ሜ/ጀነራል ገብረመድህን ፈቃዱ ወይም በቅጽል ስሙ ወዲ ነጮ የተባለው ተጠርጣሪ በአገር ክህደት ወንጀል ከነ 17 ግብረ አበሮቹ በመከላከያ ሰራዊታችንና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ዋለ ።
የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው የመገናኛ ሥርዓት እንዲቋረጥ በማድረግ በጁንታው የህዋሃት የጥፋት ቡድን ጥቃት እንዲፈፀምበት ሲያመቻቹ የነበሩ ጀነራል መኮንኖች ከነ ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ፣ በመንግስት፣ በህዝብና በሀገር መከላከያ ሠራዊት የተጣለባቸውን አደራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ፣ የጁንታው ህወሃት ሴራ አካል በመሆን የአገር ክህደት ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ጀነራል መኮንኖች ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ከጁንታው ህወሃት ጋር በመጣመር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ምሽት ላይ በትግራይ ክልል የሚገኘው የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥና ፣ የዕዙ የመገናኛ ሥርዓት ለጁንታው የህዋሃት ወንበዴው ቡድን እንዲመቻች በማድረግ የተጠረጠረው ሜ/ጀ ገብረመድህን ፈቃዱ ወይም በቅጽል ስሙ ወዲ ነጮ የተባለው ተጠርጣሪ ፣ በአገር ክህደት ወንጀል ከነ ግብረ አበሮቹ በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል።
የአገር ክህደትን በመፈጸም በዋነኛነት የተጠረጠረው ሜ/ጀ ገብረመድህን ፍቃዱ ፣ ከለውጡ በፊት በአገር መከላከያ ሠራዊት የአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይሎች አዛዥ የነበረ ሲሆን ፣ በሰራዊት ውስጥም በተለያዩ የሥራ እርከኖች አገልግሏል ።
ለውጡን ተከትሎም በአገር መከላከያ ሰራዊት የመገናኛ ዋና መምሪያ ሃላፊ በመሆን ሲሰራ ነበር ፡፡
ይሁንና ከመንግስት ፣ ከህዝብና ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተጣለበትን ከባድ አደራና ሃላፊነት አገር ለማፍረስና ለማተራመስ ከሚንቀሳቀሰው የጁንታው የህዋሃት የሴራው አካል በመሆን የሰሜን እዝ ከማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥና በከሃዲዎች ጥቃት እንዲፈፀምበት ከማድረጉም በላይ ፣ በውስጣቸው ቦንቦችና የሚሳኤል መሳሪያዎችን የያዙ 11 ሳጥኖች የግንኙነት መሳሪዎች ናቸው በሚል ሽፋን ወደ ትግራይ የጁንታው ቡድን ለመላክ ሲዘጋጅ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመልክቷል ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባደረጉት ጠንካራ ክትትልና ባካሄዱት ኦፕሬሽን ፣ ተጠርጣሪው ሜ/ጀ ገብረ መድህን ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች ጀነራል መኮንኖች ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶቻቸው በድምሩ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ።
በቀጣይም ከጁንታው የህዋሃት የጥፋት ቡድን አገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም ፣ በአገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትንና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)