በቦሌ ክፍለ ከተማ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የሀሰተኛ ብር ኖት ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን ለአቤቱታ ፖሊስ ጋር መጥተው በነበሩ ግለሰብ ጥቆማ ሰጪነት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማረጋጋት የተጀመረውን አሮጌ የገንዘብ ኖቶችን ቅያሪ ተከትሎ የሚከሰቱ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ፖሊስ ጥብቅ የወንጀል መከላከል ተግባሩን እያከናወነ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ያሬድ ታረቀኝ እንደተናገሩት ሁለት ተጠርጣሪዎች ከሀሰተኛ የብር ኖት በተጨማሪ የአሜሪካ ዶላር እና የተለያዩ አገራትን ገንዘቦችን በመኖሪያ ቤታቸው ሲያዘጋጁ ከሚጠቀሙበት የተለያዩ ቁሳቁሶች ጋር እጅ ከፍንጅ በመያዝ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የኮትዲቫር ተወላጆች ሲሆኑ ወደ ኢትዩጵያ የመጡት ለጉብኝት በሚል ሰበብ የገቡና በጉሙሩክ በኩል ምንም ዓይነት ያስመዘገቡት ንብረት እንደሌላቸው በመግለጽ ዋነኛ አላማቸው የሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለማባዛትና ለማሰራጨት እንደሆነ አስበው ወደሀገር ቤት መግባታቸውን የምርመራ መዝገባቸውን ዋቢ አድርገው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው ባስተላለፉት መልዕክት ወቅትን ጠብቀው የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላል ፖሊስ የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ በኩል የህብረተሰቡ ተባባሪነት የሚደነቅ መሆኑን አብራርተው ህብረተሰቡ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምንጭ – ፋና
Related stories   አባ ቶርቤ - የኦነግ ሸኔ'የከተማ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ" ክንፍ በነቀምቴ ግድያ ፈጸመ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *