“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጥቂት ፖሊሶች መድበን ነበር ታጣቂዎቹ ሲመጡ ፈረተው በመሸሻቸው እናዝናለን – የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት

ክልሉ ከጥቃቱ በፊት በደረሰው መረጃ በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ ጥቂት የፖሊስ ኃይሎችን የመደበ ቢሆንም ታጣቂዎቹ ሲመጡ ሸሽተው መጥፋታቸው እንዳሳዘናቸው እና ሙያዊ መገለጫ አለመሆኑንም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ሕግ በማስከበር ተጎጂዎችን የመካስ እና የማቋቋም ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡
ተጎጂዎችን ማቋቋምና በወንጀሉ የተሳተፉትን በቁጥጥር ሥር ማዋል የቀጣይ ዐበይት ተግባራት ናቸው– ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ተጎጂዎችን ማቋቋምና በወንጀሉ የተሳተፉትን በቁጥጥር ሥር ማዋል የቀጣይ ዐበይት ተግባራት መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና በቸልተኝነት ጥቃቱ እንዲፈጸም ያደረጉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሳን፣ የኢፌዴሪ መከላከለያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ፣ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ተጎጂዎች አጽናንተዋል፡፡
በጥቃቱ ተጎጂ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ የሚፈልጉ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን አጥተዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ መኖሪያ ቤቶቻቸው ፈርሶባቸዋል። ንብረታቸው መዘረፉንና መውደሙንም ለሥራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ከሕይወት መጥፋት፣ መሰደድ፣ የስነ ልቦና መጎዳት በተጨማሪ ነገን ለመኖር ስጋት ላይ በመሆናቸው መንግሥት አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጥርላቸው፤ ከመንግሥት ለልዩ ልዩ ተግባራት የተበደሩት ብድር አሁን ላይ መመለስ እንደማይችሉና አስቸኳይና ዘላቂ መቋቋሚያ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በሕይወት ያሉና በሞት የተለዩ ቤተሰቦቻቸውን ከየተሰወሩበት ለመሰብሰብ የጸጥታ ኃይሉ አብሯቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
በቡለን ወረዳ የኤጳር ቀበሌ አስተዳዳሪ ጋዋ መኔ “ክፉዎች ከነምግባራቸው ጨለማና ጫካን ነው ማደሪያ የሚያርጉት፤ በዚህ ክፍለ ዘመን ሽፍታ ጥቃት ማድረሱ አሳዛኝ ነው” ብለዋል፡፡
የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት በቀጣናው ለሚታዩ ተመሳሳይ ድርጊቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች የሚካሱት ወንጀሉን የፈጸሙና የተባባሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ነው ብለዋል፡፡
በጥቃቱ የተበታተኑ ቤተሰቦች በአጭር ጊዜ እንዲገናኙ፣ የተጎዱ ወገኖችም ሃይማኖታቸው በሚያዘው ልከ እንዲያርፉ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከዕለት ምግብ አቅርቦት ጀምሮ እስከ ዘላቂ ማቋቋም ድረስ ያሉ እገዛዎች በፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስቻልና ወንጀሉን የፈጸሙና የተባበሩ አካላትንም በቁጥጥር ሥር ማዋል የቀጣይ ዐበይት ተግባራት መሆናቸውንም አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡
በተፈጸመው ወንጀል መንገድ የመራ፣ የጠቆመ፣ ያስፈጸመ፣ የተጠቂዎችን ንብረት ያወደመ፣ የዘረፈውን ሁሉ በዜጎች ጥብቅ ተሳትፎ ለሕግ የማቅረብ ሥራ ይጀመራልም ብለዋል፡፡
ወንጀለኞች ስለሸሹ የሚቀሩ አይደሉም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጠንካራ መርማሪ ቡድን በማቋቋም በሕግ መፋረድ የመንግሥት የቀጣይ የቤት ሥራ እንደሚሆንም ለተጎጂዎች ቃል ገብተዋል፡፡
ጥፋቱ እንዲፈጸም ከላይ እስከ ታች ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሚና ምን እንደነበር በጥልቀት ይመረመራል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ በቸልተኝነትና በእንዝላልነት ጥቃቱ እንዲፈጸም ያደረጉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ፍትሕን ለመታደግ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዐይን የሆነውን የሕዳሴው ግድብ ደኅንነት ለማረጋገጥ እና ለዜጎች ሰላምና ተጠቃሚነት ዘላቂነት እንዲኖረው የአካባቢውን የጸጥታ ኃይል አደረጃጀት ለማሻሻል መከላከያ በቅርበት እንደሚሠራ መገለጹን አብመድ ዘግቧል፡፡

 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?
0Shares
0