“Our true nationality is mankind.”H.G.

“የልዩ ኃይሉና የሚሊሻ ተጋድሎ ከዛታ ተራሮች ስር ” ምስክርነት

መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ ወጣ ገባ፣ ያገጠጠ የአለት ቋጥኝ፣ ጠመዝማዛ መንገድ እና የበረታ ፀሃይ አካባቢውን ፈታኝ አድርጎታል፡፡ ጦርነትን ለማያውቅ የእኔ ቢጤ ጦርነት ግብሩ ብቻ ሳይሆን ስሙ ራሱ ያስፈራል፡፡
በታቃራኒው ግን በጦርነት የማይሸበሩ ልዩ ኃይሎችን መመልከት ግርምትን ይፈጥራል፡፡
ሰው እንዴት በጦርነት አለመረበሽን ይለማመዳል? ያልተቆራረጠ የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት፣ አስገራሚ ስነ ምግባር እና ቅድመ ሁኔታ አልባ ትዕዛዝ ተቀባይነት መርህ እስኪመስሉ ድረስ በሁሉም ዘንድ ይስተዋላል፡፡
ማረፍ አያሻቸውም፤ ማፈግፈግን አይወዱም፤ ግፍና ብሶት የወለደው ርምጃ፣ በመከራ የተፈተነ ትዕግስት እና በተፈጥሮ የተቸረ ጀብዷቸውን ለመታዘብ የግድ በወታደራዊ ሳይንስ መራቀቅን አይጠይቅም፡፡
የትዕዛዝ አክባሪነት ልጓም ባይገራቸው ኖሮ ‹‹ግፋ በለውን›› አጥብቀው ይወዱታል-የአባቶቻቸው ልጆች ናቸውና፡፡
እጅ ለሰጧቸው እና በየአካባቢው ለሚያገኙት ሰላማዊ ማኅበረሰብ ሁሉ ያላቸው ክብር የማንነታቸው ውኃ ልክ ነው፡፡ ለማንነታቸው እና ለሃገራቸው ያላቸው ፅኑ ፍቅር ወደር የለውም፡፡
ሃገራቸውን እንደ ሃገር ለማስቀጠል በጦርነት ብዙ ዋጋ ከፍለው ከዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ አሁን በተቃራኒ ከተሰለፈው ኃይል ጋር አንድ ወቅት አብረው ታግለዋል፤ ይተዋወቃሉ፡፡
ያ ያልታደለ የተራራ ሰንሰለት ከሦስት አስርት ዓመታት እፎይታ በኋላ ዳግም የጦር ነጋሪት ተጎስሞበታል፡፡ እንኳን የሰው ልጅ አካባቢው በራሱ ጦርነት እንደመረረው ያሳብቅበታል፡፡ ዳሩ ‹‹በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል›› እንደተባለው የጦርነት ነጋሪት ከጥራሪ ወንዝ ማዶ ያስተጋባ ነበር፡፡
ከፍ ብላ የከተመችው የዛታ ከተማ በተራሮች ሰንሰለት ታጅባ የጥራሪ ወንዝን ቁልቁል ታየዋለች፡፡
የዛታ ከተማ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ግሩም የጦር መነፀር ነው፡፡ ተራሮቿ ተፈጥሯዊ ምሽግ ናቸው፡፡ ከስሯ ያለውን የጥራሪ ወንዝ እና አሻጋሪ ያሉት ተራሮችን እንቅስቃሴ ለመቃኘት “ጠጠርን ከምስር እንደመልቀም” ይቀላል፡፡
ከጥራሪ ወንዝ ተነስቶ ከከፍታው ቦታ ለመድረስ በዐይን የምትታየውን ያክል ቅርብ ባትሆንም በጦርነት ወቅት ደግሞ ይበልጥ አስቸጋሪ ናት፡፡
ከግማሽ ቀን ያላነሰ የእግር ጉዞ የሚፈጀው ይህ አካባቢ ምሽጉ በእግረኛ ጦር ይፈታል ብሎ የሚያስብ ግን አይኖርም፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ደጀን የሆነው የአካባቢው ሚሊሻ ትህነግ ያዘጋጀችውን ተፈጥሯዊ ምሽግ ለመስበር ከአንድ ቀን በላይ የወሰደባቸው ጊዜ ጭማሪ የሆነ ረፋድ ብቻ ነበር፡፡
ለቆረጣ ውጊያ የወጡት እና በመሸባቸው ቦታ ላይ ድንጋይ ተንተርሰው ጨለማን ለብሰው ያደሩት የአማራ የልዩ ኃይል አባላት ጠዋት በዛታ ሰንሰለታማ ተራሮች ግርጌ ብቅ ሲሉ ለትህነግ ኃይል መብረቅ ነበር የሆኑት፡፡
የአካባቢውን ማኅበረሰብ እና ወጣቶች በግዳጅ መሳሪያ አስታጥቀው ወደጦርነት ያሰማሩት የትህነግ ልዩ ኃይል ከፊት አድርገው የሚያዋጓቸውን አባላት ትተው ከመሸሽ የተሻለ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
የተሻለ ያሉትን ሩጫ አባሎቻቸውን ሜዳ ላይ ትተው ፈፀሙት፡፡ ከፊታቸው መከላከያ ከኋላቸው የትህነግ ልዩ ኃይል የወጠራቸው ተገዶ ዘማቾች ግን ከኋላ ያለው ጦር መፈታቱን ሲያዩ ከፊት ካለው ጦር ጋር ሳይጋፈጡ በጎን ለገባው የአማራ ልዩ ኃይል መሳሪያቸውን ከፍ እያደረጉ አስረከቡ፡፡
ዛታ ያለብዙ ደም መፋሰስ ነፃ ወጣች፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ያንን ግዳጅ አጠናቀው አረፍ ባልሁባት አንዲት ጠዋትም ድንገት እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው
“እባክህ መሳሪያ ተኳሽክን ንገረኝ
ተሸካሚው ሁሉ እያንገራገረኝ፤” ።
Via – አብመድ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣
0Shares
0