“Our true nationality is mankind.”H.G.

ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀ ፣ “ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች ” መንግስት “ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም”

” ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለም” ይላል የመንግስት መግለጫ። በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን በችግሯ ያልተለዩዋት ወዳጆች የመኖራቸውን ያህል የከዷትም ነበሩ። ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያዊያን ነክቶ የተሳካለት የለምና አንድ እንሁን ሲል ለዜጎች ጥሪውን አቅርቧል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው። የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን፣ አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል። አይቀሬ ነው። የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው። ለእኛ ያለነው እኛ መሆናችንን ዐውቀን ስለ እኛ ጉዳይ እኛው ራሳችን ኢትዮጵያን አለንሽ እንበላት። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም። ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው እንደሆነ መግለጫው አውስቶ ህብረት እንደሚያሻ ጠቁሟል።
ትራምፕ እጅግ በወረደ አግባብ ኢትዮጵያ ላይ ላወጀው ጦርነት የተሰጠው የመንግስት ምላሽና ሃይሌ ሙሉ ሙሉ በሙሉ እንደወረደ ተርጉሞ ያቀረበውን ዘገባ ከታች ያንብቡ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫ 
ኢትዮጵያ በፍጣሪዋ ታምና በሕዝቧ አንድነትና ጽናት የቆመች ሀገር ናት። ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዟት በሚሞክሩ ተማምና አታውቅም። ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ። ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ነው። የገነቧት ደግሞ ልጆቿ ናቸው። እነዚህ ልጆቿ በከፈሉት መሥዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን ሠርታለች። እነዚህን አስደናቂ ታሪኮችን ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት። የከዷት ወዳጆችም ነበሩ። ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም።
ነገር ግን የዓለም ታሪክ ያረጋገጣቸው ሁለት ሐቆች አሉ። ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም የሚለው ቀዳሚው ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው። የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን፣ አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል። አይቀሬ ነው።
የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው። ለእኛ ያለነው እኛ መሆናችንን ዐውቀን ስለ እኛ ጉዳይ እኛው ራሳችን ኢትዮጵያን አለንሽ እንበላት። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም። ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው።
ማንም ገዝቶን አያውቅም። ወደፊትም ማንም አይገዛንም። ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም። ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም።
ክንዳችንን እናበርታ። ትከሻችንን እናስፋ። ልባችንንም እናጽና። ከውጭና ከውስጥ የተሠነዘረብንን ጥቃት ድል አድርገን መሻገር ብርቃችን እንዳልሆነ እናስመስክር።
በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ እንቀርም። ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም። አንድ ሆነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ ነው። ዛሬም ያንን ጋሻ በአንድነት እናንሣ። ሁላችንም፣ በየቦታችን፣ 24 ሰዓት፣ ለኢትዮጵያ እንቁም።

ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ያወጀው ጦርነት እንደወረደ
(በኃይሌ ሙሉ –Haile Mulu )
ለራሱ ሰላም የራቀው እብዱ የአሜሪካው መሪ ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በእስራኤልና ሱዳን የተከናወነውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ጋዜጠኞች በተገኙበት ከሁለቱ አገራት መሪዎች ጋር በስልክ ውይይት ባደረገበት ወቅት ከአንድ አገር መሪ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ መልኩ “ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች” በማለት በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት አዋጅ አውጇል።
ማህበራዊ ሚዲያውን ዞር ዞር ብየ ስመለከት “ግብፅ የአባይን ግድብ ታፈነዳዋለች” ከሚል አጭር ዜና ውጭ ዝርዝር ዘገባ አለመቅረቡን ስለተገነዘብኩ ትራምፕ በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ከሱዳኑ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ያደረጉትን በቅሌት የታጀበ ውይይት እንደሚከተለው ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ።
የትራምፕ እንግሊዝኛ አራምባና ቆቦ የሚረግጥ ቢሆንም context( አውድ) ጠብቄ ለማቅረብ ሞክሪያለሁ። አንዳንዱን ንግግር ቃል በቃል ብትረጉመው ምንድነው የሚዘባርቀው ማለታችሁ አይቀርም ነበር። (ትራምፕ ሁለቱን መሪዎች በስልክ ያናገራቸው ለጋዜጠኞች እንዲሰማ የስልኩን ስፒከር ከፍቶ ነበር።)
ትራምፕ – (ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ) “ከመሄደዎት በፊት እዚሁ ስልኩ ላይ እያሉ ከበርካታ አመታት በኋላ የተገነባው እጅግ ትልቁ የኢትዬጵያ ግድብ ያለበት ሁኔታ እንዴት ነው? እንዳለመታደል ሆኖ ግድቡ ወደ ናይል የሚፈሰውን ውሃ ያቆማል። ይሄም ግብፅን ችግር ላይ የሚጥል ነው። አይደል? ቢቢ (የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቁልምጥ ስም ነው) ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባች መሆኑን አንተም ታውቃለህ ብየ አስባለሁ። ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ከግብፅና ከኢትዮጵያ ጋር በተደረጉ ድርድሮች ስትሳተፍ እንደመቆየቷ መጠን በዚህ ጉዳይ ላይ እኛም ከሱዳን ጋር ስንነጋገር ነበር።
ታዲያ አሁን ያለው ሁኔታ እንዴት ነው ? አገራቱ ስምምነት ላይ ለመድረስ ምን እየሰሩ ነው? ምክንያቱም እኔ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አድርጌ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ስምምነቱን ጣሰች ። ያን ማድረግ አልነበረባትም። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በዚህም ምክንያት ለኢትዮጵያ እንሰጠው የነበረውን በጣም ብዙ የገንዘብ እርዳታ አቁመናል። ምክንያቱ ደግሞ ስምምነቱን ስለጣሱ ነው። አሁንም ኢትዮጵያ ለስምምነቱ ተገዥ ካልሆነች በስተቀር ይህንን እርዳታ አያገኙትም። የናይልን የውሃ ፍሰት የሚያቆም ግድብ ገንብተዋል። በዚህ የኢትዮጵያ ድርጊት ግብፅ ብትበሳጭ አንፈርድባትም። አይደል? እና አሁን ያለው ሁኔታ እንዴት ነው?” ሲል ተራ ጥያቄ አቀረበ።
ጥያቄው ለእርሳቸው የቀረበ የመሰላቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትኒያሁም ፈጠን ብለው “ችግሩን ለመፍታት ትልቅ ተስፋ አለ ብየ አስባለሁ” ብለው ሲመልሱ ትራምፕ ጣልቃ ገባና “እኔ እንኳን ጥያቄውን ያነሳሁት ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ነው። እና እንዴት እያረጋችሁ ነው?” ብሎ በድጋሜ ጥያቄውን ለአብደላ ሃምዶክ አቀረበ።
ጠቅላይ ሚንስትር ሃምዶክም ጥያቄውን ለመመለስ ” አዎ እእእ…” ብለው ሲጀምሩ ትራምፕ ንግግራቸውን አቋርጦ ፊት ለፊት ወደቆሙት ጋዜጠኞች እየተመለከተ ” ይሄንን ጥያቄየን መመለስ ላይፈልግ ይችላል ..” አለና የስልኩን ድምፅ ጨምሮ ምላሻቸውን ማዳመጥ ጀመረ።
በእውነቱ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር እንግሊዝኛ ባቢሎን በሳሎን ነው ማለት ይቻላል። ምን ለማለት እንደፈለጉ የሚያውቁት ራሳቸው ብቻ ናቸው። ከእሱ ብሶ ትራምፕም በእንግሊዝኛቸው ፈገግ እያለ ሙድ ሲይዝባቸው ነበር። ያም ሆኖ በግድቡ ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን ድርድር በተመለከተ እንዲህ ብለዋል።
” እርሰዎ( ትራምፕን) በድርድር ሂደቱ ላደረጉት ነገር ከፍተኛ አድናቆት አለን። ለሶስቱ አገራት ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ስምምነት ላይ እንደርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”
ከዚያም ትራምፕ ቀጠለ። “ያው እንደሚታወቀው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አድርጌ ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያ ስምምነቱን ጣሰች። ያንን ማድረግ አትችልም። ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። አሁን ያለው ሁኔታ ግን አደገኛ ነው። ምክንያቱም ግብፅ በዚህ መልኩ የኢትዮጵያን አካሄድ ተቀብላ ልትቀጥል አትችልም ። የመጨረሻዋ እርምጃ ግድቡን ማፈንዳት ነው። አሁንም ሁሉም ሊሰማውና ሊረዳው በሚችለው መልኩ ግልፅ አድርጌ እናገራለሁ። ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች። ስለሆነም አንድ ነገር ማድረግ አለባችሁ።
በእርስዎ በኩል ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባትን እንድታደርግ ጥረት ያድርጉ። እኛ ለኢትዮጵያ ስንሰጠው የነበረውን የገንዘብ እርዳታና ሌሎች ነገሮችን አቁመናል። ኢትዮጵያ የፈፀመችው ድርጊት ቀፋፊ ነው። ስምምነቱን ለመፈረም ሁሉንም ነገር አጠናቀን ነበር። ለአምስት አመታት ሲደራደሩ ነበር የቆዩት። ድርድሩ ከዚያም በላይ ጊዜ የወሰደባቸው ይመስለኛል። ነገር ግን ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ነበር። እኔ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አደረግኩ።
ይህንን ስምምነት ለመፈረም ከተዘጋጁ በኋላ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ጥሳ ወጣች። ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም። ጠቅላይ ሚንስትር ሀምዶክ በእርስዎ በኩል የሚችሉትን ያድርጉ ። ጉዳዩ በስምምነት እንዲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ቢመክሩ መልካም ነው። በነገራችን ላይ እኔም ለግብፅ የምናገረው ይሄንኑ ነው።
ግብፆች ግድቡ ከመገንባቱ በፊት ሊያስቆሙት ይገባ ነበር። ‘ግድቡ ሲገነባ ዝም ብላችሁ ስትመለከቱ ቆይታችሁ መጨረሻ ላይ “ኢትዮጵያ ግድብ ገነባች” እንዴት ልትሉ ትችላላችሁ? የሚል ጥያቄ አንስቸ ነበር። በእርግጥ የግድቡ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት ግብፆች በሌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ተጠምደው ነበር። በዚያን ወቅት ግብፅ ውስጥ ሥር ነቀል ያልሆነ አብዮት እየተካሄደ ነበር። ያ ጊዜ ለግብፅ ጥሩ አልነበረም። የሚያሳስባቸው ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ነበረባቸው። እናም እርሰዎ የበኩለዎትን ይጣሩ። በጣም አመሰግናለሁ” በማለት አደራዳሪ ነኝ ብሎ የቀረበው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለግብፅ ወገንተኛነቱን ከማረጋገጡ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ጦርነት አውጇል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን አይን ያወጣ ጣልቃ ገብነትና የእብደት ተግባር አውግዞ መግለጫ ማውጣት አለበት። አሜሪካ የምንኖር ኢትዮጵያውያኖችም ” ኢትዮያውያኖች ለባይደን (Ethiopians for Biden)” የሚል ዘመቻ ከፍተን ኢትዮጽያውያኖች በሙሉ ባይደንን እንዲመርጡ በመቀስቀስ ይሄንን እብድ ሰውየ ከዋይት ሀውስ ቤተመንግስት ማስወገድ አለብን። የእምነት ተቋማትም ምዕመናኖቻቸው በምርጫው እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   እስራኤል አልጃዚራ ቴሊቪዥን፣ አሶሲየትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች የሚጠቀሙበትን ህንጻ አወደመች
0Shares
0