“Our true nationality is mankind.”H.G.

36.4 ቢሊዮን ብር ገደል!! – ከቀረጥ ነጻ ለበረባሶ

” ዛሬ ” አሉ በጋምቤላ ቀደም ሲል መሬታቸውን ካጡ ቤተሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ኡጁሉ ” ዛሬ ጠቅላላ በሚባል ደረጃ ለእርሻ የተከለሉ ሰፋፊ መሬቶች ዳዋ በልቷቸዋል” ኡጁሉ ይቀጥላል። በምጸት እየሳቀ ” የአካባቢው ህዝብ በአቅራቢያው ያለውን ቢሮና መጋዘን ቆርቆሮ ነቅሎ ወሰደ። ትራክተሮቹ ጎማቸውን ስራ ላይ አውሏል” 

ጋምቤላ የግፍ ክምር፤ጋምቤላ ንጹሃን በጅምላ የተረሸኑበት የምስኪኖች ነፍስ የሚጮህባት ምድር። በስላም የተፈጥሮ ስጦታን እያጣጣሙ የሚኖሩ ደጎች ለዘመናት በሰላም ይኖሩባት የነበረች ገነት። ላለፉ ሃያ ሰባት ዓመታት ግን በተፈጥሮ ሀብቷ ምክንያት ሰላሟን ያታች ለነዋሪዎቿ ገሃነብ፣ ለባለጊዘዎች ሲሳይ፣ ለአገር ኪሳራን ያሳቀፉ ጉዶች የተርመሰመሱባት ድንግል አገር።

ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ ባለጊዜዎች እንደ መዥገር ተጣብተዋት፣ በውስጧ ከዛው ምስኪን የተፈጠሩ የግፍ አስፈጻሚ ተላላኪዎች የባለጊዜ አገልጋይ ሆነው ግፍን እንደ ኩይሳ የቆለሉባት ጋምቤላ ፍትህ የሚበየንላት መቼ ይሆን? ሲሉ የሚጠየቁ ቢጮሁም መልስ የለም። ይሁን እንጂ ዝርፊያው ላይመለስ ገመዱ ተበጥሷል።

“የዘራሁትን ሳላነሳ በዶዘር ማሳዬን ጠረጉት፣ በዶዘር እርሻዬ ውስጥ ገብተው አረሱት፣ መሬቴን ለምን ትወስዳላችሁ? እኔንስ የት ልትወስዱኝ ነው? ስል ጠየኩ አልሰሙኝም። በጉልበት ያሸተውን በቆሎዬን አይኔ እያየ መነጠሩት። ጨፈጨፉት። ምን ላደርግ እችላለሁ። መሳሪያ የያዙ ወታደሮች ከበውኛል። እያነባሁ አደርኩ። ጠዋት ስነሳ ማሳዬ ባዶ ሆኖ አገኘሁት … ያሸተውን ማሳዬ የለም… ” ይህ የበደል ሰቆቃ  በምስል ተደግፎ የቀረበ ህሊናን የሚቦረቡር ሃቅ ነው። ለባለጊዜዎች ግን ይህ መዝናኛ ነበር። ጎልጉል ከዘገበው

በጋምቤላ ሰፊ የኢንቨስትመንት ስራ እየተሰራ መሆኑንን የባለጊዜዎች ሚዲያ ሲደሰኩር ገና በጊዜ የውጭ ሚዲያዎች ” በሲጃራ መግዣ ሳንቲም የመሬት ባለቤት መሆን የሚፈልግ ወደ ኢትዮጵያ ያምራ” ሲሉ የውጭ አገር ታዋቂ ሚዲያዎች መገረማቸውን ሲገልጹ፣ አቶ መለስ ” ለኢንቨስትመንት ያልተሸጠው መሬት ነው የሚያሳስበን” በሚል በገሃድ በተጎጂዎች ቁስል ላይ እንጨት ይቀረቅሩ ነበር።

ጊዜ ራሱ ፈራጅ ሆኖ ለውጡ ሲያስገመግም ራሱ መንግስት ባወጣው መረጃ በጋምቤላ ዝርፊያ እንጂ ኢንቨስትመንት እንዳልተካሄደ ይፋ ሆነ።በሚገርም ዳታ ታግዞ ይፋ የሆነውና በሚኒስትር አለማየሁ ተገኑ መሪነት የተደረገው ጥናት እነማን በኢንቨስትመንት ስም ጋምቤላን ወረው የመንግስትን ካዝና እንዳራቆቱ አወጀ። አዋጁ በአሃዝ፣ በስምና በመረጃ የተደገፈ እነማን በመንግስት ካዝና ላይ ሲፈነጩ እንደነበር ያሳየ ስለነበር “ጉድ” ተባለ።

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

” የፍትህ ያለህ” ሲሉ የጮሁትን ዜጎችና ሚዲያዎች እየተከተለ ሲያስተባብል የነበረው የትህነግ የዕርም ሽንት ውላጅ የነበሩ ሚዲያዎች ቀን ደርሶ በደቦ ባለጌዜዎች በብሄር ብሄረሰቦች የፍቅር እሹሩሩ ዜማ ታጀበው የፈጸሙትንና እየፈጸሙ ያለውን ዘርፊያ ጊዜ አስገድዶ አየር ላይ ካወጡት በሁዋላ ሁሉም በየፊናው ሩጫን ያዘ። አብዛኞች ወደ ክልላቸው ገብተው መሸጉ። ሌሎች ሸሹ። ሌሎች አይነ ደረቅ ሆነው ” ብድር ተከለከልን” እያሉ ለተጨማሪ ብድር ማልቀስ ያዙ። ” በብሄራችን ሳቢያ መገለል ተደረገብን” ሲሉ የቁራ ጩኸት አሰሙ። ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑና ያንብቡ። ከ424 ዜጎች ጭፍጨፋ፤ ከ14 ዓመት መሬት ነጠቃ በኋላ የጋምቤላ “ኢንቨስትመንት” 9ቢሊዮን ብር ያህል ከስሯል ጋምቤላን በረሃ አድርጎ፤ ሕዝቧን ገድሎ፤ በተለይ የአንድ ክልል “ዜጎችን” ብቻ ጠቅሞ በጋምቤላ የተተገበረው “ኢንቨስትመንት” ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ያህል የማይከፈል ዕዳ ውስጥ መዘፈቁን ህወሓት/ኢህአዴግ አመነ

ጉዱ ሲገለጥ የተሰማው ዜና በጋምቤላ የአኙዋክ ተወላጆች ተጨፍጭፈውና ከመሬታቸው ተፈናቅለው “ለሰፋፊ እርሻ” በሚል ሲቸበቸብ ከነበረው መሬት “ወደ ሥራ የገባው” 15በመቶው ብቻ መሆኑን ህወሃት/ኢህአዴግ ማመኑንን ነበር፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊ የነበረው ኢሳያስ ባህረ ከሥልጣኑ የተነሳው “ብድር በመስጠቱ ሂደት ለተወሰኑ የባለሃብቶች ቡድን በማድላቱ ነው” ቢገለጽም፣በጋምቤላ በደል ደረሰብን በማለት አቤቱታ ያሰሙ የትግራይ “ባለሃብቶች” ለሃይለማርያም የቀረበው ሪፖርት “የተዛባ ነው” መሆኑንን ጠቅሰው ለአገርና ለውጭ ሚዲያዎች እሮሮ አሰምተው ነበር። በጋምቤላ የከሸፈው “ኢንቨስትመንት” እዚህ ላይ ይንብቡ 

ከላይ ያሉት መጠነኛ ማሳያዎች ሲሆኑ ዛጎል ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በጋምቤላ ” ባለሃብት ነን” በሚል ያላ ባንክ ማስያዣ ከፍተኛ ብድር ካግበሰበሱት በሺህ የሚቆጠሩ ባለጊዜ ነጋዴዎች መካከል ዛሬ የለውጡ አካሄድ ያላመቻቸው ክልሉን ጥለው ወጥተዋል። እንደ መረጃው ዛሬ በስራ ላይ ያሉት ሃምሳ ሁለት አልሚዎች ብቻ ናቸው። የተቀሩት በሺህ የሚቆጠሩት መዝባሪዎች መንግስትን እዳ አስታቅፈው ላይመለሱ እብስ ብለዋል።

Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች

በጨበጣ በተሰጠ ብድር መንግስት 36.4 ቢሊዮን ብር ሜዳ ላይ የበተነ ሲሆን ይህም በብድር ስም ከህዝብ ሃብት ላይ እየወጣ በአድልዎ የተረጨው ገንዘብ እ.አ.አ አቆጣጠር ከ2010 – 2018 ባለው ጊዜ ነው።

” ዛሬ ” አሉ በጋምቤላ ቀደም ሲል መሬታቸውን ካጡ ቤተሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ኡጁሉ ” ዛሬ ጠቅላላ በሚባል ደረጃ ለእርሻ የተከለሉ ሰፋፊ መሬቶች ዳዋ በልቷቸዋል” ኡጁሉ ይቀጥላል። በምጸት እየሳቀ ” የአካባቢው ህዝብ በአቅራቢያው ያለውን ቢሮና መጋዘን ቆርቆሮ ነቅሎ ወሰደ። ትራክተሮቹ ጎማቸውን ስራ ላይ አውሏል”

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ቤት ከቀረጥ ነጻ የገቡ ተሽከርካሪዎች ዳዋ በመታው ማሳ ውስጥ የሉም። ይህንን ያንብቡ ” “የጥልቅ ተሃድሶ” መንፈስ የተጠናወተው የተባለለት ሪፖርት ሌላም ጉዳይ “አጋልጧል”፡፡ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ለእርሻ ልማት ብቻ እንዲገቡ ከተደረጉት “565 ትራክተሮች ውስጥ መስክ ላይ የተገኘው 312፣ ከ731 ማረሻ የተገኘው 523፣ ከ261 ፒክ አፕ ተሽከርካሪ የተገኘው 102፣ ከ62 ዶዘር 42 ብቻ የተገኘ” ነው ይላል፡፡ በእንግሊዝኛ የሚታተመው አዲስ ፎርቹን እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ “ከ242ቱ የቀረጥ ነጻ ዕድል ከተሰጣቸው ባለሃብቶች” መካከል አንድ ስሙ ያልታወቀ “ልማታዊ ባለሃብት” 78 መኪናዎችን ሳንቲም ቀረጥ ሳይከፍል ማስገባቱን ዘግቧል፡፡ ፎርቹን ያነጋገረው የባንኩ ከፍተኛ አመራር “መኪናዎቹ ሊሸጡ አይችሉም፤ ምክንያቱም ሲገቡ ባንኩ ይመዘግባል ስለዚህ ይህ ሊከሰት አይችልም” ካለ በኋላ “ይህ ሊሆን የሚችለው ገና ከጅምሩ መኪናዎቹ ሲገቡ ካልተመዘገቡ ነው” በማለት ለማስተባበል ሞክሯል፡፡

ሪፖርቱ ይህን ቢልም አሁን ላይ የተባሉት ተሽከርካሪና ትራክተሮች እንዲሁም ዶዘሮች ወዴት እንደተጓጓዙ አይታወቅም። የትኛው ክልልና መንደር እየሰሩ እንደሆነና ማን ህጋዊ እንዳደረጋቸው በይፋ የሚታውቅ ነገር የለም። ከወደመው ከፍተኛ የአገር ሃብት አንጻር ፍትህ ወደፊት ይጠበቃል። ችግሩ ፍትህ ወደፊት ሰይፏን ማንሳቷ ስለማይቀር የፍትህ ሰጋባ ለማንሳት የተነሱትን አመራሮች ለይቶ ለማጥፋት ጥድፊያ ተይዟል።

Related stories   “አቡነ ማቲያስ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም”

ኡጁሉ እንዲህ ይላል ” አንዳንድ ማሳ ውስጥ ህዝቡ ያገኛቸውን ትራክተሮች ጎማቸውን እየቆራረጠ በረባሶ ጫማ እየሰራ ይጠቀማል። ብረታ ብረቶቹን ለእለት አገልግሎት እየፈታታ እየተጠቀመባቸው ነው። አሁን ላይ ሜዳ ላይ ዳዋ የዋጣቸው ትራክተሮችና ዶዘሮች ዳግም ጥቅም የሚሰጡም አይደሉም። ባለቤቶች ነን የሚሉም የሉም። ወዴት እንደሄዱ አይታወቅም”

የጋምቤላ ክልል ኢንዘስትመንት ቢሮን ለማነጋገር ሞክረን አልተሳካልንም። ይሁን እንጂ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው አንድ የመንግስት ሃላፊ ዶክመንታሪ ፊልም በማዘጋጀት ላይ ያሉ ተቆርቋሪዎች መኖራቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል። የሆነው ሁሉ የሚያሳዝን እንደሆነና በአሁን ወቅት ምንም ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል።

በሕዝብ ስም እየተደራጁ፣ በህዝብ ስም እየዘረፉ ሲታወቅባቸው ህዝብ ውስጥ በመመሸግ ብሄርን ከለላ የሚያደርጉ ዘራፊዎችና ሽፋን ሰጥተው የሚያዘርፉት ሃይሎች  የማይተኙት ፍትህ እንዳይበየን ካላቸው ፍርሃቻ አንጻር ነውና ሕዝብ ጠለቅ አድርጎ ሊያስብ ይገባል።

 

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0