ቂምና ቁርሾ በበጋው ንፋስ ፣ በክረምቱ ጎርፍ ይለፍ። በአዲሱ ዓመት መልካም መልካም ባህሎቻችንን ደምረን፣ ስህተቶቻችንን አርመን ለሀገራችን አንድነት እና ልማት በጋራ መቆም አለብን ሲሉ አባገዳ ጎበና ሆላ አሳሰቡ።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ጸሐፊና የቱለማ ገዳ አባገዳ ጎበና ሆላ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ አዲሱን ዓመት ስንቀበል እንደ ኢትዮጵያዊም ሆነ እንደ ኦሮሞ በቂምና በጥላቻ የከረመ ቁስልን እያከክን ሳይሆን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለጠፋው ጥፋት ይቅር በመባባል ነው።

አዲሱን ዓመት የምንቀበለው በቂምና በቁርሾ ሳይሆን ለሀገርና ለህዝብ አንድነት መልካም መልካም ነገሮችን እያሰብን የነበሩ ችግሮችንም በይቅርታ በማለፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ በጊዜያዊ ጥቅም ለፖለቲካ ትርፍ ተብሎ የሚፈጠር ግጭትን በማቆም መሆን እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

የገዳ ስርዓት ቂምና ቁርሾ በበጋው ንፋስ ፤ በክረምቱ ጎርፍ ይለፍ የሚል ነው ያሉት አባገዳ ጎበና፣ ይቅርታ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ፣ በኦሮሞ ማህበረሰብ ደግሞ እጅግ የተከበረ ነው ብለዋል። ‹‹ ይቅር እንባባል ማለት ያጠፋነው ትንሽ ነው፣ የሚቀረን ብዙ ነው፤ ከዘመን ዘመን፣ ከክፍለ ዘመናት ክፍለዘመናት ቁርሾ እና ቁስል እያከክን ከምንጠላለፍ ያለፈውን ለታሪክ ትተን በአንድነት፣ በመተሳሰብና በፍቅር እንኑር ማለት ነው ›› ሲሉም ተናግረዋል።

አባገዳ ጎበና እንዳሉት ፤ በኦሮሞ ባህል የተቀያየመ ሰው ከጎረቤት፣ ከቤተሰብ፣ አልፎ ተርፎ ከተቀያየመው ብሄር ብሄረሰብ ሁሉ ይቅር ብሎ ይቅርታ ይጠያየቃል። የገዳ ስርዓትም የሚያስተምረውና የሚተገብረው ይህንን ነው። ይቅርታ ከስህተታችን ተራርመን ለወደፊቱ ፍቅር እንድንሆን የምንሄድበት መንገድ ነው።

ይቅርታ ትልቅ ዋጋ እንዳለው አንዱ ማሳያችን በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረውን ቅራኔ እንዴት እንደተፈታና እንዴት ወደሰላም መንገድ እንደመጣን ያየንበት ነው ያሉት አባገዳ ጎበና፣ የነበረውን የሰላም መደፍረስ በይቅርታ ተላልፈን ጥሩ ወዳጅነት መስርተናል። በዚህ መሀል ብዙ ጥቅሞች ተገኝተዋል፤ ይሄ የይቅርታን ትልቅነት ማሳያ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ሀገራችንን በልማት የምናሳድገው ፣ አንድነቷ ተጠብቆ ህዝብ በሰላም የሚኖረው በህግ የሚፈለገው በህግ እየተጠየቀ፣ በይቅርታ መተላለፍ ያለበትም በይቅርታና በምህረት መተላለፍ ከተቻለ ብቻ ነው ያሉት አባገዳው፣ ይቅርታ በየትኛውም ዓለም ያለ፤ በሀገራችንም መንግስት በማረሚያ ቤት ለሚገኙ ሰዎች ይቅርታ እያደረገ እንዲፈቱ የሚያደረግበት ስርዓትአለ። ስለዚህ የይቅርታ ጉልበቱ ጠንከራ መንገዱም ረጅም ነው ብለዋል።

ለሀገር ሰላም ለህዝቦች አንድነት የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች እና አባገዳዎች ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፣ አዲሱ ዓመት በመከባበር፣ በመተሳሰብ፣ ለሀገራችን ብልጽግና በጋራ የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ። ለዚህ ደግሞ ይቅርታ ትልቅ ቦታ እንዳለው አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን እሁድ ጳጉሜን 1/2012

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *