ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ኃይል በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዛ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት ሕግ የማስከበር ያለውን ርምጃ መውሰድ ከጀመረ በኋላ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች በመቋረጡ በአብዛኛው የትግራይ አካባቢ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለማወቅ እድል አልነበረም

ከሳምንታት በፊት የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከ10 ሺህ በላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን መያዛቸውን ገልጸው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ከታገቱት የሠራዊት አባላት መካከል 7 ሺህ የሚጠጉትን ማስለቀቁን መግለጹ የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ በህወሓት ተይዘው የነበሩ የሠሜን ዕዝ አባላትን መልቀቁን ድርጅቱ ማስታወቁ ይታወሳል።

በሠሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በተቀሰቀሰውና ከሦሰት ሳምንታት በላይ በቆው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ እየተነገረ ነው። በሠራዊቱ ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ጊዜ በክልሉ ልዩ ኃይል ተይዘው ለሳምንታት የቆዩ የሠራዊቱ አባላት ምን እንደተፈጠረና አስካሁን የቆዩበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መስመር

በትግራይ ልዩ ኃይል ተይዘው ከነበሩት መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከቀናት በፊት በዋግኽምራ እና በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ አማራ ክልል መግባታቸው ተነግሯል። ከእነዚህ ውስጥም በዋግ ኽምራ በኩል የተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅን ተሻግረው ሰቆጣ ከገቡትን የሠራዊቱን አባላት ውስጥ ቢቢሲ የተወሰኑትን አናግሯል።

በምዕራብ ትግራይ አዲ ሀገራይ ከተባለችው ከተማ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዳሸተናይ በሚባል ስፍራ ውስጥ በ31ኛ አድዋ ክፍለ ጦር ውስጥ የክፍለ ጦር አባል የሆነው አምሳ አለቃ አብርሐም ባየ 22 ቀናትን በትግራይ ልዩ ኃይል አባላት በቁጥጥር ስር ቆይቶ ወደ ዋግኽምራ ከገቡት መካከል ነው።

አምሳ አለቃ አብርሐም እንደሚለው የበታች ወታደሮች ስለተከተው ሁኔታ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ከሌሊቱ 6፡15 አካባቢ የመጀመሪያዋ ጥይት ስትተኮስ ነው ከእንቅልፋችን የነቃነው ይላል።

“ስንነቃ ገደብ በሌለው ተኩስ እየተናጥን ራሳችንን በትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ተከበን አገኘነው” የሚለው አምሳ አለቃ አብርሐም የመሳሪያ መጋዘኑም ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆኖ ስለነበረ እራሳቸውን የሚከላከሉበት ተጨማሪ መሳሪያ ማግኘት እንዳልቻሉና ተኩሱም ቀጥሎ የሚደርሰው ጉዳት እየደረሰ ሌሊቱ መንጋቱን ያስታውሳል።

በአቅራቢያ የነበረው ሌላው የሠራዊቱ አሃድም በተመሳሳይ ጦርነት ተከፍቶበት ከሌሊቱ 8 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 4፡00 እንደቀጠለ ይናገራል። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ራስን ለመከላከል የሚያስችል መሳሪያ በመጨረሳቸው “አማራጭ ስላልነበር አጠገባችን ብዙ ወንድሞቻችን ከሞቱ በኋላ እኛ ተያዝን” በማለት የውጊያውን ፍጻሜ ያብራራል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በጥቅምት 27 ወደ አከሱም ዩኒቨርሲቲ 10 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አንድ ላይ በማድረግ እንደወሰዷቸው ይገልጻሉ። ከቀናት በኋላ በኅዳር አንድ ደግሞ ከአክሱም በመነሳት ወደ አብይ አዲ እንደተወሰዱ አምሳ አለቃ አብርሐም ይናገራል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

ምርኮኛ ሆነው በቆዩባቸው ቀናት በሚሊሻ እና በማረሚያ ቤት ጠባቂዎች ሲጠበቁ መቆየታቸውን የሚናገረው አምሳ አለቃ አብርሃም፣ “ምንም አይነት ንግግር አልነበረንም። በተለይ አብይ አዲ በነበርንበት ወቅት ሚሳኤሎች ሲተኮሱ በቦታው ሆነን እየተመለከትን ነበር። ከባድ መሳሪያዎች ወደ ስፍራው ሲጓጓዙ ስንመለከት በቀሪው የአገራችን ክፍል ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ስለማናውቅ በጣም ጭንቀት ውስጥ ነበርን፣ እንቅልፍም አልነበርንም” በማለት የነበራቸውን ቆይታ ይገልጻል።

መቀሌ በቁጥጥር ሥር መዋሏ በተነገረበት ዕለት አዳሩን እጅግ ብዙ የሆነ ከባድ መሳሪያ ወደ ስፍራው ሲመጣ አደረ፤ በማግስቱ ኅዳር 20 ሂዱ ብለው ለቀቁን ሲል የቆይታቸውን ፍጻሜ ያስታውሳል።

ከእገታ እንዲለቀቁ ከተወሰነ በኋላ በኅዳር 20 ወደ ተከዜ የኃይል ማመንጫ ጫፍ አድርሰዋቸው እንደተመለሱ የሚናገረው አምሳ አለቃ አብርሐም ከዚያም ወደ አማራ ክልል በመሻገር አበርገሌ ከምትባል ቦታ መግባታቸውን ገልጿል። “የአካባቢው ማኅበረሰብ ተንከባክቦ አሳደረን ከዚያም መኪና ተልኮልን ወደ ሰቆጣ ገባን” ብሏል።

ሃምሳ አለቃ አብረሐም ተከዜ ጫፍ በመኪና ከተሸኙ በኋላ ሠራዊቱ በሁለት ቀጠና መሄዱን ይገልጻል። የተለቀቁት ከ50 አለቃ በታች ማዕረግ ያለካቸው ወታደሮች መሆናቸው በመጥቀስም “ሴት ወታደሮችና ከ50 አለቃ በላይ ማዕረግ ያላቸው የት እንዳሉ አናውቅም። በሌላ በኩል ከባድ ቁስል የደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላትም ነበሩ” ብሏል።

ከ50 አለቃ በታች ያለነው ከ4 ሺህ በላይ እንሆናለን ያለው ሃምሳ አለቃ አብረሐም ይህም ኃይል ተከዜ ጫፍ ከደረሰ በኋላ የጀልባ ከፍሎ የተከዜን ሰው ሰራሽ ሐይቅ መሻገር የቻለው ወደ ሰቆጣ፣ ገንዘብ የሌለው ደግሞ በእግሩ በበየዳና ደባርቅ አድርጎ ወደ ጎንደር መጓዙን ይገልጻል።

“የነበርንበት ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፣ የተባልነውን ከማድረግ ውጭ ከባድ ቁስል ላይ ሆነን እንኳ የምንታከምበት እድል አልነበረም፣ ያንን ማየት አስቸጋሪ ነው” ይላል።

ካርታ
መስመር

ሌላኛው የሠራዊቱ አባል አስር አለቃ ኢብራሂም ሃሰን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል እኣገለገለ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

መጀመሪያ ወደ ትግራይ ሲመጣ ስምሪቱ በአክሱም ከተማ ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ አዲግራት ከተማ ነበረ። እሱም ሆነ ባልደረቦቹ ጥቅምት 24 የተከሰተው ነገር ይሆናል ብለን ፈጽመው አስባው እንደማያውቁ ይናገራል።

ስለዚህም ከቀን ውሏቸው መልስ ሁሉም በየክፍሉ አረፍ ብሎ እንዳለ ከሌሊቱ 5፡30 ላይ ተኩስ ተከፈተ።

“ከዚያም መሳሪያ አምጡ፤ እጅ ስጡ አሉን። እኛ ትጥቅ የሚያስፈታን የፌደራል መንግሥት እንጂ የክልል መንግሥት አይደለም አልናቸው። እንዴት እጅ እንሰጣለን፤ እጅ አንሰጥም ስንላቸው ነበር።”

ነገር ግን ኋላ ላይ በከበቧቸው የትግራይ ኃይል እና ሚሊሻ አባለት መያዛቸውን የሚናገረው አስርአለቃ ኢብራሂም “ጥቅምት 25 እና 26 ውለን ዓርብ በ27 እዳጋ ሐሙስ ወደሚባል ቦታ ወሰዱን። እዳጋ ሐሙስ ለአንድ ሳምንት ያክል ከቆዩን በኋላ አብይ አዲ ወደምትባል ቦታ ተወሰድን” ይላል።

Related stories   በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

ኢብራሂም ተይዘው የቆዩባቸው ቀናት እጅግ አስቸጋሪ እንደነበሩ በመግለጽ ይራቡ እንደነበረም ያስታውሳል “ጠዋት አንድ ዳቦ ይመጣል። ለምሳም አንድ ዳቦ ነው የሚሰጠን። አንዳንዴ ጠዋት ከበላን ምሳ ላይሰጠን ይችላል።”

ከቀናት ቆይታ በኋላም የተለያዩ አማራጮች ቀረቡልን ይላል “የትግራይ ልዩ ኃይልን መቀላቀል፣ ሲቪል ሆኖ ትግራይ ውስጥ መቆየት ወይም ወደ አገሬ መግባት ነው የምፈልገው የሚል ካለ መሄድ ይችላል አሉን። አብዛኞቻችን ወደ አገራችን መመለስ የሚለውን መረጥን” ሲል ተናግሯል።

ከዚያም ከሠራዊቱ መካከል የተለያዩ ሙያ ያላቸውን እንደ ኦፕሬተር እና መድፍ ተኳሾችን በመለየት አስቀሩና ሌሎቻችንን በሲምንቶ መጫኛ ተሳቢ መኪና ጭን እንድንወጣ አደረጉን ይላል አስር አለቃ ኢብራሂም።

መስመር

ሌላኛው ስሙን ያልገለጸልን የ11ኛ ክፍለ ጦር 2ኛ ብርጌድ አባል፣ እርሱ በነበረበት ቦታ ተኩሱ ምሽት 5፡30 አጉላ ላይ መጀመሩን ይገልጻል።

“እንደዚህ አይነት ኦፕሬሽን እንደሚኖር በግርድፉ ጥርጣሬ ቢኖርም መቼ እንደሆነ ግን አላወቅንም” የሚለው ይህ የሠራዊቱ አባል በወቅቱ ለጥበቃ የሚሆኑ 3 ክላሽንኮቮች ብቻ ነበሩ ለጥበቃ የወጡት። ሌላው መሣሪያ መጋዘን ውስጥ ተቆልፎ እኛም ተኝተን ነበር” ይላል ጨምሮም “ተኩሱ ሲጀመር መሳሪያ ለማውጣት ወደ መጋዘኑ ብናመራም ቀድመው ስለከበቡት ሊያስጠጉን አልቻሉም።”

እራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን እንደቀጠሉና ከመካከላቸው አንድ ቁልፍ የያዘ አባል ወደ መጋዘኑ ተጠግቶ ለመክፈት ሲሞክር ተመትቶ በመውደቁ ድጋሚ መቅረብ አለመቻላቸውን ይገልጻል።

ይህ በሚሆንበት ጊዜ “የራሴ የግል መሳሪያ በቅርብ ስለነበረኝ፣ እያየሁ ዝም አልልም በሚል አውጥቼ ለመታኮስ ስወጣ ገና 30 ሜትር እንደተጓዝኩ ተመትቼ ወደቅኩ” በማለት ለጉዳት የተጋለጠበትን አጋጣሚ ይገልጻል።

“ለተወሰነ ጊዜ ራሴን ስቼ ስለነበር እነሱም ሞቷል ብለው ዝም አሉኝ። ከዚያ እንደምንም ተጎትቼ በአጥር በመሹለክ የሠራዊቱ መኝታ ክፍል ውስጥ ገባሁ” ይላል።

ነገር ግን በቦታው ሰው እንዳላገኘ ገልጾ “ወደ ሌላኛው ቦታ ስሄድ ሰው ቤት ውስጥ ተቀምጧል። መመታቴን ስነግራቸው ቁስሌን አስረው አስቀምጡኝ። ተኩሱም እስከ ማግስቱ ቀን 6፡00 ሰዓት ድረስ ቀጠለ። ሌላ ኃይል እኛን ሊከላከለን ሞክሮ ነበር፣ ነገር ግን ጥይት ሲጨርሱ ከፍተኛ ጥቃት ደርሶባቸው ተማረኩ። እኛም ተያዝን” በማለት በትግራይ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር የወደቁበትን ክስተት አስረድቷል።

ከተማረኩ በኋላም ግማሻቸውን ወደ ውቅሮ፣ ሌሎቻቸውን ደግሞ ወደ አጉላ መወሰዳቸውን በማስታወስ፤ በውቅሮ ሆስፒታል ለሦስት ቀን ሕክምና እንደተደረገለት የሚናገረው አባሉ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ አብይ አዲ መወሰዱን ገልጿል።

ወደ አብይ አዲ ከመወሰዳቸው በፊት ግን ሹፌር፣ ቴክኒሻን፣ መሃንዲስና የመረጃ ባለሙያ የመሳሰሉትን ባለሙያዎች እየለዩ ለብቻቸው እንደሳስቀሯቸውና ከዚያ በኋላም የተለያየ ፎርም እያስመጡ እንደሞሉ የሚናገረው ይህ የሠራዊቱ አባል “ሦስት ጓደኞቻን ከተማረኩ በኋላ ተገድለዋል” ብሏል።

Related stories   “በአጣዬ እና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ኮማንድ ፖስቱ

ከቀረቡላቸው ፎርሞች መካከል ብሔርን የሚጠይቅ እንዳለ በማስታወስ በመጨረሻ የቀረበላቸው ፎርም ግን ሦስት አማራጮችን የያዘ ነበር ይላል።

“አንደኛው ከትግራይ ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ትግራይን ነጻ እንድናወጣ፣ ሁለተኛ በትግራይ ውስጥ ሰላማዊ ሰው ሆነን እንድንኖርና ሦስተኛው ደግሞ ከትግራይ ወጥተን ወደ ቤተሰብ እንድንሄድ የሚፈቅዱ ናቸው” ይላል።

“እኛም ተመካክረን ሦስተኛውን አማራጭ መርጠን እንሄዳለን አልናቸው። እነሱም ከንፈራቸውን እየነከሱ እና ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ ተቀበሉን” በማለት ከምርኮኛነት የወጡበትን ሁኔታ አብራርቷል።

ከአብይ አዲ ወደ አማራ ክልል የተሸኙት የሠራዊት አባላት በሁለት አቅጣጫ መሸኘታቸው የሚታወስ ነው፤ በዋግኽምራ እና በሰሜን ጎንደር በኩል።

እስካሁን ትክክለኛ ቁጥራቸው ባይታወቅም በሁለቱም አቅጣጫ በሺዎች የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት በሰላም መግባታቸው ይነገራል። ከእነዚህ መካከል በዋግኽምራ በኩል እስከ ትናንትናው ዕለት ድረስ ከ1240 በላይ የሰሜን ዕዝ የሠራዊት አባላት መግባታቸውን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በላይ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መስመር

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።

ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።

የክልሉ ባለስልጣናትም በበኩላቸው ፌደራል መንግሥቱ በኮቪድ ሰበብ ምርጫን ማራዘሙ “ሕገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ነው ስልጣኑን አራዝሟል” በማለት የፌደራሉን መንግሥት “ሕገወጥ” ብለው እውቅና መንፈጋቸው አይዘነጋም።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።

መንግሥት “ሕግ የማስከበር” ባለውና ከሦሰት ሳምንታት በላይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ሰር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳውቀዋል።

BBC Amharic

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *