በህግ ማስከበሩ መገባደጃ የትህነግ አንጋፋ አመራሮችና ቁልፍ የወቅቱ ባለስልጣናት ለመሸሸግ የመረጡበት ቦታ እጅግ ድንጋያማና ከፍታው ለማጥቃት የሚመች እንዳልነበር ስለ አካባቢው የሚያውቁ ሲገልጹ ነበር። በተባራሪ ሲነገር ካመሸው መረጃና የመረጃ ማስተባበያ አንጻር በወገን ሰራዊት በኩል ምን ገጠመው የሚል ጭንቀትም ሲደመጥ ነበር።
የጦርነትንና በጦርነት ቁልፍ ቦታ ይዞ የሚከላከልን ሃይል ለማጥቃት የሚከፈለውን ዋጋና ጊዜ ባለማገናዘብ ” ሰበር ዜና ናፈቀን” የሚል የፊልም ዓይነት ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ሲወተውቱ የነበሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋንያኖች እጅግ በርካታ ነበሩ። በተለይም በዩቲዩብ ሳንቲም ለቀማ ላይ የተሰማሩ ፍጹም በሚገርም ፍጥነት ሬክላም እየሰሩ ወዲያው ከይቅርታ ጋር እንዲወርድ የተደረገውን የሰቆጣ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዜና አናኝተውት ነበር።
የቲዩብ ስርጭት ጀነራሎች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋንያኖች ” ቅርብ የሆኑ” በሚል የየራሳቸውን ዜና ሲዘግቡ ቢያመሹም ከመንግስት ወገን የተሰማው ” ደስታ ለመግለጽ ጥያት አትተኩሱ፣ ለወንበዴዎች ያመቻል” የሚል የአማራ ክልል ማሳሰቢያና ምክር ብቻ ነበር። ይህ ያደናገረው ህዝብ አድሮ በነጋታው ማለዳ ምንም አለመስማቱ አሁንም ጭንቀቱን ቢያበዛውም፣ የመከላከያ ሰራዊት ክንዱን አፈርጥሞ በታላቅ ድል ላይ እየተረማመደ እንደሆነ ግን የሚጠራጠር ወገን አልነበረም።
በተቃራኒው የትህነግ የውጭ አገር ደጋፊ ከሆኑት መካከል አሉላ የሚባለው ” ከኢትዮጵያዊያን እንጀራ አትግዙ፣ ቅቤ፣ ስጋ አትሸምቱ” የሚል ጥሪ ሲያቀርብ የሰሙ ” ጨዋታው እንዳለቀ ገባው” ሲል እየተሳለቁ ዛሬ አረፋፋዱ ላይ የድል ዜና ተሰማ። ዜናው የትግራይ ክልል መሪ ደብረጽዮንን ጨምሮ መኪና ጥለው መሸሻቸውና የእግር ለእግር አሰሳው ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ አስቸጋሪ የተባለው ምሽግ ሙሉ በሙሉ መደምሰሱና በመከላከያ እጅ መውደቁ፣ በርካታ የታገቱ ንጹሃን በአንቶኖቭ ወደ ጎንደር መጓጓዛቸው በላይ በላይ ይፋ ሆነ።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የፊስ ቡክ ገጹ ላይ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜ/ጄ መሰለ መሰረትን ጠቅሶ  “የህወሃት ጁንታን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ወንጀለኞችን የማደን ተግባር ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን ተናገሩ” ሲል አወጀ።
በምዕራቡ ግንባር ፣ በእብሪት የሰከረውን የህውሃት ቡድን ከጥቅም ውጭ በማድረግ መቀሌን የተቆጣጠረው ሰራዊታችን ፣ ወደ ተንቤን አብይ-አዲ ፣ ሀገረ ሰላም የሸሹ የጁንታው አባላትን በማደኑ ተግባርም ስኬታማ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ከ700 ኪሎ ሜትሮች በላይ በሸፈነው የአውደ ውጊያ ውሎ ፣ በጥፋት ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረስ ስለመቻሉ እና የዕዝ ሰንሰለቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ስለመበጣጠሱ ሜ/ጄ መሰለ መሰረት አረጋግጠዋል ፡፡
የጁንታ ቡድኑ የፖለቲካ ማዕከል የነበረችውን የመቀሌን ለመቆጣጠር በከፍተኛ ጥንቃቄ የተንቀሳቀሰው የምዕራብ ዕዝ 24ኛ ክ/ጦር ፣ ከሌሎች ክ/ጦሮች ጋር በመሆን ያስመዘገቡት ስኬታማ ድል ፣ አሁን ላይ እየተካሔደ ላለው የማደኑ ተግባር የራሱን በጎ አስተዋፅዖ አበርክቷል ፡፡ ወንጀለኞችን የማደኑ ተግባርም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ሰለሞን ሁነኛው ( ከግዳጅ ቀጣና )

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ "ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል"

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *