“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኦንገና የህወሃት አዲስ ፍቅር !! “ህወሃት ካደረሰው መጠነ ሰፊ በደል አንጻር የኦሮሞ ህዝብ ምን ይለናል” አቶ አራርሶ ቢቂላ

ህወሃት በእኛ ላይ ሲያደርስ ከነበረው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንጻር ችግሩ ሳይፈታ ከእነርሱ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት መመስረት እንደማይቻል መስማማት ላይ ተደርሷል። ይህንንም አስመልክተን ሁኔታውን ግልጽ አድርገናል። ከእነርሱ ጋር ምንም ግንኙነት የለንም። ግንኙነት ማድረግ ካስፈለገም ሁኔታውን ግልጽ እና የኦሮሞ ህዝብ እንዲያውቀው አድርገን መሆን አለበት ይታመናል ። ህወሀት በኦነግ ላይ ካደረሰው መጠነ ሰፊ በደል አንጻር በቀላሉ ከህወሀት ጋር መስማማት ይከብዳል። ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሞ ህዝብስ ምን ይለናል። ስለዚህም ነው ይህንንና መሰል ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጠነው። እኛ ትግላችንን ማካሄድ የምንፈልገው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው። ሌላ ተልዕኮ የለንም። ወደ አገር ውስጥም ስንገባ በዚሁ አይነት መንፈስ ነው የገባነው ።

አስቴር ኤልያስ

በኦነግ ጠቅላላ ጉባዔ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የጸደቀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ፕሮግራም እንደሚያመለክተው ግንባሩ የሚታገልለት የፖለቲካ ዓላማ ሁለት ነው። አንደኛ የህዝቦች ነፃነት፣ ዴሞክራሲያዊነት እና እኩልነትን እውን ለማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ ከማንኛውም ዓይነት ጭቆና እና ብዝበዛ ነፃ እንዲወጣ ማስቻል ነው።

ይህን ዓላማውን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በምስራቅ ኦሮሚያ አካባቢ ተወልደው ያደጉትንና ወደ ትጥቅ ትግሉ በ1969 ዓ.ም በአፍላ ወጣትነታቸው የተቀላቀሉትን የግንባሩን ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላን ስለወቅታዊው የኦነግ ጉዳይ እና ግንባሩ ከሰላም አኳያ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ያካሄደውን ቃለ መጠይቅ ይዘን ቀርበናል ።

አዲስ ዘመን፡- ገና በለጋ እድሜዎ ወደ ትግል ለመግባት ያነሳሳዎት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ አራርሶ፡- በወቅቱ እኔ የተወለድኩበት አካባቢ የተለየ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲደረግበት የነበረ አካባቢ ነው። ብዙዎች የሚታሰሩበት ጊዜ ነበር። በሐረርና በድሬዳዋ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም በገለምሶ ያሉ ተማሪዎችም ጭምር ችግሮች ነበሩባቸው። በወቅቱ ቀደም ብለው ትግሉን የተቀላቀሉ ታላላቆቻችን አንዳንድ መልዕክቶችን ይልኩልን ነበር፤ እግረ መንገዳቸውንም ለትግሉ ያዘጋጁን ነበር። እኛም በእነሱ እንቅስቃሴ እንማረክና ውስጣችን ይነሳሳ ነበር።

በእርግጥ በወቅቱ እኔ ልጅ ነበርኩ። ትልልቆቹ ወጥተው የትግሉን ዓለም ሲቀላቀሉ እኔም ዱካቸውን መከተል ጀመርኩ። ትግሉን የተቀላቀልኩት መልዕክቶችን በመላላክ ነበር፣ በዚህም የበኩሌን እወጣ ነበር። መልዕክቶችን ሳደርስና እንቅስቃሴውን ሳስተውል ከቆየሁ በኋላ እኔም የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል በቃሁ።

አዲስ ዘመን፡– ያኔ ትግሉን እንደጀመሩት በዛው ቀጠሉ ወይስ በመሃል አቋርጠው ነበር?

አቶ አራርሶ፡ ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ አላቋረጥኩም። በ1977 ዓ.ም አካባቢ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ በኩል እንቅስቃሴ ታደርግ ነበር። ሐሳቧም ታላቋን ሱማሊያ መመስረት ነበር። በወቅቱ እኔም ኦነግን በመቀላቀል ስልጠና የወሰድኩበት ጊዜ ነበር። በዚያ አይነት ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ ነው ኦነግን የተቀላቀልኩት ። ከዛም በኋላ ያለው ሕይወቴ በጦርነት ውስጥ ያለፈ ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡– ትግሉን ከተቀላቀሉ በኋላ ባሳለፏቸው ረጅም ትግል ዓመታት የነበሮት የስራ ኃላፊነቶች ምን ይመስላሉ?

አቶ አራርሶ፡ በእርግጥ በድርጅቱ ውስጥ የተለያ አደረጃቶች ነበሩ፤ በወቅቱም ከአዛዦች በታች ባለው መዋቅር ስር ነበርኩ ። በኛ ድርጅት አጠራር “ጭብራ” ከሚባለው የጦር አዛዥነት ጀምሮ የተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ አልፌአለሁ። “አባ ሰግሊ ሆኛለሁ” ። ከቆይታ በኋላም ማለትም ከአራት ዓመት በኋላ “አባ ሙራሳ” ሆኜ አገልግያለሁ ፣ አደረጃጀቱ በወቅቱ ከ35 እስከ 40 ሰው ይይዝ ነበር።

አዲስ ዘመን፡– አሁን ያሉበት የአዋጊነት ማዕረግ ምን የሚባል ነው?

አቶ አራርሶ፡ እኛ ዘንድ በትግል ወቅት የሚሰጠው የኃላፊነት ደረጃ የሚሄደው እስከ “አባ ጭብራ” ድረስ ነው። በትግሉ ወቅት በምስራቅ ኦሮሚያ፣ አርሲ፣ ባሌ ዞን ውስጥ በቆየሁባቸው ጊዜያት ፣ ትግሉ ከሐረርጌ ወደ አርሲ፣ ከአርሲ ወደ ባሌ እንዲስፋፋ ሰርቻለሁ ። በተለይ እኔ እ.ኤ.አ. 1981 ከሐረርጌ ወደ አርሲ ስንቀሳቀስ ነበር ። በአርሲ ጎሎልቻ አካባቢ ነው በዋናነት የቆየሁት። ከዛ በኋላ ነው በጦሩ “አባ ሙራሳ” የሚባለውን የአዛዥነት ማዕረግ ያገኘሁት።

እ.ኤ.አ. በ1985 አርሲ ዞን ውስጥ የዞን ኮሚቴ በመሆን ሰርቻለሁ። በዚሁ የዞን ኮሚቴ ውስጥም የኢኮኖሚ ጉዳዮች ውስጥ ሰርቻለሁ። በኋላ ላይ እ.ኤ.አ. በ1988 ወደማዕከላዊ ኮሚቴ መጣሁ። ከቆይታ በኋላ ደግሞ በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ተመረጥኩ። በ1989 በዛው በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ደግሜ ተመርጫለሁ። በወቅቱም በተለያዩ ስራዎች ውስጥ ከቆየሁ በኋላ የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ1991 ሐረር አካባቢን ጨምሮ ኤጀርሳ ጎሮ፣ ጉርሱም፣ እስከ ሱማሌ ድረስ አዛዥ ሆኜ ሰርቻለሁ ። ይህ ማለት እ.ኤ.አ. ከ1991 እስከ 1992 የደርግ መንግሥት እስከወደቀበት ድረስ መሆኑ ነው። ከዚያም በኋላ እስከ 1996 ድረስ እዛው አካባቢ ነበርኩ።

እ.ኤ.አ. በ1998 በዘጠነኛው ወር ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ጦርነት ሲጀምሩ ወደ ኤርትራ ለማቅናት ተገደድኩ። እዛም በነበርኩበት ወቅት ያው በጦርነቱ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት። በወቅቱም አዳዲሶቹ የድርጅቱ አባላት ስልጠና የሚጀምሩት እኔው ዘንድ ነበር። በዚህ መልኩ እኔም በተለያዩ ግዳጆች ላይ ቆይቻለሁ ።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የእኛ ቢሮም ወደ አስመራ አቀና። ቀጥሎም እኔ ወደ ሐረርጌ ተመልሼ እንደ ዞን አጠቃላይ አዛዥ ሆኜ ተመደብኩ። ከተመደብኩ ሁለት ዓመት ያህል ሥራ ላይ ከቆየሁ በኋላ አስመራ ኮንፈረንስ ስለነበረን ወደዚያ መመለስ ግድ ሆነብኝ። እዛ ኮንፈራንስ ላይ ቆየሁ። በኮንፈራንሱ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን፣ በዚያ ላይ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠኝ።

አዲስ ዘመን፡– እስኪ ወቅታዊ ወደሆነው ነገር ልመልስዎና በኦነግ መካከል የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው?ኦነግ በአሁኑ ወቅት ምን አይነት ሁኔታ ላይ ነው ያለው?

አቶ አራርሶ፡ ኦነግ እ.ኤ.አ. በ2018 በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ለውጥ በማየት ከመጣ ጀምሮ ሰላማዊ ትግል እያካሄደ ነው ። ከዚህ በፊት የትጥቅ ትግል ሲያካሄድ ነበር የከረመው። በአሁኑ ወቅት ግን የሚያካሂደው ሰላማዊ ትግል ነው።

ሰላማዊ ትግል እያካሄድን ባለንበት ወቅት፣ በተለይ ደግሞ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ጥሩ አልነበረም። በወቅቱም እኔ በድርጅታችን ውስጥ ኃላፊነት ያላቸውን ከሰኔ 26 እስከ 27 ቀን 2012 ድረስ ጉለሌ ወደሚገኘው ፅሀፈት ቤታችን በመጥራት የተፈጠሩትን ችግሮች መሰረት በማድረግ ተሰባስበን ሊያግባቡን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል። ለሁሉም ነገር ባለን ደንብ መሰረት ሰላማዊ በሆነ መልኩ መታገል እና በጎደለው ነገር በተለይ የታሰሩትን በተመለከተ መንግሥትን መጠየቅ ፣ አቋማችንንም ዳግም ማጥራት በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ መክረናል።

በተለይ ደግሞ በመንግሥት ሲነገር የነበረው “አንደኛው እግራችሁ ሌላ ቦታ ሌላው ደግሞ ሌላ ቦታ ሆኖ ነው የምትታገሉት” የሚል ነው። እኛ ግን እንደ ድርጅት አቋም ይዘን በሰላማዊ መንገድ በመታገል ላይ መሆናችንን ነው የምንረዳው። ይህንኑ ነው ይዘን የምንቀጥለው እያልን ነው።

ከዚህ በፊት ሲነገር የቆየው ኦነግ ጉለሌ ተቀምጦ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ያደርጋል የሚል ነው። ጫካ ውስጥ ካለው ኦነግ ሸኔ ጋርም ትስስር አለው ይባልም ነበር። እየተንቀሳቀሱ ያሉት በሁለት እግራቸው ነው በሚልም በስፋት ሲነገር ቆይቷል።

አመራር ደግሞ እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር የማስተካከል ኃላፊነት አለበት ። እኛም እንደ አመራር ልናደርግ የሚገባው ስብሰባ በመጥራት አቋማችንን

ግልጽ በማድረግ ትግላችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል እንዳለብን የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው ። ስብሰባውም የተጠራው ለዚሁ ጉዳይ ነበር።

በወቅቱ ለአቶ ዳውድም ወቅታዊውን ሁኔታ በመግለጽ ለስብሰባ የጠራኋቸው አባላት እነማን እንደሆኑ ከማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት አንድ ሰው ይዤ ቤታቸው ድረስ በመሄድ አሳውቄዋለሁ። እርሱም ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ምከሩበት ብሎን ነበር። ወዲያው ግን ስብሰባው ከደንብና ስርዓት ውጭ ነው የሚደረገው በሚል የዚያኑ ዕለት ውድቅት ሌሊት ላይ በማህበራዊ ትስስር ገጽ መልቀቁን አስተዋልን። እንዲያም ሆኖ እኛም በጸጥታ ኃይል አጋዥነት ለሁለት ቀን ስብሰባችንን አካሂደናል።

በማግስቱ እኛ ለስብሰባ ወደ ቢሮ ለመግባት ስናቀና የተወሰኑ ልጆች ወደቢሮ መግባት አትችሉም ሲሉ ሞግተውናል ። እኛ ይህ አግባብ አይደለም በማለት በአካባቢው የሚገኘውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠርተን ለስብሰባ ወደ ቢሮ ለመግባት ብንሞክርም ልጆቹ ሊያስገቡን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፣ ስርዓት እንዲያሲይዝልን ለፖሊስ አሳውቀን ስብሰባችንን ለሁለት ቀን አካሂደን ማጠናቀቅ ችለናል ። ከዛም ቀጥሎ መግለጫ ሰጠን፤ የሰጠነው መግለጫ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ያለንን አቋም የሚገልጽ ነው።

አዲስ ዘመን፡– ኦነግ መቀሌ ድረስ ተጉዞ ከህወሃት ጋር ስብሰባ ተቀምጧል ይባል ነበር በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ አራርሶ፡ በእርግጥ ኦነግ ከየትኛውም ድርጅት ጋር የመወያየት መብት አለው። ነገር ግን በህወሃትና በኛ መካከል ያለው ችግር በጣም ሰፊ በመሆኑ ያ ችግር መፍትሄ ሳያገኝ ዝም ብለን መገናኘት የለብንም የሚል ሀሳብ ነበር ። ምክንያቱም በኦነግ ላይ በህወሀት ይደርሱ የነበሩ ችግሮች በደንብ የሚታወቁ ናቸው ። አንዱ ሲታሰር፣ ሌላው ከአገር ሲባረር፣ ሌላው ደግሞ ሲገደል ነው የቆየው።

ስለዚህ ህወሃት በእኛ ላይ ሲያደርስ ከነበረው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንጻር ችግሩ ሳይፈታ ከእነርሱ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት መመስረት እንደማይቻል መስማማት ላይ ተደርሷል። ይህንንም አስመልክተን ሁኔታውን ግልጽ አድርገናል። ከእነርሱ ጋር ምንም ግንኙነት የለንም። ግንኙነት ማድረግ ካስፈለገም ሁኔታውን ግልጽ እና የኦሮሞ ህዝብ እንዲያውቀው አድርገን መሆን አለበት ይታመናል ። ህወሀት በኦነግ ላይ ካደረሰው መጠነ ሰፊ በደል አንጻር በቀላሉ ከህወሀት ጋር መስማማት ይከብዳል። ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሞ ህዝብስ ምን ይለናል። ስለዚህም ነው ይህንንና መሰል ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጠነው። እኛ ትግላችንን ማካሄድ የምንፈልገው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው። ሌላ ተልዕኮ የለንም። ወደ አገር ውስጥም ስንገባ በዚሁ አይነት መንፈስ ነው የገባነው ።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ባለው ጊዜ በሰላማዊ መንገድ በመታገሉ ላይ እንደ ድርጅት የጋራ አቋም አልነበራችሁም?

አቶ አራርሶ፡- ያኔ ሁላችንም ተነጋግረን በሰላም ለመታገል ነው ተስማምተን ወደ ሀገር ውስጥ የገባነው። አዲስ አበባ የመጣነው በመንግሥት አውሮፕላን ነው። የኦነግ ሰራዊትም እንዲሁ መንግሥት ባቀረበው አውቶቡስ ነው የገባው ። በዚህ ጉዳይ ልዩነት አልነበረም ።

አዲስ ዘመን፡– ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ቤት ገብቶ፣ ትጥቅ ማነው የሚያስፈታን ሲሉም ተደምጧል ይህ ምን ማለት ነበር?

አቶ አራርሶ፡ እኛ ኤርትራ በነበርንበት ወቅት ያሉንን ሰራዊት ይዘን ወደአገር ቤት መግባታችን ይታወቃል። በወቅቱም ከመንግሥት ጋር መግባባት ላይ የደረስነው በሁለት ነገሮች ነው፤ ይኸውም ከሰራዊታችን የሚፈልግ ካለ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኃይል ጋር ተቀላቅሎ መቀጠል እንዲችል፤ ምርጫው ያልሆነ ደግሞ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ህይወቱን መምራት በሚችልበት ሁኔታ ነው ። ይህ ሳይሳካ ቀርቷል።

አዲስ ዘመን፡- ለምን አልተሳካም ? በሂደቱ ውስጥ የተለያየ ፍላጎት ነበር ማለት ነው?

አቶ አራርሶ፡- ቀድም ብሎ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ቡድን ጥሩ የሆነ አያያዝ አልተደረገለትም የሚል ነገር ተነሳ። እዛ የቀሩት ደግሞ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች የረባውም ያልረባውም ወሬ በመናፈሱ ነገሮች ወዲህ ወዲያ ሲሉ ቆዩ። እንዲያም ሆኖ ጉዳዩን የገዳ አባቶች እንዲይዙት የቴክኒክ ኮሚቴም እንዲቋቋም ተደረገ ። ቀደም ሲል በአባ ገዳዎችና በቴክኒክ ኮሚቴው አማካይነት የገባውም ገባ። የቀረውም እዛው ቀረ ።

ይህ የቀረው ደግሞ በራሱ የራሱን ውሳኔ በመውሰድ ጉለሌ ላለው አመራር አንታዘዝም፤ የራሳችንን አመራር ነው የምናበጀው ሲል በማህራዊ ትስስር ገጽ ላይ መግለጫ አወጣ። እኛም ከዚህ በኋላ ነበር መግለጫ መስጠት አለብን ብለን ከኦሮሚያ መንግሥት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ የያዝነው፤ በመካከላችንም ችግር አለ በሚል ብዙ ውይይት ስናደርግም ቆየን። የክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ኮሚቴ በማቋቋም ከእኛ ጋር ለመወያየት እንገናኝ አለ። በኋላ ደግሞ ኦነግ የታጠቀ ኃይል እንደሌለው ሊገለጽ ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት ባሉበት ኦነግ ጦር እንደሌለው በቴክኒክ ኮሚቴው መግለጫ ተሰጠ ። በሌላ ቦታ ያለውና እዛ የቀረው በእኛ ትዕዛዝ ስር አይደለም። የራሱንም መግለጫ አውጥቷል። እኛም ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለንም አሳውቀናል።

ነገሩ የተከሰተው ሁለት የድርጅቱ አመራሮች በራሳቸው ውሳኔ ጫካ ከቀረው ሀይል መቀላቀላቸው ነው ። በዚህ ምክንያትም በመንግሥት በኩል የነበረው ጥርጣሬ ከፍ እያለ መጣ። በዚህ መልኩ ነው በመንግሥት እና በኦነግ በኩል አለመተማመን የመጣው። ምክንያቱም መንግሥት ይል የነበረው አንድ እግራችሁን እዚህ ሌላኛውን ደግሞ እዚያ አድርጋችኋል ነው። እኛ ደግሞ ትግላችን ሰላማዊ ነው፤ ምንም ሌላ ተልዕኮ የለንም ስንል መግለጫ ብንሰጥም ጥርጣሬው እየበረታ መጣ።

አዲስ ዘመን፡– በጫካ ያሉትን ወደአንድነት እንዲመጡ እና በሰላም እንዲታገሉ አልሞከራ ችሁም፤ለመገናኘት ያደረጋችሁትስ ሙከራ ይኖር ይሆን?

አቶ አራርሶ፡ ሞክረናል፤ በመጀመሪያም ይህ ውሳኔ እንደተሰጠ ትጥቅ መግታት እንዳለባቸው ተወያይተናል። ውይይቱ ትጥቅ እንዲፈታም ነበር። ነገር ግን እነሱ ሲጠብቁ የነበረው እነዚያ የተግባባንባቸው ጉዳዮች ስለምን አልተከበሩም የሚል ነው። አንደኛ ኦነግ ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው የነበሩት የድሮዎቹ የተዘጉ ቢሮዎች እንዲከፈቱ ነው። በተጨማሪም አመራሮች ሲመጡ ሆቴል መያዝ ሳይሆን ቋሚ ማረፊያዎች ይቅረብላቸው ነው ።

በወቅቱ የነበሩት የክልሉ ፕሬዚዳንትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ተስፋ ቢሰጡም የኦነግ አመራሮች ሲመጡ ግን ነገሮች አልተፈጸሙም። የጉዳዩን አለመሳካት በጫካ ያለው ኃይል ደርሶታል ፣ በዚህም አንመጣም ያሉትን ውሳኔ አጽንተው እንዲይዙ እና እዛው እንዲቆዩ ይነግሯቸዋል።

እኛ ደግሞ መንግሥት የገባውን ቃል ይፈጸማል፤ ቢሮዎቹም ይሰጣሉ። እኛ ግን የወሰነውን ነገር በስራ ላይ አውሉ በማለት መግለጫ ብንሰጥም ጉዳዩ አጥጋቢ ሆኖ ስላልታያቸው አንመጣም ሲሉ ውሳኔ አሳለፉ።

አዲስ ዘመን፡– ቀደም ሲል ወዳነሳሁት ጥያቄ ልመልስዎትና አቶ ዳውድን በወቅቱ ሄደው ሲጠይቋቸው ቀጥሉበት ማለታቸው በቃል ብቻ ነው ወይስ በጽሁፍ የተደገፈ ነበር?

አቶ አራርሶ፡ በመካከላችን እርስ በርስ መጠራጠር ስላልነበረ የተፈረመ ነገር የለም። ምክንያቱም ታጋዮች ነን፤ ለረዥም ዓመት አብረን ቆይተናል። ወደእርሳቸውም የሄድኩት አንድ ሰው ይዤ ነው ፣ እርሳቸውም ቀጥሉበት ነው ያሉን። ይሁንና ተግባብተን ከተለያየን በኋላ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ጉዳዩ አግባብ እንዳልሆነ የሚገለጽ ነገር እኩለ ሌሊት አካባቢ ተለቀቀ።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ኦነግ እንደሌላው ሁሉ ወደአገር ቤት በመግባት ሰላማዊ ትግል ማካሄድ ይችላል ተብሎ በደረሰው ጥሪ መሰረት ነው በትግራይ በኩል የመጣው፤ ይህ ታዲያ በኦሮሞም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥርጣሬ የፈጠረው ለምን ይሆን? አሁን ደግሞ እየተነገረ ያለው ኦነግ ከህወሃት ጋር እየተንቀሳቀሰ ነው የሚል ነው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ አራርሶ፡- ኦነግ በትግራይ በኩል ልግባ ብሎ ሳይሆን መንግሥት ባመቻቸው መንገድ ነው የመጣው። ስለዚህም ኦነግ በትግራይ በኩል እገባለሁ ብሎ እቅድ አልያዘም። መንግሥት እንዳለው የተወሰኑ አባላቱ በአውሮፕላን ሌላው ደግሞ በትግራይ በኩል እንዲገቡ አውቶቡስም የታዘዘው በመንግሥት ነው። ስለዚህ በትግራይ በኩል ነው የምገባው ብሎ ኦነግ ያደረገው ዝግጅት የለም።

አዲስ ዘመን፡– ለዚህ ጥያቄ መነሻ የሆነኝ ነገር አንዳንዶች እንደሚሉት በፊትም ቢሆን ኦነግ ልቡ ወደ ህወሃት ነው፤ አሁንም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው እያሉ ነው እዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት ?

አቶ አራርሶ፡ ኦነግ ከህወሃት ጋር ምንም አይነት መግባባት ላይ አልደረሰም፤ ፌዴራሊስት ኃይሎች ሲሰባሰቡም ኦነግ አልተሰበሰበም። አንድ ጊዜ የፋይናንስ ሰው ለሌላ ጉዳይ ተልኮ እንደነበር አውቃለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ታዲያ በራሱ መፈላለግን የሚያመላከት አይደለም?

አቶ አራርሶ፡- ይህ የሆነው ከፌዴራሊስት ኃይሎች ጋር ለመወያየት ሳይሆን ለሌላ ጉዳይ ነው። እንደ ድርጅት ተመካከረን ሳይሆን አቶ ዳውድ ናቸው የላኩት፤ እንደ ድርጅት አይደለም። በመሃልም ይህ ለምን ሆነ ብለን ጠይቀናል።

አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ እንደ ድርጅት ተመካክራችሁና አቋም ይዛችሁ ካላካችሁ አንድ ግለሰብ በራሱ ተነሳሽነት መሄድ ይችላል ማለት ነው?

አቶ አራርሶ፡ እንግዲህ ያሰማሩት ሊቀመንበሩ ናቸው። እኛ ደግሞ እንደ ድርጅት ተመካክረን እከሌን መላክ አለብን፤ ከህወሃት ጋር መገናኘት ብለን ያሰማራነው ነገር የለም።

አዲስ ዘመን፡– የአገር ሽማግሌ የሆኑት ኃይሌ ገብሬ በአንድ ወቅት ‹‹የኦሮሞ ህዝብ ሰላም የሚያገኝ ከሆነ እባካችሁ እኔን እረዱኝና ሰላም ይምጣ ማለታቸውን ያስታውሳሉ ብዬ አምናለሁ። ታዲያ የኙህ ሽማግሌና የሌሎችም የሰላም ተማጽኖ እና እምባ ኦነግን ምንም አይገደውም ማለት ነው?

አቶ አራርሶ፡ ይገደዋል። በድርጅታችን ውስጥ ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት ለአመራሩ የሚያደላ ነው፤ ከሊደርሺፕ ጋር ግንኙነት አለው። ይህ ስርዓት ደግሞ በድርጅቱ ደንብ ውስጥ አለ እንጂ በተጨባጭ ወደ ስራ አልተተረጎመም።

ለዚህም ነው ችግርና አለመግባባት መላልሶ ድርጅቱን ለመጎብኘቱ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ። አንድ ሰው ወስኖ ሁሉን ነገር ያደርጋል። ይህ አካሄድ ደግሞ ደጋግሞ አመራሩ ላይ ጥርጣሬ የሚያጭርና አንድነት እየተሸረሸረ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው። ስርዓት የለም እንዳይባል አለ፤ ግን ችግሩ አይፈታም። ህግና ደንቡ በወረቀት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡– ኦነግ ዛሬ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላልየኦነግ አመራሮች እርስ በእርስ ሳይግባቡ ለሰፊው የኦሮሞ ህዝብ እንዴት ነው መሪ መሆን የሚችሉት?

አቶ አራርሶ፡ ይህ አካሄድ ይስተካከላል ብለን እናምናለን። ለአንድ ሰው ሲባል ድርጅት አይፈርስም። ስለዚህም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተቀምጠን ጠቅላላ ጉባኤ እስኪጠራ ድረስ ሊቀመንበሩ ከስራ ታግደው እንዲቆዩ ብለን መግለጫ ሰጥተናል። የህዝቡ የትናንት የትግሉ ተስፋ ዛሬም በቦታው ነው ። ስለዚህ አንድ ሰው ስራ አቆመ ብለን የምናቆመው ነገር አይኖርም።

ግለሰቡ ማድረግ የነበረበት ሁለት ጉዳይ ነበር፤ እንደ ኦነግ እንደሁሌም ለራሱ ክብርም ሆነ ለታሪኩም ጭምር እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲፈጠር ይቅርታ ማለቱ ተገቢ ነበር። ይህን ማድረግ ያለበት ለኦሮሞ ህዝብ ሲል ነው። የአንድ ድርጅት ሊቀመንበር ብቻ ሳይሆን የአንድ አገር መሪም እኮ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ የተሻለውን እርምጃ እንደሚወስድ የሚታወቅ ነው። ስልጣኑንም ጭምር ነው የሚለቀው።

አዲስ ዘመን፡ ከማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የአቶ ዳውድን አቋም የደገፉ አሉ?

አቶ አራርሶ፡ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የቀሩት አቶ ዳውድ ብቻ ናቸው። ሁለት ሰዎች በእስር ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከአቶ ዳውድ ጋር ማንም የለም ማለት ይቻላል። ብቻቸውን ስለመሆናቸው ግልጽ ነው።

Related stories   ሰላም፣እርጋታና የዜጎች ደህንነት ለኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ናቸው – በአሜሪካ የህዝብ ዲፕሎማሲ አማካሪ ምክር ቤት

አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ሰዓት ኦነግን በመምራት ላይ ያላችሁ ምን ያህል ናችሁግልጽ እንዲያደርጉልኝ የምፈልገው ኦነግ መካከል የተፈጠረው ነገርስ ምንድን ነው?

አቶ አራርሶ፡ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚባለው ለብቻ አለ። በኮሚቴው ውስጥ ያለው አምስት ሰው ነው። ቀደም ሲል ይህን ድርጅት ሲመሩ የነበሩት እንደሚታወቀው አቶ ዳውድ ኢብሳ ናቸው። አሁን ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ መሪውን እስኪሰይም ድረስ ከአመራርነት አግደናቸዋል። ያለው አመራር ስራውን ቀጥሏል ። በዚህ ጉዳይ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም ። ኦነግ አሁንም የቀደመውን አቋሙን ይዞ እንደቀጠለ ነው ።

ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል ። እየተጓዘ ያለውም በዚህ ሁኔታ ነው። ከያዘው ሰላማዊ ትግል ፈቀቅ የሚል ድርጅት አይደለም፣ በዚህ ማንም ጥርጣሬ ሊገባው አያስፈልግም። ቀደም ሲል ወደአገር ቤት ከገባን ጊዜ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ ትግላችንን እናጠናክራለን ብለን ቃል በገባነው መሰረት ያንን ቃል እየፈጸምን ነው ።

ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ከፌዴራል መንግሥት ጋርም ችግራችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን በመወያየትና በመመካከር እንቋጫለን እንጂ ችግር ተፈጥሯል በሚል ብቻ የምናድበሰብስ ነገር አይሆንም። ከዚህ በኋላ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት አንሆንም። እንደሚታወቀው ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ችግሮችን በጋራ ተቀምጠን በምክክር የምንፈታ ይሆናል፤ የያዝነው መንገድም ይኸው ነው ፤ የተለየ ተልዕኮ የለንም።

አዲስ ዘመን፡– በሌላ በኩል በኦነግ መካከል መንግሥት እጁን ስላስገባ ነው ችግሮች የሚፈጠሩት በሚል ጥርጣሬ ያላቸው አካላት አሉ ይህን እንዴት ያዩታል ?

አቶ አራርሶ፡ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የሚታገለውን ድርጅት በህግ በአግባቡ ያስተናግደዋል እንጂ ከሌላው ለይቶ አያየውም። ሁለት አካላት ሊገናኙ የሚችሉት በህግ አግባብ ነው። እኛ በዞኖችም ውስጥ ይሁን በወረዳዎች ውስጥ እንዲሁም በተለያዩ ከተሞች በምንቀሳቀስበትና በምንሰራበት ጊዜ ለራሳችን ሰላም ስንል እናሳውቃለን።

ይህ የአሰራር ጉዳይ ነው፤ ከዚሕ ውጪ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ድርጅታችንን ይህንን አድርግ ያን ፍጠር የሚልበት ምክንያት የለም። ይህ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንጂ አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ የሚገባበት አሰራር አይደለም ። ስለዚህም መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ግንባሩን የሚያዝበት አንዳች ነገር የለም።

ኦነግ በራሱ ነጻ የሆነ ድርጅት ነው ፤የማንንም ጣልቃ ገብነት የሚቀበል አይደለም። የራሱ የሆነ የፖለቲካ መርሐግብር እና ህግ እንዲሁም መመሪያ አለው ። ገዥው መንግሥትም ሆነ ኦነግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። ስለሆነም ልክ እንደትናንቱ ሁሉ ኦነግ ራሱን ችሎ የሚራመድ ድርጅት በመሆኑ የሚባለው ነገር ተቀባይነት የሌለው ነው።

አዲስ ዘመን፡– ሌሎች ደግሞ መንግሥት ኦነግ እንዲፈርስ ፍላጎት ስላለው ነው ጣልቃ የሚገባው ሲሉ ይደመጣሉና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ አራርሶ፡ በእኛ በኩል ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ትናንትም ሆነ በመጣንበት ጊዜም ቢሆን ተመካክረን የተግባባንበት ሁኔታ አለ። እኛ ትግላችንን ህግና ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ማካሄድ ነው። ምናልባትም ችግሮች ቢደርሱብን እነዛን ችግሮች በህግ መሰረት መፍታት እንጂ ሌላ ነገር የለንም። ስለዚህ እኛ ወደአገር ቤት ስንገባ ዝም ብለን ሳይሆን ከመንግሥት ጋር በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ መክረን ነው። ስለሆነም በሰላማዊ መንገድ የሚታገል አንድ ድርጅት በአንድም ሆነ በሌላ ከመንግሥት ጋር ሊገናኝ የሚችልባቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህ ያለፈ ሌላ ነገር የለም።

አዲስ ዘመን፡– የሰላማዊ ትግል ፅንሰ ሀሳብን ኦነግ እንዴት ይገልፃል?

አቶ አራርሶ፡ በሰላማዊ መንገድ የመታገሉ ጉዳይ ገና ጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ያለመረዳት ነገር ይታያል። አንዱ የኔ ጀግና ነው የሚለውን ሌላው ሲሰድብ ይታያል ። ለምሳሌ የቀድሞውን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላን ማየት ከተቻለ ከሁለት አሥርት ዓመት በላይ ታስረው የወጡ ናቸው። ተመልሶ ደግሞ በመቻቻልና በመከባበር መርህ አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፤ ይህን አይነቱን ነገር በአገራችን በኢትዮጵያም ቢሆን ማን ይከለክለናል ። ከዚህ ልንማር የሚገባው ነገር ትግልን በሰላማዊ መንገድ አካሂዶ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው ። ዝም ብሎ ብቻ ስለተናገሩ የሚመጣ ለውጥ የለም ። ለውጥ የሚገኘው በስራ ስለሆነ መስራት የግድ ይላል።

መንግሥትም ብቻውን ሰርቶ ሊያመጣ የሚችለው ነገር አይኖርም፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመስራት በመመካከር ነው ነገሮች ሁሉ መልካም የሚሆኑት። እኛም በሰላማዊ መንገድ እየታገለን ስለሆነ በዚህ እንስማማለን። እንዲህ ስል ግን ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

ለዚህ ሁሉ ትልቁን ውሳኔ መስጠት የሚችለው ህዝቡ ነው። ዋናው ነገር ሰላም ነውና ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት መቻሉ ለእኛም ትልቅ ውጤት ነው። ተማሪዎችም በሰላም ተምረው መመለስ መቻላቸውም እንዲሁ ከምንም ነገር የሚበልጥ ነው። ደግሞም እኛም ሰላማዊ ትግላችንን ማካሄድ የምንችለው አገር ሰላም ስትሆን ነው።

ደግሞም አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ከዚህ በኋላ የሚመረጥ መንግሥት ቢኖር መራጩ ራሱ ህዝቡ ነው እንጂ ወደ መንግሥት በመጠጋጋት አሊያም በጠብመንጃ አፈሙዝ በመታገዝ አይሆንም። ለዚህች አገርም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ችግር ውስጥ የሚከታት እንጂ ውጤት ያለው አይሆንም። ይህን ደግሞ እኛ ከጅምሩ ያመንበት ጉዳይ በመሆኑ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ በእኛና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት በህግና ደንብ መሰረት የሚካሄድ እንጂ የተለየ ግንኙነት አይደለም።

አዲስ ዘመን፡– ኦነግ ለምንድን ነው ብዙ ጊዜ የመከፋፈል አደጋ የሚጋረጥበት?

አቶ አራርሶ፡ እውነት ነው ይህ ችግር ያጋጥመዋል። ይህ የሚከሰተው ህግና ደንብን ስራ ላይ ካለማዋል የተነሳ ነው። ህግና ደንብ በአግባቡ ስራ ላይ ካልዋለ የመከፋፈል ችግር ያጋጥማል ። በአመራር ላይ ያለ አካል በየአራት ዓመቱ የሚቀየር ነው። ይህ በድርጅቱ ውስጠ ደንብ የተቀመጠ ነው።

ነገር ግን አሁን ያለው ነገር ያንን የሚተላለፍ ነው። ይህ ደግሞ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አቋም እንዲኖር በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ደግሞም ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በእርቅ የቋጨንበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ በአንድ ወቅትም እንዲህ የመከፋፈል አደጋ ተጋርጦብን መልሰን ችግሩን ለመፍታት ችለናል።

በዚህ አግባብም ካለመረዳት የተነሳ የሚከሰት ችግር እንኳ ቢኖር በመታገስና አርቆ በማሰብ ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንጂ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት መነሳት የለበትም። ከዚህ ይልቅ ለህዝብና ለአገር በማሰብ የሚፈጠረውን ችግር በደንቡ በመገዛትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመጓዝ ቋጭተን መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ። የጎደለውም ይሄ ነው ።

አዲስ ዘመን፡– ታዲያ እናንተ ያንን ሳታደርጉ የተለያየ አመለካከት ያለውን ህዝብ በዚህ መንገድ ማስተዳደር ይቻላልየሕዝቡ ጥማት ዴሞክራሲ ነው፤ እናንተ ለዴሞክራሲያዊ መርህ መሸነፍ ሳትችሉ እንዴት ነው ቀጣይ ጉዟችሁ ፍሬ የሚያፈራው ?

አቶ አራርሶ፡ ልክ ነው፤ ለውጥ ያስፈልጋል። ይለወጣል ይባላል ግን አራተኛ ዓመት ላይ ሲደረስ ይታለፋል። ይህ ማለት ደግሞ በአመራር ደረጃ ያለው ግለሰብ የሕዝብን ሳይሆን የራሱን ፍላጎት አስቀደመ ማለት ነው። በዚህም ግለሰቡ የሚስያጠብቀው ወንበሩን እንጂ ህዝብን አይደለም። ለዚህም ነው እንዲህ አይነቱ ነገር ማቆም አለበት ብለን አቋም የወሰድነው።

እንዲህ አይነቱ ነገር የሆነ ቦታ ላይ መቆም መቻል አለበት። እንዲሁ በየዓመቱ ሊከሰት አይገባም። ትናንት እንደሱ ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ ዛሬ ግን መሆን የለበትም። ትግሉ የኦሮሞ ህዝብ ነው። ህዝቡ ደግሞ ይህን አካሄድ የማወቅ መብት አለው። ስለዚህ መደበቅ የለበትም ባይ ነን ። መደበቅ እኮ ድርጅቱን ሊያጠፋ ይችላል። ለዚህም ነው መደበቅ የለብንም ብለን ለህዝብ ግልጽ ለማድረግ የተገደድነው። ምክንያቱም የድርጅቱ ራስ መልካም ከሆነ ሁሉም መልካም የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። ከራሱ ላይ ከተበላሸና ከመንገድ ዞር ካለ ግን ችግር ያንኑ ያህል ነው የሚሆነው ።

አዲስ ዘመን፡– በእናንተ በኩል ለወጣቶች ምን ለማድረግ የታሰበ ነገር አለ?

አቶ አራርሶ፡ ወደአገር ውስጥ ከገባን ጊዜ ጀምሮ ወጣቱ ላይ ለመስራት ሞክረናል። ወጣቱ ከዚህ ድርጅት ጋር ለመጓዝ ትልቅ ፍላጎት አለው ። ደግሞም ትግሉን እኛ ጀመርን እንጂ እኛው ራሳችን ልንጨርሰው አንችልም።

ትግልን አንዱ ይጀምራል፤ ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ ያስረክባል። ይህ በዓለም ታሪክ ውስጥ ያለ ነው። ትግልን የጀመረው ያ ቡድን ራሱ አይቋጨውም። በድርጅታችን ያለው አቋምም ይኸው ነው።

አዲስ ዘመን፡– በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ 16 ያህል ይጠጋሉና ኦነግ በክልል ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየትኞቹ ጋር ለመስራት አስቧል?

አቶ አራርሶ፡ እኛ በእርግጥ ወደአገር ቤት ከገባን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስናነጋግር

ቆይተናል። አብረናቸው ልንሰራ እንችላለን ካልናቸው ጋር አብሮ ለመስራት አሁንም በመነጋገር ላይ ነን። በዓላማ ከሚመስለን ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁዎች ነን። ይህ ሁሌም ቢሆን አቋማችን ነው። መተጋገዝ ተልእኮን ለማሳካት መልካም እድል እንደሚፈጥር እናምናለን ።

አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ ባወጣችሁት መግለጫ ለኦነግ ነባር ታጋዮች ጥሪ አስተላልፋችሁ እንደነበር ይታወቃልና መልዕክቱ ደርሷቸው ይሆን ? ምላሻቸውስ ምን ይመስላል?

Related stories   ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ ነው

አቶ አራርሶ፡ በእርግጥ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ላሉት ጥሪው ደርሷቸዋል ማለት ይቻላል። እነሱም ምላሽ ሰጥተዋል። እናንተ ከፈለጋችሁንና መስራት አለባችሁ ካላችሁን እንሰራለን፤ የመስራት ግዴታ አለብን። ስለዚህ ከእናንተው ጋር ነን በርቱ ብለውናል። ስለዚህ እስካሁን ባደረግነው ግንኙነት ያለው ሁኔታ መልካም የሚባል ነው።

አዲስ ዘመን፡– ለአብነት ያህል ስማቸውን መጥቀስ ይችላሉ?

አቶ አራርሶ፡– ለጊዜው የሰዎቹን ስም መጥቀሱ አስፈላጊ አይሆንም።

አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ ባካሄዳችሁት ስብሰባ ላይ ኦሮማራን አስመልክቶ ያላችሁት ነገር አለ፤ ኦነግ የኦሮማራ ግንኙነትን የሚያየው እንዴት ነውየሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ለኦነግ ምን ማለት ነው?

አቶ አራርሶ፡ በእርግጥ በአማራ ክልል ባሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ሲገደሉ ቆይተዋል። እንዲሁም በኦሮሚያ ክልልም ችግሮች ተመሳሳይ ነበር ። ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ከመደረጋቸውም በተጨማሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ያንን ነገር ሲከታተለው ቆይቷል።

በዚህም ለአስር ወር የቆየ ውይይትም ነበር። ይህ ውይይት ምንድን ነው ቢባል ሰዎች እንዴት እርስ በእርስ ተቻችለው በዚህች አገር አብረው መኖር ይችላሉ በሚለው ላይ ያጠነጠነ ነው። በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች የቆሙለትን ህዝብ እንዴት ማገልገል እንዳለባቸውና አንዱ በሌላኛው ላይ ከመዝመት ይልቅ እርስ በእርስ በመከባበር ህዝቡን ማገልገል ቢችሉ ትርፋማ መሆን ይቻላል ከሚል ሐሳብ ነው፣ ይህ አይነቱ አተያይ ደግሞ በፊትም ነበረን።

ሰው ታሪክን በተረዳው ልክ ይናገራል። ከዚህም የተነሳ ሲፈጠር የነበረ ችግር እየሰፋ መምጣቱ ይታወቃል። ስለዚህ ችግሩ ይበልጥ እንዳይሰፋ መቋጨት ስለሚያስፈልግ መነጋገር ግድ ሆኖ ልንሰባሰብ ችለናል። ለዚህ የተቋቋመው ኮሚቴ ሁሉንም ሊያግባቡ የሚችል አስር ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ሰነድ አቅርቦ በሱ ላይ ስለ መስማማታችን ፈርመናል።

በኦሮማራ የተጀመረው ምክክር እና ስምምነት አርአያነት ያለው ጅማሬ እንደመሆኑ ወደ ሌሎችም ብሄር ብሄረሰቦች ቢሰፋ መልካም ነው። የአገሪቱን ሰላም ለማስፈንም ያግዛል።

በፊትም ቢሆን ኦነግ ይቃወም የነበረው የአገዛዝ ስርዓቱን ነው። የቀድሞውኑ የደርግ እና የወያኔ ስርዓቶች መለወጥ አለባቸው በማለት ከስርዓቶቹ ጋር ሲታገል ቆየ እንጂ ከህዝቡ ጋር ምንም ችግር የለበትም። እንደ ኦነግ አማራ እንዲህ መሆን አለበት፣ትግሬም እንዲያ መሆን አለበት ማለት አይፈለግም። ግንባሩ፣ መለወጥ አለበት ብሎ ሲሞግት የነበረው ስርዓቱን ነው እንጂ የአንድን ብሄር ህዝብ አይደለም። ስርዓቱ ግን ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይገባል የሚል ጽኑ እምነት ስላለው ነው ሲታገል የነበረው። ሁሉንም የአገሪቱን ብሄረሰብ እኩል ሊያይ የተገባ ስርዓት ያስፈልጋል።

ኦነግ ያለው አመለካከት አገሪቱ የምትመራበት ስርዓት ለአገሪቱም ለብሄረሰቦቿም ይጠቅም ዘንድ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት የሚል ነው። ትናንትም ሆነ ዛሬም ኦነግ ሲል የነበረው ሁሉንም የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚያይ ስርዓት ይኑር ነው።

በአንድ አገር ውስጥ ስንኖር ሁሉም እኩል ሊሆንና ሊከበር ይገባል፤ በአንድ አገር ውስጥ የአንድ ብሄር የበላይነት ኖሮ ሌላው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሊቆጠር አይገባውም ። ኦነግ የሚፈልገውና ተመስርቶ ሊያይ የሚያልመው እንደዚህች አይነት አገርን ነው።

በአንድ አገር ውስጥ የዜጎች መብት ጥሰት ሊኖር አይገባም። የቋንቋ፣ የባህል፣ የሀብትና ሌላው ሁሉ መብት ሳይጣስና እኔ ነኝ የአንተ የበላይ ሳይባል አንድነት፣ እኩልነት በመግባባት ላይ ተመስርቶ ማየትን ነው ኦነግ የሚፈልገው።

ኦነግ፤ አማራን፣ ትግሬን፣ ሱማሌን ወይም ሌላውን ብሄር በክፉ ዓይን የማየት አባዜ የለበትም፤ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲህ የሚል ነገርም የለም። ግንባሩ እንደሱ ዓይነት ነገር ቢኖረው ኖሮ እስካሁን ድረስ ባልቆየ ነበር።

ኦነግ በኢትዮጵያ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚያከብርና እኩል የሚያይ ስርዓት በዚህች አገር ተመስርቶ ማየት ነው የሚፈለገው። እንደ እሱ አይነት ስርዓት ሲመሰረት ደግሞ ችግር ይወገዳል። ይህ ሲሆን አማራውም ሆነ ኦሮሞው ወይም ሌላው ብሄር በራሱ በመኩራት ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ይችላል። አንዱ የሌላውን መብት የሚያከብር ከሆነ ማለት የቋንቋ፣ የባህል ብሎም የታሪክ መብት የሚከበር ከሆነ አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋጭበት ምክንያት አይኖረውም። በዚህም አንድነት፣ እኩልነትም ሆነ የየራስ ፍላጎት ወሳኝ ናቸው፤ እዚህ ላይ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል። ይህ ነው የሚፈለገው እንጂ አማራውን፣ ወይም ትግሬውን ወይም ደግሞ ሌላ ብሄረሰብን ለማጥፋት አይደለም ኦነግ የሚሰራው። በፖለቲካ መርሐግብሩ እንዲህ የሚል አሰራርም ከቶውንም የለም።

ህዝብን በእኩል የሚያይ ስርዓት ሲገነባ ወላይታውም ሆነ ሱማሌው፣ ከምባታውም ሆነ ሌላው ብሄር ብሄረሰብ በኢትዮጵያዊነቱ ያለምንም ችግር መኖር ይችላል። የትኛውም ብሄር ሳይሸማቀቅ ራሱን ቀና አድርጎ ስለሚንቀሳቀስም እንደ ሁለተኛ አገር ዜጋ ራሱን አይቆጥርም። በኢትዮጵያነቱም ስለሚኮራ አገሪቱን መውደድና የእኔ ናት የሚል ስሜት ያዳብራል። ስለዚህም የየትኛውም ብሄር ተወላጅ ብሆን አንገቴን መድፋት የለብኝም። ራሴንም እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቁጠር አይጠበቅብኝም።

ይህ መብቱ ሲጓደል ግን ችግር ነው። አገርንም መውደድ አይቻልም። ኢትዮጵያ ሲባልም ምንም ስሜት ሊሰጠን አይችልም። ምክንያቱም ለእኔ የሚሆን ነገር የለምና ነው። ስለዚህ የትኛውም ብሄረሰብ ከኢትዮጵያ ስሟ ብቻ ሊተርፈው አይገባም። ሁሉም እኩል ክብር ሊኖረው ያስፈልጋል። ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰባስበው ሊነጋገሩ ፣ ሊግባቡ በሚያስችላቸው ነገሮች ላይ ሊመክሩ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ በዚህች አገር ኦሮሞና አማራ ብዙ ቁጥር ስላላቸው አገሪቱን ለማሳደግ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው ፤ ይህን የሁለቱን አይነት ግንኙነት ለማስፋት ምን አይነት አጀንዳ አለ?

አቶ አራርሶ፡- መስፋት ይጠበቅበታል። ይህ ጅምር እንቅስቃሴ ነው። በአማራና ኦሮሞ ብቻ የሚቆም አይደለም። ምንም እንኳ እነሱ ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ቢሆንም ሁለቱ ብሄሮች ብቻ አገሪቱን ማቆም አይችሉም፤ የሁለቱ ብሄሮች ጅምር ወደ ሌሎችም ብሄሮች መስፋት አለበት።

አገሪቱ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ናትና ሁሉም እኩል ድርሻ አላቸው፤ነገር ግን በኦሮሞና አማራ የመጀመሩ ምክንያት ሁለቱን ብሄሮች እርስበእርስ ለማጋጨት አንዳንዶች የየራሳቸው አጀንዳ እንዳላቸው ይታወቃል፤ ይህ አጀንዳቸው እንዳይሳካ በመታሰቡም ጭምር ነው። በኦሮማራ ተጀመረው የእርስ በእርስ ምክክር ወደ ሌሎቹም ማስፋት ተገቢ ነው። ይህ ከሆነ አገሪቱ የብሄርብሄረሰቦች መገፋፋት ቀርቶ፣ መካፋፈል ሳይኖር ብሄርብሄረሰቦች መብታቸው ተጠብቆና ተከብሮ እንዲኖሩ ያስችላል። አንዱ የሌላውን መብት አክብሮ አብሮ እንዲቀጥልም ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፡– ከምክክራችሁ በኋላ በሚያግባባችሁ ነጥቦች ላይ መፈራረማችሁ ቢታወስም ከአማራም ሆነ ከኦሮሞ በኩል አንዳንዶች እኔ የለሁበትም ሲሉ ተደምጠዋልና እዚህ ላይ ምላሽዎ ምንድን ነው?

አቶ አራርሶ፡ እንዲህ ማለቱ ተገቢ አይመስለኝም፤ ባይሆን ጥሪው አልደረሰኝም ቢሉና ጉዳዩን ቢያከብሩ የተሻለ ነው።

አዲስ ዘመን፡– በተለይ ሰላምን አስመልክተው ለኦሮሞ ህዝብ መልዕክት ካለዎ እድሉን እንስጥዎ ?

አቶ አራርሶ፡ እንደሚታወቀው ኦሮሞ እንደ ኦነግ ከ50 ዓመት በላይ ነው የታገለው። በሰሜኑ፣ በደቡቡ፣ በምስራቁና በምዕራቡ ፈተና አጋጥሞት ቆይቷል። ቤተሰቡ ተበትኗል። ሀብት ንብረቱም ወደሟል። አለኝ የሚለው ሁሉ አመድ ሆኗል። በዚህም የተነሳ በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ነው ያለፈው። በዚህ ጊዜ ከሁሉም በላይ ለኦሮሞ ህዝብ የሚበልጥበት ሰላም ነው። ጦርነት ምንም ትርፍ የለውም። በሰላም ውስጥ ሁሉም ነገር ስለሚገኝ ህዝቡ ሰላሙን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

እንደሚታወቅ በአገሪቱ በህዝብ ብዛት የመጀመሪያውን የሚይዘው ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ ቢሆንም ድህነቱም ያለው እሱ ዘንድ ነው። ከዚህ ድህነት ለመውጣት ግን ደግሞ ትልቅ ጉልበት የሚሆነው የሰላም መኖር ነው። ሰላም የግድ ያስፈልገዋል። በሰላም ውስጥ ሁሉ አለ። ሰላም ከምንም ነገር ይበልጣልና ሁሉን በሰላማዊ መንገድ እናከናውን ብል እወዳለሁ። ያገኘናቸውንም መብቶች በአግባቡ ልትጠቀምባቸው ይገባል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከምንም በላይ ትዕግስት ያስፈልጋልና መታገስ ተገቢ ነው። ደጋግሞም ማሰብ የሚጠይቅ ጊዜ ላይ ነው ያለነው። አንድነትም ያስፈልጋልና በሁሉም አቅጣጫ ያለነው በኃይማኖት፣ በባህል ሳንከፋፈል አንድነታችን ለማጠናከር መጠንከር ያስፈልገናል።

አዲስ ዘመን፡– የኦሮሞ ህዝብ ኦነግን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ሌላው ህዝብ ደግሞ ስሙ ሲነሳ ፍርሃትም ጥርጣሬም ያድርበታልና ኦነግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን እንዴት ነው የሚገልጸው?

አቶ አራርሶ፡ ኦነግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለሁሉም ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚፈልግ ለዚህም የሚሰራ ነው። የኦሮሞ ሆነ የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ግንኙነት በመከባበር ላይ እንዲሆን ኦነግ ይፈልጋል ለዚህም ይሰራል ። አንዱ የሌላውን መብት እንዲያከብር እንዲሁ ።

ኦነግ ኦሮሞንም ሆነ ሌሎች ብሄረሰቦችንም የሚያየው በእኩል አይን ነው። ህዝብ እንደ ህዝብ ደግሞ ሰላማዊ ነው። ትናንት አብሮ ነበር፤ ዛሬም አብሮ ይኖራል። ሁሌም ቢሆን የጊዜው ገዥ ሲቀያየር የማይቀየር ህዝብ ነው። ህዝብ ሁሌም አብሮ ነዋሪ ነው። በመሆኑም ኦነግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተለየ ዓላማ የለውም።

አዲስ ዘመን፡– እንደ ኦነግ ለዚች አገር ምን ታልማላችሁ?

አቶ አራርሶ፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ አገር ናት። የዓለም ፈተና በሆነው በወረርሽኙ ሳቢያ ደግሞ ወጣቱ ስራ በማጣት ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ እስካሁን በፖለቲካው በኩል የተገኙ መብቶችን በማጠናከር ወደ እሱ መቅረቡ መልካም ነው።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0