“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሠላም ዕውቅናና ምስጋና ፕሮግራምን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

“ለዘላቂ ልማትና አብሮነት የህግ የበላይነት!”
የአማራ ክልል ሕዝብ ለሕግ የበላይነትና ለሰላማዊ ሕይወት ታላቅ ከበሬታ ያለው ብቻ ሳይሆን ለሕግ መከበርና ለሰላም ልዕልና እንኳንስ ሃብቱንና ጉልበቱን ደሙን ለመገበር የማይሳሳ ስለመሆኑ ታሪክ ምስክር ነው። በዚህ ዘመንም በሚኖርበት ክልል ብቻ ሳይሆን ከወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን በጋራ በአጥንትና በደሙበገነቧት ሃገራቸው ዜጎች በማንነታቸው ሳይገፉና በህገ-ወጦች ሳይንገላቱ በየትኛውም ቦታ መብታቸው ተከብሮ በፍትህ፣ በእኩልነትና በሰላም መኖር እንዲችሉ የሚታገል ሕዝብ ነው።
የክልላችን ሕዝብ እኩልነት፣ ልማት፣ መልካም አስተዳደር እና ሠላም እንዲሰፍን ባለፉት ዓመታት ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በመሆን የለውጥ ችቦ በመለኮስ ፋና ወጊ በመሆን ታግሏል። ነገር ግን ከለውጥ በኋላ ሕዝቡ በጥበብና በአርቆ አስተዋይነት መፈታት ያለባቸው ውለው ያደሩ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሃገራችን ሕዝቦች ጋር በጋራ በመቆም ታግሎ ድል ሊነሳቸው የሚገቡ ከባድ ሃገራዊ ሥጋቶች አሉ። የክልሉን ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች ለመመለስና እንደክልልና እንደሃገር ከፊታችን የተደቀኑ ሥጋቶችን መክቶ በድልአድራጊነት ለመዝለቅ የውስጥ አንድነትና ጥንካሬ እንዲሁም ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የአማራ ሰፊ ሕዝብ ጠንቅቆ ይረዳል።
በተለይም ሠላም ወዳዱ ሕዝባችንም ሆነ የክልላችን መንግሥት እየተስተዋለ ያለውን የሠላም መደፍረስ፣ ሕገ-ወጥነትና አለመረጋጋት ቋጭቶ በክልላችን ሠላም ሰፍኖ ልማት፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንዲስፋፋ ከፍተኛ ፍላጎት አሳድሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የሕዝባችንም ፍላጎት በሕገ ወጥ መንገድ ተደራጅቶ የሠላም ጠንቅ የሆነውን ቡድን በሠለጠነና በሠላማዊ መንገድ መልክ ማስያዝና ሕዝባችን እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ፣ የክልሉ አመራርም ተረጋግቶ ሕዝቡን እንዲያገለግል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ ፍላጎቱ በክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ ቱሪዝም እንዲዳብር፣ የንግድ ሥራችን እንዲሳለጥ፣ ሕዝብ በሠላም ውሎ በሠላም እንዲገባ፣ ሥጋቱ ሁሉ እንዲወገድለት እና ሕግ እንዲከበር ነው። ለዚህ ዓላማ መሳካትም ታግሏል፤ የበኩሉን አስተዋፅኦም አበርክቷል፡፡
በተፈጠረው አንፃራዊ ሠላም ከክልሉ ውጭም ሆነ በክልሉ ውስጥ አንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ወቅቶች በነበሩ ግጭቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ ቤተሰቦች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡
በተካሄደው ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራዎች ህብረተሰቡ የሠላምና ደኅንነት ፍላጎት እንዲሟላ ከወትሮው በተለየ መንገድ ከክልሉ መንግስት ጎን ተሰልፎ በርካታ የሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራዎች ሠርቷል፡፡
በቀጣይ በክልላችን ወደ ኋላ ላንመለስ የጀመርነውን የሕግ ማስከበር ሥራችንን ሠርተን፣ አንድነታችንንና አብሮነታችንን አጠናክረን፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪስት መናገሻ ክልል ለማድረግ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንደምንቀጥል ስንገልጽ ሕዝባችን እንደወትሮው ከጎናችን እንደሚቆም በመተማመን ነው፡፡
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኝ የክልሉ ህዝብ፣ አመራሩና የሀይማኖት አባቶች ሠላምና አንድነታችንን ለማጠናከር በሙሉ አቅም በመንቀሳቀስ ችግሮችን ከሥር መሠረቱ ለመፍታት ስለሠላም፣ ስለ እኩልነት፤ ስለ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍትህ የሚደረገው ትግል የሞራልና የሀይማኖት እሳቤዎች ጋር የተዋሃደ እንዲሆን የበኩላቸውን በመወጣት ህብረተሰባችን በአብሮነትና በአንድነት እንዲኖር መስራት ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በያዝነው እልህ አስጨራሽ የትግል ምዕራፍ ሂደት ላይ ሆነን በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ የአማራ ህዝቦች ጥቅም መከበር እና በሠላም መኖር ለአፍታም ሳይዘናጋ እንደሚሰራ፣ ዝግጁና ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለው መሆኑን የክልሉ መንግስት ይገልፃል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ጳጉሜን 2/ 2012 ዓ.ም
ባሕር ዳር

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የተላላኪው ጠበቃዎች
0Shares
0