ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

እነ ጃዋር አስር ተደራራቢ ክሶች ተከፈተባቸው፤ አቃቤ ህግ በሽብር ክስ

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አድናን፣ እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN)፤ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል የፌደራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215 አስር ተደራራቢ ክሶች አስከፍቷል፡፡

ተከሳሾቹም መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አቃቤ ሕግ በእነ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ ላይ ክስ የሚመሰርትበት ቀን አርብ መስከረም 8፤ 2013ዓም ነበር። ሆኖም በዚህ ክስ ይመሰረታል ተብሎ በሚጠበቅበት የመጨረሻው ቀን ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቅረታቸው ይታወሳል።

በዚህም አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ የነ ጃዋር መሐመድ ጠበቃ አቶ ቱሊ ባይሳ ተናግረው ነበር።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ሆኖም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ መሠረት ጃዋርና ሲራጅ መሐመድና ግብረአበሮቹ በ10 ተደራራቢ ክሶች ፋይል እንደከፈተባቸውና የክስ ቻርጁም መስከረም 11፤2013ዓም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደሚደርሳቸው አስታውቋል። ዐቃቤ ሕግ ያወጣው ጽሁፍ ሙሉ ቃል እንዲህ ይነበባል፤

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

  • አቶ ጃዋር መሀመድ፤
  • አቶ በቀለ ገርባ፤
  • አቶ ሀምዛ አድናን

እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን

  • የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN) ደጀኔ ጉተማ፤
  • ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና
  • ፀጋዬ ረጋሳን

ጨምሮ በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ እንደየተሳትፏቸው፦

  • በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ፤
  • የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በመተላለፍ፤
  • የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 በመተላለፍ፤
  • የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል

መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215 አስር ተደራራቢ ክሶችን መክፈቱን ገልጿል።

ተከሳሾቹ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዐቃቤ ህግ በታገደው የእነ ጃዋር መሐመድ ንብረት ላይ የሰጠው ምላሽ መስጠቱ ታውቋል።

Related stories   "የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ላለመላክ የወሰነው የማይታዘዝና የማያጎበድድ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ነው"አንዳርጋቸው ፅጌ

አቶ ጃዋር መሐመድ “ለግል ፍጆታዬ ቤት ያስቀመጥኩት ጥሬ ገንዘብ እና ውድ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ከቤቴ ተወስደውብኛል” በማለት በጠበቆቻቸው በኩል ላቀረቡት አቤቱታ አቃቤ ህግ በሰጠው ምላሽ፤“የፌደራል ፖሊስ ለወንጀል ምርመራው ይጠቅመኛል በማለት በብርበራ ከቤቱ ውስጥ በኢግዚቢትነት የተወሰደ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ የፌደራል አቃቤ ህግ ምላሽ ሊሰጥ አይገባም” ብሏል።

ሁለተኛው የአቃቤ ህግ ምላሽ የተመለከተው በአቶ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ፣ ቦና ትቢሌ በተባሉ ሶስት ተጠርጣሪዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ስም የተመዘገቡ ስድስት መኪኖች ላይ የቀረበ አቤቱታን ነው።

አምስቱ መኪኖች የወንጀል ድርጊት የተገኙ እና ለወንጀል መፈጸሚያ የዋሉ በመሆናቸው የተያዘው ንብረት ይመለስልኝ በሚል የቀረበው አቤቱታ “ውድቅ ሊሆን ይገባል” ሲል አቃቤ ህግ ምላሽ ሰጥቷል።

አቃቤ ህግ ክርክሩን ያቀረበው አቶ ጃዋርን ጨምሮ 15 ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የንብረት እገዳ ይነሳልን አቤቱታ በመቃወም ለፍርድ ቤት ዛሬ አርብ መስከረም 8፤ 2013 በጹሁፍ በሰጠው ምላሽ ነው። ጉዳዩን የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ምላሹን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 19 ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል የአሥራት ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ በተወሰነው መሠረት ጋዜጠኞቹ ተፈትተዋል።

አቶ በላይ ማናዬ፣ ሙሉጌታ አንበርብር እና ምስጋናው ከፈለኝ ዛሬ መስከረም 9/2013 ዓ/ም ከእስር መፈታታቸውን ቴሌቪዥን ጣቢያው አሳውቋል።

Related stories   የፌደራልና የክልል ፖሊስ አዲስ የአደረጃጀት ሰነድ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቀረበ

የአሥራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ዋስትና ከተፈቀደላቸው በኋላ እንደገና ታስረው የተከፈተባቸውን መዝገብ ፍርድ ቤት ውድቅ ይታወሳል።

ጋዜጠኞቹ 2ኛው መዝገብ ውድቅ በመደረጉ ባለፈው ጊዜ በተወሰነው መሰረት አዲስ ዋስትና ማስያዝ ሳያስፈልጋቸው ነበር ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ የወሰነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ