ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

እኔ ዛሬም እዚያው ነኝ።ሥጋ ብፆት! ከግንባር የተላከው ደብዳቤ


እንዴት እረሰዋለሁ? ተመጥኖ የሚሰጠንን ውሃ ያንተ ጥም ይበልጣል ብዬ አጠጥቼሄለሁ። በረጅም አድካሚ ጉዞ ጓዜን ጓዝህ ላይ ደርበህ አጋርነትህን አሳይተኸኛል። ስንወድቅ ስንነሳ ስንደሰት ስናዝንና ስንከፋ አርስ በርሳችን ተፅናንተናል። ግንባር ድረስ አባቴ ሲመጣ ድስት ጥደህ፤ ቡና አፍልተህ ፤ መኝታህን መኝታዬ ላይ ደርበህ አስተናግደህ ሸኝተኸልኛል።
እናትህ ሲመጡ በተመሣሣይ ገንዘብ አዋጥቼ ወደ ቤታቸው ያለምንም ችግር እንዲመለሱ ከማድረጌም በላይ ፣ ፍቅራችንን ካዩ በኋላ “ለልጄ አላስብም የሚያስቡለት ከእናት ልጆች የሚልቁ ጓደኞች አሉት” ብለው እንባ ባቀረረ ዓይናቸው አፈራርቀው ካዩን ቦሀላ አገለብጠው ስመው የተለዩኝን መርሳት አልችልም።
ሞቴ የሞትህን ያህል አደይን እንደሚያማቸው አውቃለሁ። በተፈጥሮ ሞት ብሞት እንኳን የእናቴን ያህል ውስጣቸው እንደሚደማ አልጠራጠርም። ለአርቲፊሻል ዓላማ ከኃላ ወግተህ እንደገደልከኝ ቢሰሙ ፣ ልጄ ብለው ይጠሩኛል ብለህ ታስበላህ ? አይጠሩህም ሥጋ ብፆት!

የሀገር ተደፈረች ነጋሪት ሲጎሰም ፣ እምቢልታ ሲነፋ ፣ ትምህርት ንግድ ብቻ ሳይሆን የአፍላ የወጣትነት ህልምና ተስፋዬን ጥዬ ነፃነቷን ለማስከበርና የማይደፈር ገናና ስሟን መልሼ በሥፍራው ለማኖር ስመጣ ያገኘሁ ጓዴ ነበርክ።
በእንባ ታጅበን ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም ፣ እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይወደም ፡ ያ ሆማ ፣ ያ ሆማ ጉጉራን ሴንቴ ዮና ፡ ውፈር ተበገስ ፡ አፋር አለ በሎ ፣ አማራ አለ በሎ ፣ ትግራይ አለ በሎ ብለን በጋራ አዚመን ፡ ከተለያየ ባህል ፣ ቋንቋና እምነት ብንመጣም ከእናት ልጆች በላይ የጋራ ዓላማና ሀገራዊ ፍቅር ያስተሳሰረን የመንፈስ ጥንዶች ነበርን ።
ከቡሬ በረሃ እስከ የትግራይ ከፍተኛ ቦታዎች ፣ ከጠላት ልቀን ለመገኘት ስንል ከጦርነት ያልተናነሰ ወታደራዊ ልምምዶች ስናደርግ የጀመረው እኔ እብስ – አንተ ፣ እስከ አውደ ወጊያ ወሳኝ ትንቅንቅ ድረስ እንደ ዘለቀ አልረሳም።
እንዴት እረሰዋለሁ? ተመጥኖ የሚሰጠንን ውሃ ያንተ ጥም ይበልጣል ብዬ አጠጥቼሄለሁ። በረጅም አድካሚ ጉዞ ጓዜን ጓዝህ ላይ ደርበህ አጋርነትህን አሳይተኸኛል። ስንወድቅ ስንነሳ ስንደሰት ስናዝንና ስንከፋ አርስ በርሳችን ተፅናንተናል። ግንባር ድረስ አባቴ ሲመጣ ድስት ጥደህ፤ ቡና አፍልተህ ፤ መኝታህን መኝታዬ ላይ ደርበህ አስተናግደህ ሸኝተኸልኛል።
እናትህ ሲመጡ በተመሣሣይ ገንዘብ አዋጥቼ ወደ ቤታቸው ያለምንም ችግር እንዲመለሱ ከማድረጌም በላይ ፣ ፍቅራችንን ካዩ በኋላ “ለልጄ አላስብም የሚያስቡለት ከእናት ልጆች የሚልቁ ጓደኞች አሉት” ብለው እንባ ባቀረረ ዓይናቸው አፈራርቀው ካዩን ቦሀላ አገለብጠው ስመው የተለዩኝን መርሳት አልችልም።
ሞቴ የሞትህን ያህል አደይን እንደሚያማቸው አውቃለሁ። በተፈጥሮ ሞት ብሞት እንኳን የእናቴን ያህል ውስጣቸው እንደሚደማ አልጠራጠርም። ለአርቲፊሻል ዓላማ ከኃላ ወግተህ እንደገደልከኝ ቢሰሙ ፣ ልጄ ብለው ይጠሩኛል ብለህ ታስበላህ ? አይጠሩህም ሥጋ ብፆት!
በአካል ያልተገኙ ቤተሰቦቻችን በስልክና በደብደቤ እምነት ፍላጎታችንን ከልጃቸው በላይ አያውቁም እንዴ ? የሚያናግሩን በስማችን እየጠሩ ባህሪያችንን እየዘረዘሩ አይደለም ? “ሥጋ ብፆት” የጓዶች ሥጋ መሆኑን ከአንተ ከተረዳሁ በኋላ የእውነት ስንምል መተማመኛችን አልነበረም ? ነበር እንጂ !
ዝግጅቱን አጠናቀን ወደ የማይቀረው ፍልሚያ ስንገባ እኔ ቀድሜ ከተሰዋሁ አደራ ያልኩህንና ያልከኝም ትላንት እንደ ሆነ ሁሉ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። እኔ ፈንጂ ረግጨ ጓደኞቼ አልፈው ድል ያደረጉ ፤ ከአንተ እኔ ልቅደም ስንባባል ጓደዊ ፍቅር አስገድዶን እንጂ በብሔር ፣ ቋንቋና ሃይማኖት ስሌት መች ነበር ? አልነበረም።
ቀድመን በመሰዋት ለጓዶቻችን አደራ ሰጥተን የማለፍ ጠንካራ የወል ፍላጎት ይዘን ሳለን እጅግ አስገራሚ ፍቅር አሳይተውን ፣ ጀግንነት ሠርተው ያለፉ ጓዶቻችንን ስናይ ለኔ ባደረገው ብለን አልተቆጨንም ? በተረፉትና ድሉን ባጣጣሙት ሳይሆን ባለፉት፣ ሞትን እንደ ልዩ ፀጋ ቆጥረን አልቀናንም ? ቀንተናል እንጂ።
ፍቅር ከእውነተኛ ጓደዊነትና የዓላማ አንድነት ሲቀዳ ህይወት ሳይሆን የጓደኛ የክብር ሞት ያስቀናል። ከውጊያ በኋላ አፍላ ወጣትነቴ ያመጣብኝን የተቃራኒ ፆታ ፍላጎት ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ለማንም አልተናገርኩም። እንደ አንተ ሆኜ ደብዳቤ ፅፌልህ የፍቅረኛህንም መልስ በጋራ አንብበናል።
የመጀመሪያ ቀጠሮህ ቀን የሁላችንም ደመወዝ ይዘህ እንደ ወታደር ሳይሆን እንደ ባለሃብት አላንቀባረርካትም ? ቤተሰብ ፍቃድ ስንሄድ የደመወዛችን ትንሽነት ያላሳሰበን የወል እንጂ የግል ህይወት ስለሌለን አይደለም። ቤተሰብ መሀል ሆነን ክፍላችንን የምንናፍቀው ፣ ቀኑን ሳንጨርስ የምንመለሰው ጓዳዊ ፍቅሩ የእውነት አንድነትና ህብሩ እኮ ነው።
ስንጋባ ሰርግ ፣ ስንወልድ ክርስትና ፣ ኒካና ጥሎሽ አስጨንቆን የማያውቀው የእኔ ያንተ – ያንተ ሁሉ የኔ ስለነበር መስሎኝ። በዓመታት ቆይታ የገነባሁት ማንነት ሁሉ የአንተ አሻራ አለ። ሚስትና ልጆችህ ያንተን ያህል ይናፍቁኛል። አውቃለሁ። ሄጄ ሳልጠይቃቸው አልያም ካልደወልኩ ያኮርፉኛል።
ለርካሽ አላማ አድብተህ እንዳረድከኝ ቢሰሙ ሚስትህ እሰይ የኔ አንበሳ ፤ ልጆችህ ኮራንበህ አባታችን ብለው በኩራት አቅፈው ይስሙህ ይሆን? በፍፁም ! ሥጋ ብፆት! እንደገደልከኝ ሁሉ መሞትህን አምነው እርማቸውን ያወጣሉ።
በቡሬ ፣ ዛላንበሳ ፣ ፆረና ፣ ራማ ፣ ሽላሎ ፣ ባድመ ፣ ሽራሮ ወዘተ ግንባር በአግባቡ ግብዓተ መሬታቸው ያልተፈፀመው ፤ ከነወታደራዊ ዩኒፎርማቸው የተቀበሩ ጓደኞቻችንስ ቀና ብለው ቢያዩ ይሄንን ውርዳት ፣ ክደት ፣ ጭካኔና ቃል አባይነት ቢያዩ ምላሻቸው ሥጋ ብፆት የሞትነው ዛሬ ነው በማለት ደም እንደሚያነቡ ቅንጣት ታህል አትጠራጠር።
ህይወት የምትሰጠው እናት ፣ በአከባቢዋ የህክምና ተቋም ባለመኖሩ በህክምና እጦት በወልድ ማለፏን ዓይቼ ተንገብግቤ ፤ እንዴት እኔ እያለው ብዬ ፤ ፍላጎቴን ገትቼ ፣ ገንዘቤን አውጥቼ ፣ ሲሚንቶ አቡክቼ ፣ ድንጋይ ፈነካክቼ በገነባሁት ተቋም ዓይኗን በዓይኗ ማየት የቻለችው እናት ፤ ያለ ወላጅ ከመቅረት የተረፉ ህፃናት ፤ ፍቅሩንና የልጆቹን እናት በደስታ ያቀፈው አባት ፤ በአንተ ድብቅ ካራ መታረዴን ቢሰሙ አበጀህ ይሉሃል? ሥጋ ብጾት አይሉህም።
ዛፍ ሥር ተቀምጠው ፊደል ለመቅሰም ሲሞክሩ ፤ በሚነፍሰው ንፋስ አሸዋ ዓይናቸው ውስጥ እየገባ የተቸገሩ ፤ ህፃናትን በገንዘቤ በዕውቀቴና ጉልበቴ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገንብቼ ፤ ዩኒፎርም አሰፍቼ ፤ ቀለብ ሠፍሬ ፤ ባለኝ አቅም አንቀባርሬ በማስተማር የነገ መንገዳቸውን ያበጀሁላቸው ታዳጊዎች በድርጊትህ ይኮራሉ ? ሥጋ ብፆት አይኮሩም። እንዲያውም ያፍራሉ። አንገት ይደፋሉ።
ጠብመንጃ ባልያዘ እጄ ፣ ሞፈር ጨብጬ በማረስ ፣ በመዝራትና በመጎልጎል ፣ በማጨድና በማንፈስ ጎተራቸውን ሞልቼ አጋርነቴን ያሰየኋቸው “አንተ የወለድኩህ ልጄ ነህ ፤ ክፉ አይንካህ ” በማለት ከደከመ ዓይናቸው እንባ እየጨመቁ የመረቁኝ አቅመ ደካሞች ጧሪና ቀባሪ ያልነበራቸው ምንዱባን ፡ ከሩቅ ያልመጣ ክፉ መቅሰፍት እንደገኘኝ ቢሰሙ ልጃቸው የተሰዋለት ትግል ዓላማ ዘንግቶ ከሰብአዊነት ይልቅ ለከንቱ ወገንተኝነት ሲል ጓዶቹን ወደ መግደል ተሸጋግሯል ቢባሉ ዳግም በከፋ ሐዘን መርዶ አይቀመጡም?
ተራራ አፍርሼ ፣ መንገድ ሠርቼ ፣ የቀናት ጉዟቸውን ወደ ሠዓታት የቀየርኩላቸው ፤ ከኔ በላይ ኑሯቸውን አመቻችቼ ፤ ኅድሞ ቤታቸውን በቆርቆሮ ለውጨ ፣ ያኮራኋቸው ህዝቦቼ ፤ አብረን የተቀበልነውን ከራስ በፊት ለሀገርና ለህዝብ እሴት ሽረህ ፤ የጓዳዊነት እምነትህን አፍርሰህ ፣ ጀግናው የዓላማ አጋርህን በፈሪ በትር የጨለማ አስተሳሰብህን ተገን አድርገህ እንደ ገደልከው ሲሰሙ ሰውነትህን አይፀየፉም ትላለህ ? ሥጋ ብፆት ይፀየፋሉ።
ቀኑን ሙሉ የአንበጣ መንጋ ሲከላከል ውሎ ፣ ያለሁት ወገኔ የሆነ ያገለገልኩታና የደከምኩለት ህዝብ መሀል ነው ብሎ ፣ በካምፓችንም እንቅልፍ ቢጥለኝ በተራ የሚጠብቁኝና የምጠብቃቸው ጓዶቼ ናቸው በማለት ሐሳቡን ጥሎ እንቅልፍ ላይ ያለ ጓድ ላይ ፣ ከሌላ ሐይል ጋር ተሻርከህ በቦንብ ማቃጠልህ ጀግና ያሰኝህ ይሆን ? ታሪክስ እንዴት ይዘክርህ ይሆን ?
ከሳይንሳዊ መብረቅ አውራጅ ፣ ኮሎኔልን በድንጋይ ከሚማርክ ፣ በአፍሪካ ግዙፉን የጦር ሐይል በሰባት ኋላ ቀር መሣሪያ ጀምሮ ፣ ተይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ ከእራሱ እየቀማው የደመሰሰው ታሪክ እንዳለው በዘፈን ፣ በግጥም ፣ በፊልም ፣ በመፅሐፍ እና ወዘተ ለማስረፅ የሞከረ ጀግና፤ አምኖት አብሮት የተኛውን ምንም ትጥቅ ያልያዘ ወዳጁን አርዶ የሚበላ ፣ የጅብነት ባህሪይ የተጠናወተው ፈሪ ሆኖ ሲገኝ ፣ የዚያን ሁሉ ዲስኩር እውነተኝነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱና መክሰሩ አልታየህም ? ሥጋ ብፆት ከስሯል።
በረሃ እያለን የአልባሳት አቅርቦት እጥረት ነበረብን ። በጋንታ(የመቶ) አንድ ጀኬት ሲመጣ ታጋይ የሚጣላው ከኔ ይልቅ ለጓዴ ይሰጥ እያለ ነበር። ውጊያ ውስጥ የእኔ ቀድሜ ካልሞትኩ ፉክክር አስገራሚ ነበር። ደመወዝ ሁሉ አንፈልግም ያባልገናል ሁሉ ብለናል። ያልከኝ እውነት ከሆነ ሥጋ ብፆት እናንተ የነዚያን ምስኪን ተጋዳላይ አደራ በሊታዎች ፤ ታሪኩን ያቀጨጫችሁ እኩዮች እንጂ ታጋዩም ሆነ በትግሉ ብዙ ሺህዎችን ለገበረው የትግራይ ህዝብ በዓላማም ሆነ በስነ-ልቦና ባዕዳን ናችሁ።
ታምኖ መክዳት ፣ አሳድጎ አርዶ መብላት ፣ ለእንስሳትም ቢሆን ያዝ የሚያደርግ ነገር አለው። የሀገሬ አርሶ አደር ያሳደገውን አርዶ መብላት ምን ያህል እንደሚከብደው እናውቃለንና። ለአዳይ “ያንን ቀዩን ጓደኛዬ ፤ ያ እንኳን ትግርኛ ሲናገር የሚያስቅሽ” ብለሃቸው ስታበቃ “አወኩት እሱን እንዴት እረሰዋለሁ” ሲሉህ ዝና መስሎህ “ከኃላው አርጄው በድኑ ላይ ጨፈርኩበት” ብትላቸው ስሜታቸውን መገመት ትችላለህ ? ሥጋ ብፆት እኔም መገመት ይከብደኛል።
የእህትን ሠርግ መቼም አትረሳውም።ያንን የመሠለ ዝግጅትማ እንኳን ቤተሰብ ባዳም ያስታውሰዋል።ከማይረሳባቸው ምክንያቶች ደግሞ ትልቁ እኛ ያንተ የመቶ አባላት በተለያዩ የብሔረሰቦች ቋንቋ ሙዚቃዎች የሰጠነው ድምቀት ነው።
የመላው ቤተሰብህ በተለይ ሙክትና ገረወይና ጠጅ የሸለሙን አባትህ ሁኔታ መቼም የሚረሳ አይደለም።እስቲ በዚያን ቀን ለነበሩ ሁሉ ታዳሚያን “እነዚያን ወዳጆቼን በትግራይ ምድር በድናቸውን አፈር ነፍጌ ፣ ሥጋቸውን የአሞራና አውሬ ሲሳይ አደረኩት” በላቸውና ምላሻቸውን ጠብቅ – ጊዜ ካለህ ማለቴ ነው። ሥጋ ብፆት እኔ የሞትኩት ካንተ እሻላለሁ ።
ያንተ እናትና አባት እኮ ለበዓል ጠርተውን ስንሄድ ቀድመው ጓደኞችህን የሚያጎርሱ ፤ ሞቅ ብሎን ብንነታረክ ጉዳዩን ሳይሰሙ ለእኔ የሚፈርዱ “ምንም ቢሆን አንተ በዓል ከቤተሰቦችህ ጋር የመዋል እድል አግኝተሃል። እሱ ደግሞ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ከወዳጅ ዘመድ ርቆ እዚህ ከኛ ጋር ሲውል ሆድ ሊብሰው ስለሚችል ቢያጠፋ እንኳን መቻል ፣ ይቅርታ መጠየቅ ያለብህ አንተ ነህ” የሚሉ ፍትሃዊ እና አዛኝ ነበሩ።
በማንም የማይተካ ወዳጅህን ገድለህ ለአውሬ የመስጠት ድፍረትን ጁንታው እንዴት አስተማረህ ? ሥጋ ብፆት እንቆቅልሽ ነው። ህዝባችን የሚያውቀን ፣ ማንኛውንም ስብራቱን በሚጠግን አናጢነት ነው።የትኛውንም ህመም በሚያክም የጤና ባለሙያ ነው። በመንገድ ገንቢ መሐንዲስነት ነው። ተቋማትን በሚገነባ በጎ አድራጊ ነው። ከተረፈው ሳይሆን ካለው የሚያካፍል በልበ ቀና በጎ አድራጊ እና ርህሩህ ማንነታችን ነው። ለአንዴ ብቻ የሚኖራት ህይወቱን ለወገኑ ያለስስት በሚለግስ አኩሪ ልጅነት ነው።አንተን እንደ ቃየል እኔን እንደ አቤል አስቦን አያውቅም።
‘ሥጋ ብፆት’ ትርጉሙ የጓዴን ሥጋ መሆኑን አውቃለሁ።ጓደኛውን ከልቡ ለሚያፈቅር በአውደ ውጊያ በድንገት አጋሩን ከአጠገቡ ላጣ ወታደር ፣ የዓላማ ወዳጅ በጣም ትልቅ ትርጉም ስላለው የተለየ ስሜት የሚሰጥ ፤ የጠላት ጥይት የነጠቀኝን የልቤ ሰው ደጋግሜ ስጠራው በልቤ ውስጥ ሐውልቱን እንደሠራሁለት ስለሚቆጥር ከአንተ ሰምቼ እጠቀምበት ነበር። በዚህ ደግሞ መቼም አልፀፀትም።ወደፊትም እጠቀምበት ይሆናል።ምክንያቱም መቼም የጓዴን ሥጋ ብዬ በውሸት አልምልም።ሥጋ ብፆት አንተ ግን ብትተወው ይሻላል።ሌላው ቀርቶ በግድያ የተባባሩህ የልዩ ሐይል አባላት እንኳን አያምኑህም።ብፆትህ እኔ እንጂ እነሱ አልነበሩም።
ከማንም በላይ ከእናት ኢትዮጵያ በመንፈስ የተወለድን ወንድማማቾች ነን።ዝምድናችን ከብሔር ፣ ቋንቋና ሐይማኖት በላይ ነው።ያለን ዘር ሀገራችን ናት።እምነታችን ደግሞ ኢትዮጵያ ናት።ስለሆነም ለብፆቴ እሞታለሁ እንጂ አልገድለውም የሚለው እምነቴ ወደ መቃብር አብሮኝ ይወርዳል።ሥጋ ብፆት!
ሻምበል ፈይሳ ናኔቻ
Via – defense FB