በከሃዲው የትህነግ ቡድን ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር ሥራ በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ ብቻ መከተል እንደሚገባቸው የአማራ ክልል መንግስት አሳሰበ፡፡ ሚዲያዎች መረጃ እንዲሰጡ ከተመደቡ ክፍሎች ብቻ ማብራሪያም ሆነ ዝርዝር ጉዳይ እንዲጠይቁ ተጠየቀ። ሚስጢር ለጠላት ማስረከብ እንደማይገባ ተገልጿል። የአብመድ ዘገባ ይመለከቱ
በሰሜን እዝ በሚገኘው በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ እና በአማራ ክልል አንዳንድ የድንበር አካባቢዎች ከሰሞኑ ትህነግ የፈጠረችውን ጥቃት ተከትሎ የህዝቡ ስሜት በተለያየ መንገድ ሲገለፅ ተስተውሏል፡፡
ህግ የማስከበሩን ሂደት ለሚያከናውኑት የመከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የደም ልገሳ መርሃ ግብር፣ የቁሳቁስና ምግብ አቅርቦት፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ ህግ ከሚያስከብሩ አባላት ጎን ተሰልፎ ለመታገል እና መሰል የህዝብ ድጋፎች ተስተውለዋል፡፡ “ህዝቡ ላሳያው ድጋፍ የክልሉ መንግስት ምስጋና ከፍ ያለ ነው” ያሉት የአማራ ክልል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ትህነግ ለጦርነቱ ቀድማ በመዘጋጀቷ እና በየአካባቢው ሰርጎ ገብ ማስገባቷ ታዉቆ ህግ በሚከበርበት አካባቢ የሚደረግ አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍል ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“የህዝቡን ብሶት እና ስሜት መንግስት ይረዳል›› ያሉት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ህግ የማስከበሩ ተልዕኮ ግልፅ ዓላማ እና የተቀመጠለት ጊዜ ስላለው የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ ወጣቶች መከተል ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱም ተልዕኮን የማያውክ እና ላልተፈለገ አካል መረጃ የማያቀብል መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የተልዕኮ አፈፃፀምም እና ውሎ በማዕከላዊ መንግስቱ እና በክልሉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ወይም ከርእሰ መሥተዳድሩ ውጭ መረጃ መስጠት የተከለከለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህግ የማስከበሩን እርምጃ የሚመለከት መልዕክት እና መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ መስጠት በጥብቅ የተከለከለ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው የህገ ወጡ ቡድን ሴራና ዕኩይ ተልእኮ ተግባራትን በሚስጥር እንድናራምድ ያስገድዳል ብለዋል፡፡ ወጣቱ የአካባቢውን ፀጥታ በንቃት እየተከታተለ ፀጉረ ልውጥ እና ያልተለመደ እንቅስቃሴ ሲያስተውል የአማራን ህዝብ የስነ ልቦና ከፍታ በሚያመላክት መልኩ ለህግ አካላት በማስረከብ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ህግ የማስከበሩ ሥራ በታቀደለት ጊዜ ይጠናቀቃል፤ አሁን ባለው ሁኔታም የሚያሸብር ምንም ክስተት የለም” ያሉት አቶ ግዛቸው የመንግስት መደበኛ ሥራዎችን በማስቀጠል እና የአርሶ አደሩን ሰብል በመሰብሰብ ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *