የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ማንኛውንም ተልዕኮ ለመፈፀም በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንዓ ያደታ ገለፁ።
ሚኒስትሩ የመከላከያ ሚኒስቴር የ2013 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ አመት የስራ አፈፃፀምን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
“የሰራዊቱ ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠናል” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ገለልተኛ ተቋም መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል።
ሰራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ህግ መንግስታዊ መርሀን መሰረት በማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሆነም ተረጋግጧል ብለዋል።
የክልሎችን የፀጥታ ግንባታ በተመለከተ ደረጃ ለማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞም የክልሎች የፀጥታ ግንባታ ለብሄራዊ አንድነት አደጋ ካላመጣ እና ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ እገዛ የሚያደርግ ከሆነ ያን ያክል የጎላ ችግር እንደሌለውም አውስተዋል።
ሰራዊቱ ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ጥሩ እንደሆነ መገምገሙንም ገልፀዋል።
በአቅም ግንባታ ዘርፍም በሶስት ወራቱ የተለያዩ መንግስት ያስቀመጣቸውን የአቅም ግንባታ ስትራቴጂዎችን መሰረት በማድረግ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ነው ያነሱት።
በዚህም የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እና ሌሎችም ተያያዥ ስራዎች በፍጥነት መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
የቀጠናውን ሰላም በጋራ ለመጠበቅ እና ቀጠናዊ ትብብርን ለማጎልበትም ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማስቆምና አካባበውን ወደ ሰላማዊ አንቅስቃሴ ለመመለስ ሰራዊቱ በአካባቢው ከሚገኘው ኮማንድ ፖስት ጋር በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር በማድረግ የተጠረጠሩ አካላትም በቁጥጥር ስር ውለው ተጠያቂ እየተደረጉ ይገኛሉም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ሰሞኑን በአካባቢው የተከሰተው ችግር ምንም እንኳን መነሻው ግለሰባዊ ፀብ ቢሆንም ሰራዊቱ ግን በዚህ ድርጊት የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እና አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ አንዲመለስ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም በሚል ሲነዛ የነበረው ወሬ ኢትዮጵያን በትክክል ካለማወቅና ካለመረዳት የመጣ ተራ ጩኸት መሆኑን በመጥቀስም ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት እንዳለ ሀገሪቷም እንዳልፈረሰች እያየን ነውም ብለዋል፡፡
በኃይለሚካኤል ዴቢሳ – FBC

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከሃሰተኛ መረጃ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ ቀረበ፣ የተጭበረበረ መረጃ ተሰራጭቶ ነበር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *