የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ ሶሊያና ሽመልስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የግንባሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለቦርዱ በላከው ደብዳቤ ላይ ባካሄደው ስብሰባ መሰረት “አቶ ዳውድ ኢብሳ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል” ብሎ ከግንባሩ አመራርነት መታገዳቸውን ገልጿል።

ጉዳዩን በተመለከተም የፓርቲው የሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ መላኩንም በደብዳቤው አስታውቋል።

ቃል አቀባይዋ እንደገለጹት የደረሳቸው ደብዳቤ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የተፈረመ ነው።

በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እገዳ ሲያደርግ ለሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ እንደሚልክ የገለጹት ሶሊያና፤ በደብዳቤው ላይ ለኮሚቴውን ማሳወቃቸውን ከመገለጹ ውጪ ከቦርዱ የጠየቁት ምንም ዓይነት ውሳኔ አለመኖሩን ተናግረዋል።

Related stories   በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

ታግደዋል ከተባሉት ከአቶ ዳውድ ኢብሳ በኩልም ሌላ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ቃል አቀባይዋ ገልፀዋል። ነገር ግን ደብዳቤው ከዚህ በፊት በነበረው የሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ የተፃፈ ሲሆን ቀደም ሲል የተካሄዱ የፓርቲውን ስብሰባዎች የተመለከተ እንጂ ከእገዳው ጋር የተያያዘ አለመሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ቦርዱ ከሁለቱም ወገኖች የሚመጡ ደብዳቤዎችን መተዳዳሪያ ደንባቸውን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች መተዳዳሪያ አዋጅን መሰረት አድርጎ እንደሚመረምር አክለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሮ ውዝግብ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፤ በግንባሩ የረዥም ጊዜ ሊቀመነበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና በምክትል ሊቀመበሩ በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመሩ ሁለት ጎራዎች መፈጠራቸው እየታየ ነው።

በዚህም ሳቢያ አንደኛው ወገን ሌላኛውን እውቅና ከመንሳት ጀምሮ የእገዳ ውሳኔዎችን እያስተላለፈ ይገኛል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

የኦነግ ቃል አቀባይ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ቀጄላ መርዳሳ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሊቀመንበርነት መታገድ ሕጋዊ መንገድን የተከተለ ነው በማለት ሲያረጋግጡ፤ በተመሳሳይ የኦነግ ቃል አቀባይ ነኝ የሚሉት አቶ መሐመድ ረጋሳ ደግሞ አቶ ዳውድ ኢብሳን ያገዱት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከዚህ ቀደም እራሳቸው ታግደዋል ይላሉ።

አቶ ቀጄላ እንደሚሉት “ሕግ የተላለፉ፤ የሥነ ምግባር ጥሰት የፈጸሙ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊታገዱ ይችላሉ። ይህ የፓርቲው አሰራር ነው” በማለት እርምጃው ሕጋዊ እንደሆነ አመልክተዋል።

አቶ መሐመድ የአቶ ዳውድ ኢብሳ መታገድን በተመለከተ “በመንግሥት ሚዲያዎች መግለጫ መሰጠቱን ሰምተናል። ይህ መግለጫ ከኦነግ የወጣ አይደለም፤ ኦነግ አያውቀውም” በማለት መግለጫውን ያወጡት ሰዎች ከግንባሩ የታገዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ጨምረውም እገዳው አቶ ዳውድ ኢብሳ በተገኙበት ነሐሴ ወር ላይ በተካሄደ ስብሰባ የሕግና የቁጥጥር ኮሚቴ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ አራርሶ በቂላን ጨምሮ 6 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ታግደዋል ብለዋል።

Related stories   “በአጣዬ እና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ኮማንድ ፖስቱ

የሊቀመንበሩን መታገድ በተመለከተ ዕሁድ ዕለት ከድርጅቱ የወጣ ነው የተባለው ረጅም መግለጫ ላይ አቶ ዳውድ ኢብሳን ግንባሩን ጎድቷል በተባሉ በተለያዩ ጥፋቶች የሚከስ ሲሆን ድርጅቱንም ለአራተኛ ጊዜ በመከፋፈል ላይ መሆኑን ገልጿል።

መግለጫው አቶ ዳውድን የድርጅቱን ሀብትና ንብረት እንዲሁም ስልጣንን ያላግባብ በመጠቀም፣ በአባላት ላይ ሐሰተኛ ውንጀላዎችን በማቅረብና ድርጅቱ ያልፈቀዳቸውን ግንኙነቶች በማድረግ ከግንባሩ ሊቀመንበርነታቸው እንዲነሱ እንደተደረገ መግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም የሊቀመንበሩ ጉዳይ ተጣርቶ በቀጣዩ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ውሳኔ አስኪያገኝ ድረስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በወሰነው መሰረት ከኃላፊነታቸው “ታግደው እንደሚቆዩ ለድርጅቱ አባላት፣ ለደጋፊዎቹ፣ ለኦሮሞ ሕዝብና ለሌሎች አካላት እናሳውቃለን” ብሏል።

መግለጫው በማጠቃለያው ላይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጎ አዲስ መሪ እስኪመረጥ ድረስ የድርጅቱ ተወካይና መሪ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ ሆነው እንደሚቆዩ አሳውቋል።

Source – BBC Amharic

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *