“Our true nationality is mankind.”H.G.

የፍርድ ቤቶችን ነጻነት ለመለካት “ዳኞቹም በአሁኑ ጊዜ ከሚሰጡት ውሳኔ መመልከት ይቻላል” መአዛ አሸናፊ

አንድ ምሳሌ ልስጥሽ፤ እንድ ጊዜ ውጭ ሀገር ሄጄ ስመጣ የስራ ባልደረቦቼ የዳኞች የአቃቤ ህጎችና የጠበቆች ስብስባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለጠሩ ዛሬ ቀጠሮዎችን እያስተላለፍን ነው አሉኝ። አይ ቆይ እስቲ ግድ የለም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እደውላለሁ ብዬ ስልክ እንስቼ ነው የደወልኩላቸው። ዳኞችን ስብስባ ለመጥራት አስፈላጊ አይደለም ስላቸው ምንም ነገር አላሉኝም። እኛማ የህግ ባለሙያ ሲባል ሁሉንም እየጠራን ነበር አሉኝ። እኔ በዚህ በጣም ነው ያከበርኳቸው። እሱ ብቻ አይደለም እዛ ስብሰባ ላይ ደግሞ ተናገሩ፤ እኔማ ዳኞችንም ልጠራ ነበር አንተ ምን አገባህና ነው ዳኞችን የምትጠራው ተብዬ ነው ብለው ተናገሩ። እና እስከዚህ ድረስ የፖለቲካ ፍላጎቱ አለ ፍርድ ቤት ጠንካራና ነፃ ተቋም እንዲሆን።

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተወለዱ። የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በሕግ ትምህርት አግኝተዋል። በአሜሪካ ኬንታኪ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወ/ሮ መዓዛ በንግድ ሚኒስቴር የሕግ ባለሙያነት፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን በመመሥረትና በመምራት ለሴቶችና ለሕፃናት መብትና ፍትሕ ታግለዋል። በንግድ ዓለምም ውጤታማ ናቸው። የእናት ባንክን ከመሰረቱት ጠንካራ የሀገራችን ሴቶች መካከል አንዷ ናቸው።

በልጅነታቸው ዳኛ እሆናለሁ የሚል ግምት ባይኖራቸውም መብት ሲጣስ ደስ እንደማይላቸው ይናገራሉ። “ምንም ሴት ዳኛ አይደለም በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የምትገኝ ሴት ባልነበረችበት ወቅት እድሉን አግኝቼ ለዚህ መብቃቴ ያስደስተኛል” የሚሉት ወይዘሮ መአዛ እድሉን ካገኙ በኋላ ግን ድምፅ ለሌላቸው ሴቶች ድምፅ በመሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ይናገራሉ። የለውጥ ሀይሉ ለሴቶች ትኩረት ሰጥቶ ሴቶችን ወደስልጣን ማምጣቱ የሚያስመሰግን ነው ይላሉ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊን የፍትህ ስርአቱ በኢትዮዽያ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምን መልክ እንዳለውና ተያያዥ ጉዳዮችን አነጋግረናቸው እንዲህ አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን ፦ ከታሪክ አንጻር የፍትህ ጉዳይ በኢትዮዽያ እንዴት ይገለጻል ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ ፍትህ በሀገራችን ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ነው። በሰው ስነ ልቦና ውስጥ፤ የእለት ከእለት ኑሮ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ አለው፤ በየትኛውም ባህል ቢሆን ፍትህ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ብዙ ሰው የፍርድ ቤት ክርክር ጉዳይ ሊያጋጥመው ይችላል። ወይም ደግሞ ቀጥታ ባያጋጥመው በሌላ ማለትም በዘመድ ጓደኛ አማካይነት ፍርድ ቤት የሚያደርሰው ነገር አይጠፋም። እሱ ብቻ አይደለም አንድ ሰው እድሜ ልኩን ፍርድ ቤት ላይመጣ ይችላል። ነገር ግን የስነልቦና ተስፋ ማለትም ችግር ቢደርስብኝ ከህግ ውጪ አልጠየቅም፤ ከህግ ውጪ አልታሰርም፤ ከህግ ውጪ ንብረቴ አይወሰድም፤ ጉዳት አይደርስብኝም የሚለው ተስፋ የግድ ሰው ውስጥ ሊኖር ያስፈልጋል። ብጎዳ ችግር ቢደርስብኝ በህግ እጠበቃለሁ፤ በህግ እከሳለሁ፤ ህግ ይጠብቀኛል፤ መንግስት ይጠብቀኛል የሚለው የስነልቦና ተስፋ ቀላል ነገር አይደለምና ይሄ ፍትህ በሀገራችን በየትኛውም ባህል ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

በኛ ሀገር ዘመናዊ የፍትህ ስርአት ከ1928 ዓ.ም ጀምሮ በታወቀ ተቋም ፍርድ መሰጠት ጀመረ። በታወቀ ተቋም መሰጠት ቢጀመረም ግን ያን ጊዜም ዛሬ እንደሚታወቀው የአስፈፃሚው ክፍል፤ ህግ አውጪው ክፍል፤ የዳኝነቱ ክፍል ተብሎ በተለያየ ዘርፍ በተከፋፈለ ሁኔታ አልነበረም። አብዛኛውን ጊዜ አስተዳዳሪዎች ራሳቸው ሀገረ ገዥዎች ናቸው ፍርዱን የሚሰጡት። በኋላ ግን ተለይቶ የዳኝነት ስርአቱ ቅርፅ ይዞ ስራ የጀመረው ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አይነት አደረጃጀቶች አወቃቀሮች እየተሞከሩ አሁን ላለንበት የህግ ስርአት ለመድረስ ችለናል።

አዲስ ዘመን ፦ ባህላዊው የፍትህ ስርአት በሀገርና በማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ የነበረው ሚና ምን ይመስላል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ ቀደም ሲል ዘመናዊ ህግ መጥቶ ዘመናዊ የህግ አተረጓጎም ስርአት ከመዘርጋቱ በፊት ህዝብ የሚተዳደረው በባህላዊ ስርአት ነው። ይህ ስርኣት ወጥ አይደለም። ይህም ማለት ሁሉም ህብረተሰብ የየራሱ ስርኣት አለው ማለት ነው። ለምሳሌ በአማራው ባህል ተጠየቅ የሚባለው ባህላዊ የሙግት ስርኣት ነው። በዚህ ስርኣት ዋናው ህግ ላይ ሳይሆን ትኩረቱ የክርክር ሂዱ ላይ ነው። ስርአቱ ሲታይ በጣም ደስ ይላል ድራማ አይነት ነው። በኦሮሚያ በኩል የገዳ ስርአት የራሱ የህግ አሰጣጥና አተረጓጎም ስርአት አለው። በደቡብም እንዲሁ ለምሳሌ የጉራጌ ብሄረሰብና ሌሎቹ የራሳቸው ስርአት አላቸው። እነዚህን ለምሳሌ እናነሳለን እንጂ በሀገራችን የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ባጠቃላይ የየራሳቸው የህግ ስርአት ነበራቸው። ዘመናዊ የህግ አተረጓጎም ስርአት ከተዘረጋ በኋላ ባህላዊ የህግ ስርአቶች በመደበኛነት ስራ ላይ አይውሉም። ይሄ ማለት ግን ህብረተሰቡ አሁንም የነዛን ስርአት ቅሪቶች ይጠቀማል። ሁሉም ህብረተሰብ ዘመናዊ ፍርድ ቤት ለመድረስ አይችልም። ከዛም በተረፈ ዘመናዊ ፍርድ ቤት ጋር ለመድረስ ጊዜ ይወስዳል፤ ውድ ነው። በዚህ የተነሳ በተወሰነ መልኩ ህብረተሰቡ ለተለያዩ ጉዳዮች ባህላዊውን የህግ ስርአት ይጠቀማል።

በአብዛኛው በአሁን ሰአት ህብረተሰቡ የጋብቻና የፍቺ ጉዳዮችን፤ የንብረት ክርክርን በሽምግልናና በተለያዩ ባህላዊ ዘዴዎች ይዳኛል። ሀገሪቱ በአሁን ሰአት ዘመናዊ የህግ ስርአትን በቋሚነት ትከተላለች።

አዲስ ዘመን ፦ የጋብቻ ጉዳዮችን ካነሳን በዘመናዊው የፍች ስርአት ፍትሃዊነትን ከማስፈን አንፃር፤ በተለይም ሴቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ምን ስራዎች ተሰርተዋል ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ የባልና ሚስት ክርክሮች ጉዳይ በፊት በፍትሀብሄር ህግ በቤተዘመድ ጉባኤ ነበር የሚሰራው። የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ላይ እየሰራን ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስርአቶች እንዲሻሻሉ ተደርገዋል። ቀደም ሲል ንብረት የማስተዳደር ሀላፊነት የባል ብቻ ነበር። ህጎቹ ከተሻሻሉ በኋላ ግን በተግባር የሚታዩ ችግሮችም አልጠፉም። ለምሳሌ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ህጉ በወንጀል ያስቀጣል እያለ በተግባር ግን ህብረተሰቡ አንድ ከተማ ውስጥ ሆነው በተለያየ ቀበሌ 2 ቤተሰብ ይመሰርታል። በክልሎችም ለስራ ሲሄድ 2 ጋብቻ ይኖራል።

በዚህ ሂደት አንድ ችግር ሲፈጠር የተፈራው ንብረት ለሁለቱም ቤተሰብ እንዲከፈል እየተደረገ በመሆኑ በቤተሰቡ አበላት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ነው። ሌላው ግልፅ ያልነበረው የሁኔታ ፍቺ የሚባለው ነገር ነው። ሰዎች ጋብቻ ይመሰርቱና ለአመታተ አብረው ስላልኖሩ የተፋቱ ይመስላቸውል። በህግ ስርአቱ ግን ይህ ሁኔታ ተቀባይነት የለውም። በህግ ካልተፋቱ ፍቺ ተፈፅሟል ማለት አይቻልም። የሆነ ችግር ሲፈጠርም አብረን ባላፈራነው ንብረት እንዴት እንከፈላለን የሚሉ ክርክሮች ይነሳሉ። ህበረተሰቡም ይህ ክርክር ትክክል እንዳልሆነ ተረድቶ በጊዜ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ አለበት።

ሌላው በቀደመው ህግ ለወንዶች ሀብትን የማስተዳደር ሀላፊነት ተሰጥቶ በመቆየቱ የሀብት ማሸሽ ነገር በወንዶች በኩል ይታያል። የጋራ ሀብትን ለማሸሽ የሚደረገውን ጥረት ዳኞች እስከ ጠርዝ ድረስ በመሄድ ንብረት የሚያስመልሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

አዲስ ዘመን ፦ ዘመናዊው የኢትዮጲያ የፍትህ ስርአት ሲነሳ ዋነኛው ችግር ምንድነው ? ችግሮቹ መቼ ነው የጀመሩት ብለው ያስባሉ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ የፍትህ ስርአት ስንል ትንሽ ሰፋ ይላል። የፍትህ ስርአቱ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ እድገትና ጉዞ ሊለይ አይችልም። ይህም ሲባል አገሪቱ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ሁኔታ፤ እንደምንፈልገው ህዝቡ እንደሚያስበው፤ መሪዎች እንደሚመኙት ቀጥ ያለ ጉዞ አልነበራትም። በሂደቶቹ መውደቅና መነሳት ወደፊት መሄድና ወደኋላ መመለስ ሂደቱ የሀገራችን የጉዞ ሂደት ብዙ ፈታኝ ነገሮች ያለፉበት እንዲሆን አድርጎት ነው የቆየው። ስለዚህ የፍትህ ስርአቱ ወይም የፍርድ ቤት ዳኝነቱ ዘርፍም ከዚህ የተነጠለ አይደለም። ቀጥ ያለ የልማት ጉዞ ብቻ ቢኖረን፤ የተደላደለ የፖለቲካ ጉዞ ቢኖረን፤ ፍርድ ቤቶቻችንን ዛሬ የምንመኘው ቦታ ጋር ለመድረስ ይችሉ ነበር ማለት ነው።

ግን እነሱም የዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ሰለባ ስለሆኑ ህዝቡን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት አልተቻለም። ያም ሆነ ይህ በተለያየ ጊዜ የነበሩ የሀገሪቱ መሪዎች፤ የፍርድ ቤቶቹ አስተዳዳሪዎች ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በጥረታቸውም ዘመናዊ መዋቅር ለማዘጋጀት ፍትህ ስርአቱን ካደጉ ሀገሮች ጋር የተቀራረበ ሂደት እንዲኖረው ለማድረግ በሰው ሃይል ስልጠናም የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። አሁን እኛም የምንሰራው በዛን ጊዜ በተጀመሩ ጥረቶች፤ በወቅቱ የነበሩት የፍርድ ቤቱ አመራሮች በጣሉት መሰረት ላይ ነው። እነሱ ያስቀመጡት መሰረትን ጥረታቸውን አዳብረን ፍሬ እንዲያፈራ ጥረት እያደረግን ያለነው። መች ነው ችግሮቹ የጀመሩት ሲባል የፍትህ ስርአቱ ከሀገራዊ እድገት ተነጥሎ ስለማይታይ በአጠቃላይ እንደሀገር ይወሰዳል እንጂ በተናጠል የፍትህ ስርአቱ በዚህን ቀን ተጀመረ የሚለው ጉዳይ የለም ።

Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?

አዲስ ዘመን ፦ የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ዘመናዊውን የኢትዮጲያ የፍትህ ስርዓትን ምን ያህል እየፈተኑት ነው?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ እንግዲህ ምናልባት ቀደም ብዬ ካልኩት ጋር የተገናኘ ነው። ምክንያቱም እንደተባለው አንድ ዘመናዊ የሆነ የፍትህ ስርአት ለመዘርጋት በቂ ሀብት ያስፈልጋል። የሰለጠነ የሰው ሃይል ያስፈልጋል። የሰለጠነ ስል በቅጡ የተማረ የሰው ሃይል ያስፈልጋል። ወደ ፍርድ ቤት ሲመጣ ነፃነት ያሰፈልጋል፤ ፍርድ ቤቶችም እንደ ተቋም ነፃ መሆን አለባቸው። ዳኞችም ነፃ መሆን አለባቸው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ባለመሟላታቸው ምክንያት የህዝብ አመኔታ ያገኘ ተቋም የመመስረት ነገር አስቸጋሪ ጉዞ ሆኖ ቆይቷል። የሀገራችንም ሁኔታ እንደልዩ ሁኔታ የምንወስድበት ምክንያት አይኖርም። በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ እድገታቸው የተዋጣ ደረጃ የደረሱ ሀገሮች ናቸው የፍትህ ስርአታቸውን የጠራ መንገድ ይዞ የመጣው እንጂ ሌሎች ሀገሮች ተመሳሳይ ውጣ ውረድ ውስጥ ነው የሚያልፉትና ያሉት። ያም ሆኖ ግን በሂደትና በቁርጠኝነት ከተሰራ እያደገ የሚሄድ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። በሀገራችንም የለውጥ ጅማሬ እያየን እንገኛለን። በተለይም በቅርቡ ለውጦችን እያየን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን ፦ የፍትህ ስርአቱ ውስንነትን በምን ይገለፃል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ ውስንነቱ የሚገለፀው ለምሳሌ ውሳኔዎች በጊዜ አለመሰጠታቸው፤ አንድ መብት አለኝ የሚል ሰው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ይዞ መጥቶ ሶስት አራት አመት የሚጉላላ ከሆነ ይሄ አንድ ውስንንት ነው። እንዲህም ሆኖ ደግሞ ውሳኔው ተገማች ካልሆነ ይሄም ሌላ ውስንነት ነው። መቼም ሁልጊዜ አንድ ሰው ክስ ስለቀረበበት ወይም ስላልቀረበ ይፈረድለታል ማለት አይደለም። ነገር ግን ደግሞ ብዙ ጊዜ ከህግ ውጪ የሆኑ የማይጠበቁ ውሳኔዎች ከሆኑ ችግር አለ ማለት ነው። ይህም በዳኞቹ ላይ የብቃት ጥያቄ ያስነሳል። ወይም ነፃ ሆኖ የመስራት ችግር ይኖርባቸዋል ማለት ነው። በሶስተኛ ደረጃ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መጉላላት ካለ፤ ለምሳሌ ሰው መጥቶ ሊያስፈፅም የፈለገውን ጉዳይ በእለቱ አስፈፅሞ በጊዜ በትህትና በአክብሮት ተስተናግዶ ካልሄደ ይሄም ሌላ ችግር ነው። ስለዚህ እንግዲህ አሁን ፍርድ ቤቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች የመካተት ስራ ሰርተናል።

ይህም ሲባል አንደኛ ጉዳዮች በተቻለ ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንዲወሰኑ የሚያግዙ ስርአቶችን እያበጀን ነው። ሁለተኛው የፍርድ ጥራት እንዲሻሻሉ ስልጠናዎችን በመስጠት አንዳንድ ጊዜ የኢንስፔክሽን ክፍል በመመስረት፤ ውሳኔዎችን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንዲታዩ በማድረግ ዳኞች እንዲታገዙ የሚያስችል አሰራር እየፈጠርን ነው። ለምሳሌ ባለፈውና በዚህ አመት 185 ረዳት ዳኞች ተቀጥረዋል። ይህ ለምንድነው ዳኞች እንዲታገዙ ነው፤ እና ሲታገዙ የያዙትን ጉዳይ ቶሎ ቶሎ እንዲመለከቱት በማድረግ ጥረታቸውንም ለማሻሻል ያግዛል ተብሎ ነው። ሶስተኛው አገልግሎት አሰጣጥን ለመሻሻል ወደ 70 ሬጅስትራሮች ተቀጥረዋል። በየደረጃው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች ይህ ለምንድ ነው ? ሰው መጥቶ ረጅም ሰልፍ ይዞ እንዳይጉላላና ቶሎ ተስተናግዶ ወደቤቱ እንድሄድ ለማድረግ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የዳኞች ነፃነት ማጣት ስንል በህጉ ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አለው እያልን ይሆን ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ይሄን እንግዲህ እኔ ከምለው በላይ አሁን ዳኞች በተጨባጭ በስራቸው እያሳዩት ያለ ይመስለኛል። እኔ በተደጋጋሚ ስጠየቅ የምሰጠው መልስ አንድ ነው። ምንም አይነት የፖለቲካ ጫና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አልደረሰብኝም። እንደውም የሚጠቅም ከሆነ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ፤ እንድ ጊዜ ውጭ ሀገር ሄጄ ስመጣ የስራ ባልደረቦቼ የዳኞች የአቃቤ ህጎችና የጠበቆች ስብስባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለጠሩ ዛሬ ቀጠሮዎችን እያስተላለፍን ነው አሉኝ። አይ ቆይ እስቲ ግድ የለም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እደውላለሁ ብዬ ስልክ እንስቼ ነው የደወልኩላቸው። ዳኞችን ስብስባ ለመጥራት አስፈላጊ አይደለም ስላቸው ምንም ነገር አላሉኝም። እኛማ የህግ ባለሙያ ሲባል ሁሉንም እየጠራን ነበር አሉኝ። እኔ በዚህ በጣም ነው ያከበርኳቸው። እሱ ብቻ አይደለም እዛ ስብሰባ ላይ ደግሞ ተናገሩ፤ እኔማ ዳኞችንም ልጠራ ነበር አንተ ምን አገባህና ነው ዳኞችን የምትጠራው ተብዬ ነው ብለው ተናገሩ። እና እስከዚህ ድረስ የፖለቲካ ፍላጎቱ አለ ፍርድ ቤት ጠንካራና ነፃ ተቋም እንዲሆን።

ዳኞቹም በአሁኑ ጊዜ ከሚሰጡት ውሳኔ መመልከት ይቻላል፤ አሁን በነፃነት ህጉን ብቻ ተከትለው እየሰሩ ይገኛሉ። በሂደት ደግሞ በበለጠ ፍርድ ቤቱ እየተፈተነና እየጠነከረ ይሄዳል።

አዲስ ዘመን፦ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ አዳዲስ ህጎች ይወጣሉ ከሚወጡት ህጎች ብዛት የተነሳ ዳኞቹም አያውቋቸውም የሚባል ነገር አለ እርሶ በዚህ ላይ ምን ሀሳብ አሎት?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ ህግማ ይወጣል። ህግ መውጣት አለበት። ባደገው ሀገር በአመት በሺዎች የሚቆጠሩ ህግች ናቸው የሚወጡት። ይህ ከህብረተሰቡ እድገት ጋር የተያያዘ ነው ። አዲስ ፍላጎት ሊመጣ ይችላል ለዛ ፍላጎት መልስ ለመስጠት ህጎች ይወጣሉ። ነባር የሆኑት ህጎች ደግሞ ምናልባት ከህብረተሰብ ለውጥ ጋር ተያይዞ መሻሻል ሊኖርባቸው ይችላል። ስለዚህ ቀጣይ ስራ ነው ህግ የማውጣት ስራ። ትልቁ ጉዳይ ዳኞች በዚህ ረገድ አዲስ የሚወጡ ህጎች ላይ ምን ያህል ክትትል እያደረጉ ራሳቸውን እያሳወቁ ይሄዳሉ የሚለው ጥሩ ጥያቄ ነው።

እሱን በተመለከተ የዳኞች ስልጠናን ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ለዚህም እንደ ምሳሌ የማነሳልሽ አራት አዲስ የወጡ ህጎች ላይ ለዳኞቻችን ስልጠና ተዘጋጅቷል። ይህም የፀረ ሽብር ህግ፤ የአስተዳደር ህግ ስነ ሰርአት፤ ማለት የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ ወደፍርድ ቤቶች በምን ሰአት ነው የሚመጣው የሚለውን በተመለከተ የሚወጣውን ህግ፤ የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ ህግ፤ ውጭ ሀገር የሚወሰኑ ውሳኔዎች በሀገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች አፈፃፀማቸው ምን ይምስል በሚለው ላይ ስልጠና ይሰጣል። ከስር ከስር አዲስ ህግ ሲመጣ ዳኞቹ ይሰለጥናሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ህግች ሲወጡ ዳኞችም አስተያየት የሚሰጡባቸው መድረኮች ይመቻቻሉ። የተለያየ አዋጆች ሲወጡ በህግ አተረጓጎም ምን ችግር አስከተለባችሁ ከዚህ ቀደም የታዩ ችግሮች ምን ይመስላሉ የሚለውን ከህግ አውጪዎች ጋር በተጠናከረ ሁኔታ አሁንም በቀጣይም ይሰራል።

አዲስ ዘመን ፦ አሁን በፍትህ ስርአት ውስጥ ምን እየተሰራ ይገኛል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ በዚህ አመት 134ሺ ጉዳዮች በሶስቱም ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶች እልባት አግኝተዋል። በመሃል ትእዛዝ አለ እግድ አለ ብይን አለ ብዙ ነው የመዝገብ ስራ ኣለ። በበጀት ደረጃ ቋሚ በ2010 ዓ.ም እና በ2011ዓ.ም የፍርድ ቤቱ ጠቅላላ በጀት ስንመለከት ወደ 98 ሚለዮን ብር አካባቢ ነበር። ዘንድሮ 138 ሚሊየን ብር ተበጅቷል ይህም ማለት ከባለፉት ዓመታት 40 በመቶ ጭማሪ አድርጓል። ሌላው ብዙ ጊዜ ፍርድ ቤቶች የሚመዘኑበት ቅልጥፍና ጉዳይ ነው። ይህን ስንመለከት ፍርድ ቤቶች አሁን ላይ ውሳኔዎች ቶሎ ቶሎ እየተሰጡ ናቸው። የሚፈለገው ደረጃ ላይ ባንደርስም መሻሻሎች አሉ። የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ብቻ ብነግርሽ ከ15 ሺ በላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተወሰኑት መዝገቦች ውስጥ 94.8 በመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች ከአንድ ዓመት በታች ባለ ጊዜ የተወሰኑ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ እስከ 5 አመት 6 አመት ይቆያሉ የሚባሉ መዝገቦች አሉ። ይህ እውነት ነው። እነሱ ግን ውስን እየሆኑ ነው። አሁን በዚህ ሰአት ያልተገደበና የተንዛዛ ቀጠሮ ላይ ገደብ እየተበጀ ነው። በዛ ረገድ ጥሩ አፈፃፀም ላይ ነን ለማለት እችላለሁ።

አዲስ ዘመን፦በቅርቡ የፍትህ ስርአቱን ለማዘመን የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች እንዴት ይገለጻሉ? ምን ደረጃ ላይ ደርሰዋል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ የሪፎርም ስራን በተመለከተ በርካታ የሪፎርም ሰራዎች እየተሰሩ ነው። ትልቁ ሪፎርምን ሙሉ ለሙሉ እንድንገባበት ያደረጉ ሁለት መሰረታዊ አዋጆች ተዘጋጅተው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበዋል። አንዱ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን የተመለከለተ ነው። ይህ ጉባኤ ዳኞችን የሚያስተዳድር ጉባኤ አካል ነው። የፍርድ ቤቱ አስተዳደር አለ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ደግሞ አለ። ይህ ጉባኤ በፍርድ ቤቱ ፕረዚዳንት የሚመራ ሲሆን የዳኞችን ሹመት ምልመላ፤ ጥቅማ ጥቅምና የስነምግባር ጉዳይ የሚመለከት ነው። ይህን ጉባኤ ስልጣኑን ለማስፋት እንደገና ደግሞ የጉባኤውንም ጥንቅር ለማሻሻል በተለይም ደግሞ የዳኞች ፍላጎት በበቂ ሁኔታ እንዲወከል ለማድረግ በጣም ዘመናዊ የሆነ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለፓርለማ ቀርቧል።

Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች

ሌላው ደግሞ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ነው። እሱም ብዙ የሚለውጧቸው ጉዳዮች አሉ። ከፍርድ ቤቱ የድጋፍ ሰራተኞች አስተዳደር ጀምሮ ማለት ነው። የድጋፍ ሰራተኞች በሲቪል ሰርቪስ ስር ቢሆኑም ፍርድ ቤቱን ውጤታማ ለማድረግ እነዚህን ሰራተኞች ወደ ፍርድ ቤቱ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ለማምጣት አዋጅ ውስጥ ተካቷል። ፍርድ ቤቱ የበጀት ነጻነት እንዲኖረው ተካቷል። ፍርድ ቤቱን ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሁለት አዋጆች አሁን ለፓርላማ ቀርቧል። በኮረና ምክንያት ፓርላማ ሙሉ ለሙሉ ባለመስራቱ የተነሳ ተወያይተው ለማፅደቅ ሳይችሉ ቀሩ እንጂ በአዲሱ በጀት አመት ፓርላማ ሲከፈት በመጀመሪያ እንደሚታይ ቃል ተገብቶልናል።

ፓርላማው እስኪከፈት ድረስ ግን እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ አላልንም። ከስር ከስር ሌሎች የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ ነው። ከስራዎቹም መካከል የረዳት ዳኞች ቅጥርና የማሰማራት ስራ፤ ምቹ የስራ ቦታ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው። ፍርድ ቤቶች በምቹ ቦታዎች ስራቸውን እንዲያከናውኑ ህንፃዎችን ተከራይቶ ከማስቀየር በላይ አዳዲስም ለመስራት እቅድ ተይዟል።

አዲስ ዘመን፦ አሁን ካለው የፍትህ ስርአት ውጪ የባህላዊው የፍትህ ስርአት ትኩረት እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ አለ ? ለምሳሌ፡ ጥፋት እየተፈፀመ ፍርድ ቤት ከደረሰ በሁዋላ ሽምግልና የሚባልበት ሁኔታ አለ። ይህን እንዴት ያዩታል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ የመደበኛ ፍርድ ቤቶች ስራ መደበኛውን ህግ መተርጎም ነው። መደበኛው ህግ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ነው። የባህላዊ ስርአቶችና ባህላዊ ህጎች አስፈላጊ አይደሉም ማለት ግን አይደለም። በተለይ ከአለማቀፍ ደረጃ ጋር የተጣጣሙ ከሆኑ መደበኛውን ህግ የማይጥሱ እስከሆኑ ድረስ ባህላዊ ስርአቶች ይበረታታሉ። ህዝቡ በሽምግልና በባህላዊ ስርአት ጉዳዮችን ቢፈታ ጥሩ ነው። ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌላ የፍትህ አካላት ሁሉን ጥያቄ ለመመለስ ከህዝቡ ብዛት አንፃር በጣም አስቸጋሪ ነው። በመደበኛው የፍትህ ስርአት ውስጥ ግን ተካቶ አይሰራም። ባህላዊ ፍትህ ስርአት ከሚያከናውኑ አካላት ጋር በመመካከር የሰዎችን መብት በማይነካ መልኩ ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲያልቅ ሲደረግ የፍርድ ቤት ጫናን ስለሚቀንስ ይበረታታል።

አዲስ ዘመን ፦ ባህላዊውን የፍትህ ስርአት አሁን ካለው የፍትህ ስርአት ጋር አነፃፅረው ቢነግሩኝ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ በዚህ ጉዳይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ከኔ የተሻለ ስለዚህ ጉዳይ ይናገራሉ። ግን በእኔ በኩል ዘመናዊ የፍትህ ስርአት በብዛት አለም አቀፍ ደረጃዎችን ነው የተከተለው። በፍትሃብሄርም ሆነ በወንጀል ብዙዎቹ ህጎቻችን በስልሳዎቹ የወጡት የሌሎች ሀገሮች በተለይም ኮንቲነታል የሚባሉት እንደ ፈረንሳይ ያሉ ሀገሮች ህግ ተከትሎ ነው ።

ባህላዊ ህጎችና ሰርአቶች ደግሞ የሃይማኖት ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዱ ደግሞ ከአኗኗር ዘዬዎች ሲወራረስ የመጣ የፍትህ ስርአት ይሆናል። ሁለቱን ለማወዳደርና ለማመሳከር አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ዘመናዊ ህጎችም ቢሆኑ ምንጫቸው መሰረታቸው ወይም መነሻቸው ከዛው ከህብረተሰቡ አኗናርና ባህላዊ ስርአት ጋር የተገናኘ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ በህዝብ ዘንድ የፍትህ ስርኣቱ ተአማኒነት እንዲረጋገጥ የናንተ ጥረት እስከምን ዘልቆዋል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ፦ ይህ ሁሉ የሚደረገው ጥረት የህዝብን ተአማኒነት ለማግኘት ሲባል ነው። ትልቁ ራእይም የህዝብን ተአማኒነት ለመመለስ ነው። ተአማኒነቱንም ለመመለስ ሶስት ነገሮችን ነው ማድረግ ያለብን። አንዱ ተገማች ውሳኔ መስጠት ነው። ሁለተኛው የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ማለትም ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት። ለተገልጋዩ አገልግሎትን በትህትናና በአክብሮት መስጠት። ሰው ፍርድ ቤት ሲመጣ ብዙ ሀሳብና ጭንቀት ይዞ ነው የሚመጣው። ቢያንስ እዚህ ሲመጡ እንደየ ተገልጋዮቹ ሁኔታ ቅድሚያ መስጠት ለሚገባው ቅድሚያ በመስጠት የተገልጋዮችን ችግር እንደረሳችን ችግር አድርገን በማሰብ ብናገለግል ተአማኒነትን መመለስ ይቻላል።

በዚህ ረገድ የተለያዩ ስለጠናዎች ለዳኞችና ለአገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች በመስጠት ተአማኒነትን የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው። አሁን በተደረገ ቀላል ጥናት በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወደ 80 በመቶ ተገልጋዮች የአገልግሎት አሰጣጡ እንደተሻሻለና እርካታ እንዳገኙ ለመመልከት ተችሏል።

በሶስቱም ፍርድ ቤቶች በሚገኘው ግብረ መልስ የተሻሉ ነገሮችና ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች መኖራቸውን ያሳያሉ። ዳኞች በነፃነት ስራቸውን መስራታቸው፤ የፍርድ ቤት አስተዳደሮች የተገልጋዩን ቅሬታ ለማዳመጥ መቻላቸው፤ ኢንስፔከሽን ክፍል ተቋቁሞ በዚህ አመት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ 250 አቤቱታዎች በዚህ ክፍል መስተናገዳቸው የእንቅስቃሴው አካል ናቸው። ሌላው የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ክፍል ተቋቁሞ የትኛው ጉዳይ መቼ ማለቅ እንዳለበት የሚመራ መመሪያ ተዘጋጅቶ ጉዳዮቹ የሚያልቁበትን ጊዜ በማስቀመጥ ከዳኞች ጋር በመግባባት ላይ የተደረሰበት ሁኔታ አለ። ሁሉም የፍትህ አካላትና አገልግሎት ሰጪዎች ተቀናጅተው ተገልጋዩን ህብረተሰብ ወደማርካት ስራ እየሄዱ ነው። በሌላ በኩል ሁለት ተከራካሪዎች ባሉበት ሁለቱንም ወገኖች የሚያስደስት የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን እውነትንና ህግን በያዘ መልኩ ውሳኔ ተሰጥቶ ካልረኩ በተለያዩ ደረጃዎች ይግባኝን ማቅረብ ይቻላል። ካልሆነ ግን ውሳኔዎችን አክብሮ መቀበል በህብረተሰቡ ሊለምድ የሚገባው ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የፍትህ ስርዓቱን ውጤታማ በማድረግ ሂደት ውስጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦዎች በምን ይገለጻሉ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ እስካሁን የተነጋገርናቸው ነገሮችን ያጠቃለለ ጥያቄ ነው የጠየቅሽኝ ። ከእነዚህም መካከል የፍርድ ቤቱን እንደ ተቋም ነፃ እንዲሆን ማድረግ፤ በጀት ራሳችን በፓርላማ ተደራድረን ለማምጣት መቻላችን፤ በጀት ለማሳደግ መቻላችን፤ ዳኞች ነፃ ሆነው እንዲሰሩ ግልፅ የሆነ አቋም በፍርድ ቤቱ በመያዙ ከሌሎች አካላት ተፅእኖ አለመኖሩ፤ የዳኞች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነው ጥቅማ ጥቅምና ደሞዝ ሁኔታ ውሳኔ ማግኘቱ፤ ተጀምሮ ለረጅም ጊዜ ቆሞ የነበረው የዳኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ መጠናቀቁ፤ አገልግሎቱን ለማሻሻል ተጨማሪ ሬጅስትራሮችን የመቅጠራችን ጉዳይ፤ ረዳት ዳኞችን መቀጠራቸው እነዚህ ሁሉ አዋጆች እንዲወጡና የህግ ስርአቱ እንዲዘረጋ የማድረግ እርምጃ መወሰዱ፤ ምቹ የስራ ቦታ እንዲፈጠር ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ለመስራት መመከሩና ውጤትም ማየታችን፤ በቀጣይ አመት የከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ፍርድ ቤት ህንፃ ለመገንባት ስራ መጀመሩ በጎ ጎን ነው ብዬ አስባለው።

በበለጠ ግን ተገልጋዩ ህዝብ ፈራጅ መሆን ይችላል። ስለስራችን ሁሌም አስተያየቶች ገንቢ ስለሚሆኑ ስራዎችን የተሻለ ለማድረግ ህብረተሰቡ ባገኘው አጋጣሚ አስተያየቱን ቢሰጥ መልካም ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፦ የዳኞች ጥቅማ ጥቅም ስንል ምንድን ናቸው? ስለቤቶቹም በዝርዝር ቢያስረዱን?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦የዳኞች ጥቅማ ጥቅም ስንል መጓጓዣ አበልና የመኖሪያ ቤት አበል የሚመለከት ነው። አበል ካልሆነ ደግሞ የመኖሪያ ቤት መስጠት ነው። እነዚህ ጥያቄዎች የረጅም ጊዜ የዳኞች ጥያቄዎች ነበሩ። በዚህ አመት እነዚህን ጥያቄዎች መመለሳቸው ትልቅ ነገር ነው። ዳኞች ደሞዛቸው ተመሳሳይ ስራ ከሚሰሩ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ያነሰ ነበር፤ ከፍተኛ ኃላፊነት ለሚጠበቅበት ደኛ ይህ ተገቢ አይደለም። አንድ ዳኛ ከፍተኛ የስነ ምግባር ዝግጁነት ሊኖረው ይገባል። ስራው ፋታ የሚሰጥ አይደለም። ቢሮ እና ቤት የሚሰራው ስራ ቢያንስ በሀገሪቱ አቅም ልክ ህዝብን የሚያገለግሉ ዳኞችን ፍላጎት የሚያረካ መሆን አለበት።

በዚህ ረገድ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ወስኖ በመንግስት በኩል የደሞዝ ጉዳይ ተፈፃሚ ሆኗል። የህንፃ ጉዳይ በቀደሙ አመራሮች የተጀመረ ጉዳይ ነው። ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል፤ መገናኛ አካባቢ የተሰራው ሁለት መቶ ሰባ ቤቶች ያለው ዘመናዊ አፓርትመንት ተሰርቶ 80 ቤቶች ቤት ለሌላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ በተቀመጠ መመሪያ መሰረት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዳኞች ተደልድለዋል። ቀሪዎቹ ቤቶች በሁለት ወር ውስጥ የሚጠናቀቁ ይሆናል። ሁሉም የመጨረሻ ስራቸውን ሲያጠናቅቁ ደግሞ ሁሉም ዳኞቻችን ቤት ይኖራቸዋል ማለት ነው።

Related stories   ኦሮሞ ኦሮሞን አድፍጦ እየገደለ ነው፤ ኦነግ ሸኔ ለስራ የሚጓዙ አምስት ኦሮሞዎችን ገደለ

ይሄ ታላቅ ታሪካዊ ጉዳይ ነው። ይሄም ፍፃሜ እንዲያገኝ በርካታ ጥረት ተደርጎ ፤ የኮንስትራከሽን ሚኒስትር ትኩረት ሰትቶ ነው ስራውን የሰራው።

አዲስ ዘመን፦ ከደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ ጋር ዳኞች በሙስና ይታማሉ ይህ ችግር መፈታቱ የተባለውን ነገር ይቀንሳል ብለው ያምናሉ?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦የስነ ምግባረ ብልሹነት ከገቢ ጋር ይገናኛል ወይስ አይገናኝም የሚባለው ጥናት የሚያስፈልገውና በርካቶችም ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩበት ጉዳይ ነው። የስነ ምግባር ጉዳይ የአንድ ሰው ማንንትና እምነት ጋር የሚያያዝ እንጂ በገቢ ምክንያት አይደለም የሚሉና፤ መሰረታዊ ነገር ካልተሟላለት ችግር ውስጥ ያለ ሰው ሊፈተን ይችላል የሚሉ አሉ። ‘ ዞሮ ዞሮ ኃላፊነትን ምክንያታዊ ሁኔታዎች እስከተመቻቹ ድረስ ሀላፊነትን በአግባቡ መወጣት የግድ ነው። ይህን ተግባር የሚፈፅም ሰውም መወገዝ የሚገባው ነው።

ስለጉዳዩ እስካሁን በተጨባጭ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ህብረተሰቡ ደላሎች እንዳሉና ስጋት እንዳለባቸው ጥቆማ ይሰጣሉ። ይህን የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ደግሞ ጥቆማ ስጡን ሲባሉ ለመስጠት ያፈገፍጋሉ። በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ይሄን ችግር ለመቅረፍ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ቢሰጥ ከሀሜትና ከስሞታ በዘለለ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል።

የፍትህ ስርአቱ እንዲፀዳ ህዝቡ በተቋሙ ላይ እምነት አሳድሮ የሙስና በሮችን መዝጋት ይኖርበታል። በአሰራርም እየፀዳ ሲሄድ ይህ የሙስና ጉዳይ ከፍትህ አካባቢ እንዲጠፋ ማድረግ የሚቻል ይሆናል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፦የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናው ምን ያህል እየተሻሻለ ነው?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማስተካከል በተለያዩ ችሎቶች ቁጥር የመስጠት፤ ለደካሞች ቅድሚያ ለመስጠት የሚቻልበት ሁኔታዎች እየፈጠርን ነው። አሁንም ግን ከሰው ቁጥር መብዛት ጋር መጉላላት ቀርቷል ለማለት አያስደፍርም። በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የተገልጋይ ቁጥር ለማርካት እየተሞከረ ነው።

ህብረተሰቡም ለለውጥ በአስተያየት መስጫ ሳጥኖች ስላጋጠሟቸው ጉዳዮች ቢፅፉ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ለመስራት ጥረት ይደረጋል።

አዲስ ዘመን ፦ ክልሎች በውክልና የሚሰሩት የፍትህ አሰጣጥ በእናንተ እይታ ምን ያህል ስኬታማ ነው?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ በውክልና የሚሰሩ አምስት ክልሎች አሉ ሶስት ክልሎች ደግሞ በተዘዋዋሪ ችሎት ኣገልግሎቱ ይሰጣል። እነዚህ ሶስቱ ደቡብ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ናቸው። እንደ አማራ ኦሮሚያ ትግራይ ያሉ አካባቢዎች የፈዴራል ጉዳዮችን በክልል ወክለው ይሰራሉ። ይህም ህገ መንግስቱ ላይ ተቀምጧል። ከዛ ውጪ ከማንኛውም ክልል ይግባኞች ወደ አዲስ አበባ በሁለት መልኩ ይመጣሉ። አንድ ወደ ሰበር ችሎት ወይም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይመጣሉ። ይህ ምንድ ነው በሁለት ክልል የሚኖሩ ተከራካሪዎች ወይም ተቋሞች ውስጥ ያሉ ክርክሮች ናቸው።

በዚህ አመት ከክልሎች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጡ ጉዳዮች 565 ናቸው። ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ የመጡት 8ሺ 664 መዝገቦች ናቸው። የውሳኔ አሰጣጥ ተመሳሳይነት በአጠቃላይ በሀገሪቱ ምን ይመስላል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ለዚህ እንደማሳያ የምንመለከተው ከመጡት ይግባኞች ውስጥ ወደ ሰበር ከመጡት ጉዳዮች 2.5 በመቶ ብቻ ነው ውሳኔው የተቀየረው። ይህ ማለት የክልል ፍርድ ቤቶች ጥሩ እየሰሩ ነው ማለት ነው።

በሁለት ክልሎች መካከል የሚነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ በይግባኝ የተለወጡ ጉዳዮች 11 በመቶ ናቸው። እነሱ ትንሽ ከፍ ቢሉም ይሄን ያህል መጥፎ አይደለም። ከዛ ውጪ እንደተግዳሮት የሚታየው የመዝገብ ግልባጭ አለመነበብ፤ ትርጉሞች ግልፅ አለመሆን፤ መዝገብ ይምጣ ሲባል የመዘግየት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ።

ህዝቡ በአካል ካለበት ተነስቶ በምምጣት እንዳይጉላላ እኛ ኢ ፋይሊንግ በሚባል የኦላይን ስርአት አቤቱታዎች ቀጥታ እንዲመጡ በየክልል ፍርድ ቤቶች የተቀመጡ ሰራተኞች በመኖራቸው ህዝቡ በእነሱ በኩል እየተጠቀመ ይገኛል። ይሄም አንዱ የሪፎርሙ አካል ነው። በዚህ በኮረና ጊዜም ዳኞች የመዝገብ ውይይት በኦን ላየን ማድረግ መጀመራቸውም አንድ ለውጥ ነው።

አዲስ ዘመን ፦በዚህ አጋጣሚ የፍትህ ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ምን እየሰሩ ነው?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦የኮሮና ጉዳይ አስጊ በመሆኑ ምክንያት መጋቢት ወር ውስጥ ፍርድ ቤቱ በከፊል ለመዝጋት የተገደደበት ሁኔታ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ በአንድ ቀን ፌደራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ ወደ 18 ሺ ሰው ይመጣል። ይህም ከባድ የሰው ጥግግት ነው። የሚያደርሰውም የአደጋ መጠን ስላልታወቀ ፍርድ ቤት በከፊል ቢዘጋም ስራ ሳይቋረጥ ቆይቷል። በኮረና ዘመን ከመጋቢት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ከ7ሺ በላይ መዝገቦች ውሳኔ ተሰጥቷል። ከሀምሌ 13 ጀምሮ ደግሞ ፍርድ ቤት ሙሉ ለሙሉ ክፍት ተደርጓል። የፍትህን በር ዘግቶ ለረጅም ጊዜ መቆየት ስለማይቻል የፍርድ ቤት እረፍትን ገፋ አድርጎ እስከ ነሀሴ መጨረሻ በመስራት መስከረምን ያርፋሉ።

ምን አይነት ጥንቃቄ ላልሽው ፍርድ ቤቱ ሲከፈት መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ለማድረግ እየተሰራ ነው። እጅ መታጠብን፤ የሙቀት ልኬት ይደረጋል፤ ለሰራተኞችም ከለጋሾች ድጋፍ በመጠየቅ ዩ ኤስ ኤድ ለጥንቃቄ የሚያገለግሉ ድጋፎችን በማድረጋቸው ሰራተኞችም ራሳቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን ፦ ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ በስፋት የሚነገረውን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?

ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፦ በወቅቱ የሚነሳውን ነገር እንደ መረጃ ከማየታችን በፊት በሀገሪቱ የተደራጀና የተሟላ የመረጃ ስራ ያስፈልጋል። አንድ ነገር ሲከሰት መነገሩ ጥሩ ሆኖ ሳለ በመረጃ የተደገፈ ጠንካራ ነገር አለመኖሩን ነው የማውቀው። ባለፈው ዓመት ማርች 8 አስመልክቶ ፖሊስ አቃቤ ህግ ዳኞችን በመሰብሰብ ስለ ጉዳዩ ውይይት አድርገን ነበር። በውይይቱ ላይ የተነሳው ሀሳብ ፖሊስ ምርመራ አድርጎ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት በአነስተኛ ዋስ ይለቃል የሚል ትችት ይቀርባል። ከዚሀም በተጨማሪ ተጠርጣሪዎቹ ሲለቀቁ ደግሞ አይመለሱም የሚል ነገርም አለ። ዳኞቹ ደግሞ በህጉ መሰረት ነው የምንሰራው ይላሉ። በዋስ ወጥተው ቀሩ የተባለውም በዚህ አመት በታየ መረጃ 2 ሰው ብቻ ነው።

በቂ ቅጣት አይሰጥም የሚል ቅሬታም በዳኞች ላይ ይነሳል። እሱም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አለ ቅጣት የሚሰጥ መመሪያ አለ። ከዛ ውጪ ተወጥቶ ውሳኔ ኣይሰጥም ተሰጥቶ ከተገኘም በይግባኝ ማስተካከል ይቻላል። ወጣ ያሉ ነገሮች ካሉ ደግሞ በስነ ምግባር ዳኞች ይጠይቃሉ። ለዚህ ግን ተጨባጭ መረጃ ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ፍርድ ቤት የደረሱ ጉዳዮች በሙሉ ይወሰናሉ። በዚህ አመት 2012 የፆታዊ ጥቃትን የተመለከቱ 302 መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል። ፍርድ ቤቶች በየጊዜው መረጃ ባለመስጠታቸው ወቀሳዎች ቢበዙም ውሳኔዎች እየተሰጡ ነው። ከእነዚህ መዝገቦች ውስጥ 44 መዝገቦች በኮረና ጊዜ ውሳኔ የተሰጠባቸው ናቸው። ይሄውም የጥቃት ጉዳይ ላይ ችሎቶች ስራ እንዳያቆሙ መመሪያ ተሰጥቶ ስለ ነበር ነው።

ችግሮቹን ለማንሳት ጥቃቶች ላይ በጊዜ መረጃ አሰባስቦ ክስ መመስረት ቀላል ጉዳይ አይደለም። በዳኞች በኩል ያለው ቅሬታ ማስረጃው በትክክል ተደራጅቶ አይቀርብልንም የሚል ነው። ውሳኔ ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ አይኖርም። ከሀኪሞች ምርመራ ጀምሮ በጥንቃቄ የማይሰራበት ሁኔታ አለ። ፍርድ ቤት በማስረጃ ስለሆነ የሚሰራው በቅንጅት የተደራጀ መረጃ ቀርቦ በቂ ውሳኔ ለማሰጠት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2012

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0