“Our true nationality is mankind.”H.G.

በመተከል በንጹሃን ግድያ አስተባባሪነት የተጠረተሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፤ የ”ኢንቨስተሮች” እጅ አለበት

በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ግድያ የተጠረጠሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይፋ ሆነ። በክልሉ “ኢንቨስተር” ወታቶችን በመልመልና በማደራጀት እጃቸው እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሲያስታውቁ ህወሃትን በስም ጠቅሰው ከሴራው ጀረባ እንዳለችበት ደርሰንበታል ብለዋል። ሕዝቡ በሚሊሻ ተደራጅቶ ራሱን  እንዲከላከል ትወሰኗል።
የመንግስት ሚዲያዎች የአማራና የቢኒሻንጉል መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ጠንካራ የተባለ ግምገማ ካደረጉ በሁዋላ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማኮላሸት የሚያስችል ውሳኔ መወሰኑን ተስምቷል። ሚዲያዎቹ ይፋ ባያደርጉትም ሰፊ ቁጥር ያላቸው የአማራና የአገው ተወላጆች ለዘመናት በኖሩበት ክልል ውስጥ እንደብዛታቸው በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው አቅጣጫ መቀመጡን የዛጎል መረጃዎች አመልክተዋል።
በዚሁ አቅጣጫ መሰረት መተከልና አካባቢው ላይ ህዝብ ራሱን የሚያስተዳድርበት አግባብ እንደሚመቻችና ከራሱ የተውጣጣ የጥበቃ ሃይል የማደራጀት ስራ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ይህንንም ሁለቱ ክልሎች ከፌደራል የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን እንዲያደራጁ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ፋና በከፊል ይህንን ዘግቧል።
የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡በመግለጫቸውም በተደጋጋሚ በክልሉ መተከል ዞን በንፁሃን ላይ የሚፈፀመው ጥቃት መንስኤው ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመሬት ይዞታ እና ለውጡን ተከትለው ያኮረፉ አካላት የሚፈጥሩት የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ከንፁሃኑ ግድያ በስተጀርባም የህወሀት እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
ይህን ድርጊት ለማስፈፀም ወጣቶችን በመመልመልና አንዳንድ በኢንቨስትመንት የገቡ ባለሀብቶችን በመጠቀም ችግሮቹ እንዲባባስ ህወሃት ስራ ስትሰራ ከርማለችም ነው ያሉት፡፡
የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በክልሉ ተዋቅሮ ያለውን የኮማንድ ፖስት አፈፃፀም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመሆን መገምገማቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የመከላከያ ኃይሉ በአካባቢው የመሸጉ ታጣቂ ቡድኖችንና ሽፍታዎችን የመደምሰስ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅር ጋር የጣምራ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ነዋሪነታቸው በቤኒሻንጉል ክልል በመሆኑ የክልሉ መንግስት ደህንነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለበት አንስተዋል፡፡
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ የፖለቲካም፣ የሕግም እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በሚሊሻ በማደራጀት ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እንደሚደረግ በመጥቀስም በክልሉ ለሚፈጸም ጥቃት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጠያቂ መደረጋቸውን አውስተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከአማራ ክልል ጋር በመሆን ጠንካራ ሥራ እንዲሠራ እና ያጋጠሙትን ችግሮች ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ አቅጣጫ መሰጠቱም በመግለጫው ላይ ተነስቷል።
በሃይለሚካኤል ዴቢሳ
ፎቶ – በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››
0Shares
0