ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

«ትውልዱን በማደንቆር የተካኑ ፖለቲከኞች ጡረታ ይውጡ…» አቶ ሙሳ አደም

የመጀመሪያው መሆን ያለበት በብሔርተኝነት አመለካከት ወደኋላ እየመለሱ ትውልዱን በማደንቆር የተካኑ ፖለቲከኞች ጡረታ ይውጡና አዳዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብና እውቀቱ ያላቸው አካላት ወንበሩን ይረከቡ። የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ፖለቲካዊ አካሄዶች በመርህ፤ በፖሊሲ ላይ የተመሰረቱና ከአገርና ከህዝብ ጥቅም አንጻር የተቃኙ መሆን መቻል አለባቸው። በሙያ፤ በእውቀት፤ በምርምር የሚደግፉ ወጣት ፖለቲከኞችን ማፍራት ይጀመር። መሪውም የሚመጥነው ሙያ፤ እውቀትና አቅም ያለውም ሊሆን ይገባል። ክርክሮች የግል ጸብ በሚመስል መልኩ ሳይሆን በፖሊሲና በእውቀት እንዲሁም በአገር ልጅነት አስተሳሰብ ማድረግ ከተቻለ ትክክለኛ ፖለቲካ ይፈጠራል። አገርም በሁሉም መስክ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ መሻገር ትችላለች።

By – ጽጌረዳ ጫንያለው

የአገሪቱ ፖለቲካ ጉዳይ የተረጋጋ አለመሆኑ ዜጎች በየጊዜው ዋጋ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው ለመሆኑ ምስክር አያሻም፡፡ በተለይ ወጣቱ ከመስራትና አገር ከመለወጥ ይልቅ ምርጫውን በተሳሳተ መንገድ አድርጎ እንዲጓዝና ያለምንም ምክንያት መስዋዕትነት እንዲከፍል እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ደግሞ እናትና አባቶች እያዘኑ፤ መንግሥትም ቢሆን ምን ማድረግ እንዳለበት ሲቸገር ይታያል፡፡ ይህ ብቻ ሳይበቃ አገርም የተለየ ማንነት እንዲሰጣት እየሆነች ነው፡፡ እናም ይህ ዋጋ መክፈል እንዴት መጣ፤ ፖለቲካው መልኩ ምን ይመስላልና መሰል ወቅታዊ ጉዳዮችን በማንሳት ከፖለቲካ ሳይንስ መምህሩና ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ቃለምልልሱንም እንደሚከተለው አቅርበናል፤

አዲስ ዘመን፡- ፖለቲካ ምንድነው? ፖለቲከኛና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርስ ?

አቶ ሙሳ፡- ፖለቲካ ቀደም ባለው ጊዜ ህዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ሰፍቶ አንድ የሚያደርግ ድልድይ ነው። በተለይም በመንግሥት በኩል ያለው አስተዳደራዊ ክፍሉ የሚፈተሽበት ፤ የሚመዘንበት፤ የሚለካበት መሳሪያ ነው። ማን ምን አገኘ፤ እንዴት አገኘ፤ ለምን አገኘ የሚለውን የሚታይበት፤ የሚፈታበት መሳሪያ ነው። አሁን በተሻሻለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ፖለቲካ መንግሥትና ህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ወይም በተቋማትና በህዝብ መካከል ያለውን ቁርኝት የሚፈተሽበት ፤ የሚተዳደርበትና አቅጣጫ የሚያዝበት መሳሪያ ነው የሚለውን ብያኔ ይይዛል። በተለይ የህዝብ ችግር አፈታት ሥርዓቱ የሚታይበት መሳሪያ እንደሆነ ይነገራል።

ፖለቲከኛ ወደሚባለው ሲመጣ ደግሞ የህዝቡም ሆነ የአገሩ ጉዳይ አሳስቦት የተማረው ትምህርት ሳይገድበው በተደራጀ የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶ ለስልጣን የሚወዳደር ፤ በፖሊሲና በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እይታ ጎራ ለይቶ የሚፎካከር ሰው ማለት ነው።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ማለት ደግሞ በፖለቲካው ላይ ጥልቅ ምርምርና ጥናት እንዲሁም ትንተና የሚያደርግ ሰው ነው። ሆኖም እነዚህ ነገሮች በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ አንድ ተደርገው ይወሰዳሉ። እንደውም ምሁሩን ያገለሉ ናቸውም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ደግሞ አገር ላይ መስመሩን የያዘ ፖለቲካ እንዳይኖር አድርጓል። ሁሉም ተንታኝ የሆነበት አካሂድ ተፈጥሯል። በዚያ ላይ ፖለቲከኛው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑን አያማክርም፤ ሁሉን በራሱ የሚያውቅ ስለሚመስለው በተሰማው ነገር ብያኔ እየሰጠ ተንታኝነቱን ሲያስቀጥል ይታያል። በዚህም ምሁሩ ለአገር ማበርከት ያለበትን እንዳያበረክት ሆኗል።

አዲስ ዘመን፡- ከእሳቤው አንጻር እንደ አገር ፖለቲካና ፖለቲከኛ አለ?

አቶ ሙሳ፡- እንደእኔ እምነት ሁለቱም በአገር ውስጥ ገና አልተፈጠሩም። ምሁራኑ በመገለላቸው በመርህ፤ በእውቀት፤ በምርምርና በልምድ የተመራ የፖለቲካ አካሄድ ደብዛው ጠፍቷል። አሁን በተግባር ላይ ያለው ፖለቲካ በዘፈቀደ የሚጓዝና የበላዩ ሲያኮርፍ የሚያኮርፍ ፤ ደስ ሲሰኝ ደግሞ አብሮ የሚፈነጥዝ ነው። ለአገር ደጀን የሚሆን ፖለቲከኛ እስካልተፈጠረ ድረስ ሁለቱም ሊኖሩ አይችሉም። ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጥ በሌለበት፤የሚያነብና ስለ አገሩ የሚገደው፤ ፖለቲካውን በሚገባ የተረዳ፤ ለቀጣይቱ አገር ተስፋና ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን የሚለይና የሚያመለክት ፖለቲካና ፖለቲከኛ ሳይኖር አለ የሚለውን ልናነሳ አንችልም።

ህዝብና አገር እስካሉ ድረስ ፖለቲካው ይኖራል። ግን በእኛ አገር ሁኔታ ፖለቲካን ፖለቲካ አስብሎት የሚሄደው ነገር ጠፍቷል ። የፖለቲካው ስነ ምህዳር ለፖለቲካና ለፖለቲካው ምቹ ተደርጎ አልተሰራም። በሃሳብ ነጥብ ለማስቆጠር የሚለፋ ፖለቲከኛ በሌለበትና የእኔ ብሔር እንዲህ ሆነ በሚል መልኩ የሚጓዝ ባለበት ሁኔታ ፖለቲካም ሆነ ፖለቲከኛ አለ ሊባልም አይችልም።

አገር በተለይ አንባቢ ፖለቲከኛ ሲኖራት የሚመራት አገኘች ፤ ፖለቲካውም መስመር ሊይዝ ተተክሏል ልንል እንችል ይሆናል። ነገር ግን አይደለም የቀደሙትን በቅርብ የተጻፉትን ማስታዎሻዎች እንኳን ያነበበ ጥቂት ነው። እንደውም ከቀደመ ማንነታቸው መላቀቅ ስለማይፈልጉ ማየትም አይሹም። ከሌሎች መማርን መዋረድ አድርገው ይወስዱታል። ይህ ደግሞ ፖለቲካውንም ሆነ ፖለቲከኛውን የሉም ሊያስብላቸው የሚችል ነው። ሀገርንና ህዝብን ለማስተዳደርም የሚችሉበት ቁመና ባለመኖሩ ከእሳቤው አንጻር ሁለቱም ገና ተስፋ ላይ ናቸው። በዚህም አሁን ያለው ፖለቲከኛ ሙሉ ለሙሉ ጡረታ ሊወጣ ይገባዋል። ምክንያቱም በድሮ አስተሳሰብ እየኖሩ በአዲሱ ኃይል ጉልበት፤ እጣ ፋንታ፤ የወደፊት ራዕይ ላይ ይጫወታሉ። እናም ታሪክን እያነሱ ዛሬን ሳይሆን ድሮን እንድንኖር እየፈረዱብን ስለሆነ በቃ ልንላቸው ያስፈልጋል።

የዓለም ፖለቲካ በጣም ተለዋዋጭ ነው። ትናንት የነበረው የፖለቲካ አረዳድ ዛሬ አይሰራም። እነርሱ ግን ገና ኃይለስላሴና ምኒልክ ዘመን ላይ በመሆናቸው አገርንም ሆነ ትውልድን ወደ ኋላ እየሳቡት ይገኛሉ። ይህ ማክተም ካልቻለ ወደፊትም ፖለቲካውም ሆነ ፖለቲከኛውም አይፈጠርም። እነዚህ አካላት ወቅቱ የሚጠይቀው አካሄድ ተጠቅመው ብዙ ሰርተዋል፤ ለአገርም ያበረከቱት ነገር አለ። ይሁንና ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› አባባላቸው ዛሬም ቀጥሏል። ይህ ደግሞ ወጣቱን እንዳይሰራና አገሩን እነርሱ በሰሩት ላይ ጨምሮ እንዳያሻግር እንቅፋት ሆነውበታል። እናም ፖለቲካውና ፖለቲከኛው በተሻለ መልኩ አገር ወስጥ እንዲፈጠር ከተፈለገ ለተተኪው ወንበር መልቀቅ ግድ ነው።

የቀድሞ ታሪክ እየነገሩ ወደ ድሮ እየወሰዱ ማጋደል ለማንም አይበጅም። እነርሱ በአእምሮ ያልተሻገሩና እዛው ላይ ያሉ በመሆናቸው ብዙ ነገር እያፈረሱ ይገኛሉና ይህንን ማስቆም የዛሬው ተተኪ ትውልድ ኃላፊነት ነው። የቀድሞ የፖለቲካ አካሄድ መልካምም መጥፎም ታሪኮች ነበሩበት። ግን በዘመናቸው የነበረው የፖለቲካ አረዳድ ይህንን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋልና አድርገውታል። እኛም ስንረዳው ያንን ታሪክ አድርገን እንጂ ኑሯችን አድርገን መሆን የለበትም። ታሪኩ እንደ ታሪክነቱ ይነበብ፤ ይታወቅ፤ እውነታውን ሁሉም ይረዳው ግን ከዚህ ባለፈ በዚያ ታሪክ እንድንኖር ሊፈረድብን አይገባም። ነጋችንም እንዲበላሽ መፍቀድ የለብንም። ምክንያቱም ዛሬ ብዙ ነገሮች ተለውጧል። በዛሬው አካሄድ የዛሬው ትውልድ መሰራት አለበት። ነገን እያነሱ ትውልዱን ወደትናንት መውሰዱና ማበጣበጡ ማክተም አለበት። በተለይ የፖለቲካውን መፈጠር የሚያመጣው የትናንቱን ለትናንት በመተው የዛሬን ለውጥ ለዛሬ በመስጠት ነውና ይህ ሊደረግ ይገባል።

ወጣት ፖለቲከኛ የለም። በስብስባችን ውስጥም ትንሹ እኔ ነኝ። እናም እነርሱ አዲሱን የፖለቲካ አመለካከት መቀበል ስለማይፈልጉ ቃል እየሰነጠቁ ወደኋላ መመለስ ብቻ ነው ልምዳቸው። ዛሬን መኖርን አይፈልጉትም። ኢትዮጵያ ተሰርታ አልቃለች። ይህችን የተሰራች አገር ደግሞ ይዞ ማስቀጠሉ አሁን ያለው ትውልድ ድርሻ ነው። እናም አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለፉት ዓመታትን የምንኖርበት ሊሆን አይገባም።

ፖለቲከኞቹ ሌላ ሰው እንዲመጣባቸው አይፈልጉም፤ ወጣት ፖለቲከኛንም ማየት ያማቸዋል። ይህ ደግሞ ፖለቲከኛም ሆነ ፖለቲካው እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ ወጣቱን የእሳት እራት እንጂ የመስራት ባህል ያለው እንዳይሆን አድርጎታል። ሱሰኛና አገር ጠል እንዲሆንም ተፈርዶበታል።

የተማረና የተመራመረ፤ የተሻለውን ለአገር ለማምጣት የሚጥር፤ ጉልበት ያለው ሯጭ ፖለቲከኛ አገር ያስፈልጋታል። እንደውም ‹‹ የተማረ ይግደለኝ›› እንደሚባለው የአገር ፖለቲካ መፈጠር የሚጀምረው ፖለቲከኛውም ፖለቲካውም በእውቀትና በአዲስ አስተሳሰብ ሲቃኝ ብቻ ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳቡን ያልተረዱ ሰዎች እየመሩን ግራ ከሚያጋቡን መፍትሄው በእጃችን ስለሆነ ይህንን መወሰኑ ላይ መስራት ይጠበቅብናል።

ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመረጠው የትምህርት መስክ ጭምር ለፖለቲካው የሚቀርብ አልነበረም። ይህ ደግሞ በአገር ላይ ሌሎች የትምህርት መስኮች ማበርከት ያለባቸውን እንዳያበረክቱና ባልተረዳው መስክ በመምራቱ በህዝብና በመንግሥት መካከልም ተስማሚነት ያለው ሥራ ተሰርቶ ለውጥ እንዲመጣ አላስቻለም። እናም በሙያቸው ብዙ መስራት የሚችሉት ነገር ስላለ ቦታውን መስጠት ያስፈልጋል።

Related stories   አውሮፓ ህብረት - ላለፉት 28 ዓመታት በኢትዮያ ተላላኪ መንግስት እንደነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ አመነ

አዲስ ዘመን፡- ካነሳነው አንጻር የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረታዊ ችግር ምንድነው ?

አቶ ሙሳ፡- በምክር ቤት ደረጃ ተምርጬ ከገባሁ አጭር ጊዜ ቢሆነኝም ችግሮቹን ግን እንዳይ እድል ሰጥቶኛል። በዚህም ችግሮቹ በርካታ ቢሆኑም በዋናነት የሚነሱት ግን በቅንነት አይቶ ወደመፍትሄ አለማምራት ፤ ከህዝብና ከአገር ይልቅ ራስን ማስቀደም፤ ለስሜት መገዛት፤ የእኔ ብቻ ኃያል ነው ማለት፤ ቁርጠኛ አለመሆን፤ አለመናበብ፤ አንዱ የሰራውን አንዱ ማፍረስ ልምድ መደረጉ፤ እሴት ለመጨመር አለመፈለግ የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በንግግሮች መካከል የተተነፈሰው ሁሉ በምን አስቦ ይሆን መተርጎማቸው፤ ፖለቲካዊ ቅንነት አሁን በሚመራውም ሆነ ወደፊት አገርና ህዝብን እንመራለን በሚለው ፖለቲከኛ ላይ አለመታየት፤ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ምሁሩ ያላቸው ሚና በውል አለመለየት፤ አንዱ ለሌላው አጋዥ ሆኖ አለመቀጠልም ሌላው ችግር ነው። ስሜትን መግለጽና ፖለቲካ መተንተን በውል የተለዩ አለመሆናቸው፤ ባለቤት አልባ ሥራዎች መኖራቸውም አገር የፖለቲካ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።

ፓርቲ የሚባለውም በዘመድ ተሰባስቦ የሚመሰረት ነው። ይህ ደግሞ አገር ለመምራት ሳይሆን ቤተሰብ ለማስተዳደር ብቻ የሚያስብ የሚያደርገው ተግባር ነው። እናም መሰረታዊ የፓርቲ ቁመና ያለው በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ፓርቲ ከሌለ ፖለቲካም ፖለቲከኛም ሊፈጠር አይችልም። ሁለቱም ያለመኖራቸው መንስኤ ነው አሁን ለአገር ፈተናና ዋጋ ማስከፈል ያበቃው። ፓርቲው እንደ ፓርቲ የሚሰራው ሥራ የለም። ህዝቡም ከፓርቲው የሚጠብቀውን እያገኘ አይደለም። ስለዚህም ህዝብ ከመጠቀም ይልቅ በችግር ውስጥ ተዘፍቆ ዓመታትን ዋጋ እየከፈለ እንዲኖር አድርጎታል።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጥ በኋላ በአገር ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎችን እንዴት ይገመገማሉ?

አቶ ሙሳ፡- የተዛባ ፖለቲካ አገር ላይ ተፈጠረ ማለት ማህበራዊውም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፈታት አይችሉም። ምክንያቱም ፖለቲካ ማለት ሰላም ነው፤ ሰላም ከሌለ ደግሞ ማንኛውም መሰረተ ልማት፤ የሰው ሀብት ልማት፤ የኢኮኖሚ እድገት አይታሰብም። ሰብአዊ መብት ጭምር ሊከበርበት የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። ቁርሾና ነቆራን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ተዛምዶ መሄድም ያዳግተዋል። እናም ፖለቲካው ከኢኮኖሚውና ከማህበራዊ ክንውኖቹ ጋር ተጋምዷል ለማለት የሚያስችልበት ሁኔታ አለ። ግን ለውጡ ትንሽም ቢሆን ጭላንጭሎችን እያሳየ መምጣቱን ማንም አይክደውም። ህዳሴ ግድቡ አንድ እርምጃ

መጓዙ፤ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መመረቅ መጀመራቸው በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊው ላይ ለውጥ እያመጡ ነው። ግን ፖለቲካው የለም ስላልን የእርሱ ለውጥ አሁንም አልታየም።

አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካው ምክንያት አገር እየከፈለችው ያለውን ዋጋ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ሙሳ፡- ዋጋው ከባድ ብቻ ተብሎ የሚታለፍበት አይደለም። የመኖርንም የነብስን ዋጋ የሚጠይቅ ነው። በእርግጥ ዓለም ላይ ያሉ አገራት ጭምር ዝም ብሎ አገር ሆነው አልተገነቡም። ህዝቦች ዋጋ ከፍለው ነው የመሰረቷቸው። ስለዚህም እንደ እኛም አገር ህዝብ ዋጋ ሊከፍል ይገባው ። ነገር ግን ክፍያው ምን አይነት ይሁን፤ ምን ውጤትስ ማምጣት አለበት የሚለው መታየት አለበት። ይህ ደግሞ እንደየዘመኑ ይለያያል። እናም በዚህ ዘመን መክፈል የነበረበት ዋጋ በድርድርና በክርክር እንዲሁም በመግባባት ዙሪያ የሚወሰደው ጊዜና አስተሳሰብ ነው። ሆኖም ለውጥ ለማይታይበት ነገር ነብስ እየተከፈለ ነው።

አሁን ባለንበት ዘመን ዓለም እንኳን ችግሮቿን ለመፍታት ነብስ እየገበረች አይደለም። እኛ ግን በቀላሉ ማሻገር የሚያስችሉን የለውጥና የተፈጥሮ ባለቤቶች ሆነን ሳለን በድሮ በሬ ማረሳችንን ምርጫችን አድርገን ነብስ እንገብራለን። ዘመኑን ያልዋጀ፤ አገርን ከፍ ለማድረግ በማያስችል ጉዳይ ላይ መስዋዕት እየከፈልን እንገኛለን። በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ መደረግ የሌለባቸው አስተሳሰቦችን እያንጸባረቅንም ሰውን አባልቶ፤ የሃይማኖት ተቋማትን አቃጥሎ የፖለቲካ ስኬትን ለማግኘት እንሯሯጣለን። በዚህ ደግሞ መሞት ብቻ ሳይሆን ብዙ ዘመናትን ወደኋላ ተጉዘን እንድንኖር ተገደናል።

የዋጋው ንረት ትውልዱን ኖሮ እንዳይደሰት፤ ሞቶ ደግሞ ነብሱ እንዳታርፍ ጭምር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ ኖሮ የት ላይ መድረስና ከየት መነሳት እንዳለበት እንዳይረዳ አድርጎታል። ለራሱ መኖሪያና ጡረታ በሚያመቻቸው ፖለቲከኛ ምሪትም የማይሆነውን እንዲሆን ተፈርዶበታል። ፖለቲካው ላይ እንዳይሳተፍ፤ ሥራ እንዳያገኝም ብዙ እድሎች ይዘጉበታል። በዚህም ኑሮው ሁሉ ተስፋ ቆርጦ ከተቻላቸው የረብሻ ምንጭ ካልተቻለ ደግሞ ሞቱን እየተመኘ እንዲቀጥል አድርገውታል። ስለዚህም የሚከፍለው ዋጋ ለአገር እድገት ሳይሆን ለግለሰቦች መበልጸግ ብቻ ይሆናል። ጥቅመኞች ተጠቅመውበት ገብረውት ካለፉ ደግሞ የነብስ ዋጋን ከዚያ አለፍ ሲል ነብሱ ሳታርፍ ገዳይ ደንቡ ነው እየተባለ ሲወቀስ ይኖራል።

አዲስ ዘመን፡- በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዴት ይታያል?

አቶ ሙሳ፡- ከእላይ የተባለው ሃሳብ ነው እዚህም የሚደገመው። ምክንያቱም እኛ አገር ፖለቲካ የለም። መገለጫውም ህዝብንና አገርን ያስቀደመ ሥራ አለመታየቱ ነው። በሃሳብ ደረጃ የሚከራከርና የሚነጋገር ፖለቲከኛ በአገር ውስጥ አልተፈጠረም። ይልቁንም እርሱን ፍልጠው ቁርጠው የነገሰበት ነው። ይህ ደግሞ ፖለቲካ ሳይሆን የጉልበተኞች ጨዋታ ነው። እንደ ሳይንሱም ሆነ እንደ ዓለም ፖለቲካ የግብርና ፤ የጤናና የትምህርት እንዲሁም የኢንቨስትመንትና መሰል ፖሊሲው ላይ ይህ ልክ ነው፤ ይህ መሻሻል አለበት ማለት የሚችል ነው። ህዝቡ እንዲመለስለት የሚፈልገውን መሰረታዊ ችግር የሚፈታ ነው።

ኮሮና፤ እንደ እንቦጭና የጎርፍ መጥለቅለቅን የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች፤ እንደህዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ሥራዎች አገር ላይ ችግር ሆነው አንድ የሚያደርጉን የጋራ ጉዳዮች ላይ መስራት መቻል ነው። ነገር ግን እንደ እኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ እነዚህ ችግሮች የህዝብን መኖርና አለመኖር የሚፈታተኑ ሆነው ሳሉ ፖለቲከኛውም ሆነ ፖለቲካው ግን ይህ አያሳስበውም። ጉዳዩ አሁንም ምኒልክ ይህን አደረገ አላደረገ ላይ ነው። ድሮ ተከሰተ አልተከሰተ የሚለው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። እናም ድሮን እየኖርን ፖለቲካ አለን፤ ፖለቲከኛም ፈጥረናል ልንል አንችልም። ስለዚህም ከዓለም አንጻር ስንታይ እኛ ትናንት ያለ ያላደገው ፖለቲካ ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- ዜጋው ለምን በፖለቲካው አያምንም?

አቶ ሙሳ፡- እንደእኔ እምነት ከአንቺ በተቃራኒው ነው የማየው። ሊያምነው የሚችል ምንም መሰረት የለውም። ግን አምኖት አድርግ የተባለውን እያደረገ ይገኛል። እኛ ፖለቲከኞች ፍለጥ ፣ቁረት፣ ተነሳ፣ ተቀመጥ ስንለው ሳያወላዳ ያደርጋል፤ሃሳባችንንም ያስፈጽማል።

ከዚህ ውጪ ደግሞ የማመኑ መገለጫ ሊኖር አይችልም። ግን ፖለቲከኛ በሌለበትና ፖለቲካው ምንም ለውጥ ባላሳየበት ሁኔታ ይህንን አምኖ መከተል አልነበረበትም። በሰላም ቤቱ እንዳይገባ፤ ሰርቶ እንዳይውል እየሆነ መቃረን እንጂ መደገፍ ፍጹም ትክክል አልነበረም።

የአገር ፖለቲካው እድገት በምሁራን እስኪመራና እስኪሰራ፤ ከቤተሰብ ፓርቲ ወጥቶ በአግባቡ መግባባትና የቀጣይ ተስፋን ማስቀጠል በሚችል መልኩ እስኪዋቀር ድረስ እንዲሁም ፖለቲካው በአገር አዲስ ተስፋ አምጪ ወጣት ሀይላት እስኪተካ ድረስ ዜጋው አሁንም ፖለቲካውንም ሆነ ፖለቲከኛውን ሊያምነው ይገባል ብዬ አላስብም።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ምን ይመስላል?

አቶ ሙሳ፡- አሁንም ሆነ ትናንት የነበረው የፖለቲካ አካሄድ የተለየ አንድምታ አለው ብዬ አላምንም። ለውጥ መቷል ቢባል እንኳን በግለሰብ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ፖለቲካው ተለውጧል ለማለት ያስቸግራል። አሁን ያለው መንግሥት ወይም የለውጡ መንግሥት የዶክተር አብይ አስተሳሰብና ፍላጎት የተንጸባረቀበት ነው። እርሳቸው ለአገራቸው ካላቸው ራዕይ አንጻር አእምሯቸውን በመጠቀም በዘመናቸው ሰርተው ለማለፍ በመጣራቸው አገርን ወደተሻለ መንገድ እያስገቧት ነው። ሆኖም እያንዳንዱ ፖለቲካ ውስጥ ይህ አስተሳሰብ ሰርጾ ባለመግባቱ ርዕዮት ዓለሙ አልተለወጠም። ጥገኛ የሆነ የአገር ለውጥ ነው ያለው። መዋቅራዊ ለውጥም አልታከለበትም።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

እንደውም ከራሳቸው ፓርቲ አንጻር እንኳን ብቻ ቢታይ በደንብ ተረድቶ የሚያንቀሳቅሰው ጥቂት ነው። ስለዚህ ይህ የፖለቲካ ርዕዮት የዶክተር አብይ ብቻ በመሆኑ እርሳቸው የሆነ ነገር ቢሆኑ መዋቅር ስላልተሰራለት ሁኔታው ያከትማል። እንደውም የእርሳቸው ፈተናም የሚሆነው ይኸው ብቻ ይመስለኛል። ታችኛው ድረስ አስተሳሰቡን አውርዶ አገርንና ህዝብን መጥቀም መቻል ከባድ ፈተና ነው። ወደ ተቋማዊ ሥርዓት ማውረዱም እጅግ ይፈትናቸዋል። ምክንያቱም ሁሉም ተቋም ባይባልም ብዙዎቹ በለመዱት የሌብነት ሥራና ራስ ወዳድነት ውስጥ ናቸው። ዛሬም የብሔራቸውና የሃይማኖታቸው ጉዳይ ነው የሚያሳስባቸው። ይህ ደግሞ አገርን ለመስራትም ሆነ አገራዊ ፖለቲካን ለመፍጠር ፈተና ብቻ ሳይሆን ችግርም ጭምር ነው።

ያለፉ አጠቃላይ ዓመታት የተሰሩበት ሥርዓት የተበላሸ ነው። አሁንም ፖለቲካው አንዳንድ የሚንቀሳቀሱ እንደ ዶክተር አብይ አይነት ሰዎች ቢኖርም ፖለቲካው ግን ያንን ከማስቀጠሉ አራቀም። ስለዚህ ሥርዓቱ ከእንደገና ፖለቲካው መሰራት ይኖርበታል፤ አስተሳሰቦች በአዲስ መልኩ መቃኘት አለባቸው። ለውጡም ቢሆን ከግለሰብ ወደ ተቋምና አገር እንዲሰፋ የሚያደርጉለት ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩለት ይገባል። መተማመኛ ያለው ፤ ህዝባዊ ተቀባይነት ያለው ተቋም መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ በዶክተር አብይ ዘመን ብቻ የሚጠናቀቅ አይሆንምና ተረካቢው ማስቀጠሉ ላይ ሊበረታ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን የለውጥ ኃይልና ለውጥ እንዴት ይገመግሙታል? የለውጥ ኃይል አለ ብለው ያስባሉ?

አቶ ሙሳ፡- አለ። ለዚህም አብነቱ ዶክተር አብይ ናቸው። ከእርሳቸው ጋር የሚተባበሩ ለአገራቸው ጥሩ ራዕይ ያላቸው ሁሉ የለውጥ ኃይል ይባላሉ። በአገር ላይ እያሳዩ ያለው ለውጥም በርካቶችን ያስደስተናል የአገርን ምስል የቀየረ ነው። ሆኖም በዚህ ካልቀጠሉና ተቋማዊ ካላደረጉት እንዲሁም መሬት ላይ እየታየ የማይሄድ ከሆነ የለውጥ ኃይልነታቸው ያከትማል። ስለሆነም በጥቂቶች እያንሰራራ ያለው ፖለቲካ በብዙዎች ካልተደገፈ አደጋው የከፋ ይሆናል። በተለይ ፖለቲከኞች ይህንን በማድረግ ዙሪያ ከፍተኛ ሚና አላቸው። እናም መርህ አልባ ተቃውሟቸውን ወደ ጎን በመተው መደገፉ መበርታት ይጠበቅባቸዋል። አሁን ማንም ሰው በአገሪቱ ላይ ለውጥ አልመጣም ሊል አይችልም። የሚታዩ በርካታ ነገሮች አሉ። ግን በግለሰቦች ጫንቃ ላይ ያለ በመሆኑ አምልጦ ከተሰበረ አደጋ መሆኑ አይቀሬ ነው።

ሁሉም የእኔ በሚል ቆንጨራውን አንስቶ መፋጀት ላይ ይሰማራል። እናም ፈተናም ቢሆን ከሥራው ጎን ለጎን መዋቅራዊ ሥርዓትና የአገር ሀብት መሆኑን ማሳመን ላይ መሰራት አለበት። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ርብርብን ይጠይቃል።

በዶክተር አብይ ዙሪያ ብዙ ተቃውሞዎች አሉኝ። ብዙ የምከራከርባቸውም መድረኮች ይኖራሉ። ግን እንደ ግለሰብ ጥሩ መሪና የፖለቲካ አሰራርን የሚከተሉ መሆናቸውን አደንቃለሁ። አሁን ካለው ፖለቲከኛ የተሻሉም እንደሆኑ አምናለሁ። ሆኖም ሥርዓት ግን አላበጁም። የራሳቸው ፓርቲ እንኳን ከእርሳቸው አስተሳሰብ ጋር ተዛምዶ አይሄድም። ከአገር ይበልጥ ለራስ ጥቅም የሚሮጡ፤ ርዕዮት አለሙን የማይረዱ፤ ከመሪያቸው ጋር በሃሳብ የማይገናኙና የሚያደርጉትን የማያውቁ፤ ያልተባሉትን የሚፈጽሙ ናቸው። እንደውም እርሳቸውን በመረበሽ የተካኑና ህዝብ እንዳያምናቸው የሚያደርጉም ናቸው። እናም የፖለቲካ ሀሳቡ ጥንስስ እንኳን እንዳይታይ ፈተና ሆነውባቸዋል እንጂ ጅማሯቸው መሰረት ነበረው።

ዶክተር አብይ በለውጥ ጉዟቸው መጀመሪያ አካባቢ ፍትህን ለማምጣት፤ በህዝቦች መካከል መቀራረብን ለመፍጠር፤ ሰላምን ለማረጋገጥ ብዙ ለፍተዋል። ሰውኛ ሰውኛ የሚሸት ፖለቲካዊ አካሄድም የታየው በእርሳቸው ዘመን ነው። ሆኖም ይህ ሁሉ በዜሮ ይባዛ ዘንድ አገር ሰላም ሆና ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው የሚፈልጉ ሀይላት ችግር ውስጥ ከትተዋቸዋል ። መተሳሰርም የተጀመረው በዚህ የተነሳ ነው። ይህ ስሜት ደግሞ በጎራ እየከፋፈለ ማባላቱን አስቀጠለው። እናም ለውጡ ቢኖርም ሹክቻው እንዲጎላ እድል ሰጠ። ግን አሁንም ቢሆን ብዙ ዋጋ ሊከፈል ይችላል እንጂ አገር አትፈርስም። የተጀመረውም ለውጥ ይቀጥላል።

አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካው መስክ ለውጥ አለ ብለው ያምናሉ?

አቶ ሙሳ፡- አዎ። ግን በሃሳብ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ ሊደገፍ ይገባዋል። ሀሳብ ሲታቀድበት፤ ሲተገበርና ሲገመገም ነው ውጤታማነቱ የሚረጋገጠው። ከዚህ ውጪ ሃሳቡ ሃሳብነቱ ቀርቶ ህልም ይሆናል። እናም ድርጊቱን በስርዓትና በመዋቅር ደረጃ መደገፍ ያስፈልጋል። ጥሩ ሲሰራ ማበርታት፤ መጥፎ ነገሮች ሲሆኑ ደግሞ የማረም ባህሉንም ማዳበር ይገባል። አሁን እየሆነ ያለው ፖለቲካን ለመፍጠር መሰረት መጣል ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ ጥንስሱ የዶክተር አብይ ቢሆንም በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትልቅ ክስተት ተብሏል። የሌሎች አጋርነትን ጭምር ያመጣ ነው።

ችግኝ መትከል የተጀመረው ከምኒልክ ጀምሮ ነው። ሁሉም ወጥነት ያለው የአገር አበርክቶ ነበራቸው። ካለፈው ኢህአዴግ መንግሥት በስተቀር። እርሱ ለአገር ሳይሆን በክልል ደረጃ ሰርቷል። ትግራይን ከበረሀ ወደ ለምለም ምድር ቀይሯታል። ግን በእኛ አስተሳሰብ የመንግሥት ጉዳይ ብቻ ተደርጎ ይታመናል። ሁሉም መንግሥታት በሚታይ ነገር ለአገራቸው አሻራቸውን ያሳርፋሉ። ይህ ክስተት ግን ፖለቲካን ያሳየ የሆነበት ምክንያት ተዓምር በሆነ መልኩ መንቀሳቀስ በመቻሉ ነው። ስለዚህም መሰረት እየተጣለ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።

በሌላ በኩል ወደ አንድ እንድንመጣ የሆነውም በዚህ መንግሥት ዘመን ነው። ለምሳሌ ሁላችንም የተንሰፈሰፍንበትን ምርጫ በአንድ ድምጽ እንዲራዘም የሆነው ፤ ህዳሴ ግድቡ ላይ ሁሉም ያለልዩነት የበኩሉን የሚያበረክተው፤ በተፈጥሮ አደጋዎች ላይ እጅ መዘርጋት የተጀመረው እንደ አገር በመጥፎም ሆነ በጥሩ ነገር ተጋምደን ያለን በመሆናችን ነው። ችግሩ ባይሰራበት ለእኛም የሚተርፍ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደረገን ደግሞ አንድ የሚያደርጉ መድረኮች በመፈጠራቸው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።በዶክተር አብይ የተጀመሩ ጅማሬዎች መልካም ናቸውና ሊደገፉና የበለጠ ሊጨመርባቸው እንዲሁም የመጡ ችግሮችም በጋራ ሊደፈኑ ያስፈልጋል።

የአገር ጉዳይ በማንኛውም ነገር ላይ ቅድሚያ ሊያገኝ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከማክበር መጀመር አለበት። አስተሳሰቡ ከማንም ይምጣ ከማንም ጥቅሙ ለአገር ሆኖ ሳለ መቃወም ብቻ ተግባራችን ካደረግን አገርን ከመክዳት አይተናነስም። ምክንያቱም ማበድ እንኳን የሚቻለው አገር ስትኖር ነው። እናም ለውጥ አለ ስል ዶክተር አብይ አገርን በማበልጸጉ ዙሪያ የሚሰሩት ሥራ ለእኔም የሚበጅና የሚደርስ ነገር አለ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ብዙ የምንቃወማቸው ነገሮች ይኖራሉ። ሆኖም ያንን ደግሞ ማሳመን እስክንችል ድረስ መከራከር፤ ውጤታማነቱንም በማስረጃ ማሳየት ይጠበቅብናል። ይህንን ማድረጋችን ደግሞ የለውጡ ደጋፊና ኃይል እንጂ የአገር ጠላት አንሆንም። ፖለቲከኛ ነኝ የሚያስብለንን ማዕረግ የምናገኘውም ይህንን ጊዜ ነው። ግን የአገርን ጥቅም ትቶ ለውጡ አይጠቅምም እያሉ ማቀንቀኑ ተገቢነት የለውም።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የመደመጥ ፖለቲካ አለ ብለው ያምናሉ?

አቶ ሙሳ፡- ተጀምሯል የሚል እምነት አለኝ። ተስፈኛ መሆን ለተሻለ ነገር ያበቃል። በዚህም ተስፋ ሰጪ ነገሮች መኖራቸውን አይቻለሁ። ባለንበት ላይም እንቀጥላለን የሚል ምልከታ የለኝም። የተሻለውን እንደምናይ አስባለሁ። ንግግር አገርን ያተርፋል፤ የስልጣኔ ምንጭም ነው። ምክንያቱም በእርሱ መዋደድ ፤ መላመድና አንድ መሆን ይመጣል። ይህ ደግሞ በአንድ ሃሳብ የሚመራ ለህዝብና ለአገር የሚያስብ ፖለቲካን ይፈጥራል። ግለኝነትንም ያጠፋል። ስለሆነም ባለው ላይ በመተጋገዝና በቅንነት ነገሮችን በማየት ጨምረንበት የመደመጥ ፖለቲካው ይበልጥ እንዲያድግ ማድረግ እንችላለን። ይህ ደግሞ ፖለቲካው የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዲያመጣ ይረዳዋል። ትንሽም ቢሆን የመደመጥ ፖለቲካ በመድረኮች እንዲጀመርም መሰረት ሆኗል። አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። ሁሉም ዜጋ መናገር፤ የውስጡን መተንፈስና ማድመጥ እንዲሁም መደማመጥ እየጀመረ መጥቷል።

በምክር ቤት ውስጥ እንኳን ብዙ የማንግባባቸው ነገሮች ኖረው እንደማመጣለን። ላለመግባባታችን ዋና ምክንያቱ የትውልድ ልዩነት ነው። አረጋውያኑን ወጣቱ እየተካ የሄደበት ፖለቲካ በአገር ውስጥ አልተገነባም። በዚህም እኔ የምናገረውና እነርሱ የሚናገሩት የተለያየ ይሆናል። መደማመጥ ላይም እንቸጋገራለን። የቃሉን አመጣጥ እንጂ አሁን ምን ለውጥ ያመጣል የሚለውን አይመለከቱትም። ግን በሚፈጠሩ መድረኮች ትንሽም ቢሆን የመደመጥ ፖለቲካው ተስፋ እያሳየ ነው።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

በፖለቲካው ውስጥ ቆይቻለሁ የሚሉትንም ለመግራት እንዲሁ ከባድ ነው። ነገር ግን መሞከር አይከፋምና በተቻለ መጠን ይህንን አቻችሎ ለመሄድ እየተሞከረ ነው። ሁኔታዎች ዛሬ መፈታት የሚችሉ አይነት ባይሆኑም ነገ ሊሆንበት የሚችለው ብዙ ነውና ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠሩ መጓዝ መጀመራቸው ጅማሮውን ያሳያል።

አዲስ ዘመን፡- እርሶ የኢትዮጵያ የፖለቲካ

ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ እንደመሆንዎ መጠን የምክር ቤቱ አላማ ምንድነው?

አቶ ሙሳ፡- አላማው በዋናነት ጽንፍ የወጣውንና የተራራቀውን ፖለቲካ መሰብሰብ ነው። በአንድ ጠረጴዛ አድርጎ የጋራ ሀሳብ እንዲኖር ማስቻልም ነው። መቀራረብ፤ መነጋገር እንዲጀመር ማድረግ፤ ማንኛውም ፓርቲ በእኩል የሚወከልበትና የሚናገርበት እንዲሁም ውሳኔ የሚያገኝበት መንገድ መፍጠር ነው። በፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማስተካከል፤ በፓርቲዎችና በመንግሥት ወይም በተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የጠራ ማድረግም አላማው ነው።

ሌላው እንደ ህግ ፓርቲና መንግሥት የተለያዩ ናቸው። ሆኖም በተግባር ማሳየቱ ላይ ክፍተት አለ። ምንም እንኳን ተወዳድሮ ያሸነፈው ፓርቲ መንግሥትነትን ሊቀበል ቢችልም ከተመረጠ በኋላ ግን ጎራ ይለያል። ከዚያ የመንግሥት ሥራ ከህዝብ ጋር መተሳሰርና ህዝብን ማገልገል ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። እንደፓርቲ ደግሞ ከፓርቲዎች ጋር መሆን ያለበትን ይመክራል። ስለሆነም ይህ እንዲተገበር ማድረግንም ምክርቤቱ አልሞ የሚሰራው ነው።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ያደረጋችሁት መድረክ ፖለቲካውን ከመግራት አንጻር ምን ትርጉም ነበረው?

አቶ ሙሳ፡- ብዙ ትርጉም ነበረው። የመጀመሪያው ወደፊት ልንሰራበት ላለምነው ብሔራዊ መግባባት ሂደት መሰረት ጥሏል። የመማሪያ መድረክ ሆኗል፤ የብዙ ሰዎች አስተሳሰብንና የልብ ትርታንም ለማየት አስችሏል፤ የመድረክ ልምድም የተቀሰመበት ነው። የሚነበቡ ነገሮች፤ የሚነሱ ጥያቄዎችና የሚሰጡ ምላሾች በራሳቸው የሚያስተምሩት ነገርም ነበራቸው። እያንዳንዱ የነበረው ክስተት የቀጣይ መነሻና ትምህርት እንዲሆን ያስቻለም ነበር።

በተለይ በዚህ ውይይት የማንም እውነት እንዳይቀበር የማንም ውሸት እንዳይገን የተደረገበት ስለነበር በመነጋገር ውስጥ እውነቱ የቱ ነው የሚለውን ለመረዳት ፍቱን መፍትሄ የሰጠ ሆኖ አግኝተነዋል። ህዝብም ማን ምንድን ነው የሚለውን በራሱ እንዲወስንም አስችሏል። የፖለቲካ ጨዋታም ጅማሮ ማሳያ ሆኖ አገልግሏል። ግን ሚዲያው እንዳራገበው ባይሆንም ክፍተቶች ነበሩበት። ለብሔራዊ መግባባት ተወጥቶ ልዩነቶችን ማስፋት ተገቢነት ባይኖረውም ይህ ሲስተናገድ ነበር። ብሔራዊ መግባባት ማለት ልዩነታችንንም እናስተናግድ ማለት እንጂ ሀሳቡን ሳንቀበለው እንመንበት ማለት አይደለምና ይህንን አስተካክሎ ለመጓዝም አቅጣጫ ያሳየ ነበርና ትርጉሙ ከቃል በላይ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ጅማሮ እንዲጠናከር ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሙሳ፡- ውይይቱ የሚቋረጥ አይደለም። በየጊዜው የተሻለ ሀሳብን በማምጣት ይቀጥላል። እንደውም በየሳምንቱ ለማድረግም እቅድ አለን። ምክንያቱም አብሮ መዋል በራሱ መዋደድን፤ መቀራረብን፤ መግባባትን፤ ለአገር በአንድነት መቆምን እንደሚያመጣ በጅማሮው ታይቷል። ስለሆነም እስከዛሬ ተበታትኖ በብሔራዊ መግባባት ላይ ሲሰራ የቆየው ተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ለማስቻልና ከገንዘብ፤ ከጊዜ፤ ከጉልበት ብክነት አገርን ለማዳን ሲባል ሥራውን ወደ አንድ በማምጣት በጉዳዩ ዙሪያ ከሚሰሩ 10 ድርጅቶች እና ተቋማት ጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመናል። ከዚህ በኋላም ሥራው በዋናነት በዴስቲኒ ኢትዮጵያ፤ ሰላም ሚኒስቴርና ምክርቤቱ እየመራው የሚሰራ ይሆናል። ተባባሪ አካላትም በዚህ ሁኔታ የሚጓዙበት መንገድ ይፈጠራል። በመሆኑም የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት እውቅና ውጪ አይከናወንም።

አዲስ ዘመን፡- በህወሀትና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ለአገራችን ፖለቲካ ተጨማሪ ችግር አልሆነም?

አቶ ሙሳ፡- በደንብ ሆኗል። መነጋገርና መፍታት የሚቻለው ጉዳይ በእሰጣ ገባ መክረር አልነበረበትም። በሁለቱ መካከል የነበረው አካሄድ ያልተገባ ነበር። ህውሀትን ለመመለስ የተሄደበት ሁኔታ ትክክል አይደለም። እነዚህ ሰዎች አጥፍተዋል፤ ሰው በድለዋል፤ ቀምተዋል፤ አሰቃይተዋል። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ ኢህአዴግ በሚለው ጥላ ስር ሆነው ነው። በዚህ ውስጥ የነበረው ሌላው ፓርቲ ግን የበላይነቱን ከመጠን በላይ አሳልፎ መስጠቱም ይህንን አምጥቷል። ከዚያም በኋላ ቢሆን ለማቀራረብ እንዳይቻል የስድብ ፖለቲካ መጀመራቸው አዳጋች አድርጎታል። የትግራይ ህዝብ ለውጡን በጣም ደግፎ ነበር። ሆኖም የስድድብ ፖለቲካው በአመራሩ ተጧጡፎ መቀጠሉ ህዝቡ አኩርፎ ከህውሀት ጎን የሚቆመውን አበርክቶታል።

ከእርሱ እንዳይርቁ ደግሞ ሊወሩህ ነው፤ ሊያጠፉህ ነው፤ ዝመት እያሉ ያነቃቃል። ስለዚህም በእነዚህ ክፍተቶች ምክንያት ሁኔታው ከሮ ለማቀራረብ እንዳይቻል አድርጎታል። እንደውም እንደ ጋራ ምክርቤቱ ለመግባት ያልተቻለውም አንዱ በአንዱ ላይ የከፈተው የስድድብ ፖለቲካ ነው። የህውሀቶች ጥያቄ የሚፈለግና በቀላሉ የሚደረግ ነው። እርሱም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ይደረግ ሲሆን፤ ይህንን ደግሞ መንግሥትም ይፈልገዋል። ሁለቱም ገዢ ፓርቲዎች በመሆናቸው ሌላ አካል ጣልቃ ሳይገባ ከፉክክር ቤት አውጥቶ በመነጋገር መፍታት አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- የህውሀትን የምርጫ አቋም የጋራ ምክርቤቱ እንዴት ያየዋል?

አቶ ሙሳ ፡- ተገቢነት የሌለው ነው የሚል ምልከታ አለን። ምክንያቱም በተጨባጭ የአባላቶቻችንን መብት ጭምር የሚጋፋም ነው። የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎችን ያላሳተፈ ምርጫ በምንም መልኩ ሊደገፍ አይችልም። እርሱ የሚፈልጋቸውን ብቻ አካቶ ምርጫ ማካሄድም በየትኛውም ስርዓት የሚታገዝበት ሁኔታም አይኖርም። የአባሎቻችንን መብት ለማስከበር እንደ መቆማችንም በተደጋጋሚ ምርጫውን እንደምንቃወምና ተገቢነት እንደሌለው ደብዳቤ ጽፈናል።

በተወካያቸው አማካኝነትም የጋራ ምክርቤቱን አሰራር እንደተጻረሩ፤ በዲሲፕሊን መመሪያችን መሰረት የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ይህንን የማይቀበል ከሆነ ሁለተኛው አካሄዳችን የሚሆነው ከአባልነት መሰረዝና ከዚያም አለፍ ሲል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ሰርተፍኬቱን እስከመንጠቅ ይደረሳል። በእርግጥ ነገሮችን ማጋጋልና ማጋጋም ተገቢ ነው ብለን አናምንም። ሁሉንም የምንወክል አካል በመሆናችንም በብሔራዊ መግባባት ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ ለመቀየስ እንጥራለን ። ሆኖም ስርዓቶች ከታለፉ ግን ልንታገስ አንችልም።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ አገር አሻጋሪና ተስፋ ሰጪ እንዲሆን ማን ምን ይስራ ?

አቶ ሙሳ፡- የመጀመሪያው መሆን ያለበት በብሔርተኝነት አመለካከት ወደኋላ እየመለሱ ትውልዱን በማደንቆር የተካኑ ፖለቲከኞች ጡረታ ይውጡና አዳዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብና እውቀቱ ያላቸው አካላት ወንበሩን ይረከቡ። የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ፖለቲካዊ አካሄዶች በመርህ፤ በፖሊሲ ላይ የተመሰረቱና ከአገርና ከህዝብ ጥቅም አንጻር የተቃኙ መሆን መቻል አለባቸው። በሙያ፤ በእውቀት፤ በምርምር የሚደግፉ ወጣት ፖለቲከኞችን ማፍራት ይጀመር። መሪውም የሚመጥነው ሙያ፤ እውቀትና አቅም ያለውም ሊሆን ይገባል። ክርክሮች የግል ጸብ በሚመስል መልኩ ሳይሆን በፖሊሲና በእውቀት እንዲሁም በአገር ልጅነት አስተሳሰብ ማድረግ ከተቻለ ትክክለኛ ፖለቲካ ይፈጠራል። አገርም በሁሉም መስክ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ መሻገር ትችላለች።

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2012