣ የሁመራ-ኦማህጅርን መስመር ክፍት በማድረግ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከርና በአንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ በአካባቢው ጅኦፖለቲክስ ወሳኝ ድል ያስመዘግባል፣ ከሁሉም በላይ በተለይ በወልቃይት በኩል የሚደረገው ጣልቃ ገብነት እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ መልኩ ትህነግ ከሱዳን ጋር ያላውን ግንኙነት በመቁረጥ የትህነግ ፍጻሜ ማሳራጊያ ይሆናል።

ስለሆነም የቅዳሜው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ትህነግ በወልቃይት እና ራያ ላይ ለበርካታ አስርት ዓመታት ስትፈጽመው የኖረችውን ግፍ እና መከራ ፍጻሜ እንደሚያስከትል የምንጠብቅ ሲሆን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአካባቢዎቹ የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ተባብሶ ሃገራዊ ቀውስ ቢያስከትል የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፌዴራሉ መንግስት ኃላፊነቱን የሚወስዱ ይሆናል።

© መልካሙ ሹምዬ ኮከብ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0