ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

እውነት ‹‹ትግራይ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?››

በአበራ ሣህሌ

ባለፈው ሳምንት በዚህ  ጋዜጣ ላይ ‹‹ትግራይ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?›› በሚል ርዕስ በ“ሳይንሳዊ ሥራ” የሚያምኑ ግለሰብ ትግራይ ውስጥ ስላሉ ችግሮች ሀተታ አቅርበዋል። ጽሑፉ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት ሲለውም የጊዜውን ዘፈን ተቀብሎ ማስተጋባትን ዋነኛ ጭብጥ አድርጎ የቀረበ ነው። ድፍረት ግን ዓይነተኛ መለያው ነው። የሚገርመው ስለሳይንሳዊነት የሚሰብኩን ጸሐፊ ሀተታቸውን ለመደገፍ ሳይንስ ሠፈር ዝር አይሉም።

ጸሐፊው በሥራ አጋጣሚ የትግራይ አካባቢዎችን ለማየት ዕድል አግኝቻለሁ በሚል፣ ሕዝቡ በፀባዩ እንዲህ ነው እንዲያ ነው የሚሉ ብያኔዎችን ሰጥተዋል። የሚገርመው ጸሐፊው የሚያወሩት ከአዲስ አበባ ሁለት ሰዓት በማይፈጅ በረራ ስላለ ክልል ሳይሆን፣ በማርስና በጁፒተር መካከል ስለተገኘ አዲስ ፕላኔት ይመስላል። ምን ዓይነት ናሙና ተወስዶ እንደተረጋገጠ ባይታወቅም፣ ‹‹ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር የመኖር ችሎታው የወረደ›› የሚል ዕርቃኑን የቆመ ድምዳሜ አሥፍረዋል። አንድን ማኅበረሰብ ሰብስቦ አንድ ሳጥን ውስጥ ከትቶ የመፈረጅ ጉዳይ እንዴት “በሳይንሳዊ ሥራ” ከሚያምን ሰው እንደመጣ ማሰብም ይከብዳል።

ጸሐፊው የትግራይ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንደ ‹‹አጥር›› ሆኖ በርካታ ችግሮች እንደፈጠረ አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል። በዚህ የተነሳ እዚያ ያደገ ሰው ‹‹ባህሪው ለየት ያለ›› እንደሆነ ነግረውናል። ግልባጩ የእሳቸው ዓይነት ሰዎች ባህሪ የተመቸ ነው ማለትም ነው። ካነሱት ዘንድ የትኛውን ዓይነት ባህሪ ቢኖረው መልካም እንደነበረ ቢጠቁሙን መልካም ነበር። እውነቱን ለመናገር የክልሉ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ችግር መሆኑ ከአካባቢው አርሶ አደር ብንሰማው ደግ ነበር። ያ ታሪኩን ወደ ኋላ ለብዙ ሺሕ ዓመታት ሄዶ መናገር የሚችል ማኅበረሰብ እዚያ ላይ መቆየቱ የሚያሳየው ነገር ከተፈጥሮው ጋር መነጋገር መቻሉን ነው። አለበለዚያ እኔ አውቅልሃለሁ ከማለት የዘለለ ጉዳይ አይሆንም።

የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጦች ፀጋዎች ናቸው። ዓለምም የምታምረው ሰዎች እልም ካለ በረሃ ጭልጥ እስካለ በረዶ ውስጥ በመኖራቸው ነው። እነዚያ መልክዓ ምድሮች የራሳቸው የሆኑ የዕፀዋትና የእንስሳት መፍለቂያዎች ናቸው። ምናልባትም ዋሊያ በሰሜን ተራሮች የሚገኘው ለእሱ ተስማሚ መሬት እዚያ ብቻ በመገኘቱ ሊሆን ይችላል። የዋልታ አካባቢ ድብም ከቅዝቃዜ ውጪ መኖር ባለመቻሉ በራሱ ለአካባቢው አንድ መስህብ ነው።

ለማንኛውም ግን የመሬቱ አቀማመጥ ምንም ይሁን ምንም ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ችጋር ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ጠፍቶ አያውቅም። ለአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ በደርግ ጊዜ በዓለም ደረጃ የታወቅንበት ጉዳይ ነው። ‘በምግብ ሰብል ራስን መቻል’ም ይሁን ‘የምግብ ዋስትና’ እያልን አሪፍ ቃል የምንፈልግለት ረሃብ አሁንም ሥጋት ነው፣ በበርካታ ሥፍራ!

አንዳንዴ እንደ ማስረጃ የሚቀርበው ‹‹የተከዜና የመረብ ወንዞችና ሸለቆዎች›› እንደ ችግር መነሳታቸው የሚያስፈልግ ነው። ወንዝ ባለበት ሸለቆ አለ። ይኼ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። ዓባይ ወንዝ በመኖሩ እሱን ተከትሎ ሸለቆ አለ፣ ጊቤም እንደዚሁ። እነዚህ ሸለቆዎች አስቸጋሪነታቸውን ለመግለጽ በተለምዶ ዓባይ በረሃ ወይም ጊቤ በረሃ ይባላሉ። የተከዜ ሸለቆዎች ከእዚያ በተለየ እንቅፋት የሚሆኑበትና “ለሕዝብ ግንኙነት” አመቺ ባለመሆን የሚኮነኑበት ጉዳይ ምን እንደሆነ አይታወቅም።

ስለትግራይየኢኮኖሚሁኔታየተሰጠውአስተያየት ‘አዲዮስኢኮኖሚክስ!’ ነው።ስለተራራአለመኖር፣ ስለውኃእጥረት፣ስለታዳሽኃይልዝርዝርቀርቧል።እነ ሐረሪ፣እነ ሶማሌናእነጋምቤላበተራሮቻቸውይታወቃሉ?ወይስትግራይላይየተለየመመዘኛመጠቀምአለብን?ይህንንሁሉእንተውናአንድቀላልየምጣኔሀብትመርህንእናንሳ።ሁሉምአገሮችሁሉምነገርየላቸውም።በተጨማሪምአንዳንድነገርለመሥራትካላቸውሁኔታአንፃርአዋጪላይሆንይችላል።

ፑማ የጀርመን ስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ነው። የእዚያ አገር ሠራተኛ ለጉልበቱ ብዙ ፍራንክ ስለሚጠይቅ፣ ኩባንያው ቱታውንም ሆነ ጫማውን ካምቦዲያ ወስዶ የሚያሠራው የጉልበት ዋጋ ስለሚረክስ ነው። ርካሽ ጉልበት በማቅረብ ካምቦዲያ አንፃራዊ ብልጫ አላት። ነዳጅ ያላቸው የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ስንዴም ሆነ ሩዝ ከሌሎች ይሸምታሉ። እነኮሪያም ሆኑ ሲንጋፖር በተፈጥሮ ሀብት የሚታወቁ አይደሉም። ለም አፈር ምናምን የሚባለው ነገር የእኛን ውስንነት የሚያሳይ እንጂ ዘመናዊ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ አይደለም። ከወንዙ ሸንተረሩ በላይ ትልቁ ሀብት ሕዝቡ ነው።

ጽሑፉ አንዳንድ ቦታ ሰብዓዊ መብትን በሚጋፋ መልኩ ዛቻ ያዘለ መልዕክት ይዟል። ጸሐፊው የሚወርፏቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለምን መከላከያን ደግፈው ሠልፍ አልወጡም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ‹‹የእንትናን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም›› ይባላል። ለነገሩ አምባሳደር ሥዩም መሥፍን ባድመ ለእኛ ተሰጠ ብሎ መፈክር አስይዞ ካስወጣን በኋላ ሠልፍ ሊያንገሸግሸን ይገባ ነበር። ሆኖም መውጣትም ሆነ አለመውጣት መብት ነው። እሱን አስታኮ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ መገፋፋት አግባብነት የለውም። በቅርቡ በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች “በቤታቸው እንዲቆዩ” ውሳኔ ያሳለፉባቸው ሠራተኞች አሉ። ይህ ተቀባይነት የለውም።

ምንም እንኳ በቅርቡ ሌላኛው ወገን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ስለመፈጸሙ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም፣ ተጠያቂነት በግል እንጂ የአንድ ማኅበረሰብ ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብ ተጋሪ በመሆን አይደለም። መንግሥት ሙሉ ማስረጃ ቢኖረውም እንኳ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ከማቅረብ ውጪ የጅምላ ብቀላ ዕርምጃ መውሰድ  አይችልም። ሁለት ጥፋት አንዱን ልክ አያደርገውም።

አሁን እንደ ፋሽን የተያዘው መከላከያን በመደገፍ የሚባለው ሠልፍ አስተዛዛቢነት አለው። ይህ ጦርነት ከሌላ አገር ጋር የሚደረግ የሉዓላዊነት ጉዳይ አይደለም። ግጭቱ ቀን ጥሎን የደረስንበት እጅን በእጅ የመብላት ክፉ ዕጣ ነው። ‹‹የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ›› የምንባባልበት እንጂ፣ አሸናፊና ተሸናፊ እያልን ‘ማታ ነው ድሌ’ የምንጨፍርበት አይደለም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እርስ በርስ መተኳኮሳችን መነጋገር የማንችል እልኸኞች መሆናችንን እንጂ፣ ጀግንነታችንን የሚያሳይ ተግባር አይደለም። ይህ ግጭት መቼም ይለቅ መቼ ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን።

ግን ‹‹ትግራይ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?›› ይህን መሰል ፍረጃ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው astebeka@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡