በመጀመሪያ ደረጃ በተለምዶ ዝም ብሎ የሚነገረው ነገር መቆም አለበት። ብዙ ጊዜ የኢዜማ መሠረት ከተሞች ላይ ነው የሚባለው ነገር ተቀባይነት የለውም። ይህንን የሚሉ ሰዎች በጥናት ያረጋገጡት ነው ብዬ አላምንም። እኛ ይህንን ጉዳይ ብንናገር ያምራል። ምክንያቱም ስናደራጅ ወደ ሕዝቡ ስንወርድ የምናያቸው ነገሮች የሕዝቡን ስሜት በአግባቡ ያሳወቁን በመሆኑ ነው። ለምሳሌ መቶ በመቶ ደቡብ ክልል ላይ ቀድመን አደራጅተናል። አማራ ክልል በመጀመሪያ 90 በመቶ ነበር በሂደት መቶ በመቶ ማድረግ ችለናል።

ማህሌት አብዱል

የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ጎንደር ክፍለሀገር ደቡብ ጎንደር ውስጥ በምትገኝ ቀሳ በምትባል አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው። እስከ 12 ዓመታቸው ድረስ በዚያችው መንደር በሚገኝ ደብር ቅስና ሲማሩ ቆዩ። በ1977 ዓ.ም ደግሞ አዲስ አበባ ከሚገኙት አያታቸው ቤት በመምጣት ዘመናዊ ትምህርት ቀድሞ መስከረም ሁለት አሁን ደግሞ ባታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ተማሩ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ምንም እንኳ ትምህርታቸውን ዘግይተው ቢጀምሩም በቤተክህነት የቆጠሩት ፊደል እገዛ አደረገላቸውና በዓመት ሁለት ጊዜ ክፍሎችን በማለፍ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከዕድሜ እኩያዎቻቸው ጋር ማጠናቀቅ ቻሉ። ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ደግሞ ዘጠነኛና አስረኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ሴንጆሴፍ ትምህርት ቤት በመግባት ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ በአገራቸውና በታሪክ ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ካውንስል ውስጥ የአካዳሚክና አድሚኒስትሬሽን ሊቀመንበር እንዲሁም ከ12ቱ ሥራ አስፈፃሚ አባላት መካከል አንዱ በመሆንም አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ማህበረሰብ የሚባል ማህበር ውስጥ ለሁለት ዓመት ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል። ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ ደግሞ የራሳቸውን ፓርቲ ከጓደኞቻቸው ጋር ለማቋቋም ቢያስቡም ኢዴፓ ተመስርቶ ስለነበር ፓርቲውን ተቀላቀሉ። ፓርቲው በ1997ዓ.ም በቅንጅት ስር እስከሚዋሃድ ድረስ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል። እንግዳችን አቶ አንዷለም አራጌ ቅንጅት ከምርጫ ጋራ ተያይዞ ከገዢው ፓርቲ በነበረው ግጭት ከታሰሩት አመራሮች አንዱ ሆነው ለሁለት ዓመታት ወህኒ ቆይተዋል።

ከእስር ከተፈቱ በኋላ ግን ፖለቲካን እርግፍ አድርገው ፊታቸውን ወደ ግል ሕይወታቸው ለማዞር ተገደው ቢቆዩም፣ በአገሪቱ የነበረው ጨቋን እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመታገል አንድነት ፓርቲን ከሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ጋር መሰረቱ። በትግል ውስጥ እንዳሉም ዳግም ለእስር ተዳረጉ። በወህኒ ቤትም የአዕምሮ መቃወስ የሚያደርስ ጫና የተደረገባቸው እኚሁ የፖለቲካ ሰው በአገሪቱ ለውጥ መምጣትን ተከትሎ ከእስር የመፈታት ዕድል አጋጠማቸው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢዜማን ከመሰረቱት አንኳር ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ሆኑ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ፓርቲውን በምክትል መሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአቶ አንዷለም አራጌ ጋር በግል የፖለቲካ ሕይወታቸውና ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ቃለምልልስ አድርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካው መስመር የገባህበትን አጋጣሚ አስታውሰንና ውይይታችን እንጀምር?

አቶ አንዷለም፡- የአገር ፍቅር ዕዳ በሚለው መጽሐፌ ላይ በስፋት እንደጠቀስኩት እኔ ያደግሁት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው። ቤተክርስቲያን ውስጥ ደግሞ ሃይማኖታዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ስለሀገርና ስለ ሰላም ይሰበካል። በተለይ ስላሴ ቤተክርቲያን የጀግኖች አባቶቻችን አፅም ያረፈበት በመሆኑ የእነሱን ታሪክ እየዞርኩ እያነበብኩኝ ነው ያደግሁት። እንዲሁም አጎቴ የሰበሰባቸው የኢህአፓ ጊዜ የተፃፉ የፖለቲካ መጻሕፍቶች አነብ ነበር። ትምህርት ቤትም ከፍተኛ ውጤት የማስመዘግበው ፖለቲካና ታሪክ ትምህርቶች ናቸው። በነገራችን ላይ ስድስተኛ ክፍል እያለሁ ነው ወደ ፖለቲካ እንደምገባ የወሰንኩት። ከዚያ ያንን እያሳደኩኝ ነው የመጣሁት። በሌላ በኩል ቤተመንግሥት አጠገብ በማደጌ በራሱ ተፅእኖ እንደፈጠረብኝ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ በተቃዋሚ ጎራ ለመሰለፍ የተለየ ገፊ ምክንያት ነበርዎት?

አቶ አንዷለም፡- ጥሩ ጥያቄ ነው! እንዳልኩሽ ሳድግ ስለኢትዮጵያዊነት፤ ስለሀገር ክብር፤ ስለ ዳር ድንበር፤ ስለባህር በር፤ ስለ ሀገሪቱ ታሪክ እና ገናናነት እንዳውቅ ተደርጌ ነው የተገነባሁት። ኢህአዴግ ሲመጣ ግን ያንን ለዘመናት የተገነባሁበትን ማንነት ናደብኝ። የባህር በር ጉዳይ ታሪክ ሆኖ ቀረ። በተለይ ለታሪክ ዝቅ ያለ ዋጋ እንዲሰጠው መደረጉ ሥርዓቱን መቀበል አቃተኝ። በእርግጥ በወቅቱ ልጅ ስለነበርኩኝ ስለፖሊሲው ጉዳዮች በሚገባ ገብቶኝ ሳይሆን ግን በዋናነት ለሀገር ምሰሶ የሚባሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፤ ታሪኩን ባህሉን ለዚያ የነበረው እይታ ማንነቴን ተፈታተነው። ጥላቻው ከዕለት ዕለት እየጨመረ በመምጣቱ አምርሬ እንድታገለው አደረገኝ። እንደሚታወቀው ደግሞ ኢዴፓ፤ ቅንጅትና አንድነት ፓርቲዎች ውስጥ በነበርኩበት ውስጥ ኢህአዴግን በድፍረት ከሚታገሉት ሰዎች አንዱ ስለነበርኩኝ። በዚህም በድምሩ ለስምንት ዓመት ተኩል ታስሬያለሁኝ።

አዲስ ዘመን፡- ለረጅም ዓመታት እስርቤት ቢያሳልፉም ልክ እንደሌሎቹ ፖለቲከኞች ያሳለፉትን ችግር መናገር አይወዱም፤ ለዚህ የተለየ ምክንያት ይኖርዎት ይሆን?

አቶ አንዷለም፡- እኔ ስላሳለፍኩት ነገር መናገር የማልፈልገው በሦስት ምክንያቶች ነው። አንደኛው ለዚህች አገር ከእኔ በላይ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ሰዎች አሉ። እኔ ያሳለፍኩት ችግር ከእነሱ የሚበልጥ ወይም የሚጋነን ነው ብዬ አላስብም። ብዙ ሰዎች የመጨረሻ የሚባለውን ዋጋ ከፍለዋል። እኔ እግዚአብሔር ይመስገን በሕይወት ቆይቼ የሰው ፍቅርና ክብር አግኝቼ ዛሬ ታሪክ እየተናገርኩ ነው። በሁለተኛ ውስጤን የሚያሙኝና ላስታውሳቸው የማልፈልጋቸው ነገሮች አሉ። እሱንም ማስታወስና መቀስቀስ ስለማልፈልግ ነው የማልናገረው። በተጨማሪም ደግሞ አሁን ላይ እኔ ስለመቻቻልና ስለፍቅር እንድናወራ እንጂ ያለፈው ዘመን እስረኞች እንድንሆን አልፈልግም። እኔም የእስርቤት ሕይወቴን እያሰብኩ ቀሪ ሕይወቴን እስረኛ ሆኜ ማሳለፍ አልፈልግም። ያለፈውን ነገር ባነሳሁኝ ቁጥር እዚያ ህመም ውስጥ ይመልሰኛል። እንደዚህ ዓይነት ቁስል ውስጥ መቆየት አልፈልግም።

ግን ዞሮ ዞሮ የታሰርኩት በድምሩ ስምንት ዓመት ተኩል ለሚሆን ጊዜ ቢሆንም በተለይ ያለፉት ስድስት ዓመት በጣም ከባድ የሚባል እስር ነው። የአዕምሮ ጤንነቴንም ችግር ውስጥ የሚከት ነበር ማለት እችላለሁኝ። ግን ምንም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ነፃነት ዝም ብሎ አይገኝም፤ ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል። ዛሬ ላይ ስማቸው የማይነሳ ነገር ግን የእኛን ግማሽ ዕድሜ ያልኖሩ ወጣቶች ሞተዋል። ስለዚህ እንዲያውም የእኔ መባረክ ነው፤ እግዚአብሔር ትንሿን ነገር ባረከልኝ። አንዳንዴ እንዲያውም ይሰማኛል፤ በእኔ ምክንያት ሌሎች የተከለሉ ይመስለኛል። እኔ በእርግጥ አዕምሮዬን የሚፈታተኑ ነገሮች አጋጥመውኛል። ሊያሳብዱኝም ብዙ ጥረት አድርገዋል። ይሁንና ይሄነው የሚባል አካላዊ ዱላ አልደረሰብኝም። ሌሎቹ ግን የአካልም ሆነ የጭንቅላት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ተፈፅሞባቸዋል። በአጠቃላይ የእኔ ሊነገር ብዬ ብዙ አላምንም። እንዲያውም ፈጣሪን አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ከአንተ ጋር የታሰሩና ተፈተው የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች አሁን በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈው አሁንም እስርቤት ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ አለ፤ ይህንን ሲያዩ ለውጥ ስላልመጣ ነው ሰዎቹ በራሳቸው የተለየ ችግር ስላለባቸው ነው?

አቶ አንዷለም፡- አየሽ በየምዕራፉ የሰውልጅ እይታ ይለያያል። አንዳንዶቹ ለእኔ ከወንድም በላይ ናቸው። ለምሳሌ እኔ በሰላማዊ ትግል የማምን ሰው ብሆንም የእኔ ታናሽ ወንድም በትጥቅ ትግል ነበር የሚያምነው። ከዚህ ወንድሜ ጋር የአንድ እናት ጡት ጠብተን ብናድግም ግን እሱ በኃይል ትግል ያምን ስለነበር ኤርትራ ሄዶ ሲታገል ሞቶ እዛው ነው የተቀበረው። እናም የአንድ እናት ልጅም ሆነሽ በአስተሳሰብ ልትለያዪ ትቺያለሽ። በሌላ በኩል ግን እኔ እውነቱን ለመናገር በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ብዙ መናገር አልፈልግም። ደግሞም ይህንን ስሜት አውቀዋለሁ። ታስታውሺ እንደሆነ እኛ እስርቤት ሳለን «አኬልዳማ» የሚል ፊልም ሰርተውብናል። በወቅቱ እኛ መናገር በማንችለበት ሁኔታ ያንን ፊልም በቴሌቪዥን ያሳዩ ነበር። በወቅቱ በአንዳንዶቹ ጋዜጠኞች በጣም አዝን ነበር። ልክ እንደእውነተኛ ታሪክ ለማስመሰል ሲሉ ደምስራቸው እስኪገታተር ነበር የሚያነቡት። በተለይ ወጣቶች ሆነው ከተማሩበት ሥነምግባር ውጪ የሆነ ሥራ ስለታዘዙ ብቻ ሲሰሩ በጣም አዝን ነበር። እናም አሁን እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ መናገር አልፈልግም። ደግሞም በእኔ መርህ መሠረት አንድ ሰው በፍርድ ቤት እስከሚፈረድበት ድረስ ንፁህ ሆኖ የመቆጠር መብት አለው። ስለዚህ አሁን እኔም ይሄነው ብዬ በትክክል የማውቀው ነገር የለም። የፍርድቤት እስኪያልፍ ድረስ በመንግሥትም፤ በእኛም በኩል ለፍርድቤቱ ነፃነትም ክብርና ንፅህና ሲባል በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ አይመስለኝም።

አዲስ ዘመን፡- ኢዜማ ሲመሰረት ሕዝብ ከጣለበት እምነት አንፃር እየሰራ አይደለም፤ እንዲያውም የመንግሥት ታማኝ ተቃዋሚ ሆኗል በሚል ይተቻል፤ እርሶ ይህንን አስተያየት እንዴት ያዩታል?

አቶ አንዷለም፡- እኛ አገር አየሽ ችግሩ ሁሉም ሰው የራሱ ጀግና ይፈልጋል። በራሱ አስተሳሰብና ምናባዊ እይታ ከአቅምሽ በላይ ይስልሻል። ከዚያም ጎልያድን አሳክሎ ይስልሽና መጨረሻ ላይ ያንን አላከለችም ብሎ መልሶ ይጥልሻል። ታዲያ ይህ የማን ችግር ነው? እኔ ሰው በሚስለኝ ልክ ልሆን አልችልም። እኔ መሆን የምችለው በአቅሜ ነው። ደካማውን እኔን ነው መሆን የምችለው። ሰዎችን ለማከል ብዬ ስወጣጠር አልኖርም። በአቅሜ፤ በችሎታዬ ያዋጣል በምለው መልኩ ነው የምሄደው። ፓርቲም ቢሆን የሚሉትን ለማከል ብሎ ሊወጣጠር አይችልም። ሰው ቁጭ ብሎ ተስፋ ሊያደርግና ሊሰንቅ ይችላል። በእኛ በኩል በአቀድነው መሠረት እየሄድን ነው፤ ስትራቴጂክ ግብ አስቀምጠናል። ዋነኛው ስትራቴጂክ ግባችን ደግሞ ለትውልድ የሚተርፍ ፓርቲ መፍጠር ነው። ፓርቲው ደግሞ የይስሙላ ሆኖ በሁለትና በሦስት ዓመት የሚጠፋ ሳይሆን ፈጣሪ ከረዳን ለረጅም ዘመን ለልጆቻችን መድህን የሚሆን የጠነከረ እየተሻሻለ የሚሄድ ፓርቲ ለማምጣት ነው እየሰራን ያለነው። ያንን ለመፍጠር ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልናል ብዬ አምናለሁኝ። ብዙ ጥሩ ሥራ ሰርተናል። መድገም ካልሆነብኝ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ435 በላይ ወረዳዎች ላይ ተደራጅተናል። 278 ቢሮዎች ከፍተናል። ወደ 45 ፖሊሲዎችን እየሰራ ነው፤ 20ዎቹ ተጠናቋል። 19ኙ ደግሞ በጅምር ላይ ናቸው። ይህንን ሁኔታ ከአገራችን ሁኔታ አንፃር ስታዪው የትኛውም ፓርቲ ይህንን አያደርግም። ስለዚህ አሁን ግባችን ተሳክቷል።

ሁለተኛው ግባችን ደግሞ አገሪቱ ሰላም፥ መረጋጋትና ፍቅር እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ሲኖሩ ነው ዴሞክራሲ ሊኖር የሚችለው። ባልተረጋጋ አገር ላይ ዴሞክራሲም ሆነ ምርጫ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ጭቃ እየተቀባንም አገር እንዲረጋጋ እየሰራን ነው። አሁን ላይ ብልፅግናም ስትተቺ የብልፅግና ሰዎች መሳደብ ጀምረዋል። ብልፅግና ጥሩ ሲሰራ ያንንም እውቅና ስትሰጪ ሌላው ይሳደባል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውንም አቋም ይዘሽ የማትሰደቢበት ሁኔታ የለም። ስድብ እንደፖለቲካ ፋሽን ተወስዷል። እኔ በስድብ የተገነባ አገር አላውቅም። ችግር ካለ መወያየት ነው የሚያስፈገው። በእኛ አገር ያው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንደሚባለው ሁሉ ኢዜማ ልክ የመንግሥት ተለጣፊ ተደርጎ እየተሳለ ነው። እኛ ግን የሚሉትን አይደለንም፤ እንዲያውም ነገ ከነገወዲያ ትልቁ ግብ ግብ ከእኛ ጋር እንዳይሆን ነው ስጋቴ።

Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

በያዝነው መንገድ ግን አንናወጥም፤ እንፀናለን። አንዳንድ ጊዜ ማዕበሉ ወደእዚህ ሂጅ ሲልሽ የምትሄጂ ከሆነ፤ ከማዕበሉ ጋር አብረሽ የምትቀዝፊ ከሆነ አንቺ መሪ አይደለሽም። መሪ ማዕበሉን አቅጣጫ አስቀይሮ ወደ ትክክለኛ መስመር የሚያስገባ ነው። የእኛ ድርጅት ይህንን አቅጣጫ ይከተላል። መቼ ምን ማለት እንዳለብን፤ በምን ያህል መጠን መታገል እንደሚገባው የምናውቀውና የምንወስደው እኛ ነን። ይህም ሆኖ ግን ከሚወቅሱን በላይ የሚያከብሩ ይበልጣሉ። በተለይ ስለመረጋጋት በመስበካችን፤ ስለሰላም በመስራታችን፤ የሚያከብሩን በርካቶች ናቸው። ደግሞ አሁን በተግባር እየታየ ነው። ካልሰከንን ምን ልንሆን እንደምንችል እያየሽው ነው። አገር ይፈርሳል፤ ሕዝብ ይተላለቃል። በታሪካችን ቀርቶ በህልማችን አይተነው የማናውቀው አሰቃቂ ነገር እያየን ነው። እኛ ህመም አለብን። አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ ሰው ሲሞት፤ ሲጎዳ፤ ያልተገባ ነገር ሲደረግ ያሳዝነናል። ግን እኛም ስሜታችንን ሳንጫን በለው ብለን ወጣቱን ግፋ ብንለው ዛሬ በቀላሉ በለው ያልነው ወጣት በአንድ ሺ ቃል ተናግረን አንመልሰውም። እንዲያውም በዚያን ጊዜ ሰይፉን ወደ እኛ ሊመልሰው ይችላል። አንዴ ደም መቃባት ከጀመርሽ ደግሞ አታስቆሚውም።

ስለዚህ የእኛ ጭቃ መቀባት ይሻላል ሕዝባችን ከሚያልቅ። ግን ለእኛ ብልጽፅግናም ቢሆን የምንመርጠው ፓርቲ አይደለም። የተሻለ ፓርቲ ነው ብለን አናስብም። የኢህአዴግ ደመነፍስ አሁንም አለው። ጨርሶ ካለፈው ነገር ፀድቷል ብለን አናምንም። በጣም ብዙ ይቀረዋል። እርግጥ ነው የተወሰኑ በጎ ጅምሮች አሉ። በጎ አስተሳሰቦች አሉ። ግን አንዳንዴ ደግሞ በመሪ ደረጃ ያልተገባ ነገር የሚናገሩበት ሁኔታ አለ። ይህ ሁኔታ የሚሉት ነገር ከልብ እንዳልሆነ እንድንጠራጠር ያደርገናል። እኛ በብልፅግናም አይደለም የምንታመነው፤ በሚያወግዙንም ሰዎች ላይ አይደለም እምነታችን። የምንተማመነው በፈጣሪ፤ በያዝነው መርህና በራሳችን አካሄድ ነው። ተስፋ አለን፤ ሊሳካልን ይችላል። ባይሳካልንም እንኳን የምናምንበትን እያደረግን ነው የምንሞተው።

አዲስ ዘመን፡- እንደጠቀሱት ፓርቲው በርከት ያሉ ፖሊሲዎችን በማውጣት ረገድ ምንአልባት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አንፃር የመጀመሪያው ነው፤ እነዚህ ፖሊሲዎች ከብልጽግና ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች በላቀ ተወዳዳሪ ያደርጉናል ብለው ያምናሉ?

አቶ አንዷለም፡- አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ ወደ 20 የሚሆኑትን ፖሊሲዎች ላይ ከዘጠኝ ወር በፊት ምሁራን ጋብዘን አቅርበነዋል፤ የተሰጡትን ትችቶች ተቀብለናል። ለምሳሌ በኢኮኖሚ ዘርፍ አኳያ ከሰባት ያላነሱ ፖሊሲዎች አሉን፤ ከተፈጥሮ ሀብት፤ ከግብርና ጋር የተያዙ ፓኬጆች አሏቸው። በተመሳሳይ በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት የጤና እና ሌሎችም ተዘጋጅተዋል። እርግጥ ፖሊሲ በየጊዜው የሚሻሻል ነው። ወደፊት ለሕዝብም ይፋ እናደርጋለን። የማኑፌስቶ ዝግጅት ይኖረናል። በተጨማሪም አሁን ላይ የራሳችንን የማህበራዊ ትስስር ገፅ እያበለፀግን ነው። ይህም እያንዳንዱ ወረዳዎቻችን ሳይቀር ዳታ ማስቀመጥ የሚችሉበት ነው። በአጠቃላይ በጣም ዘመናዊ በሆነ መንገድ ነው እየተደራጀን ያለነው። ስለዚህ ከየትኛው ፓርቲ በላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት እየተዘጋጀን ነው ማለት ይቻላል። ምንአልባት ሕዝቡ በሚለው ደረጃ ላንደርስ እንችላለን፤ ነገር ግን እየገነባን ያለነው ፓርቲ ፈረንጆቹ በዝግታ ግን በእርግጠኝነት እንደሚሉት ዓይነት ጥሩ ሥራ እየሰራን ነው ያለነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን እየሰራችሁት ያላችሁት ሥራ ምንአልባት በምርጫው አሸናፊ ብትሆኑ መንግሥት ለመመስራት ያስችለናል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?

አቶ አንዷለም፡- ተስፋ የምናደርገው በዚህ አገር ትክክለኛ ምርጫ ይካሄዳል ብለን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የትኛውም ፓርቲ መቶ በመቶ ያሸንፋል ብለን አናምንም። የሕዝብ ሃሳብም መቶ በመቶ አንድዓይነት አይደለም። ብልጽግና የተወሰነውን ሊወስድ ይችላል፤ እኛ የተወሰነውን ልንወስድ እንችላለን፥ ሌሎችም እንደዚሁ። በእኛ እምነት ዴሞክራሲ በአንድ ምርጫ የሚጠናቀቅ አይደለም። ለምሳሌ እኛ 80 በመቶ ቢሳካልን በሚቀጥለው ዓመት 85 በመቶው የተሻለ ይሆናል። በ20 ዓመት ውስጥ ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ለመፍጠር ነው እየሰራን ያለነው። እናም ሽግግሩ የ20 ዓመታትም ሊሆን ይችላል። በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ከሌሎች ወገኖች ጋር ተቀራቦ መስራትን ይጠይቃል። እውነት ለመናገር ኢዜማ ከኢህአዴግ ያነሰ ፓርቲ አይደለም። ይህም ሲባል ደግሞ እኛ ፍፁማን አድርገን ራሳችንን አንቆጥርም። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፤ ብዙ ምሁራንና ብዙ ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች አሉባት። አንቺ መሪ ስትሆኚ ያለውን ሀብት ተጠቅመሽ አገር ማልማት እንዳለብሽ ማሰብና ለዚያ በጎ ፍቃድ መኖር ነው።

ምርጫ ስላሸነፍሽ ብቻ ሁሉንም ሕዝብ ካድሬ ታደርጊዋለሽ ማለት አይደለም። አንዳንድ በግልጽ ከሙያ ጋር የተያዙ ጉዳዮችን ለባለሙያዎቹ መተው ይገባሻል። ኢትዮጵያውያን ለዚህ ዝግጁ ናቸው። ዘር ወይም ብሔር የምንለው ነገር አይኖርም። የእኛ ሚና በውጭም ሆነ በአገር ያለ ሰው ለአገሩ እንዲሰራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ከዚያም ባሻገር ኬሎች ፓርቲዎች ጋርም ቢሆን ተቀራርበን መስራት አለብን። አሁን ያለውን የሰው ኃይል በደንብ ብንጠቀምበት ለኢትዮጵያ አይበቃም። ምክንያቱም ያለንበት የችግር አረንቋ ጥልቅ በመሆኑ ነው። ወደፊት በጣም መስፈንጠር አለብን። የወጣቱም ሆነ የሥራ አጡ ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው። እናም ተቀራርበሽ ችግሩን ለመፍታት ካልሞከርሽ የሰው ኃይልሽን ተጠቅመሽ ይህችን አገር ወደፊት ማስፈጠር በራሱ ፈታኝ ነው።

ስለዚህ አሁን ላይ በእኛ በኩል መንግሥት ለመመስረት አቅሙ አለን ብለን ብናምንም ዝም ብለን እናምናለን። ይሁንና የግብር ይውጣ ሳይሆን ጥሩ ውጤት ለማምጣት ሲባል ከሁሉም ኢትዮጵያውያኖች ጋር በወንድማማችነት ተቀራርበን እየተወያየን ለመስራት ነው የምናቅደው። ምክንያቱም መንግሥት ሲባል በእርግጥ የአንድ ፓርቲ የተወሰኑ ሰዎች ስብስብ ብቻ አይደለም። መንግሥት ሕዝቡም ሆነ ሠራተኛው ሁሉ ያለበት ነው። ለእኛ ትልቁ ነገር የፓርቲ ግዝፈት ሳይሆን የአስተሳሰቡ ጥራት ነው። ከምናወራው ነገር በላይ ቁርጠኝነታችንን በተግባር ማሳየትን ነው የምንመርጠው። በዚህ ረገድ ምሉዕ ነን ባንልም እስከምርጫ ድረስ የተሻለ ሥራ እንሰራለን ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡- ብሔርተኝነት ወይም የዘውጌ ፖለቲካ በአገር ደረጃ ስር በሰደደበት በዚህ ወቅት ኢዜማ የሚከተለው የዜግነት ፖለቲካ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል ብለው ያምናሉ?

አቶ አንዷለም፡- በመጀመሪያ ደረጃ በተለምዶ ዝም ብሎ የሚነገረው ነገር መቆም አለበት። ብዙ ጊዜ የኢዜማ መሠረት ከተሞች ላይ ነው የሚባለው ነገር ተቀባይነት የለውም። ይህንን የሚሉ ሰዎች በጥናት ያረጋገጡት ነው ብዬ አላምንም። እኛ ይህንን ጉዳይ ብንናገር ያምራል። ምክንያቱም ስናደራጅ ወደ ሕዝቡ ስንወርድ የምናያቸው ነገሮች የሕዝቡን ስሜት በአግባቡ ያሳወቁን በመሆኑ ነው። ለምሳሌ መቶ በመቶ ደቡብ ክልል ላይ ቀድመን አደራጅተናል። አማራ ክልል በመጀመሪያ 90 በመቶ ነበር በሂደት መቶ በመቶ ማድረግ ችለናል። ደቡብ ላይ ያለው የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ፍቅር በዚህ ዘመን የማይጠበቅና በጣም የሚያስገርም ነው። ከዚህ በፊት በጣም ለኢትዮጵያዊነት አርማ ሆነው የሚታዩት ክልሎች አሁን ላይ ወደ ዘረኝነት ያደሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ። በ1997ዓ.ም በነበረው ምርጫ ምሥራቅ ጎጃም ላይ ቅንጅት ትልቅ ሕዝባዊ መሠረት ነበረው። በወቅቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ እንኳን የምሥራቅ ጎጃም ገበሬን ያህል አልነቃም ነበር። በተለያየ ዓመታት ትግል ስላደረገ ገበሬው በጣም ከፍ ያለ ንቃት ነበረው። እንዲያውም ሁለቱ ጎጃሞች የሚባል ታሪክ አለ። ምሥራቁ ክፍል ካድሬዎቹን ይፋለማቸው ነበር። ምዕራቡ ደግሞ ዝም ብሎ ነበር። ልክ የምርጫው ጊዜ ሲደርስ ምሥራቁን ሄደው አፈኑት። በከፍተኛ መስዋትነት ድምፁን ዘረፉት። ምዕራቡ ላይ ግን የእኛ ነው ብለው ስላመኑ ለቀቁት። ሆኖም ምዕራቡ ክፍል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቅንጅትን መረጠ። ከአንድ ወንበር በስተቀር ማለት ነው። እናም የገጠሩ ሰው ብሔርተኝነት ያጠቃዋል የሚባለው ነገር ተገቢ አለመሆኑን ይህ አጋጣሚ ጥሩ ምስክር ነው። ትግራይም ሆነ ኦሮሚያ ላይ ያለው የገጠር ሕዝብ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጣም ነው የሚያምረው። አክቲቪስቶችና የብሔር ፖለቲካ ካድሬዎች በጣም ሊያስጮሁት ይችላሉ። እኛ በእነሱ ጩኸት ልክ እየጮህን ስላልሆና አየሩ ላይ የእነሱ ጩኸት ስለሚሰማ ኢትዮጵያ በብሔር ትበጣጠሳለች ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው።

ኦሮሚያ ላይ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ኃይል አይደለም ሕዝቡን ያቆመው። ሕዝቡን ያቆመው የባጀ፤ የኖረ የኢትዮጵያዊነት ስሜት፤ ተቻችሎ የመኖር እሴቱና ሃይማኖታዊ መርሁ ነው። የፖሊስ ሰራዊት ያቆመው ይመስልሻል? የፖሊስ ሰራዊት ወደነበረበት ሲመለስ እኮ ተመልሶ ግጭቱ ሊቀጥል ይችል ነበር። ፅንፈኞቹ ሌላውም ብሔር እየተከታተሉ ሲያጠቁ እየደበቀና እየተከላከለ ያቆመው ሕዝቡ ነው። ይህን ያደረገው በኢትዮጵያዊነቱ ስለሚያምን ነው። የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አሁን ላይ ፀጥ እንዳለ ባህር ሆኗል። ዝም ብሎ እንደሚፈስ ውሃ። ጥቂቶች ደግሞ እንደሚረብሸው ሞተር ድምፅ እያሰሙ በባህሩ ላይ የሚሄዱ ጀልባዎች ይመስላሉ። እናም ያ ጩኸት የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አንድነት መንፈስ የሌለ አስመስሎታል። ሚዲያው ሲፈጠር፤ ሥራችንን ስንሰራ፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እነዶክተር አብይ ሲመረጡ ሆ ብሎ የወጣው፤ 1997ዓ.ም ኢትዮጵያዊነት ሞተ ሲባል አገሩን ሞልቶ የቆመው አስቀድሞም ሕዝቡ ውስጥ ስሜቱ ስለነበረ ነው። እርግጥ ነው ከዚያ ወዲህ ዘረኝነቱ በከፍተኛ መጠን እንደተስፋፋ ይታወቃል። ግን ኢትዮጵያዊነት ጠፍቷል፤ ዘረኝነት ነግሷል የሚባልበት ደረጃ አይደለም። ነገ ከነገ ወዲያ የትግራይ ሕዝብ እንዲህ የሚሉትን ያሰፍራል። ኢትዮጵያዊነቱ ጎልቶ ሲወጣ ለኢትዮጵያዊነት ክብር ሲቆም እናየዋለን። ዛሬ ግን ሕወሓት ስለሚጨፍርና ስለብሔር ብቻ ስለሚያወራ የትግራይ ሕዝብ አንደበት ተደርጎ ሊወሰድ አይቻልም። እኛ አስቀድሜ እንዳልኩት ትልቁ ግባችን ኢትዮጵያውያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሄዱ ነው። በዚያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንግዲህ ነገሮች ከተከፋፈሉ የውይይቱ ሜዳ ለሁላችን እኩል ከሆነ፤ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ከተካሄደ ካድሬው እንደለመደው ተፅእኖ የማያደርስ ከሆነ ምርጫ ቦርድ እንደሚጠበቀው በፍትሃዊነት የሚያገለግል ከሆነ በጣም ትልቅ ውጤት እናመጣለን ብለን እናምናለን። ግን አገሪቱ በትክክል ምርጫ ተደርጎበት የጨለማ ዘመን ቀርቶ ወደ ብርሃን ዘመን እንደመሸገ ነው የምንቆጥረው። በአጠቃላይ እኛ የምንናፍቀው የኢትዮጵያ ንጋት ማየት ነው። በግሌ የሚያጓጓኝ ምክር ቤት መግባት ሳይሆን ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ነው። እኛ እዛ የሚከፈለኝ ደመወዝ ሌላ ቦታ ተቀጥሬ ላገኘው እችላለሁ። እሱ አይደለም ግባችን ። እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንሰራበት ዘመን ነው። ሕወሓትም ሆነ ብልፅግና ውስጥ ያሉ አካላት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ያስፈልጋሉ። ከዚህ ቀደምም ብዬዋለሁ አሁን የምንደግመው ነገር የሰው ትርፍ የለውም የሚለውን ነው። ሁሉም ሰው ክቡር ነው። ስለዚህ ያለንን ኃይል ሁሉ እንዴት እንስራ የምንልበት ስለሆነ የያዝነውን ወንበር ይዘን ከሌሎች ጋር ኢትዮጵያዊነትን በማሳደግ ወደፊት መግፋት ነው የምንፈልገው።

አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህንን ቢሉም በተለይ አማራ ክልል ላይ የኢዜማ ተቀባይነትና የሕዝብ አመኔታ እየተሸረሸረ መምጣቱን ይነሳል። በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?

Related stories   በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ ዶላር ተያዘ

አቶ አንዷለም፡- በዚህ ሃሳብ አልስማማም። ነገር ግን በተለይ ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ ግንቦት ሰባት ላይ የነበሩ ወታደሮች ማቋቋሚያ ገንዘብ ድርጅቱ ከጀርመን መንግሥት ጋር ተደራድሮ ያስገኘው ብዙ ሚሊዮን ዩሮ አለ። ያ ገንዘብ ለእነዚያ ትጥቅ የፈቱ ወታደሮች ማቋቋሚያ እንዲውል ቢወሰንም እስካሁን ድረስ ካለመሰጠቱ ጋር ተያይዞ አማራ ክልል ላይ የተፈጠረ ቅሬታ አለ። ይህም ጉዳይ ለአማራ ክብር ስሌላቸው ነው ወደሚል ተተረጎመ። የአማራ ልጆች ተዋግተው መጥተው እነሱን አላቋቋማችሁም የሚል ወቀሳ ነበር የነበረው። ግን ዋናው ፍሬ ነገር ግንቦት ሰባት ገንዘቡን ካስገኘ በኋላ የአባላቱን ስም ዝርዝር መዘገበ። ከዚያም በአሜሪካና በጀርመን መንግሥት መካከል «እኔ ነኝ ፕሮጀክቱን የማስተዳድረው» በሚል ውዝግብ ተፈጠረ። የጀርመን መንግሥት ገንዘቡን ኔ ስላመጣሁኝ እኔ ማስተዳደር አለብኝ ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ በበኩሉ የልማት ድርጅቶች ገንዘቡን ስለሚበሉ እኔ ነኝ ማስተዳደር ያለብኝ በሚል አለመግባት ተከሰተ። በእኔ አረዳድ ግን ይህንን የሚያደርጉት ሆን ብለው ይመስለኛል። በመንግሥት አንዳንድ ሰዎች በኩልም ኢዜማን ከሕዝቡ ጋር በማጋጨት ስለተፈለገ ይመስለኛል ገንዘቡን አየር ላይ ያቆዩት። ገንዘቡ እኛ ጋር የለም፤ ለመንግሥት ገብቷል። ስም ዝርዝሩም ለመንግሥት ተላልፏል። እኛ ልናደርግ የምንችለው ግፊት ማድረግ ብቻ ነው። ያ ብር ደግሞ አማራ ክልል ላይ ለነበሩ አባላት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም ለሚገኙ የተሰጠ ነው። እናም ቅሬታው በዚህ የተፈጠረ ነው።

ሌላው እኔ ጎንደር በሄድኩበት ጊዜ አጋጠመ የሚባለው ችግር ረብሻ ያስነሱት 12 የሚሆኑ ልጆች ብቻ ናቸው። ሌላው ሰው በጨዋነት አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ቁጭ ብሏል። ግን አዳራሽ ላይ የተወሰኑ ወጣቶች እንዲረብሹ ተደርገዋል። በመንግሥትም፤ በአንዳንድ ፅንፈኞችም ረብሻው ሲደገፍ ነበር። ፖሊስም ኃላፊነቱን ሊወጣ ስላልፈለገ ደም እንዳይፈስ በመስጋት ስብሰባውን ዘግቼዋለሁኝ አለ። ያም ሁኔታ በአማራ ክልል አካባቢ ተቀባይነት እንደሌለን ተደርጎ ይነሳል። ይህም ሆኖ ግን የጎንደር ሰው ጠልቶኛል ብዬ አላምንም። እንዲያውም በክብር በሆቴልም ባረፍኩበት ቦታ ወጪ አውተው ተንከባክበው ነው የላኩኝ። አማራ ክልል ልክ እንደሌሎቹ አካባቢዎች ከፍተኛ ተቀባይነት አለው። የብልፅግና ኢዜማ ለአገር ግንባታ ብዙ አስተዋፅኦ ቢያደርግም የብልፅግና ሰዎች ተሳስተው እንኳ በጎ ነገር ተናግረው አያውቁም። ምክንያቱም የእነሱ ዋነኛ ትኩረት ስልጣን በመሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን በአማራ ክልል በህወሃት ዘመን የነበሩ ሕዝቡን ሲያፍኑ የነበሩ ካድሬዎች ዛሬም በቦታቸው ሆነው አድራጊ ፈጣሪ ሆነው ነው ያሉት።

አዲስ ዘመን፡- ፓርቲያችሁ በአገር አቀፉ ምርጫ በትግራይ ክልል ዘጠኝ የምርጫ ወረዳዎች ላይ ለመሳተፍ ቢሮ መክፈቱ ይታወቃል፤ የክልሉ መንግሥት በቅርቡ ለማካሄድ ባቀደው ምርጫ ይሳተፋል? ባይሳተፍ የሚያጣው ነገር አይኖርም?

አቶ አንዷለም፡- ሁለት ነገሮች ላይ መናገር እፈልጋለሁ። በአንድ በኩል መንግሥት ምርጫውን ማራዘሙ የሚወቀስበት ነገር ነው ብለን አንወስድም። ምክንያቱም በዓለምአቀፍ ደረጃ በኮሮና ምክንያት በርካታ ምርጫዎች ተራዝመዋል። ሌላው ይቅርና በጣም ደማቅ የሆነው የአሜሪካ ምርጫ እንደከዚህ ቀደሙ አይደለም። ቅስቀሳዎችንም ሆነ ንግግሮች የሚደረጉት በባዶ አዳራሽ ውስጥ ሆኖ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ሕዝቡን ተደራሽ ለማድረግ ነው ጥረት እያደረገ ያለው። ስለዚህ በኢትዮጵያ በኩልም ምርጫው መራዘሙ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅሰው ነው ብለን አንወስድም። ግን ሲራዘም እንደ ሥነ-ከዋክብት ስሌት ይሄና ያኛው ነገር ከገጠመ ተብሎ ዝም ብሎ አየር ላይ አይለቀቀም። እናም በእኛ በኩል እስከአንድ ዓመት ቢሆን ብለናል። ምርጫ ቦርድም ሁኔታዎችን በትክክል ለማስኬድ እየሞከርኩኝ ምርጫውን ማካሄድ እችላለሁ ብሏል። ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ተዘጋጅቶ ሎጅስቲኩን አሟልቶ መቼ መካሄድ እንዳለበት መናገር ይገባዋል። ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከዘጠኝ ወር ብለዋል። ግን የእሳቸው ኃላፊነት ነው ብዬ አላምንም። ምርጫ ቦርድ በይፋ መናገር ነበረበት።

በሌላ በኩል ህወሓትን በሚመለከት ከዚህ ቀደምም በሌላ መድረክ ጠቅሼዋለሁ እኛ ብናምንበትም፤ ባናምንበትም ሕገመንግሥቱን ያወጣው ራሱ ነው፤ ሲመራበት ነበር። እሱን አላከበራችሁም እየተባልን ብዙ በደል ደርሶብናል። አሁን ግን መልሶ ራሱ የወለደውን ልጅ ራሱ እየገደለ ነው። ተገቢ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ደም የሚያቃባ ነገር ሰራዊት አዘጋጅቶ ማስፈራሪያና ዛቻ ማድረግ አይጠበቅበትም። የሚያሳዝነው ነገር አንዱም የህወሓት ባለሥልጣን ሄዶ አለመሞቱ ነው። በተመሳሳይ የብልፅግና አመራር ሄዶ አይሞትም። የሚሞተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። የሚጋደሉት የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። ይህንን ግፊት እያደረገ ያለው ደግሞ በዋናነት ህወሓት ነው። ሕወሓት እንደሌሎቻችን ታግሶ መጠበቅ ሲኖርበት በተለየ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለመምሰል ሲባል ሕዝብ ለማጫረስ ጥረት እያደረገ ነው። ዕድሉ በነበረው ጊዜ ዴሞክራሲ በአገሪቱ ማስፈን ሳይችል አሁን ላይ ለዚያውም ሕገመንግሥት ጥሶ በሚያካሂደው ምርጫ ዴሞክራሲ ለማስፈን ነው ቢል ተቀባይነት አይኖረውም። ከብልፅግና ሰዎች ጋር በተጋባው እልህ ምክንያት እንዲህ ዓይነት የተዛባ ነገር መስራት ትክክል አይደለም። ምንም ጥያቄ የለውም። በመንግሥት በኩል ደግሞ ምንም ያልተገደበ ሁኔታ ነገሩን ዝም ብሎ መተዉ ትክክል አይደለም። እናም ከፉከራው፤ ከዛቻው አልፎ ግን ከመጋረጃ በስተጀርባ ትላልቅ ሥራዎች መስራት ይጠይቃል። በእርግጥም ይህንን ዘመን የምንመጥን ከሆነ የኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎች እንሆናለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ቁጭ ብለው ማውራት ይጠበቅባቸዋል። አባቶቻችንም በዚህ መንገድ ነው ያለፉት። ከብዙ ደም መፋሰስና ፍጥጫ መሃል አንዱ ሌላውን ይቅር ተባብሎ የኖሩበት ዘመን አለ።

አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንዳሉት በአገር ሽማግሌዎች በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጥረት ተደርጓል፤ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ይህ ጉዳይ በሽምግልና ይፈታል ተብሎ ይታመናል?

አቶ አንዷለም፡- እኔ መንግሥት ወደ ኃይል እርምጃ አለመግባቱን እደግፈዋለሁ። ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሚሰራው ለሰው ልጅ ነው። እናም የዜጎችን ደም እያፈሰስሽ ደግሞ ለዜጎች እቆረቆራለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው። ለዜጎች ክብር የማትሰጪ ከሆነ፤ የእነሱ መሞት ግድ የማይሰጥሽ ከሆነ ስለዜጎች እቆረቆራለሁ የሚለው ነገር ብዙ አያስኬድሽም። ስለዚህ በመንግሥት በኩል የትግራይ ሕዝብም እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት ጠግቧል፤ ችግር ጠግቧል፤ መከራ አይቷል፤ ብዙ ልጆችን ቀብሯል። አሁን ደግሞ እንደገና ሌላዓይነት ደም መቃባት ውስጥ መግባት የለበትም። ስለዚህ ወደ ጦርነት አለመገባቱን በጣም ነው የምደግፈው። በእኛ አጉል ፉክክር ልጆቻችን መሞት የለባቸው። በእርግጥ አንድ ወቅት ላይ ጦርነት ተደርጎ አንዱ ሊያሸንፍ ይችላል። በሌላ ዘመን ደግሞ ለሌላ ቂም በቀል ያዘጋጅሻል። ይህን ጉዳይ መዝጋት የሚቻለው በሰላም መንገድ ነው። እርግጥ የሰላም መንገድ ብዙ ጊዜ ከባድ ነው። ግን ውጤቱ ደግሞ በጣም ጣፋጭ ነው። እናም አንድ ሙከራ ስለተካሄደ በቀጣይ አይሳካም ማለት አይደለም። በነገራችን ላይ ሙከራው የከሸፈው ከቀናነት እጦት ነው። በአንደኛው ወገን ቀናነት ጎድሏል ማለት ነው እንጂ ይህ የማይፈታ ችግር ስለሆነ አይደለም። ችግሮች እንዳይፈቱ የማያደርገው የገዢዎችና ተወያዮች የአስተሳሰብ ችግር ካንሰር ሆኖ ሲቆይ ነው። ይህ ዓይነቱ ካንሰር ያለባቸው ሰዎች የሞት ሽረት ካልሆነ ብለው አሻፈረኝ ይላሉ። እንዲህ ዓይነቱን ሰዎች ወደጎን ማድረግና ቀናነት ያላቸው ሰዎች ወደመድረኩ የሚመጡ ከሆነ ችግሩ አይፈታም ብዬ አላስብም።

በሌላ በኩል ግን የትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለጊዜው ብዙ ችግር ላይኖር ይችላል። ግን ደግሞ አገር አቀፉ ምርጫ ሲካሄድ ትግራይም ውስጥ መካሄድ አለበት። አሁን ላይ በትግራይ ለዓመታት ተቃዋሚ ሆኖ የቆየው አረናን ጨምሮ ሌሎችም አይሳተፉም። ምንአልባት ህወሓት አንድ ሁለት ፓርቲዎችን ይዞ ብቻውን ሊወዳደር ይችላል። በእርግጠኝነት ደግሞ በከፍተኛ ልዩነት አሸነፍኩኝ ሊል ይችላል። ከዚያ በኋላ አገር አቀፉ ምርጫ ትግራይ ላይ ሲካሄድ ምንድን ነው የሚሆነው? በእኔ እምነት ያን ጊዜ ትልቅ ፍጭት ይፈጠራል። ምክንያቱም አንዴ ተመርጬያለሁ መንግሥት ነኝ ማለቱ አይቀሬ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የሚቆይ ግን የሚጠብቀን ሌላ ችግር እንዳለብን ነው የማስበው። መዘዙ ሰንሰለት ሆኖ ከሚመጣ ግን አንዱ ለሌላው የወንድ በር ሰጥቶ በመግባባት ችግሩን ማስቆም ይገባል።

አዲስ ዘመን፡-የወንድ በር ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ አንዷለም፡- የወንድ በር የሚለው ቃል በፖለቲካው የተለመደ ነው፤ ለምሳሌ በባህላችን የማርያም መንገድ ይባላል፤ አንድ ሰው ባለው ጠባብ መንገድ አጥሮ አላሳልፍ ቢልሽ የማርያም መንገድ ስጠኝ ትዪዋለሽ። እናም ትንሽ ኮሪደር ይሰጥሽና ታልፊዋለሽ። አንቺ ያጋጠመሽ ችግር ካለ፥ በሰው ፊት አንቺን የማያዋርድ የሚመስለውን ነገር በርዘግቶ አንቺን ከማዋረድ ያንቺን ክብር ጠብቆልሽ አንቺም ማድረግ የሚገባሽን ማድረግ እንደማለት ነው። ልክ እንደዚያ ሁሉ ሁለቱም በመሸናነፍ ለመግባባት ዕድሉን መክፈት ይገባቸዋል ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡- ኢዜማ በትግራይ ክልል ምርጫ ይወዳደራል ግን?

አቶ አንዷለም፡- አይ እኛ አንወዳደርም።

አዲስ ዘመን፡- ፓርቲያችሁ ምርጫውን በሚመለከት በይፋ የህወሓትን አካሄድ የማይቃወመው ምንአልባት ብንወዳደርም አናሸንፍ ከሚል መነሻ ይሆን?

አቶ አንዷለም፡- አቋማችንን በቅርቡ ነው የገለፅነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳልሽው በሰዎች ዘንድ እንወቀሳለን። ግን ደግሞ የህወሓት አካሄድ ትክክል አለመሆኑን ብዙዎች ይናገሩታል፤ የእኛ መጨመር አለመጨመር የሚቀንሰው የሚጨምረው ነገር አይኖርም። ግን ማሳወቅ እንዳለብን አናምንም። እንደተባለው ትግራይ ላይ በስፋት አልተደራጀንም። ወደ ዘጠኝ ወረዳዎች ላይ ነው የተደራጀነው። የእኛ መነሻ ግን ምንያህል ወረዳ ሸፍነናል ወይም አልሸፍንም አይደለም። እኛ ለሰዎች ግልፅ ለማድረግ እየሞከርን ያለነው ለአገር ይጠቅማል አይጠቅምም ነው። አንድም ወረዳ ላይኖረን ይችላል፤ ግን የኢትዮጵያ ነገር ይመለከተናል እስካልን ድረስ አንድ ቦታ የሚሰራው ሥራ ለአገር ምን ያህል ይጠቅመናል የሚል ነው መነሻችን። ጉዳዩ ስለምንወዳደር ወይም ስለማንወዳደር አይደለም። እኛ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ደጋግመን የምንናገረው ካስፈለገ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ይሁን እንጂ ባንመረጥም ችግር የለብንም። አንዳንዶቹ እንዲያውም «ፓርቲ ሆናችሁ እንዴት እንዲህ ትላላችሁ?» ይሉናል። እርግጥ ነው መመረጥ እንፈልጋለን፤ ግን የመጀመሪያ ግባችን አገሪቱ ሰላም ሆና ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሸጋገር ከቻለች ለእኛ ከድል በላይ ነው። እኛ የምናሸንፈው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ነው። ግን ለምሳሌ ምርጫ በሆነ ምክንያት አሸንፈን አገር ብትሸነፍ ትርምስ ውስጥ ብትገባ ለእኛ ውርደት እንጂ ድል ወይም ክብር አይደለም። እኛ የምንፈልገው የእኛ ዕጩዎች እዚያ ተወዳድረው ማሸነፍ አለማሸነፋቸው አይደለም። በዚህ ሁኔታ አገሩ ያሸንፋል ወይ የሚል ነው። ይህ ደካማ አስተሳሰብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የራያና ወልቃይት ሕዝብ በተለያየ መንገድ በህወሓት ጭቆና እየደረሰበት እንደሆነ ይገልፃል፤ በዚህ ላይ የፓርቲያችሁ አቋም ምንድን ነው?

Related stories   "በፕሮፓጋንዳ እስካሁን የተወናበድኩት ይበቃኛል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብም ይገባል ... ወጣቱን ያለ እድሜው ህይወቱን ይቀጩታል"ሌ.ጀ ዮሐንስ

አቶ አንዷለም፡- በአጠቃላይ ህወሓት አምባገነን ፓርቲ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ህወሓትን የሚመሩት በዚያ አምባገነን ሥርዓት ውስጥ ያለፉ ናቸው። ግን የህወሓት አምባገነንነት አስኳል የሆነውና የመጨረሻውን ምሽግ ያደረገው የትግራይ ሕዝብ ላይ ነው። በዚያ ክልል ውስጥ ያለው ሕዝብ የዚያ አምባገነንነት ገፈት ቀማሽ እንደሆነ እናውቃለን። ስለዚህ ህወሓት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫውን ካካሄደ ያሸንፋል ብለን አንጠብቅም። እኛም ትግራይ ውስጥ የተደራጀነው ህወሓትን በሰላማዊ መንገድ ለማሸነፍ ነው። ብልፅግናንም ቢሆን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማሸነፍ ነው የምንፈልገው። ስለዚህ አሁን ችግሮች አሉ፤ የድንበር ጥያቄውም መፈታት አለበት ብለን እናምናለን። ለእኛ ይህ የድንበር ችግር መፍታት ያን ያህል የኑክለር ሳይንስ ዓይነት ከባድ አይደለም። ትግራይም ሆነ ሌላው አካባቢ የኢትዮጵያ አካል ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ክልል ሄዶ መስራት ይችላል። ስለዚህ በዚያ ቋት ውስጥ ስላየነው እንጂ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሲታይ ያን ያህል የሚያጋድለን አይደለም። ምክንያቱም ድንበር በውጭ አካል ቢነካ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም እንዳደረግነው ወጥተን እንሞታለን። የጎንደር አካባቢም በሱዳን ቢጠቃ በተመሳሳይ እናደርጋለን። አፄ ዮሐንስም ይህንን ነው ያደረጉት። አፄ ዮሐንሰ የትግራይ ድንበር ላይ አይደለም የሞቱት። ዮሐንስ የሞቱት መተማ ላይ ነው። አሉላ አባነጋ ዕድሜ ዘመኑን በሙሉ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ላይ ቆሞ ያረጀ ጀግና ነው። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ነው እንጂ ለአንድ ጠባብ ክፍል ተብሎ የሞተ ጀግና የለንም። አሁን ችግሩ የመጣው የከፋፍለህ ግዛው ሥርዓት በመዘርጋቱ ነው። ይህ ሥርዓት ታዲያ በአስተሳሰብም በስጋም እየለያየን የየራሳችን ጎጥ እያበጀን እንድንሄድ አድርጎናል። ሌላው ግን አገሩ አልበቃው ብሎ ከሌሎች አገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር እያደረገ ዓለም እየዳሰሰ ነው ያለው። ከዚህ አልፎ ወደ ፕላኔቶች እየሄደ ነው ያለው። እኛ ደግሞ ጠበን ጠበን ከአገር ወደ ክልል ከክልል ዞን ከዞን ወረዳ ቀበሌ ደርሰናል። ስለዚህ ይሄ የዘር ስሌት ነው እንጂ ችግሩ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለ የድንበር ጥያቄ ደም ሊያቃባን አይገባም። በድንበር ኮሚሽን ረገድ ይህ ጉዳይ እንደተያዘ አውቃለሁ። የአገር ሽማግሌዎችንና ታሪክን የሚያውቁ ምሁራን እስከተሳተፉ ድረስ ችግሩ በአግባቡ ይፈታል ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡- ህወሓት አደርገዋለሁ ብሎ እየተዘጋጀ ካለው ምርጫው ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግሥት ምንዓይነት እርምጃ መውሰድ ይገባል ይላሉ?

አቶ አንዷለም፡- መንግሥት ከህወሓት ጋር ጦርነት እንዲገጥም አንፈልግም። ምክንያቱም የህወሓት ሰዎች ስላልሆነ የሚዋጉት ሕዝብ ከወንድሙ ጋር እንዲጋደል አንፈልግም። ሌላው ይቅርና ሰዎች ያለፍላጎቶታቸው ካርድ እንዲወስዱ ማድረጉ በራሱ የሚወገዝ ተግባር ነው። ነገር ግን ይህ የማንአለብኝነት ተግባሩ ሲቀጥል ጦርነት አማራጭ አይደለም። እኛ ደግሞ በሰላማዊ ትግል የምናምን ሰዎች ነን። በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ ችግሮች መፈታት አለባቸው። ይህም ባህል እንዲዳብር እንፈልጋለን። ስለዚህ ችግሩ ወደ ውይይት ጠረጴዛ መመለስ አለበት።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ከየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ከሚከተል ፓርቲ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላችሁ ገልፃችኋል። ይህ ፍላጎት ግን በተለይ እንደኦነግ ያሉ ፓርቲዎችን ያካትታል? ከሆነስ ከወዲያኛው አካል ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል?

አቶ አንዷለም፡- እንዲያውም መነጋገር ያለብን እንደኦነግና ህወሓት ካሉ ፓርቲዎች ጋር ነው። በጣም ከተቀራረብሽና ብዙ ልዩነት ከሌለሽ ብዙ ችግሮች ይፈታሉ ብለን እናምናለን። ደግሞም የራስን ሃሳብ ለመግለፅ ብዙ መቀራረብ ላያስፈልግሽ ይችላል። የተለየ ሃሳብ ካለው ኃይል ጋር በሰራሽ ቁጥር ስህተቱ ማን ጋር እንደሆነ ለማወቅ ያስችላል። እሱን ደግሞ በቀናነት ተቀራርበሽ መነጋገር ትቺያለሽ። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ወጣ ያሉ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር ያስፈልጋል። ታስታውሺ እንደነበረውም በዴስቲኒ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ላይ ከአቶ ዳውድና ከአቶ ቀጄላም ጋር ተቀራርቦ ለማውራት ዕድል አግኝቼ ነበር። እኔ ሁለቱን ግለሰቦች እንዳየዃቸው በችግር ረመጥ ውስጥ የበሰሉ ሰዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁኝ። ብዙ ያለፉበት ነገር ብዙ ያስተማራቸው ተነጋግረሽ በተጨባጭ አሳማኝ በሆነ ነገር የምትግባቢያቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው።

የነበረኝ ትውውቅ በእርግጥ በግል ነበር። ስለዚህ ተቀራርበን መስራት እንችላለን። ይህንን ደግሞ የምለው ለይስሙላ አይደለም። በተጨባጭ መሬት ላይ እንዲወርድ ነው የምንፈልገው። ምክንያቱም ይህች አገር የሊሂቃን ውይይት ያስፈልጋታል። ምክንያቱም ማዕበሉን ወደዚህም ወደዚያም የሚላጋው ሊሂቃን በመሆናቸው ነው። በሊሂቃን በኩል የሚደረግ ስምምነት መቀራረብ መግባባት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያመጣው ጥሩ ነገር ይኖራል። ስለዚህ ኢዜማ ኃላፊነቱን ይወስዳል። ችግር በኃይል አይፈታም። ችግር የሚያባብስ መሆኑን ከኢትዮጵያ በላይ ምስክር የለም። ያለፍንባቸው ነገሮች ይህንን ነው የሚያሳዩት።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ባለፈው ሁለት ዓመት መንግሥት ሕግ ማስከበር ላይ የላላ አካሄድ ነው እየተከተለ ያለው እየተባለ ሲተች ነበር። ከቅርብ ጊዜ ደግሞ ሕግ ማስከበር ሲጀመር አፈና ተካሄደብን የሚል ቅሬታ እየተሰማ ነው። እነዚህን ሁለት ፅንፎች ሊያቀራርብ የሚችል ምን ነገር ሊኖር ይችላል ብለው ያምናሉ?

አቶ አንዷለም፡- መቼስ ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር እንደሚባለው ሁሉ ዓይነት በእኛ አገር እየሆነ ያለው። እኛ ለዚህ በአንድ በኩል ብዙ ለመፍረድ ብዙ ለመተቸት የማንፈልገው። የመንግሥት ጫማ ስር ለመቆም ስለምንሞክር ነው። እናም ላለፉት ሁለት ዓመታት በጎ ፍቃድና ተነሳሽነት ካላቸው ወደ ጥሩ አቅጣጫ ሊሄዱ ይችላሉ። ግን ሁለት ዓመት ደግሞ በሌሎች አገሮች ሙሉ ዝግጅት ተደርጎ አገር ወደ ዴሞክራሲ የሚሸጋገርበት ነው። እናም የወሰዱት ጊዜ ቀላል አይደለም። በዚህ ጊዜ አገርን በደንብ ማረጋጋት የሚችሉበትን አቅም ማዳበር ይገባቸው ነበር። መጀመሪያ አየሽ ለዴሞክራሲ መሠረቱ የሕግ የበላይነት ነው። የሕግ የበላይነት ደግሞ በአንድ ምሽት የሚረጋገጥ አይደለም። የሥራሽ መጀመሪያ ግን መሆን የሚገባው ሕግ ማስከበር ነው። በደንብ ሕግ እየተከበረ በሄደ ቁጥር የመንግሥት ህልውና የሚረጋገጠው።

እንደሰው ፍቅርና መቻቻልን መስበክ ልታበዢ ትቺያለሽ። ነገር ግን ይህ ዓለም የህልም ዓለም አይደለም። የተለያየ የሰው ባህሪና ፍላጎት አለበት፤ ብትወጂውም ባትወጂውም ሕግ ማስከበር እንደመንግሥት ግዴታሽ ነው። እናም ብዙ ጊዜ በሕግ የበላይነትና በሆደ ሰፊነት መካከል ያለውን ደረቅ መሬት መፈለግና እዚያ ላይ ቆሞ በሚዛኑ መስራት ይጠበቃል። በእኛ በኩል ሁለቱ ነገሮች ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ እየነገርናቸው ነበር። ሁሉም ነገር ሲጠፋ ዝም ብሎ የማየት ነገር እየተበራከተ መጣ። አየሽ ትናንት አስር ሰዎች ሲገደሉ ዝም ካልሽ ከአንድ ወር በኋላ መቶ ይሆናሉ፤ ከዚያም አንድ ሺ እየሆነ መጥቷል። ከመጀመሪያውም ጥብቅ አሠራር መከተል ነበረባቸው። ለዚሁ ሁሉ ችግር መሠረት ግን ካድሬው ነው ባይ ነኝ። ለምሳሌ ደቡብ ላይ ከኋላ ነገሮችን እያቀጣጠለ እየገፋ ያለው ካድሬው ነው። የካድሬ ግብ ግብ ነው ወደ ሕዝብ ግብግብ እያደገ የመጣው። በጣም ቅር የሚለኝ ግን ብዙ የሰው ሕይወት እየጠፋ ባንዲራ እንኳን ዝቅ ብሎ አይውለበለብም። ወጥተው በመሪ ደረጃ አያወግዙም። ልክምንም እንዳልተፈጠረ ይቀጥላሉ። ነገ ደግሞ ሌላኛው ይቀጥላል።

አሁን ደግሞ ሕግ ማስከበር ተጀምሯል። ተገቢ ነው እንጂ መጥፎ አይደለም። ግን አሁን ሕግ ማስከበር ሲባል ሕግ በሚፈቅደው ደረጃ ተጠያቂ ማድረግ ማለት ነው። በማንአለብኝነት ዝም ብሎ አስፈራርቶ ሕግ ለማስከበርም አይቻልም። የሰው ልክ ክቡር ነው። መብቱ የሚከበረው በሕግ እንደተደነገገው ነው። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የበዛና ሕግን ያላገናዘበ ዝም ብሎ በማናለብኝነትና የጎረምሳ ተግባር የሚመስል ነገር እየታየ ነው። እሱ መታረም አለበት። ጀማሪዎች ነን። ወደ ሕጉ መመለስ አለባቸው። አሁን ደግሞ በአምባገነንነትና በሆደሰፊነት መካከል ያለውን ደረቅ መሬት ማየት ያስፈልጋል።

በፍርድቤት የተዘያዙ ጉዳዮች ላይ ብዙ መናገር አልፈልግም። ነገር ግን ፍርድ ቤት የፍትህ ቤተመቅደስ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። እኛ በታሰርንበት ጊዜ እንደምታስታውሺው ፍርድ ቤት የፍትህ የምትሰቀልበት አደባባይ ሆና ነበር የቆየችው። በውሸት እየተመሰከረብን ዳኞች ከቤተመንግሥት በቀጥታ ትዕዛዝ እየተቀበሉ የሚፈርዱበት ሁኔታ ነበር የነበረው። በኢትዮጵያዊነትሽ የምታፍሪበት ቦታ ነበር። ያ እንዲለወጥ እንፈልጋለን። ያ እንዲሆን ደግሞ ከፈለግን ከወዲሁ የመሰለንን አስተያየት መስጠት የለብንም። ምክንያቱም ወደዚህም ወደዚያ ልናዛባው ስለምንችል ማለት ነው። ተጠርጣሪዎቹ መናገር በማይችሉበት ቦታ ላይ ቆሞ እንዲህና እንዲያ ማለት ተገቢ አይመስለኝም።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2012

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *