“Our true nationality is mankind.”H.G.

” ከቤት አትውጣ ስባል ወጥቼ ለዘመናችን አስከፊ በሽታ ተዳረግኩ” የ76 ዓመቱ አዛውንት ምስክርነት

“ከቤት አትውጣ ስባል ወጥቼ ለዘመናችን አስከፊ በሽታ ተዳረግኩ” ይላሉ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ የ76 ዓመቱ አዛውንት። በሚሌኒየም የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ውስጥ ለ19 ቀናት በሞትና በህይወት መካከል ያሳለፉት አዛውንት አቶ ልጅ ዓለም ገዳ “የቤተሰቤን ምክር ባለመስማቴ ለሞት ተዳርጌ ነበር” ብለዋል።
ከማዕከሉ አገግመው የወጡት የሁለት ልጆች አባትና የልጅ ልጅ ያዩት አቶ ልጅ ዓለም በቫይረሱ የተያዙበትን በውል ባያውቁትም ረጅም መንገድ በእግር መጓዝ ያዘወትሩ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው ከዛሬ 24 ቀን በፊት እንደልማዳቸው የእግር ጉዞ ለማድረግ ከቤታቸው ከወጡ በኋላ የረሃብ ስሜት ተሰምቷቸው ደረቅ ምግብ ገዝተው እንደተመገቡ ያስታውሳሉ።
ከጥቂት ደቂቃዎችም በኋላ የማጥወልወልና የማንቀጥቀጥ እንዲሁም መላ ሰውነታቸውን የሕመም ስሜት እንደተሰማቸውና በታክሲ ወደ ቤታቸው እንዳቀኑ ይናገራሉ።
ነገር ግን የሕመሙ ስሜት ትኩሳት ታክሎበት እየባሰ በመሄዱ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል አቅንተው ለአራት ቀናት በከፍተኛ የሕመም ስሜት ውስጥ እንደቆዩ አቶ ልጅዓለም ያወሳሉ።
በሆስፒታሉም በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ እንደዳለባቸው በመረጋገጡ ወደ ማዕከሉ ተላክሁኝ ይላሉ ።
ቀድሞም የደም ግፊትና የስኳር ሕመምተኛ የነበሩት አዛውንት ”ከቤት አትውጣ” እየተባሉ ወጥተው በቫይረሱ በመያዛቸው ”ከእኔ አልፎ ቤተሰቤን አስይዤ ይሆን?”ከሚል ጭንቀት ተዳምሮ በጽኑ መታመማቸውን ይገልጻሉ።
ሕመሙ በጀመራቸው ሰሞን ራሳቸውን እስከ ማጥፋት የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ተገፋፍተው እንደነበር ተናግረዋል።
በሐኪሞች ጥረትና በፈጣሪ ዕርዳታ ከበሽታው አገግመው መውጣታቸውን ገልጸዋል።
”ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ የሚነገረውና የሚሰጠውን ምክር ቸል አትበሉ። ሰምታችሁ ተግብሩ። ዛሬ በቫይረሱ ሳቢያ ከሞት ጋር ግብ ግብ የተያዙ በርካታ ናቸው።” ሲሉም ይመክራሉ።
”በሽታው ከሚነገረው ባላይ አስከፊ ነው” የሚሉት አቶ ልጅ ዓለም፣ በማዕከሉ የሚገቡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ እንክብካቤ አግኝቶና አገግሞ ለመውጣት አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ።
ለመሞት አንጣደፍ። ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፈውን ሕይወታችንና በምናሳየው ቸልተኝነት የምንወዳቸውን ሰዎች ማጣት አይገባም” ሲሉም ምክራቸውን ያስተላልፋሉ።
ኢዜአ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”
0Shares
0