“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ወታደሩ እጁን ከሰጠ በኋላ በታንክ ደፈጠጡት፤መትረፍ የሚችሉ ቁስለኞችን ሳይቀር ገደሏቸው” ታግተው ካመለጡት አንደበት

አስር አለቃ ቤቴልሄም በዛ ትባላለች፡፡ የ11ኛ ክፍለ ጦር 2ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አባል ነች፡፡ የከሀዲው ህወሓት ጁንታ ታጣቂዎች በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመውን የጭካኔ ጥግ ተመልክታለች:: ደርሶባታልም፤ የጁንታው ጭካኔ እንኳንስ በወገን ላይ ቀርቶ በሰው ልጅ ላይ ሊታሰብ የማይችል መሆኑን ትናገራለች።
‹‹ሁኔታው ከመፈጸሙ በፊት በሰራዊቱ ውስጥ የጁንታው ተላላኪዎች የሆኑ የሻለቃው አባላት እየተደበቁ በየቀኑ ይሰበሰቡ ነበር፡፡ የዋርዲያ ተራቸውን ጠብቀው ስለማይሰሩም የተቀረው ወታደር ያለእረፍት የእነርሱንም ጭምር ሲሸፍን ቆይቷል። የተቀረው ሰራዊት ቀን ቀን አንበጣ እንዲያባርር ይደረጋል። ደምም ሰጥተናል፡፡ በብዙ ሌሎች ነገሮችም ማህበረሰቡን እንደግፋለን” ትላለች አስር አለቃ ቤቴልሄም፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት እለትም ቀኑን በሙሉ አንበጣ ሲያባርሩ ውለው ጎናቸውን ለማሳረፍ ጋደም ባሉበት ቅፅበት ነዉ አብረዋቸው በኖሩ በሰራዊቱ ውስጥ በነበሩ ከሀዲ የጁንታው ተላላኪዎች ከጀርባ የተወጉት:: አስር አለቃ ቤቴልሄም ትናገራለች፤ “በዕለቱ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ተኩል ከውጭ ወደ ውስጥ የጥይት ሩምታ ተከፈተብን፡፡ ከውስጥ ደግሞ እነዛ አስቀድመው ሲሰበሰቡና ሲያሴሩ የቆዩት የጁንታው እኩይ አላማ ፍፃሚ የሰራዊቱ አባላት የገዛ ጓደኞቻቸው የሆኑ የሌላ ብሄር ተወላጆችን እየመረጡ በተኙበት በጥይት መምታት ጀመሩ፡፡ ከተኛንበት እየተጣደፍን ወደ ውጭ ወጣን፤ ትጥቃችን ወዳለበት መጋዘን ሄድን። የመሳሪያ ግምጃ ቤቱ ግን ተቆልፏል፡፡ የመጋዘኑን ቁልፍ የያዘውን ወታደር አስቀድመው ገድለውታል” ትላለች አስር አለቃ ቤቴልሄም፡፡
በእለቱ ዋርድያ ላይ የነበሩ የሰራዊቱ አባላት በኮለኔል ሀጎስ መገደላቸውን የምትናገረው አስር አለቃ ቤቴልሄም፤ “ባዶ እጃችንን ስለሆንን እራሳችንን ለመከላከል አልቻልንም፡፡ ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ የሚከላከሉት፡፡ ብዙዎችን ገደሉ፡፡ እጅ የሰጡትንም ጭምር ገደሏቸው” ትላለች።
የጁንታው ታጣቂዎች ግፍና ጭካኔ የትየለሌ መሆኑን የምተናገረው አስር አለቃዋ፤ “አንድ የአራተኛ ክፍለ ጦር አባል የነበረ ወታደር እጁን ከሰጠ በኋላ በታንክ ደፈጠጡት፡፡ መትረፍ የሚችሉ ቁስለኞችን ሳይቀር ገደሏቸው፡፡ ሬሳቸውን ሳይቀብሩ የራሳቸውን ሰዎች ሬሳ ብቻ አንሰተው ሄዱ” ስትል ነው የጓዶቿ በከሀዲ የሰራዊቱ አባላትና በጁንታው ታጣቂዎች የተፈጸመባቸውን ግፍ የምትናገረው።
ከዚህ ሁሉ ግፍና ጭካኔ በኋላ የተረፉትን እንድነ አስር አለቃ ቤቴልሄም ያሉ የሰራዊቱ አባላትን የጁንታው ታጣቂና ከሀዲ የሰራዊቱ አባላት በሲኖትራክ ጭነው አጉላ ወደተባለ ትምህርት ቤት ወስደው እንዳጎሯቸው ትናገራለች፤ “በህይወት የተረፉና ከሻምበል በላይ የነበሩ የኦሮሞና የአማራ ተወላጅ የሆኑ የጦር መኮንኖችን ለብቻቸው አስቀመጧቸው፡፡ ትኩረታቸው በነሱ ላይ ነበር፡፡ እስከ አሁንም የት እንዳደረሷቸው አላውቅም፡፡
ሴቶችን ለብቻችን በአንድ ክፍል ውስጥ አጎሩን፡፡ ሞባይላችንን፣ ልብሳችንንና ያለንን ዶክመንት፣ ገንዘባችንን ሁሉ ዘረፉን፡፡ ያለምግብና ውሃ ለሶስት ቀን ወንበር ላይ እየተኛን አሳለፍን፡፡ አንዳንድ የወታደር ሚስት የሆኑ ነዋሪዎች ምግብ ሊሰጡን ሲሞክሩ ይከለክሏቸው ነበር፡፡ በረሀብ የተነሳ በጣም ተዳከምን፡፡ በመጨረሻ ጥሬ እየቆነጠሩ ይሰጡን ጀመር”
አፍኝ ቆሎ እየሰጡ አጉረው ለሁለት ሳምንት ያቆይዋቸውን የሰራዊት አባላት እጃቸውን ጠርንፈው አስረው ወደ መቀሌ እንዳመጧቸው ትነገራለች፤ “መቀሌ የእንሰሳት ጤና ኮሌጅ ውስጥ አስቀመጡን፡፡ ስድብ፣ እርግጫና ማንጓጠጥ ይደርስብን ነበር፡፡ ሌላ አካባቢ የሴቶችን ጡት እንደቆረጡም ሰምተናል፡፡ በእኛም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊቱ የሰጡ የጁንታው ታጣቂዎች ተናግረዋል፡፡ ህዳር 21 እቅዳቸውን ለመፈጸም ሲዘጋጁ ህዳር 20 የመከላከያ ኮማንዶዎች ደርሰው ነጻ አውጥተውናል” ስትል በሰራዊቱና በፈጣሪ ታምር መትረፋቸውን ተናግራለች።
ጁንታው ለእኩይ አላማው ያልተባብረውን ሁሉ ከማጥፋት የማይመለስ ጨካኝና ከሀዲ ነዉ ያለችው አለቃ ቤቴልሄም በትግራይ የኩያ ተወላጁን ወታደር ተጋድሎም ታስታውሳለች “የአራተኛ መካናይዝድ አባል የሆነ የኩያ አካባቢ ተወላጅ ከእኛ ወገን ቆሞ ያደረገውን ተጋድሎ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ልጁ ታንከኛ ነው፤ ታንክ ውስጥ እንዳለ እጅህን ስጥ ይሉታል፡፡ እኔ የቆምኩት ለኢትዮጵያ ስለሆነ እጄን አልሰጥም ብሎ በታንክ መዋጋት ጀመረ፡፡ ታንክ ከታንክ ጋር ገጠሙና ተረባርበው ገደሉት”፡፡
ሌላዋ የአይን ምስክር ኮንስታብል አለምነሽ ገመዳ የሰባት ወር እመጫት ናት። የፌደራል ፖሊስ አባል ስትሆን የጁንታው ታጣቂዎችነ የሰራዊቱ ከሀዲ አባላት ለእሷና መሰል እመጫቶች እንኳን እንዳልራሩላቸው ትናገራለች።
ኮንስታብል አለምነሽ ምድብ የጥበቃ ስራዋ አክሱም አየር መንገድ ውስጥ ነው፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ አየር መንገዱ ውስጥ በጥበቃ ስራ ላይ ባሉ የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸመውን ክህደት ስታነሳ እንባዋን መቆጣጠር አትችልም።
“እኔ የሰባት ወር እመጫት ስለነበርኩ መሳሪያዬን ለሌሎች ሰጥቼ ማረፊያ ቤት ውስጥ አራስ ልጄን ይዤ ተቀምጬ ነበር፡፡ ጋንታ አመራሩ የጁንታው ተላላኪ ነው፡፡ ላካስ ከታጣቂዎች ጋር ተመካክሮ ጨርሷል፡፡ በጫካው በኩል አድርገው ወደ ጊቢው ገቡና እጅ ስጡ አሉ፡፡ እርሱ ቶሎ ብሎ መሳሪያውን ሰጣቸው፡፡ ሌሎቹ አንሰጥም ብለው አፈገፈጉ፡፡ ከዚያም ተኩስ ተጀመረ፡፡ አንድ ሃይል አመራር ከማማው ላይ ሆኖ ለመከላከል ሞከረ፡፡ መጨረሻም እጁን እንዲሰጥ አደረጉት፡፡ እጁን ከሰጠ በኋላ ግን በረንዳው ላይ እጁን በሰንሰለት አስረው በዱላ ጨፈጨፉት›› ትላለች ኮንስታብል አለምነሽ።
ኮንስታብል አለምነሽ በከሀዲዎች የተፈጸመው ግፍ ዛሬም ድረስ ከአይኗ አልጠፋ ብሎ አይኖቿ በእንባ እንደተሞሉ ሳግ እየተናነቃት ነበር ሁኔታውን የነገረችን።
“ከዚያ ወደ እኔ መጡ ቤቴን ዘግቼ እንደተቀመጥኩ የጥይት እሩምታ አወረዱብኝ፤ ውጪ አሉኝ ህጻን ልጅ ስለያዝኩ አልወጣም አልኳቸው፡፡ ጨካኞ ናቸው ለአራስ ልጄ እንኳን አልራሩም:: አስገድደው ገቡና ቤቱን ፈተሹ ፤ አንድም ነገር ሳልይዝ ባዶ እጄን አስወጡኝና ልጄን እንዳቀፍኩኝ በሶምሶማ ሩጪ አሉኝ፤ ከእኔ ጋር ሌላም አንድ ልጅ የያዘች ሴት ነበረች፡፡ እርሷ ግን ጭንቅላቷ አካባቢ ተመታ ደሟን እያፈሰሰች ሩጪ ተባለች። ሁለታችንም ህጻን ልጅ ይዘናል፤ እሩጡ እያሉ አስሮጡን፡፡ ስላሴ ወደሚባል ቤተክርስቲን ጫካ ውስጥ ወሰዱንና የሞቱ የነሱን ታጣቂዎች ተሸከሙ አሉን፡፡ ልብሳችንን ጫማችንም አስወልቀው በባዶ እግራችን አስኬዱን፤ እንደዚ አድርገው ወደ ሽሬ አመጡን፤ እጅ የሰጡ አመራሮቻችንንም ገደሏቸው፡፡ በተለይ ኦሮሞና አማራን እየለዩ አስቀሯቸው፡፡ የደቡብ ተወላጆች ላይም አይናቸው ላይ በርበሬ እየጨመሩ ያሰቃይዋቸው ነበር፡፡ በረሀብም የሞቱ አሉ፡፡ የሞቱትን አስፋልት ላይ ሲጎትቷቸው ነበር፤ አንዳንዶቹን አፍነው የት እንደወሰዷቸው አናውቅም፡፡ ከባለቤቴ ጋር እስከ ሽሬ ድረስ አብረን ከመጣን በኋላ እርሱን እዛው አስቀሩት፤ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አላውቅም” ከዚህ በላይ ኮንስታብል አለምነሽ መናገር አልቻለችም፤ እንባዋንም መግታት ተሳናት፡፡
ጁንታው በህግ ማስከበር ዘመቻው በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ከሁሉም የትግራይ አካባቢዎች ተወግዷል:: ከጁንታው አባላት መካከል እጃቸውን መስጠት የጀመሩ ያሉ ሲሆን ቀሪ የጁንታው አባላት በጠባብ አካባቢ መከላከያ ሰራዊቱ በቅርብ እየተከታትላቸው እንደሚገኝ መንግሥት መግለፁ ይታወሳል::
በኢያሱ መሰለ
(ኢፕድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “አቡነ ማቲያስ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም”
0Shares
0