አሁን ጊዜው ዜሮ ሰዓት ላይ ነው። ሳምሶን አዳነ እንደሚለው የግንኙነት መስመር ተበጥሷል። የዕርቅም ሆነ የድርድር በሮች የተዘጉ ይመስላሉ። ይህ ግምት ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች በገሃድ ሕዝብ እየሰማ ያረጋገጡት ሃቅ ነው። እናም የዜሮ ሰዓት ውጥረት የሚቸከለው በስለላና ስለላውን መሰረት አድርጎ በሚፈጸም ኦፕሬሽን ብቻ ይሆናል። ኦፕሬሽኑ ውስጥ በርካታ እጆች ይሳተፉበታል።

ቀጣዩ የስለላ ግብግብ አንደኛውን ወገን አሸናፊ እንደሚያደርገው የህግ ባለምያው ሳምሶን ያምናል። ስለ ስለላ አቅምና ብቃት ያነሳው ሳምሶን ከለውጡ በፊትም ሆነ በሁዋላ ሰፊ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ይናገራል። በዚሁ መነሻው ምልከታውን የሚጀምረው ትህነግ የገነባውን የደጅንነት መዋቅር በማስቀደም ነው።

ለውጡ እውን በሆነ ማግስት ጀምሮ ለተወሰኑ ወራቶች አሜሪካ መቀሌ የከተመውን ሃይል ለማግባባት ሞክራ ነበር። ከፍተኛ ባለስልጣኗን ሳይቀር መቀሌ ልካ እርቅ፣ ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ አቅርባለች። ይህ ሁሉ ቢደረግም ትህነግ በውል ባልታወቀ ምክንያት ሙከራውን አልተቀበለም ቢባልም ዋናው ምክንያት ግን የቀደሞ የአገር መረጃና ደንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይ ነው።

በጌታቸው አሰፋ የታገቱት የትህነግ አዛውንቶች

ይህ በተላያዩ ጊዜያትም የተለያዩ ማብራሪያዎች የቀረቡበት ነው። ዳሩ ግን ሚዲያዎቹ ዋናውን ጉዳይ እንዳላገኙት ሳምሶን የሚያስረዳው ትህነግ ወደ መቀሌ የሸሸው በጌታቸው የሂሳብ ስሌት መሆኑንን በማስቀደም ነው። ጌታቸው አሰፋ ወደ መቀሌ ሲያመራ በሙሉ ዝግጅት እንደሆነም ሳምሶን ልብ ሊባል እንደሚገባ ያሳስባል።

ቀደም ሲል ወደ መቀሌ የሄዱት የትህነግ አዛውንት አመራሮች እንደዚህ አይነት ውጥንቅጥ ውስጥ ለመግባት ፈጽሞ እንዳላሰቡ በጎንዮሽ ትግራይ በነበረበት ወቅት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት ተረድቷል። ለዚህም ማረጋገጫው ዶክተር ደብረጽዮን አስቀድሞ ያራምደው የነበረው አቋም ማረጋገጫ ሲሆን የሚቴክ ሃላፊ ጀነራል ዳኘውን አሳልፎ መስጠቱ ደግሞ ዋና ምልክት ነበር። ከዛ በሁዋላ ነው ጌታቸው ስብሰባ ጠርቶ ነበሩን ሁሉ በማስተንቀቂያ የገለበጠው።

ጌታቸው በጠራው ስብሰባ ላይ ከማዕከል ጋር ግንኙነት በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድና ምህረት እንደሌለ በይፋ ተናገረ። ውስን ቁልፍ የትህነግ ሰዎች ብቻ በተገኙበት የምህላ ስብሰባ መከዳዳት ከተጀመረ ጨዋታው እዛው እርስ በርስ እንደሚያልቅ አወጀላቸው። በሌላ ቋንቋ መታገታቸውን አበሰራቸው።

በጉዳዩ ላይ ሰፊ መረጃ መሰብሰቡን የሚናገረው ሳምሶን እንደሚለው ዛሬ ላይ በመቀሌ የመሸገው ሃይል ከማንም በላይ የሚፈሩት የቀድሞ የደህንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋን ነው። ጌታቸው አሰፋን የሚፈሩት ደግሞ ወደው ሳይሆን ባለው አቅም ነው። መለስ ዜናዊ ሞት ቀደማቸው እንጂ ጌታቸው አሰፋን ለማንሳትና እየገነባ ያለውን ጡንቻ ለሟሟት እቅድ እንደነበራቸው ከሻብያ ሰላዮች ሙሉ መረጃ መውጣቱን የሚገልጸው ሳምሶን፣ ጌታቸው ሁሉንም የትህነግ አቅም ጠቅልሎ እጁ የከተተው መለስ ከሞቱ በሁዋላ እንደሆን እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል።

አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገራት በይፋ ጌታቸው አሰፋ እጃቸውን ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። መንግስትም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አውጥቶበት ተላልፎ እንዲሰተው ቢጠይቅም ትህነግ “ አላደረገውም” የሚል አቋም የመያዙ ሚስጢር ይህና ይህ ብቻ ነው። የጌታቸው አቅም!!

ማንኛውም ዓይነት የሰላም ንግግር እሱን ወደ ህግ ፊት ስለሚገፋው ጌታቸው ቀደም ሲል በዘረጋው መስመር አማካይነት ልዩ ሃይሉንና ደህንነቱን ስለሚመራ ሌሎች እንዳይለሳለሱ ጋሬጣ ሆኖባቸዋል። የትህነግ እጅ መስጠት ወይም ከብልጽግና ጋር ተስማምቶ መቀጠል ለጌታቸው አሰፋ ተረኛ የሚጠብቅ ሸምቀቆ በመሆኑ ያልተቆረጠውን እጁን ራሱን ለመጠበቅ ሲል ይጠቀማል። እናም በዚህ ሳቢያ ሁሉም ታጋቾች ሆነዋል።

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

ያልተቆረጠው የጌታቸው አሰፋ እጅ

አቶ ጌታቸው በመላው አገሪቱ ያልተበጠሰ ሰንሰለት እንዳለው እምነቱን በመግለጽ ማብራሪያውን የሚቀጥለው ሳምሶን፣ በአንድ ስብሰባ ላይ “ ከተከዳዳን መጀመሪያ ሁሉም ነገር የሚካሄደው በመካከላችን ነው” ሲል ጌታቸው ማስጠንቀቂያ ማስጠቱን ከቅርብ ሰው መስማቱን የሚናገረው በምክንያት ነው።

በዚህም ሳቢያ ጌታቸው የፌደራል መንግስትን እንቅስቃሴ ከሚከታተለው በላይ በመቀሌ ያሉትን ውስን ባለስልጣናት የቅርብ ሰላይ መድቦ እግር በእግር ይሰልላቸዋል።

በመሆኑም የትህነግ አንጋፋ አመራሮች ከመቀሌ ወዴትም መሄድ ያለመቻላቸው፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መልኩን በቀያየረ ስልት የሞከሩዋቸው መንግስትን የማልፈስፈስ ሙከራ ውጤታማ እንደሚሆን ቅድመ ትንተና ሰርተው ስለነበር ያንን በማመን ጭልጥ ብለው ሊታረቅ ወደማይችል ፖለቲካ አመሩ። በዚህም አቋማቸው እለት እለት እየከረረ ለመጣው ልዩነት ማርገቢያ ሃሳብ ማቅረብ እማይችሉበት ደረጃ ደረሱ።

ያልተቆረጠው የጊታቸው እጅ ድፍን ኢትዮጵያ ላይ ያለው የስለላ መዋቅሩ ነው። ጊታቸው የዚህን የስላላ መዋቅር ዘርዝርና የግንኙነት ኮድ ወደ መቀሌ ይዞት በመሄዱ አሁን በአመራር ላይ ያለው ሃይል ከሚታወቁት በቀር ጌታቸው የዘረጋውን የስላላ መዋቅርና ቁልፍ ሰላዮች አያውቃቸውም።

ጉዳዩ ግራ የሚጋባ ቢሆንም ሳምሶን እንደሚያስረዳው ጌታቸውና የእሱ ውስን ቁልፍ ሰዎች በኮድ ቁጥር የሚያውቋቸው ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ወይም ተቋማት ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም የሚላክላቸው ቁልፍ የስላላው አውታሮች አሉት።

እነዚህ ሰላዮች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚሰሩ፣ እምነት ተቋማት ውስጥ ያሉ፣ በጡረታ የተገለሉ፣ የሚፈለጉ ባለስልጣናት ሚስቶች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ቁልፍ የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ፣ ከፓርቲ መዋቅር ጀርባ የተመለመሉ፣ ባለሃብቶች፣ ደህንነቱ ሃብታም ያደረጋቸው፣ ተማሪዎች፣ ፣ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ቀበሌ አስተዳደር፣ ገበሬ ማህበራት፣ የታዋቂ ሰዎች ሚስቶችሲሆኑ ከሚታወቁበት ስራ ውጪ የደህንነት ሰራተኞች ስለመሆናቸው ከራሳቸው በቀር የሚያውቅ የለም። መረጃ የሚያቀብሉትም በራሳቸው ኔት ዎርክ ብቻ ነው።

ይህ ትሥሥር ዛሬ ድረስ ያልተበጣጠሰ መሆኑንን ሳምሶን በርግጠኛነት ይናገራል። ይህ መዋቅር አገሪቱን እንደሚያምስ ግልጽ ነው። በዚህ መዋቅሩ አማካይነት ጌታቸው መከላከያና ልዩ ሃይሎችን የሚቆጣተር ሲሆን ለውጡ ሲመጣ የመከላከያና የፖሊስ ሃይሉ ኮድ ሙሉ በሙሉ በመቀየሩና በውጭ አገር ባለሙያዎች የታገዘ ሪፎርም በመደረጉ ጌታቸው አሰፋ በመከላከያና በክልል ልዩ ሃይል ዘንድ ያለው ሃይል ቢሟሟም ርዝራዡ አለ ነገር ግን የሚያስፈራ አይደለም።

የስለላው መዋቅርና የትግራይ ልዩ ሃይል በፍጹም እሱ እጅ ያሚገኝ እንደሆነ ሳምሶን ማረጋገጡ ይናገራል። ከለውጡ በፊትና በሁዋላ መቀሌ ለመሄድ እድል ያገኘው ሳምሶን እንደሚለው፣ ይህ የስላላ መዋቅር አቅም ሲዳከም የሚሰል በመሆኑ መንግስት የጌታቸውን አቅም ለማስለል የጀመረው የገንዘብ ለውጥና ስለላውን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ በትህነግ በኩል ይህ ከመሆኑ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አስተዳደር አጣድፎ ለማስወገድ ሃሳብ አለ።

Related stories   የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው - ሎረንስ ፍሪማን

የትግራይ ሕዝብ – ፕሮፓጋንዳ

በለውጡ ማግስት የትህነግ አመራሮች ወደ መቀሌ ከገቡ በሁዋላ ከሕዝብ ጋር ውይይት ሲጀመሩ ህዝብ “ የት ታውቁናላቹህ” ነበር ያለው። ዛሬ እድሜያቸው 30 ዓመት የሞላቸው ልጆች አያውቋችሁም በሚል የከረረ ተቃውሞ መሰንዘሩን ላስታወሰ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ትቂት ወራቶችን ትግራይ ላይ የመስራት እድል ቢሰጠው ዛሬ ትህነግ በተረሳ ነበር በሚል ትግራይ ያነጋገራቸው ወገኖች እንደነገሩት ያስታውሳል።

ይህ እንደሚሆን እሙን ስለነበር እነ ጌታቸው አሰፋ የሚፈልጉትን ይዘው ወደ ትግራይ እስኪኮበልሉ ድረስ እነ ዶክተር አብይ ባይደጋገምም የትግራይ መቀሌ ላይ ሕዝብ ሰብስበው የማነጋገር እድል ነበራቸው። መንግስት ለውጡን በይቅርታ መንፈስ እየመራ እነ ጌታቸውን መላ ሊላቸው አድፍጦ በነበረበት ወቅት ጌታቸው ዘዴ ዘየደ።

በየክልሉ ያለውን የስለላ ሃይል በአዲስ ለማዋቀር በሚል በለውጡ ማግስት ሶማሊ ክልል ልዑክ ይዞ ሄደ። እዛ በተለይ ምን ሰርቶ እንደመጣ ባይታወቅም ውጤቱ ግን በሶማሌ የሆነው ነበር። ከዛም ሁለት ክልሎች በተመሳሳይ ከሄደ በሁዋላ ውቀደ አማራ ክልል ለተመሳሳይ እንደሚሄድ አስታውቆ አማራ ክልል ሲጠበቅ መቀሌ ተገኘ።

ሳምሶን እርግጠኛ ባይሆንም ጌታቸው አሰፋ አማራ ክልል ቢገባ ኖሮ ጨዋታውን እዛው ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር። ምክንያቱም እሱን አዲስ አበባ ላይ አስሮ ማቆየት ካለው ኔትዎርክ አንሳር፣ ለውጡም ገና ዳዴ እያለ ስለነበር ቀውስ ሊያስነሳ ስለሚችል “ አማራ ክልል አሰረው” በሚል በድርድር ስም ጊዜ ሊፈጅና እጁ ላይ ያለውን መዋቅር በሙሉ ለመረከብ ታቅዶ ነበር።

ምንም እንኳን የመቀሌ ሕዝብ የት ታውቁናላችሁ፣ ዛሬ ነው ትዝ የምንላቹህ ቢልም ከመሃል መንግስት በኩል በነበረው ያለመጥራትና ያለመረጋጋት ሳቢያ ትህነግ አፈር ልሶ እንዲነሳ የሚያስችል እድል አገኘ። “ተከበናል” በሚል ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ አሸበሩት። ልክ እንደ አሜባ ክፉውን ጊዜ መቀሌ ሆነው ሴራ በማምረትና ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ስራ በመስራት “ አታውቁንም” ያላቸውን ሕዝብ በፍረሃት ቆፈን እንደ አሜባ የክፉ ቀን ማለፊያ አደረጉት። ከዛም አልፎ መሳሪያ ይዞ እንዲፎክር አስቻሉት።

ለአደን ያደፈጠው ድመት – ሻዕቢያ

ዛሬ ከየአቅጣጫው እንደሚሰማው ሳይሆን ሻዕቢያ ልክ አደን ላይ እንዳለች ድመት ይመሰላል። ሳምሶን እንደሚለው ሻዕቢያ አሁን ቢተነፍስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ዝምታን መርጧል። ይሁን እንጂ አይተኛም።

ትግራዋይ በሚል ታቤላ የኤርትራን ደጋማ አካባቢዎች ነጥሎ ለማሳመጽና ኤርትራን ለመበታተን የሚወጠነውን ውጥን ከማክሸፍ፣ በውል ከመከታተል በዘለለ የትህነግን ስለላ ይበረብራል። ዘወትር የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት በሻዕቢያ ይመራል በሚል ትህነግ ተቃውሞ የሚሰነዝረው ከዚሁ ፍርሃቻ አንጻር እንደሆነ ሳምሶን ይናገራል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስትና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግስት በሱዳን በኩል በጥምረት በር መቆለፋቸው፣ ሱዳን ሙሉ በሙሉ ተባባሪ መሆኗ፣ አንድ ላይ ተዳምሮ የትህነግን ሃይ እንደሚያዝለው ቢታመንም፣ መንግስት በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ሰላምን ካላረጋገጠና ያልተቆረጠውን የጌታቸው አሰፋን የስለላ መዋቅር ሙሉ በሙሉ መድፈቅ ካልቻለ መንገታገት ሊመጣ እንደሚችል ሳምሶን ያምናል። አያይዞም አሁን ግጥሚያው በስለላ በመሆኑ፣ የሻዕቢያ የስለላ አቅምና የትህንግ የስለላ ኔትዎርክም የሚፈተሽበት ወቅት ነው። ምክንያቱም “ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ ኤርትራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ታደርጋለች” በማለት ኢሳያስ አፉወርቂ በግልጽ ተናግረዋልና። ከዚህም በተጨማሪ ሃላኖቹ ትህነግን ዝም ብለዋል። አሁን ችግሩ ህዝብ በጥልቀት መረዳት አለመቻሉና የማይረዳውን ጉዳይ መፈትፈቱ ነው።

Related stories   የ80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ

የሕግ ባለሙያው ሳምሶን “ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ከፌደራል መንግስት ጋር የገባበት እሰጥ አገባ ወደ ዜሮ ሰዓት የፍጻሜ አውድ ሲያመራ ምዕራባዊያኑና አሜሪካ ለምን ዝም አሉ? የሚለው ጉዳይ በሃያላኑ ዘንድ አንድ ፍላጎት እንዳለ አመላካች ነው” ይላሉ። ይህም ፍላጎት ትህነግን ጠፍቶ ወይም ከስሞ ማየት ሲሆን፣ ፍላጎቱ ደግሞ በኦፕሬሽኑ ዙሪያ ያሉት በርካታ እጆች ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው።

አቶ ሳምሶን ያልናቸው ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ሲሆን ስማቸውን ለዚህ ጽሁፍ የተጠቀምንበት እንጂ ዋና ስማቸው አይደለም።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *