በምዕራብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮችን የማስተካከል እና የቀጠናውን ሰላም የማስጠበቅ ተግባር የሚወጣው የምዕራብ ዕዝ ፣ በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ከተሰጡት ቀጠናዎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አንዱ ነው፡፡
ከሰሞኑም በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ውስጥ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር የማረጋጋት እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራዎች በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በቡለን ወረዳ ኤጳራ ቀበሌ ውስጥ ሞጂ እና ኮሼቦንጂ በሚባሉ መንደሮች የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ በህዝቦች መሃል የእርስ በርስ ግጭቶችን ቀስቅሶ አካባቢውን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ ያለሙ ኃይሎች ነሃሴ 29 እና 30 ምሽት ላይ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
የድርጊቱን መፈፀም ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እንዲሰማራ የክልሉ መንግስት በጠየቀው መሰረት ጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ/ም ወደ ቦታው የተንቀሳቀሰው ሰራዊታችን ፣ በኤጳራ ቀበሌ ውስጥ አሰሳ በማድረግ በአጥፊዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል፡፡
በቡድኑ ታግተው የነበሩ 27 ንፁሃን ዜጎችንም ማስለቀቅ የቻለ ሲሆን ፣ አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሰራዊታችን የስምሪት ቀጣናውን በማስፋት በቡለን ፣ በወንበራ ፤ በጉባ፤ በዲባጢ ፤ በዳንጉር እና በማንዱራ ወረዳዎች የድርጊቱ ፈፃሚዎችን የመቆጣጠር እና አካባቢውን የማረጋጋት ስራ በስፋት በመስራት ላይ ነው፡፡
በየደረጃው ከሚገኙ የክልሉ የመስተዳድር አካላት ፣ የፀጥታ ሃይሎች እና ከህብረተሰቡ ጋር በጥምረት በተሰሩ ስራዎችም አሁን ላይ አካባቢው ወደ ተረጋጋ ሁኔታ በመመለስ ላይ ነው፡፡
ሰራዊታችን መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር አካባቢውን እና ክልሉን ለማተራመስ ባለሙ ሃይሎች የተቀሰቀሰውን ግጭት አስቁሟል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ግን በአንዳንድ ድረ-ገፆች እና ሚዲያዎች ኃላፊነት በጎደላቸው አካላት እየተሰራጩ ያሉት የሰራዊታችንን መልካም ስም የሚያጎድፉ ፣ እውነታን ያላገናዘቡ እና ግጭትን የሚያባብሱ ዘገባዎች ተገቢነት የሌላቸው በመሆናቸው ፣ ይህን የሚያደርጉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን ፡፡ ሰራዊታችን በህዝባችን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ፈፅሞ በቸልተኝነት እንደማይመለከት ማስገንዘብም እንወዳለን ፡፡
በዚሁ ቀጣና የተለያዩ ግጭቶችን በመቀስቀስ የሃገራችንን ሰላም ለማደፍረስ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችንን የግንባታ ሂደት ለማስተጓጎል የሚጥሩ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ የፀረ-ሰላም ሃይሎችን ለመቆጣጠር ዕዛችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡
በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ በተፈፀሙት ጥቃቶች ህይወታቸውን ባጡት የህብረተሰባችን ክፍሎች ፣ የምዕራብ ዕዝ የተሰማውን ልባዊ ሃዘን እየገለፀ ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዞን እና የወረዳ የመስተዳድር አካላትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች እና ህብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላም ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ የምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ያለውን አክብሮት ይገልፃል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የኢትዮጵያ “ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም” ተመስገን ትሩነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *