“አሜሪካ እንዲህ ያለ ቀላል ሰው የመረጠች ጊዜ ተዋርዳለች። አሜሪካ የገነባቻቸው ተቋማትና ዓለም ላይ የነበራት ክብር ወድሟል። አሜሪካ ተሰሚነቷ ላሽቋል። በጥቅሉ ትራምፕን የመረጡ ሁሉ የጃቸውን አግኝተዋል። ተዋርደዋል” በማለት ነው ኦባንግ ሜቶ አስተያየታቸውን የሚጀመሩት።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ በተለይ ለዛጎል እንዳሉት ትራምፕ ኢትዮጵያ ላይ ያወጀውን የጦርነት አዋጅ ሲሰሙ አልገረማቸውም። ምክንያቱም ከእንዲህ ያለ ሰው የሚጠበቅ መልካም ነገር የለም።

ኦባንግ “ ከዝንብ ማር አይጠበቅም። ዝንብ ቆሻሻ ናት። የመታመርተውና የምትውለው ቆሻሻ ላይ ነው” ሲሉ የትራምፕን ፖለቲካ “ የዝንብ ፖለቲካ” ይሉታል። ይህን ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ “ ሰውየው መሪ ከሆነበት እለት አንስቶ አሜሪካን እያገደለ፤ ታክስ እያጭበረበረ፣ ታላላቆች የገነቡትን ተቋማት እያወደመ፣ የሰው ልጆችን መብት እየጣሰ፣ ተንቆ አገሩን እያስናቀ ያለ ሰው ነው”

ትራምፕ ግብጽ ትልልቅ ግድቦች እንዳላት ያውቃል ብለው እንደማይገምቱ ያስታወቁት አቶ ኦባንግ ይህ ታሪክና ህግ የማይረዳ ሰው አባይ በቦንብ ቢመታ ውሃው ወዴት እንደሚፈስ መረዳት እንኳን ያቃተው የትልቅ አገር ትንሽ መሪ መሆኑንን አመልክተዋል።

“ግን” አሉ ኦባንግ “ ግን አንድ ትልቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ተደውሏል” ባይ ናቸው። እንደ አገር ኢትዮጵያ ብሎ ሊያስፈራራን ሞክሯል። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ … ብሎ አልጠራንም። ስለሆነም ከማስመሰል አንድነት ባስቸኳይ በመውጣት በአድዋ መንፈስ በነበረው ቀናነት የተሞላው መንፈስ አንድ መሆን ግድ የሆነበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ገልጸዋል።

ትራምፕም ሆነ ማንም አገር ሊያስፈራራንና ጉልበተኛ ሊሆንብን እንደማይችል ማሳየት የሚቻለው ከልብ በሆነ አንድነት ስንቆም እንደሆነ ያመለከቱት ኦባንግ ግብጽ የጉዳዩ ቁልፍ፣ የውሃው መፍቻ፣ የድርድሩ አስኳል፣ የመፍትሄው ምንጭ ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ማሳወቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንን ማሳመን ከያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል።

“ ግብጽ እብድ አትመስለኝም የህዳሴው ግድብ ላይ ቦንብ ለመጣል አታስብም” ሲሉ የገለጹት ኦባንግ አስዋን ግድብ ከተመታ ካይሮ እንደምትወድም የማያወቀው ትራምፕ ብቻ በመሆኑ ምክሩና ማስፈራሪያው ከንቱ እንደሆነ አመልክተዋል።

Related stories   Ethiopian Prime Minister Arrives in Jeddah

ትራምፕ እጅግ ፈር በለቀቀ ጋጠወጥ አነጋገር ያስተላለፈው መልዕክት ሰሚ እንደሌለው ኦባንግ አስታውቀዋል። ምንም እንኳን ለተባበሩት መንግስታት፣ ለጋር አገሮች፣ ለዓለም ማህበረሰብ ይህንን እብሪት የተሞላው ማስፈራሪያ ማሳወቅ አስፈላጊ ቢሆንም ትራምፕ ውሸታም፣ የሚያምታታና ለራሱ ጭምር ክብር የሌለው ሰው መሆኑንን ስለሚረዱ ብዙም አዲስ ነገር እንደማያመጣ ገልጸዋል።

“ ትራምፕ የራሱ መሪ ነው” የሚሉት ኦባንግ እንዲህ ያለ መረን የወጣ መሪ ይህን አለ ብሎ መደነቅና ትርጉም ሰጥቶ መወዛገብ የሰውየውን ባህሪ አለመረዳት መሆኑንን አመልክተዋል። ወደ ስልጣን ከመጣበት ቀን ጀምሮ እንዲህ ያለውን የወረደ፣ የሰው ልጆችን መብትና ክብር የሚገፍ ሰው ዓለም ሁሉ ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ግድቡን ለመጨረስና በፍትሃዊነት ለመጠቀም ቅድሚያ መስጠቱ የዜግነት ግዴታ መሆኑንን ተናግረዋል።

“የጥሪውን ደወል ለበጎ በመጠቀም ከአስመሳይ አንድነት ወደ ቀናነት የተላበሰ ህብረት ተሸጋገረን ክንዳችንን ልናሳይ ይገባል” ሲሉ ኦባንግ አጽንዖት ሰጥተው ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያዊያን ብሩ ይቀራል እንጂ ማንም ክብራቸውን ሊነካ፣ ሊያስፈራራቸውና በጉልበት ከጀመሩት ተግባር ሊያቆማቸው የሚችል ሃይል እንደሌለ ማሳየት እንደሚገባቸውም አክለው ገልጸዋል።

2 Comments

  1. እግዚአብሔር ይስጥህ ኦባንግ : በትክክል ገልጸኸዋል:ትልቁ ችግር አንድ በሽተኛ የተናገረው ምንም አያመጣም ብሎ ማቅለል ሳይሆን ለግብፆች ማደፋፈሪያ ከመሆኑም ሌላ ምን ዓይነት መሣርያ ሲያስታጥቃችው እንደቆየ ማወቅና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ከማድረግ መዘናጋት እንደሌለብን ከወዲሁ ሊታሰበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል እላለሁ::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *