“Our true nationality is mankind.”H.G.

የደመራ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጓሜ፣ አንድምታና ታሪካዊ ዳራ በጥቂቱ

ደመረ ማለት አንድ ሆነ፣ ጨመረ፣ ሰበሰበ ማለት ሲሆን ደመራ ደግሞ መብስብ፣ መጨመር፣ መከመር የሚል ትርጓሜ እንዳለው የተናገሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን መምህር መሪጌታ ዮሴፍ ዳኜ ናቸው፡፡ ንግሥት ኢሌኒ ከቆስጠንጥንያ ወደ ኢየሩሳሌም በማቅናት 300 ዓመታት ተቀብሮ የነበረውን የክርስቶስ መስቀል አስቆፍራ እንዲወጣ ያደረገችበትን ሁነት በማሰብ በመስቀል በዓል ደመራ እንደሚደመርም ነግረውናል፡፡ ኪራኮስ የተባሉ አባት ንግሥት ኢሌኒን “‘እንጨት አስከምረሽ አቃጥለሽ ፍሙ ላይ ዕጣን አድርጊበት፤ ከዚያም ጭሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ተራራ ያመላክትሻል’ ብለው በነገሯት መሠረት አሁን ላይ በምሳሌነት እንጨት ተሰብስቦና ተከምሮ እንዲህ ነበር ለማለት ይቃጠላል” ብለዋል፡፡

እንደመሪጌታ ዮሴፍ ዳኜ ማብራሪያ በኢትዮጵያ በዓሉ አከባበሩ ከሌላው የዓለም ክፍል የተለየ የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሐዋርያት ትምህርት ይዛ መቀጠሏ ነው፤ መሠረቱም ስለሆነ በኢየሩሳሌም በተመሳሳይ ሲከበር እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ለረጅም ዓመታት እስራኤላውያን ተበታትነው ቆይተዋል፤ ወደ ነበሩበት መሬታቸው ከተመለሱና እስራኤልን ከመሠረቱ 71 ዓመታቸው ነው፤ ባህልና ታሪኩ ተዘንግቷል፤ በሌላው የዓለም ክፍልም በቅኝ ግዛትም ሃይማኖታዊው ሥርዓት፣ በዓሉና አከባበሩ ሊረሳ የሚችልበት መንገድ እንዳለ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግን ከነዚህ ጫናዎች ውጭ ስለሆነች ከትውልድ ወደ ትውልድ የበዓሉ ሥርዓት ሊሸጋገር እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ ደመራ በሚደመርበት ጊዜ እርጥብ እንጨት መላጥ፣ በአበባና በሌሎች ነገሮች ማስዋብ ይስተዋላል፡፡ መስቀሉ በሚወጣበት ጊዜ ብርሃን ታይቶ ነበር፤ በሰማይ እንደሚታይ ከዋክብት መስቀሉ ብርሃን መስጠቱ በምሳሌነት የሚመላከትበት ነው፡፡

ደመራ በባህላዊ አንድምታው ደግሞ ከአዲስ ዓመት ብስራት ወይም ከዘመን ሽግግር ጋር የተገናኘ እንደሆነ የነገሩን በባሕር ዳር የኒቨርሲቲ የፎክሎር (ባህል ጥናት) ትምህርት ክፍል መምህር ዋልተንጉስ መኮንን (ዶክተር) ናቸው፡፡ ከጨለማ ዘመን ወይም ከአስቸጋሪ ሕይወት ወደ አዲስ ተስፋ የመሻገርን የመለወጥን ባሕሪ ይዞ እንደሚመጣ ገልፀዋል፡፡ እንደ ምሁሩ መረጃ በሃይማኖቱም በባህሉም እሳት መሠረታዊ መስፈረት ሆኖ ብቅ ይላል፤ እሳት በባሕሪው ሦስት ነገሮችን አነባብሮም ይይዛል፤ እሳት ውስጥ ብርሃን፣ አቃጣይነት (አብሳይነት) እና የመሞቅ ባህሪያት ናቸው፤ እሳት ጥሬውን ያበስለዋል፤ ጠጣሩን ያላላዋል፤ የላላውን ያተነዋል፤ በባሕሪው ነገሮችን ይለውጣል፤ የዘመን መለወጥ ከእዚህ እሳቤ ጋር ይያያዛል፡፡

ክፉ ነገሮችን ያጠፋል፤ ሁለተኛ ትርጉሙ ጨለማውን ብርሃን ያደርጋል፤ ይህ ማለት ሚስጥርን ግልፅ ያደርገዋል፤ ስውሩን በገሃድ ያወጣዋል ማለት ነው፤ ዕውቀት ገላጭ፤ ብሩህነትና የተስፋ ምሳሌ ተደርጎ ይታያል፤ ደመራው ከተደመረ በኋላ እሳቱ በሚነድበት ጊዜ አዲስ ዘመንን የሚያበስሩ የእህል ዘሮች ይቀርባሉ፤ በቆሎ በዋነኝነት ተጠቃሽ ነው፤ በአባባል ‘‘የጎመን ምንቸት ውጣ፤ የገንፎ ምንቸት ግባ’’ ይባላል፤ የክረምት ምግቦች ተደርገው የሚወሰዱት ጎመንና ድንች ክፉ ዘመንን አሸጋጋሪ ሆነው ይወሰዳሉ፡፡
‘‘ሰኔን በዘናዘር፤
ሐምሌን በጎመንዘር፤
ነሐሴን በምን ባላ ይሻገሩታላ?’’ ይባላል፡፡
ክረምት በቆየው ልማዳችን የችጋርና የመከራ ወቅት ተደርጎ ይታያል፡፡ እንደአሁኑ ዘመን መንገድ ባልተሠራበት፣ ድልድይ ባልተገነባበትና የሞላ ውኃን ለመሻገር በሚያዳግትበት ጊዜ ሰዎችም ግንኙነታቸው ይቋረጣል፤ ክረምቱ ሲያልፍ ሰው ለሰው የሚጠያየቅበትና የፍቅር አመላካች ነው፡፡

በውክልናም እሳት ይመጣል ያሉት ዶክተር ዋልተንጉስ ናቸው፡፡ እሳትን የአዲስ ተስፋ አመላካች አድርጎ የማየት ልማድ አለ፤ በቆየው የኢትዮጵያ ባህል እሳትን አቀጣጥሎ የመሻገር ልማድም ነበር፤ እሳት ለዋጭ ኃይል ነው፤ ጉልበተኛ (ኃይለኛ) ነው፤ ብርሃን (ሚስጥር ገላጭ) ነው፤ በሰው ፍጥረት ውስጥ የእሳትነት፣ ነፋስ፣ ውኃና መሬት ባህሪያት አሉ ተብሎ በእምነቱ ውስጥ ይጠቆማል፡፡

ለአብነት አዲስ ዓመት ጭስ ይጨሳል፤ የሚበሉ ምግቦች አሉ፤ ገላን መታጠብ አለ፤ ቤት ውስጥ ቁሳቁሶች በጷግሜን ውኃ ይጸዳሉ፤ ማሳም ይረጫል፤ የመታደስ ትርጉም ያለው ነው፤ የደመራው መሠረታዊ ንድፈ ሐሳብ እሳቱ እንደሆነ ዶክተር ዋልተንጉስ አስረድተዋል፡፡

መልካም በዓል! ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ (አብመድ)

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0