ግሪጎሪ፤ የሩሲያን ምስጢር ለዓለም ዘርግፎ በመስጠቱ ነው ከፑቲን ዓይን ተሰውሮ እንዲኖር የተገደደው።
ስለዶክተር ግሪጎሪ ሮድቼንኮቭ አድራሻ የሚያውቁት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። ጠበቃው ጂም ዋልደን እንኳ ግሪጎሪ የት እንደሚኖር አያውቅም። የሩሲያ ሰላዮች ግን ፍለጋቸውን አላቆሙም።

በአውሮፓውያኑ 2018፤ ሰርጌ ስክሪፓል የተሰኘው የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ ሳሊስበሪ [እንግሊዝ] ውስጥ መመረዙን ተከትሎ አሜሪካ 60 የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከአገሯ ታባርራለች። ይሄኔ ነው ጠበቃ ዋልደን ደንበኛው ዶ/ር ግሪጎሪ በሩሲያ ሰላዮች እየተፈለገ መሆኑን የተረዳው።
“ኤፍቢአይ [የአሜሪካ የአገር ውስጥ ወንጀል ምርመራ ቢሮ] ከተባረሩት ዲፕሎማቶች መካከል ሦስቱ ግሪጎሪ ለማሳደድ የተላኩ መሆናቸውን ነገረን። ይሄኔ ነው ደንበኛዬ አደጋ ላይ እንዳለ ያወቅሁት” ይላሉ ጠበቃው።
ግሪጎሪ የቀድሞው የሞስኮ መድኃኒት ምርመራ ኃላፊ ነበር። ሰውዬው ሩሲያውያን አትሌቶች በ2012ቱ የለንደን ኦሊምፒክና ከሁለት ዓመት በኋላ በተካሄደው የሶቺ የክረምት ጨዋታዎች ወርቅ ጠራርገው እንዲወስዱ ያደረገ ‘ሊቅ’ ነው።
ነገር ግን የፀረ-አበረታች መድኃኒት ተቆጣጣሪው ዋዳ የሩሲያ አትሌቶች አበረታች መድኃኒት እንደተጠቀሙ መረጃው አለኝ ብሎ ምርመራ ሲጀምር ግሪጎሪ ወደ አሜሪካ እግሬ አውጭኝ አለ።

ኢካረስ የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ለኦስካር ሽልማት መታጨት የቻለ የጥበብ ሥራ ነው። ፊልሙ ግሪጎሪ እንዴት አድርጎ ወደ አሜሪካ እንደሸሸ ያሳያል። ግሪጎሪ ሞስኮን ከድቶ አሜሪካ በመግባት ብቻ አላበቃም። ስለ አበረታች መድኃኒቱ የሚያውቀውን ምስጢር ሁላ ለዋዳ አሳልፎ ሰጠ።
አንዳንድ ሩሲያውያን ግሪጎሪ ከሃዲ ነው ይሉታል። ፕሬዝደንት ፑቲን “በአሜሪካ ሰላዮች ቁጥጥር ሥር ያለ፤ ብዙ ችግሮች ያሉበት ደደብ ሰው” ሲሉ ገልፀውት ነበር። ዋዳ ደግሞ ሰውዬው ወንጀል በማጋለጡ ሊመሰገን ይገባዋል ይላል።
- “ሥልጣን ለደም ግፊት አጋልጦኛል” ኃይሌ ገብረሥላሴ
- ሩሲያ ለአራት ዓመታት በስፖርት ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ ታገደችሩሲያ ከሁሉም ስፖርታዊ ውድድሮች ልትታገድ ትችላለች
- የሞ ፋራህ የቀድሞ አሠልጣኝ ከአትሌቲክስ ታገዱ
ግሪጎሪና የሩሲያ አበረታች መድኃኒት መሥሪያ ቤት የተቀያየሙት 2011 ላይ ነበር። ሰውዬውና እህቱ መድኃኒት በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር ተወንጅለው ለእሥር ተዳረጉ። ወንጀለኛ ነኝ ብሎ እንዲያምን የተገደደው ግሪጎሪ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አደረገ።
ጠበቃው እንደሚሉት፤ ግሪጎሪ ራሱን ለማጥፋት መሞከሩን ተከትሎ ወደ ተለያዩ የአእምሮ ጤና ሕክምና ተቋሟት ተልኮ ነበር፤ ነገር ግን ሕይወቱን ያዳነው ከለንደን የመጣለት ግብዣ ነው።
2012 ላይ እንግሊዝ ተገኝቶ ከአንድ የለንደን መርማሪ ጋር የፀረ-አበረታች መድኃኒት ምርመራ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበለት። ደብዳቤው ቀጥታ ለእሱ የተላከ በመሆኑ ከእሥር ተፈቶ ወንጀሉም ተፍቆለት ወደ ለንደን እንዲያቀና ሆነ።
ግሪጎሪ፤ ሩሲያውያን አትሌቶች ወጣም ወረደ እንደሚጋለጡ ያውቅ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ አትሌቶች አበረታች መድኃኒት ተጠቅመው እንደሆን የሚለው አዲስ ዓይነት መመርመሪያ ዘዴ ጥቅም ላይ ሊውል ዝግጅት ላይ ነበር።
ይህ አዲስ የምርመራ መንገድ አትሌቶች አበረታች መድኃኒት ከረዥም ጊዜ በፊት ተጠቅመው ቢሆን እንኳ መለየት የሚያስችል ነው።

ሳይንቲስቱ ሩሲያውያን አትሌቶች የሚወስዱት አበረታች መድኃኒት ከረዥም ጊዜ በኋላ ቢሆን እንኳ ሰውነታቸው ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ያውቅ ነበር። እንዲያውም ይህን በተመለከተ አንድ ጥናት አሳትሞ ነበር። ታድያ ይሄን እያወቁ ለምን አትሌቶቹ መድኃኒቱን ሲወስዱ በዝምታ መመልከት መረጠ? እስከዛሬ ምስጢር እንደሆነ ነው።
በ2012ቱ ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ተሳትፈው አበረታች መድኃኒት ተጠቅማችኋል ተብለው ውጤታቸው ከተሰረዘ 140 አትሌቶች መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ሩሲያውያን ነበሩ።
ግሪጎሪ 2012 ላይ አዲስ መድኃኒት ፈብርኮ ነበር፤ ‘ደቼስ ኮክቴል’ የተሰኘ። መድኃኒቱ የእርሻ እንስሳት የሚወስዱት ዓይነት ነው። የሦስት ቅመሞች ቅይጥ የሆነው ይህ መድኃኒት በምርመራ ወቅት ሊገኝ የሚችል አልነበረም።
በ2014ቱ የሶቺ የክረምት ጨዋታ ላይ ሩሲያውይን ይህን መድኃኒት በአልኮል መጠጥ ወስደውታል። በአልኮል መጠጥ መደባለቅ ያስፈለገው ደግሞ መድኃኒቱ ሥራውን ወዲያኑ እንዲጀምር ነው።
መድኃኒቱ የሚዋጥ አይደለም፤ የሚጉመጠመጥ እንጂ። አትሌቶቹ መድኃኒቱን ከአልኮል መጠጥ ጋር ደባልቀው ከተጉመጠመጡት በኋላ ይተፉታል። ዋናው ጠቃሚ መድኃኒት ከጉንጭ ሴሎች ጋር ተያይዞ ወደ ውስጥ ይገባል።
ኢካረስ በተሰኘው ፊልም ላይ እንደተመለከተው መድኃኒቱ የሩስያ አትሌቶች ሽንት ወደ ዋዳ ቤተ-ሙከራ ከመግባቱ በፊት በንፁህ ሽንት ይቀየራል። ይህን ሥራ ይሠሩ የነበሩት የሩሲያ ደኅንነት ሰዎች ነበሩ።
ሩሲያውያን በ2014ቱ የሶቺ የክረምት ኦሊምፒክ 33 የወርቅ ሜዳሊያዎች አፈሱ። ፑቲንም ፈገግ አሉ። ከሦስት ዓመታት በፊት ለእሥር ተዳርጎ የነበረው ግሪጎሪ ሮድቼንኮቭም በሩሲያ መንግሥት ተሸለመ።
ነገር ግን ይህ የሩሲያ ድል ፈንጠዝያ ብዙም አልቆየ። አንድ የጀመርን ቴሌቪዥን ጣብያ የሠራው ዘጋቢ ፊልም ዋዳ በሩሲያ አትሌቶች ላይ ሰፊ ዘመቻ እንዲከፍት አደረገው። በቀጣዩ ዓመት ሩሲያ አበረታች መድኃኒት ለአትሌቶቿ በማቃም ኦፊሴላዊ ክስ ተከፈተባት።
የዋዳ ዘገባ በወጣ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሮድቼንኮቭ ከአንድ ጓደኛው በሩሲያ መንግሥት እየተፈለገ እንደሆነ የሚጠቁም መረጃ ደረሰው። ይሄኔ ነው ግሪጎሪ ሻንጣውን ሸክፎ ሚስቱንና ልጁን የስንብት ስሞ ወደ አሜሪካ የሸሸው።
ከዚያ በኋላ ሳይንቲስቱ ሙሉ መረጃ ለመርማሪዎች አሳልፎ መስጠት ጀመረ። መርማሪዎች ከእሱ ባገኙት መረጃ መሠረት የሩስያ መንግሥትን ከሰሱ።
በዚህም ሳቢያ የሩሲያ የትራክ እና ፊልድ አትሌቶቹ እንዲሁም ክብደት አንሺዎችም በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ እንዳይሳተፉ ታገዱ።
ግሪጎሪ ሩሲያ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ መጨረሻው ላያምር ይችል እንደነበር ጠበቃው ይናገራል። ግሪጎሪ ሞስኮን ጥሎ ወደ አሜሪካ በሸሸ በቀናት ልዩነት ውስጥ የሩስያ ፀረ-አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ ሁለት አመራሮች ሞተው ተገኙ።
ሩሲያ፤ ከ2019 ጀምሮ ቀጣዩ የኦሊምፒክ ውድድር ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለአራት ዓመታት የታገደችው በግሪጎሪ ምክንያት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ራሱን ሰፊ ክፈፍ ባለው ባሕር ዳርቻዎች አካባቢ በሚዘወተር ባርኔጣ ሸፍኖ ከአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ሆኖ ለቢቢሲ ቃለ-ምልልስ የሰጠው ግሪጎሪ እኔም ብሆን አትሌት እያለሁ አበረታች መድኃኒት ወስጄ ነበር ይላል።
በቅርቡ ስለዚሁ ጉዳይ በዝርዝር ጽፎ ያሳተመው መፅሐፉ ‘ዘ ሮድቼንኮቭ አፌር’ ይሰኛል።
ግሪጎሪ ለአንዳንዶች ከሃዲ ነው፤ ለሌሎች ደግሞ ጀግና። ዋዳ ሰውዬውን ጀግና ባንለው እንኳ ደፋር መሆኑን አንክድም ይላል።
ቀሪውን ዘመኑን ከሩሲያ ሰላዮች ተደብቆ መኖር ግን ሊያመልጠው የማይችለው ‘ዕጣ ፈንታው’ ነው።
BBC – Amharic
- ፈረሱላ ቡና – (Cup of Excellence – Ethiopia) ኢትዮጵያዊ ምልክት!ፈረሱላ ወይም ፈረሲላ ሲነሳ ቅድሚያ የሚታወሰን አንድ ጉዳይ ነው። ይህም ጉዳይ አረንጓዴ ወርቃችን ነው። አረንጓዴው ወርቃችን ደግሞ ቡናችን ነው። ይህ የአገራችን ማሕጸን አስቀድሞ የወለደው ቡናContinue Reading
- አትሌት ለተሰንበት ግደይ በቶክዮ ኦሎምፒክ ትሳተፉለች!!“በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት የአትሌቷ ልምምድ ተስተጓጉሎ ይሆን?” የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ቼክ የቀረበለት አልጣኝ ሀይሌ “በነበረው ችግር ምክንያት አርፍደን መጥተናል። እኛ የነበርነው ደቡባዊ ትግራይ አካባቢContinue Reading
- ዝነኛው የቴሌቭዥን መርሀ ግብር መሪ ላሪ ኪንግ አረፈዝነኛው አሜሪካዊ የቴሌቭዥን መርሀ ግብር መሪ ላሪ ኪንግ በ87 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ሎስ አንጀለስ ውስጥ በሚገኝ ካዳርስ-ሲናይ በተባለ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ እንዳለፈ ተገልጿል።Continue Reading
- በኢትዮጵያ ከፍተኛ መረጃ የመሸከም አቅም ያላቸው ማዕከላት ሊገነቡ ነውአዲስ አበባ በሚገኘው አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ከፍተኛ መረጃ የመሸከም አቅም ያላቸው የመረጃ ማዕከላት (ዳታ ሴንተር) ሊገነቡ ነው፡፡ ዊንጉ አፍሪካ በተሰኘ ድርጅት የሚገነቡት እነዚህ የመረጃ ማዕከላትContinue Reading