“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት መኖሩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት እንዳለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልጿል። ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች መደበኛ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።

በፌዴራል ደረጃ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ የተወሰኑ ቡድኖች በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም በተለያየ መልኩ ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ኢዜአ ይህን ጉዳይ ጨምሮ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ዙሪያ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አፈ-ጉባኤው እንዳሉት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ-መንግሥታዊ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ምርጫውን አራዝሟል።

ሆኖም ለሕገ-መንግሥቱ ተገዥ ያልሆኑና ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች ሕዝቡን የማወናበድ ሥራ እየሠሩ መሆኑንም አመላክተዋል።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የትግራይ ክልል መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ”በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ክልሉ ሕገ-መንግሥቱን አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል።

Related stories   ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች

“ምርጫ ማስፈጸም የምርጫ ቦርድ ሥራ ሆኖ ሳለ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መልኩ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም፤ አግላይ በሆነ መንገድ ምርጫ አካሂዷል ነው” ያሉት።

“አካሄዱ በግልጽ የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስና ክልሉም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለ ይቆጠራል” ብለዋል።

ክልሉ ይህን ድርጊት ፈጽሞ በመገኘቱ ሕገ-መንግሥታዊ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል በቂ የሕገ-መንግሥት መሠረት እንዳለም አመልክተዋል።

ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ሕግ አውጪውንና ሕግ አስፈጻሚውን ማገድ የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ አካሄድ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቀጥሎ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግሥት ማቋቋምና የፌዴራል የፀጥታ አካላት በማሰማራት ሕገ-መንግሥቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት መቆጣጠር ሌላው መሆኑን ይገልጻሉ።

አፈ-ጉባኤው አያይዘውም ከዚህ በኋላ ሕዝቡም ሆነ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ለሚነዙ ቡድኖች ጆሯቸውን ሳይሰጡ መደበኛ ሥራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል።

እነዚህ ቡድኖች ለጥፋት መንገዳቸው ያመቻቸው ዘንድ በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉም ይገልጻሉ።

በመሆኑም በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶች እንደተለመደው አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠርና የመከታተል ሥራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

”ይህ ቡድን አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታውን አሐዳዊ የማስመሰል እንቅስቃሴ ይስተዋልበታል” የሚሉት አፈ ጉባኤው ”እንደውም አሐዳዊነት ከለውጡ በፊት ነበር” ብለዋል።

ከለውጡ በፊት በየአካባቢው ሕገ-መንግሥቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ሰፋፊ ክፍተቶች ይታዩ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በየክልሉ የሞግዚት አስተዳደሮች ተመድበው ይሠሩ እንደነበር ያስታውሱት አፈ ጉባኤ አደም ”ከለውጡ ወዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጦች እየታዩ ነው” ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የተዛቡ ትርክቶችን መነሻ ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝቦችን እያጋጩ መሆኑንም አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

እነዚህም ማንነትን፣ ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው በሕዝቦች ወንድማማችነት ላይ የራሳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኙም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶችም ነገሮችን ከየአካባቢያቸው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ሰፋ አድርገው ማየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አፈ ጉባኤው ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

አብመድ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0