የሐሰተኛ ገንዘብ ሥርጭቱ ሊጨምር እንደሚችል፤ ሕጋዊ ገንዘቡም በሕገ ወጥ መልኩ ሊዘዋወር እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በ2012 ዓ.ም ክልሉን ለማዳካም በትኩረት የሚሠሩ አካላት በክልሉ ሃሰተኛ ብር ረጭተው ለፍትህ አካላቱ ተቸማሪ የስራ ጫና ሆኖ ነበር። ከዚ ልምድና መሰረታዊ እውነታዎች በመንሳት በውስጥ ቁጥጥርና የማስተማር ስራ፣ በድንበር ሃሰተኛ ብር እንዳይገባ ከመከለከያና የፌደራል ልዩ ሃይላት ጋር ላፍታም ሳይተኛ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ግልጽ አድርጓል

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሐሰተኛ የብር ኖት ስርጭትን እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ነባሮቹን ባለ10፣ 50 እና 100 የብር ኖቶች መተካታቸውና አዲስ ባለ200 ብር ገንዘብ ትናንት ይፋ አድርጋለች፡፡
የብር ኖቶች ለውጥ መደረጉን ተከትሎም ከኢትዮጵያ ውጪ ያለአግባብ የተከማቸ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ሀገር ይገባል ተብሎ ይገመታል፡፡ የሐሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችልም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ፖሊስ ኮሚሽኑ እንደገለጸው በአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት የሐሰተኛ ገንዘብ ሥርጭት ነበር፡፡ በተለይም በበዓላት ጊዜ በስፋት ይሠራጭ እንደነበር በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ ወንጀል መከላከል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጀማል መኮንን ተናግረዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም ክልሉን ለማዳካም በትኩረት የሚሠሩ አካላት ተሰማርተው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ይህ የወንጀል ድርጊት ማኅበረሰቡን ለችግር መዳረጉንና ለፀጥታ ኃይሉም ተጨማሪ የሥራ ጫና እንደነበር ነው ኮማንደር ጀማል የተናገሩት፡፡ ኮማንደር ጀማል እንዳሉት የብር ኖት ለውጥ መደረጉ ለስርጭት የተዘጋጀ ሐሰተኛ የብር ኖትን ለማክሸፍ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
በዚህ ምክንያት የሐሰተኛ ገንዘብ ሥርጭቱ ሊጨምር እንደሚችል፤ ሕጋዊ ገንዘቡም በሕገ ወጥ መልኩ ሊዘዋወር እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የክልሉ ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊዎች የማኔጅመንት አባላት ዛሬ መስከረም 5/2013 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርገው ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልበትን አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በዚህ መሠረት እስከ ቀበሌ ያሉ የፀጥታ ኃይል አባላት ማኅበረሰቡ በሕገ ወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፍ በማስተማር፣ በማስጠንቀቅና በመቆጣጠር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩም ታውቋል፡፡ ኮማንደር ጀማል እንደተናገሩት በሱዳን በኩል ገንዘብ እንዳይገባም የክልሉ የልዩ ኃይልና የመደበኛ ፖሊስ አባላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ጠረፍ ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡
ሐሰተኛ ገንዘብ ወደ ማኅበረሰቡ ከገባ ሕዝቡ ለኪሳራ ይጋለጣል፡፡ ሐሰተኛ ገንዘብ ይዞ የሚገኝ ግለሰብም በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ነው ኮማንደር ጀማል ያስታወቁት፡፡
ማኅበረሰቡ በእጁ ያለውን ገንዘብ በሕጋዊ የገንዘብ ተቋማት በመጠቀም ሕጋዊ ገንዘቡን ከሚያሳጡ እና የተከለከሉ ነገሮችን ከማድረግ እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡ ሕገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ ሕዝቡ በተለመደው አግባብ ለፀጥታ ኃይሉ ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ሐሰተኛ የብር ኖቶችን እና ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ማስቆም ወንጀልን ከመከላከል ባሻገር በሀገር ላይ የሚደርስን ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ መታደግ ነው” በማለትም በየደረጃው ያሉ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በቆራጥነት ሕግ የማስከበር ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   The Legend of the “Greater Republic of Tigray” and the Delirious TPLF Media

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *