የባህር ዳር ከንቲባ የነበሩት መሐሪ ታደሰ (ዶ/ር) ከሥልጣን ርቀው ስለቆዩበት አስገዳጅ ሁኔታ እና የተነሱበትን መንገድ በግልጽ ይፋ አደረጉ ያንብቡት

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ!! የተወደዳችሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች። ከብዙ ወንድምና እህቶቼ ለቀረቡልኝ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት፤ የሚታዩ ብዥታዎችን ለማጥራትና አንዳንድ ከእውነት የራቁ ዘገባዎችን ለማስተካከል የሚከተለውን አቀርባለሁ። ከሁሉ አስቀድሜ በገጠመኝ የቤተሰብ ጉዳይ ከሚገባው በላይ በመዘግየቴ የምወደውን የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ፤ የከተማ አስተዳደሩን ምክር ቤት፤ አብረውኝ የሚሠሩ የከተማ አስተዳደሩን ሠራተኞችና የክልል አመራሮችን ይቅርታ በመጠየቅ እጀምራለሁ።
ቤተሰቤ የሚኖረው አዲስ አበባ ነበር። መጋቢት ወር ላይ የልጆቼ ትምህርት ቤት በኮረና ምክንያት በመዘጋቱ ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ አድርጌ እኔ ባሕር ዳር ከተምኩ። ነገር ግን ከተለያየን ከሦስት ወር በላይ በመሆኑ ቤተሰቤን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ መሄድ እንዳለብኝ በግንቦት ወር ለክልል አመራሮች አሳወቅሁ።

ጉዳዩን በጋራ ተወያይተውበት አንዳንድ ነገሮችን ጨርሼ እንድሄድ ተስማምተናል። እኔም ቶሎ ደርሼ ለመመለስ አስቤ ብጓዝም የልጃችን ፓስፖርት የተሰጠው ቀነ-ገደብ ሊያልቅ በመሆኑና ኢትዮጵያ ስትመለስ አገር ውስጥ መግባት ስለማትችል ማሳደስ ግድ ሆነብን። ከዚህ በፊት የአውሮፕላን ትኬት እያሳየን በአንድ ቀን ያልቅ የነበረው ፓስፖርት በኮረና ምክንያት ለብዙ ሳምንታት እንደሚዘገይ ተነገረን። ከመጋቢት ወር ጀምሮ የተጠራቀመ ወደ አንድ ሚልየን የሚጠጋ የፓስፖርት ጥያቄም እንዳለ ተረዳን።

ሠራተኞችም በኮረና ምክንያት በቤታቸው እንዲቆዩ በመደረጉ ነገሩን የባሰ አጓተተው።ይህ ለእኛ ከባድ መርዶ ነበር። በአፋጣኝ ፓስፖርት የሚታደስበትን መንገድ ስንጠይቅ በሦስት ምክንያቶች ሊሰጡን እንደሚችሉ ተረዳን። የቤተሰብ አባላት (እናት፤ አባት፤ልጅ፣ የትዳር አጋር፣ ወንድም/እህትና አያት) ለሞት የሚያበቃ ጉዳት ከደረሰባቸው ወይም ሞተው ሬሳቸው ካለበት ሆስፒታል ከሐኪም ወይም ባለሙያ የተጻፈ ማስረጃ ካለ ብቻ እንደሆነ ተረዳን። አንዳንድ ሰዎች የውሸት ማስረጃ አስጽፈው አቅርበው ጉዳያቸውን እንደጨረሱም ሰምቻለሁ።

የአሜሪካ መንግስት ይህንን ቢያውቅ የሚያመጣባቸውን ጣጣ መገመት አያስቸግርም። ይህንን ያልኩት በዚህ መንገድ እንድንጨርስ የሚገፋፉን ስለነበሩ ነው። እኛም አመልክተን ስንጨርስ ባለቤቴ ኢትዮጵያ ተመለሰች። እኔም ልጆቼን ይዥየ ለመመለስ ፓስፖርቱን ከመጠበቅ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም።
አሜሪካ ከመጣሁ ጀምሮ የተለያዩ እህትማማች ከተሞች ጋር የተጀመሩ ኅብረቶችን ለማጠናከርና አዳዲስ ኅብረቶችንም ለመፍጠር ደፋ ቀና እያልኩ ከረምኩ። የባሕር ዳር ልጆችንና ወዳጆችን በራሴ ወጪ በአካል ተጉዤና በኢንተርኔት የቪድዩና የስልክ ኮንፈረንስ በማድረግ በከተማችን እድገት ላይ እንዲሳተፉ እያበረታታሁ ያሏቸውን ጥያቄዎች ሳስተናግድ ከረምኩ። በዚህ መካከል የጊዜው መርዘም አሳሰበኝ። ነገር ግን ልጄን ለማን ጥየ እመጣለሁና ተቸገርኩ። ለልጄ ካልሆንኩ ለከተማም አልበጅም። ደግሞ መቼ ፓስፖርቱ እንደሚመጣ መረጃ አይሰጡም። በዚህ መካከል ቶሎ ነገሬን ጨርሼ እንድመለስ ከክልል አመራር መልእክት ደረሰኝ። ይህ ትክክለኛ ጥያቄ ነበር። ያለሁበትን ሁኔታ አስረድቼ እንዲታገሱኝ ጠየቅሁ። እውነቱን ለመናገር ታግሰዋል። በማስከተልም እስከ ነሐሴ ሰላሳ የሥራ ገበታየ ላይ እንድገኝ ካልሆነ ግን ቀጣይ ውሳኔ እንደሚያሳልፉም ተነገረኝ። እኔም ይህንን አቋማቸውን ተቀበልኩ። በሥራ ገበታየ ላይ እንድገኝ የተሰጠኝ ቀን አለፈ። ከመስከረም አምስት ጀምሮ የክልል አስተባባሪ ኮሚቴና የከተማው አመራር ከኃላፊነት እንድነሳ መወሰኑን ከክልሉ የበላይ አመራር ተረዳሁ። እኔም በአክብሮት ውሳኔውን ተቀብያለሁ።
የመሰናበቴ ዜናም ሲሰማ የተለያዩ የዜና አውታሮች ሲዘግቡት የተናገሩት ነገር ግራ አጋባኝ። አንደኛው አሜሪካ የቆየሁበት ጊዜ ከሦስት ወር ከዐስራ አምስት ቀን በላይ ነው ብሎ ተናገረ፡፡ ካናዳ እንደምኖርም ዘገበ። ሁለቱም እውነት አይደሉም። ሌሎች የዜና አውታሮችም እንደወረደ ተቀብለው ከሦስት ወር ከዐስራ አምስት ቀን በላይ ሲሉና ካናዳ መኖራቸው ይታወቃል እያሉ ሲዘግቡ እኔም በግርምት ነው ያዳመጥኩት። እኔ ካናዳ ለጉብኝትና የምርምር ሥራየን ለማቅረብ ሄጄ አውቃለሁ። ካናዳ ኖሬ ግን አላውቅም።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

አሜሪካም የመጣሁትም ከሀጫሉ ሞት በኋላ ነበር። የሚድያ ሰዎች ጉዳዩን ለማጣራት የከተማችንን የኮሙኒኬሽን ገጽ እንኳን አለማመሳከራቸው ገርሞኛል። ምክንያቱም ሰኔ ወር መገባደጃ ላይ አባይ ማዶ አፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ለወገኖቻችን የሚሠራውን ቤት ለማስጀመር የመሠረት ድንጋይ ስናስቀምጥ የተዘገበው ዜናና ሌሎችም ጉዳዮች ተጽፈው አሉና። የተሰናበትኩ ቀን ሁለት ወር ከዐስራ አንድ ቀኔ ነበር። ይህንን ስል ከእረፍት ፈቃዱ ጋር ከሁለት ወር በላይ ከከተማየ መለየቴ ትክክል ነው እያልኩ አይደለም።
ከዚህ ጋር አያይዤ ከውሳኔው በፊት ግፊት ፈጣሪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ማንሳት እፈልጋለሁ። አንደኛው ባሕር ዳር ከተማንና ሕዝቤን ሳገለግል ደመወዝ አለመቀበሌን ሲያውቁ አቫንቲ ሆቴል እየተቀለበ የአገር ብር (ሁለት መቶ ስልሳ ሺህ ብር) አጥፍቷል የሚለው ዜና ነው። ማስረጃ እንዳላቸውም ተናግረው ነበር።

ይህ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ እየተሽከረከረ በመቆየቱ ብዙ ሰዎች እባክህ ግልጽ አድርግልን ብለውኛልና እነሆ። ለሥራ ባሕር ዳር ስመጣ ያመጣኝ አካል (የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤና የክልሉ መንግስት) ያሳረፈኝ አቫንቲ ሆቴል ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት ካለኝ የሥራ ኃላፊነትና ስሾም ከነበረው ስጋት ይመስለኛል። ወዲያውኑ የምኖርበት ቤት እንዲሰጠኝ የከተማ አስተዳደሩን ቤቶች ጠየቅሁ። አንድ ወንድሜም በጣም አገዘኝና የት ማመልከት እንዳለብኝና ማንን ማናገር እንደሚኖርብኝ አስረዳኝ። ደህና ጥበቃ ያለበትም ቤት እንዲሆን ጠየቅሁ። የማመልከቻም ደብዳቤ ጽፌ በስልክ ደጋግሜ ለመንኩ። ነገር ግን ቤት አልተገኘልኝም ነበር። በኋላ ላይ ተራየ ዐስራ አንደኛ እንደሆነና ዐስራ አንድ ሰው እስኪለቅ እንድጠብቅ ተነገረኝ። ነገሩ ስላልጣመኝ ክቡር ፕሬዝደንት ተመስገን ጥሩነህ የቅድሚያ ደብዳቤ እንዲጽፉልኝ ጠይቄ በሚገርም ፍጥነት ደብዳቤውን ጻፉልኝ።

እኔም ክብደት እንዲኖረውና ቶሎ የማርፍበት ቤት እንዲሰጠኝ ደብዳቤውን በአካል አደረስኩ።ለጊዜው ተራየ ሁለተኛ እንደሆነና በጊዜው ቤት እንደሌለ ተነገረኝና ስጠብቅ ገስት ሐውስ አንድ ክፍል እንደተገኘ ሰማሁ። ሙሉ ነገሩ ሳይሟላ ቶሎ ገባሁ። ፍራሽ የለውም። ሽንት ቤቱ አይሠራም። የግድግዳ ሶኬቶችም አይሠሩም (ቆጣሪው ስለሚመልስ)። ፍራሽ እስኪገዛም ስሊፒንግ ባግ አምጥቼ ጣውላ ላይ እያደርኩ አገለገልኩ። ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ (ቀኑን በትክክል አላስታውስም) የኖርኩት ገስት ሐውስ ነው። ዝርዝር ውስጥ የገባሁት እንዲታዘንልኝ ሳይሆን ቅንጡ ኑሮ እንደመራሁ ለሚያስቡትና ለሚያራግቡት ትምህርት እንዲሆናቸው ነው። ሰውም የራሱን ፍርድ ይውሰድ።
ከአቫንቲ ተላከ የተባለውንም ወጪ የከተማ አስተዳደሩ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ወደ ባሕር ዳር ያመጣኝ አካል እንዲከፍል ደጋግሜ ጠይቄአለሁ። ወጪ ነው ተብሎ የቀረበው አንድ መቶ አምሳ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ ሰባት ብር ከዐስራ አንድ ሳንቲም ነው። ዝርዝሩን ስላላየሁት ነው እንጂ ለኮረና ጉዳይ ስብሰባ ያደረግንበት የአዳራሽ ኪራይ፤ የአስተባባሪ ኮሚቴ ምሳ የበላበት ሂሳብና ከአዲስ አበባ ለሙያዊ እገዛ የመጣ ሰው ያደረበትንም ያካትት ይሆናል። ይህ ደግሞ በእኔ የተጀመረ ሳይሆን የክልል አመራሮችም ሲመጡ ለደህንነታቸው ሲባል የተደረገና የሚደረግ ነው። እስከ ዛሬም ሳይከፈል የቆየው ከተማ አስተዳደሩ እንዳይከፍል ብየ ነው። ይህን ብየ አሁንም ያመጣኝ አካል የማይከፍል ከሆነ እኔ ራሴ እከፍላለሁ። ሊታወቅ የሚገባው እውነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ብዙ ሰው የሚሳትፍባቸው ጉዳዮች ሲኖሩና ጎብኚዎች ሲመጡ እነርሱን ለማስተናገድ በአንድ ቀን የሚወጣ ወጪ መሆኑም ይታወቅ። እግሯ የሚውረገረግና ነዳጅ መቁጠር እንኳን የማትችል መኪና እያሽከረከርኩና በጥንቃቄ ከክስና ከወቀሳ ነጻ የሆነ ኑሮ ለመኖር እየተጋሁ እንደ ደላኝ ተደርጎ መቅረቡ ትክክል አልነበረም። የእኔ እርካታየ ሕዝቤን ማገልገሌ ነበር። ከከተማ አስተዳደሩ ለሥራ አዲስ አበባ ስሄድ ከተከፈለው የአየር ትኬት (ምናልባትም ከሰባት እስከ አስር ጊዜ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ) በስተቀር ለመኝታም ሆነ ለምግብ እንዲሁም ለውሎ አበል መቼም የወሰድኩት ገንዘብ የለም። የተጓዝኩባቸውን ቀናትና ምክንያቶች የገንዘብ ማወራረጃ ትኬቶቹ ላይ ስለጻፍኳቸው ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር መምርያ ሄዶ ማጣራት ይቻላል።
ሌላው ከትውልድ ቦታየ ጋር ተሳስሮ ይደረግ የነበረው ዘመቻ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የጎጥ አተካራ በመፍጠር ውዥንብር ተዘርቷል። እኔ ራሴ እስኪገርመኝ ድረስ ስወለድ የነበሩ እስኪመስል ድረስ ለተለያዩ ፍጆታዎች መጠቀሚያ ሆኗል። እኔ የተወለድኩት ደሴ ህጻናት ሆስፒታል ነው። ቤተሰቦች ከሁሉም የአማራ ክፍለ ሐገሮች የተጋመደ ማንነት ቢኖራቸውም መሠረታቸው ግን አምባሰል ነው። እኔም በወሎ፤ አዲስ አበባ፤ ሐረርና ሰሜን ሸዋ ተምሬያለሁ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም ያጠናቀቅሁት ጀግናው ኃይለማርያም ማሞ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፤ ፈረሱን እንደሰው አስታጠቀው ሱሪ የሚለውን ግጥም እያነበብኩና አስማረ ዳኜ ከነመትረየሱ በጎዳናዎቻችን ሲንጎማለል እያየሁ ያደግሁባት ደብረ ብርሃን ከተማ ናት። በዚህ እውነት ውሸቱን ማጥለል ትችላላችሁ። እኔ የማምነው ከሰውነት ባልወረደ ኢትዮጲያዊነትና ከኢትዮጲያዊነት ባልወረደ አማራነት ነው (ይህንን አሳብ ያገኘሁት አቶ ዮሐንስ ቧያለው በአንድ ወቅት ካደረጉት ንግግር ነው)። ባሕር ዳር ስመጣ የማውቃቸው ሰዎች አምስት አይሞሉም ነበር። አሁን ግን ብዙ እናትና አባቶች እንዲሁም እህትና ወንድሞችን አትርፌአለሁ። አመሰግናለሁ።
ዝም ያልኩት ከተማችን በእንደዚህ ዓይነት ድራማ እንድትታመስ ስለማልፈልግ ነው። አላስፈላጊ ፍትጊያም አያንጽም። ምክንያቱም ባሕር ዳር እንድትታወቅ የምፈልገው በእድገትና ልማት እንጅ በእንደዚህ ዓይነት ድራማ ሊሆን አይገባም ነበር። ባሕር ዳር የመጣሁት የአቅሜን ያክል ትንሽ እገዛ ለማድረግ በፍጹም ደስታ፤ ቅንነትና መሰጠት ነው። በቆይታየም ቀን ሳልመርጥ የሳምንቱ ቀን ምን እንደሆነ እንኳን እስኪጠፋኝ ድረስ ቅዳሜና እሁድም ጭምር በትጋት አገልግያለሁ። በፍሬ የተገለጠ ሥራ አሳይቻለሁ። ይህንን ስል ግን ብቻየን ነው የሠራሁት አልልም። እንደ መሪ ግን ያለኝን ሰጥቻለሁ። በዚሁ አጋጣሚ የከተማችንን ነዋሪዎች፤ እናት አባቶቼን፤ እህት ወንድሞቼን፤ የክልል አመራሮችን፤ የባሕር ዳር ከተማ አፈጉባኤና ምክር ቤት አባላትን፤ የአስተባባሪና የከንቲባ ኮሚቴ አባላትን፤ የከተማ አስተዳደሩ የመምርያና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን፤ የክፍለ ከተማ አመራሮችንና መላውን የከተማ አስተዳደሩን ሠራተኞች የከበረ ምስጋናየ ይድረሳችሁ እላለሁ። የተሠራውን ሥራ በተመለከተ አሁን ዝርዝር ውስጥ አልገባም። ወደ ፊት ግን እመለስበታለሁ።
በመጨረሻም አንድ የባሕር ዳር ልጅ በአሜሪካን አገር ተልእኮ ተሰጥቶት ዶክተር አይመለስም ቀርቷል ብለው ሰዎች እንዲዘግቡ በመንገርና ውዥንብር በመፍጠር እንዲሁም ህዝቤን ትቼ ለመቅረት መልቀቂያ እንዳስገባሁ አስመስሎ ለማቅረብ የተቀናጀ ነገር ሲሠራ መቆየቱን ተረድቻለሁ። የተለያዩ ሰዎችም ተመሳሳይ ተልእኮ ተሰጥቷቸው እንደነበርና አሁን እንደተጸጸቱ ነግረውኛል። በተፈጠረው ነገር ያዘናችሁና ለህመምም የተዳረጋችሁ ብዙ መሆናችሁን ከመልእክቶቻችሁ ተረድቻለሁ። ከአቅሜ በላይ በሆነ ጉዳይ ብዘገይም ለደረሰባችሁ ስብራት ዝቅ ብየ ይቅርታ እጠይቃለሁ። አልተመለስኩም እንጅ አልቀረሁም። ለቀጣዩ የባሕር ዳር ከንቲባ መልካም የሥራ ዘመን እያልኩ በምችለው ሁሉ ለማገዝና ለከተማችን የምችለውን ሁሉ የማደርግ መሆኑን አሳውቃለሁ። በመጨረሻም የምለምናችሁ ይህንን መልእክት ፌስቡክ ለማንበብ እድል ለሌላቸው እናቶቼና አባቶቼ እንድታደርሱልኝ ነው። ሼር በማድረግ ተባበሩኝ።ስለሰጣችሁኝ የማገልገል እድል እግዚአብሔር ይስጥልኝ። የልጄም ፓስፖርት መምጫው ስለደረሰ በቅርቡ አገሬ እገባለሁ። ለዛሬ አበቃሁ።
መሐሪ ታደሰ (ዳላስ-ቴክሳስ)
መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም
Mahari Tadesse Dr

 • የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?
  ከቁጥጥር ውጪ የሆነው የቻይና ሮኬት አካል ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል? ። የቻይናው 5 ቢ ሮኬት ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ወደ መሬት ለመምዘግዘግ ምድርን በመሽከርከር ላይ ይገኛል። 5 ቢ ሮኬት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነበት ከሚያዝያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. እንስቶ በከፍተኛ ፍጥነት በመሬት ዙሪያ እየተሸከረከረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ስፔስContinue Reading
 • ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ
  ጠላቶቿ ፈርሰው ያልቃሉ እንጂ ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም፤ አዲስ አበባም ከሰላማዊ የብልፅግና ጉዞዋ አትስተጓጎልም! ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ለበርካታ ጊዜያት ከውጭ ጠላቶች ወረራ እና መሰል ጥቃቶች ተሰንዝሮባታል፤ ሁሉንም የውጪ ወረራ እና ጥቃቶችን በጀግኖች ልጆቿ በመመከት ጠላትን አሳፍራ መመለስ የቻለች ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ከአብራኳ የወጡ ከሃዲዎች እና ባንዳዎች ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ሲያደሟትContinue Reading
 • አቡነ ማቲያስ መነጋገሪያ ሆነዋል – ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻው እንዲከር ጥሪ አቅርበዋል
  ከትሀንግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጃ የተያዘባቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሰፊ መነጋገሪያ ሆነዋል። በአዎንታና በአሉታዊ ጎን የተሰነዘረባቸው ተቃውሞ መነሻው ” ታፈንኩ” በማለት ሲናገሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ወዳጆቻቸው ወይም የቅርብ ታዛዦቻቸው ካሰራጩና ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በኤፒ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በቲውተር ገጻቸው ካሰራጩት በሁዋላ ነው። ቪዲዮውን ተከትሎ ሙስሊም የኢትዮጵያ ልጆች የአፍጢር ስነContinue Reading
 • Warshaan Keenyaa tiraaktaroota 950 qonnaan bultootaaf dabarse
  Magaalaa Shaashamanneetti kan argamu Warshaan Meeshaalee Qonnaa Ammayyaa Keenyaa kaleessa tiraaktaroota 950 qonnaan bultootaaf dabarse. Sirni walharkaa fuudhiinsaas qonnaan bultoota, dargaggoota waldaan gurmaa’aniifi dhaabbata Keenyaa gidduutti taasifameera. Sirnicharratti Pirezdaantiin Mootummaa Naannoo Oromiyaa, Obbo Shimallis Abdiisaa dabalatee hoggantoonni olaanoo federaalaafi naannolee, akkasumas abbootiin gadaa argamaniiru. Tiraaktaroota 950 qonnaan bultootaafi dargaggoota waldaanContinue Reading

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *