የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው

የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚከበሩት የደመራና የመስቀል በዓል እንዲሁም መስከረም 23 እና 24 ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል የሚታደሙ ሰዎች ባጅ ወይንም የይለፍ ካርድ የያዙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበዓላቱ ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባጅ ወይንም የይለፍካርድ ያስፈለገበትን ምክንያት ዘርዝረዋል፡፡ በዚህም ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የጤና ሚኒስትር በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የተወሰደ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ከዚህ ቀደም በበዓሉ አዘጋጆች እና በመንግስት ደረጃ በዓላቱን በድምቀት ለማክበር የተወሰነ መሆኑን አንስተው የጸጥታ አካላቱም በዚህ መሰረት ጥሪ የተደረገላቸው የበዓላቱን ታዳሚዎች ያስተናግዳሉ ብለዋል፡፡ ወደ በዓሉ የሚመጡ አካላት ባጅ ከሌላቸው እንደማይስተናገዱ ገልጸዋል፡፡

በበዓላቱ ላይ ህጋዊ ዕውቅና የሌላቸው አርማዎችን ሰንደቅ አላማዎችን እንዲሁም ብሄርን ከብሄር ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ ጽሑፎችን መያዝ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ ይህንን በሚተላለፉ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የመዲናዋ ጸጥታን ለማደፍረስ የሚሞክሩ ኃይሎች መኖራቸውን ያነሱት ኮሚሽነሩ የእነዚህ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ርችት መከልከሉን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ከተፈቀደለት አካል ውጪ በዋዜማውም ሆነ በበዓሉ ቀን በጋራም ሆነ በተናጠልም በሚደረጉ የደመራ በዓላት ላይ ርችት መተኮስ መከልከሉን ጠቅሰዋል፡፡

በዓላቱ በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ የመዲናዋ ነዋሪዎች ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት በጋራ ሰላም መጠበቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ የሚያጋጥመው ችግር ካለ በነጻ የስልክ መስመር በ991 እና በ011 11 01 11በመደወል ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ሲል ፖሊስን ጠቅሶ ፋና ዘግቧል።

Related stories   የአዲስ አበባ ትልቁ “የጉርሻ” ምግብ መሸጫ ተዘጋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *