“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሰርግ ሰርጎ ለቅሶ – የሰሞኑ ዘፈን – ጭራ ቀንድ ልሁን ሲል

ነጻ አስተያየ

ሲያልፍ ሁሉም ይረሳል። “ታሞ የተነሳ አምላኩን ረሳ” እንደሚባለው። ትናንት ኢትዮጵያ ውስጥ ተተክሎ የነበረው አገዛዝ ምን ይመስል ነበር? እውነት እንነጋገር ከተባለ ይህ ቀን እንዲህ በቀላሉ ይመጣል ብለን አስበን ነበር? ጠዋት የደገፍነው ፓርቲ ጀንበር ሳይጠልቅ መበተኑ ስንሰማ። ያመናቸው በርካታ “ ታጋዮች” እጅ ከፍንጅ እየከዱን አንብተን ተስፋ ቆርተን አልነበር?

እንደው ለመሆኑ ዛሬ በራያ፣ አላማጣ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራ ሕዝብ እንዲህ እየቦረቀ ሃሳቡን ይገልጻል የሚል ህልም እንኳን ነበረን? ግን ሆነ። “እገሌ ከእገሌ ሳይባል ለዚህ ታላቅ የነጻነት ቀን ላበቁን ሁሉ ክብር ይሁን!!” ብለን ሳንጨርስ አክራሪዎችና ተከፋይ ተዋንያኖች ሴራ አከፋፋይና ተንታኝ ሆነው ተነሱብን።

ኢትዮጵያችን በሴራ፣ ህዝቧ በሴራው ወላፈን እየነደዱ ሁለት ዓመታት አሳለፍን። ሶስተኛው ዓመት ተተካ። ብሄርተኞች ሲቆሉንና ሲነገረግቡን ጁናትዎቹ ይስቁብን ነበር። ቀውስ እያመረቱ ሲረጩብንና ሲያስረጩብን ሳይገባን እርስ በርስ በገባቸው ቀለብተኞች እየተነዳን መከራችንን  አረዘምን። አቤት የሰማነው የግፍ መዓት፣ አቤት ሲነጋ ምን እንደማ ይሆን እያልን ጭንቀታችን፣ አቤት ያየነው የክፋት ጥግ…

ጥጋቡ ልክ ያለፈው የትህነግ ቁንጮ በግፋና በመከራ አዝሎ ሊበላን ሲነሳ ቅድሚያ እብሪቱን የለኮሰው በሚፈራውና በሚወደደው መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ነበር። ድመት ለሞቷ እንዲሉ ምሱን አገኘ።

የሚገርመው ይህ ትዕቢት የገነገነበት ሃይል እንዲመታ ውሳኔ ሲተላለፍ፣ “ አለቀላቹህ፣ አብይ በቃው፣ ጦርነት ባህሉ ከሆነ አካል ጋር መግጠም…” ተብሎ ተዘፈነ። ያሳከምናቸው፣ የደረስንላቸው፣ ሰው ያደርግናቸው፣ በይቅርታ የታለፉ ዘፈኑ። ከዛም አልፈው “ ብለን ነበር” ሊሉ ተዘጋጁ።

ትዕቢትንና ግፍን የሚጠየፈው አምላክ ተበትነው በበረሃ ለሚንከራተቱት የመከላከያ አባላት ክብርና ብርታት ሆነ። የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እሳት ጎርሶ ተመመ።የተፈጸመበት ግፍ ያንገበገበው አንበሳው ሰራዊት ጥሙንና ረሃቡን ነክሶ ዳግም ተነሳ። በአየር ሃይል የህዋ ላይ ሙዚቃ እየታገዘ ግፈኞች ላይ አንድ ሆነው ደነሱ።

ድሉ እየተደራረበ ጫፍ ሲደርስ “ሽሚያ” ተጀመረ። ተሸናፊዎች ቀለብ በሚሰፍሩላቸው አማካይነት ተነሱ። አፈሩን ልሰው ሊነሱ የንትርክ አጀንዳ አስቀመጡ። ገና ያስቀምጣሉ። በዚሁ የተነሳ ሰርጉን ወደ ሃዘን ለመቀየር የሚተጉ እስኪመስሉ የሌለ ልዩነት የሚያራግቡ ቀስ እያሉ ወረራ ጀመሩ። ኢንተርኔቱ ሲከፋፈት በደንብ ወደ ማልቀሱ እንደምናመራ ምልክት አለ።

Related stories   የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለአሶሼትድ ኘሬስ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ኦሮሞን ለይቶ ከብልጽግና ውስጥ ማውገዝ ለምን?

በግል አሁን ያለውን የፌደራል ስርዓት እጠላዋለሁ። በርካታ እኔን መሰሎችም በተመሳሳይ የጎሳ ፌደራሊዝም እያሉ ያጣጥሉታል። ትክክልም ነው።በግሌ መጥላት ብቻ ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ ሃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ህግና ስርዓት አክብረው እንዲለውጡት የበኩሌን ጠጠር እወረውራለሁ።

ሰሞኑን ብልጽግና ” እውነተኛ ፌደራሊዝምን እገፋበታለሁ” ሲል በግልፅ ለህዝብ ማሳወቁን ተከትሎ የተነሳው አዋራ መነሻውም መድረሻውም ግልጽ አይደለም። እንደው ለመሆን ፓርቲ አቋሙን ሲገልጽ ሃሳቡን ከመቃወም በዘለለ ውርጅብኝ አስፈላጊ ነው?

ብልጽግና በአንድ ትልቁ ጥላው ስር በርካታ የክልል ፓርቲዎችን ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ ብልጽግና አንድ አቋም ሲያራምድ የሁሉም አቋም ነው። በሁሉም አቋም ላይ ተነስቶ ፓርቲውን መውቀስ፣ መተቸት፣ ድጋፍ እንዲያጣ መቀስቀስ ስልጡን አካሄድ ነው። ይደገፋል። ደግ የመማሪያ መድርከ ይሆናል። ሕዝብ አማራጭ ያይበታል።

ከዚህ ውጪ ብልጽግና እንደፓርቲ በያዘው አቋም ላይ ለይቶ አንድን ወገን መስደብ፣ ማንጓጠጥ ወይም ” ጁንታው ሲመታ አኮረፈ” በሚል መፈረጅ ማንም ቢለውም ክብረ ነክ ነው። እውነታውንም አያንጸባርቅም።

ትንሽ ግልጽ ለማድረግ በብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ ላይ ሃረግ እየመዘዙ ለይቶ ኦዲፒን ለዛውም ታዬ ደንደአን በስም ጠርቶ መኮርኮም በግል አግባብ ሆኖ አላገኘሁትም። “መርህ ይከበር፣ ለአክቲቪስቶች ጩኸት ሲባል የሚደረግ ነገር የለም” ማለት ምን ክፋት ኖሮት ለስድብ እንዳበቃ መርምሮ ማግኘት ሳይሆን ለማሰብ መሞከሩ ልብን ይነዝራል።

ለይቶ ኦሮሞ ላይ የመዝፈን እሳቤ ከሆነ እንኳን ዛሬ በፊትም አይሆንም። “የፌደራል አስተዳደሩን እውነተኛ አድርገን እናስቀጥላለን” በማለት ብልጽግና መግለጹን ተከትሎ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የሃረሪ፣ የደቡብ ህዝቦች፣ የሲዳማ፣ የአማራ … መሪዎች ስማቸው ተጠቅሶ አልተሰደቡም። ይህ የሚያሳየው ኦሮሞ ላይ ያለ ድብቅ ጥላቻ መኖሩን ነው። ሌላ ምንም ምክንያት አይቀርብበትም። እንዲህ ያለውን በመርዝ የተለወሰ አሳብ እያቀነቀኑ ስለ ብሄር ፌደራሊዝም ጥላቻ ማውራት ለድራማው ስም ለማውጣት እንኳን አይመችም።

እንደ ታዬ ደንደአ ያለ እሳቱን የዋጠና ሳይቀልጥ ያለፈን የመከራ ውጤት የሆነ ሰው ቢያጠፋ እንኳ  በጨዋ መምከር፣ መገሰጽ ወይም በጨዋ አግባብ በተፈለገው ጽንፍ ጎራ ለይቶ በሃሳብ ማበጠር ሲቻል ” የጀግና ረሃብተኛ ህዝብ በሰኮንድ ጀግና ባደረጋቸው” ሙጃዎች ዳራ እየጎረፉ መሳደብ ልክ እንደማይመጣ ማሰብ አግባብ ይመስለኛል።

Related stories   ይናገር ደሴ -"እየተዶለተብንና እየተቀመመልን ያለው ኢትዮጵያን የመበተን ሴራ ጉዳይ ለእኛ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም"

ጽንፈኛ አመለካከትን አጥብቆ በመውጋት የሚታወቅን ሰው፣ እንደገና ዳግም ጽንፈኛ አድርጎ መሳል ቢያንስ ከሚከበረው የሰላሌ ህዝብ ያጣላል። ታዬን ሕዝብ ውስጥ ልወሽቅና ልክበው ፈልጌ ሳይሆን አገራችን በቀውስ ነፍርቃ መተንፈስ በተቸገረችበት ወቅት የሰራውን ኢትዮጵያዊ ድንቅ ስራ እንደ ሰላሌዎች እንደምኮራበት ለመጥቀስ ያህል ነው።

ስቋጨው ብንጠላውም ብልጽግና “ፌደራሊዝም ወይም ሞት” ብሏል። መፍትሄው ከተቻለ ተደራጅቶ በምርጫ ማስወገድ እንጂ ገበያ እንዳጣች ኮማሪት ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ ተሸሽጎ ማሽሟጠጥና ስድድብ መወራወር እርባና አያስገኝም። እዚህ ላይ የጉዳዩ መነሻ ስለሆነው ጉዳይ ጥቂት ልበል።

ሕዝብ በራሱ አንደበት ከ30 ዓመታት በሁዋላ በነጻነት የመሰለፍ እድል አግኝቶ እንዳስረዳው፣ በተለያየ መድረክ በግል የደረሰባቸውን ሰቅጣጭ ግፍ ሲያስረዱ እንደሰማነው፣ በማስረጃነት የቀረቡትን የጅምላ ግድያ መቃብሮችና ፍርሃቱ የሚያንዘርዘራቸው እማኞች በአይናችን በብረቱ እያየን እንዳብራሩልን፣ ምንም ጥያቄ የሌለው ህጋዊ የማንነት ምላሽ ያሻቸዋል።

እኚህ ዜጎች ከነገሩን በላይ ግፍ ስለመፈጸሙ እያሰብን ከመንገፍገፍ ውጪ፣ ለነዚህ ወገኖቻችን ፍትህ ለመመኘት ሰው መሆንን እንጂ አካባቢው ጋር ቀረብ ብሎ መወለድን አይጠይ።

በአጭር ቀን በቅንጅት ለተገኘው ድልና የተገፉትን ለሚደግፍ አምላክ ምስጋና ይግባውና “ፍትህ ተዛብቷል” ብሎ የተነሳውን ህዝብ አሸንፏል። ፍትህ አሸንፋለች እንል ዘንድ በጥበብ አንድ ላይ ተነስተን አላፈርንም። ሊጠናቀቅ ጥቂት ቢቀርውም ከድሉ ማግስት የተጀመረው  “ከኔ በላይ አያገባህም” አይነት ባዶ ስካር በርካቶችን አስደንግጧል።ጉዳዩን የሚያራግቡት እነማን እንደሆኑ ስለሚታወቅ፣ ለምን ይህን ማለት እንደተፈለገ ሰብሰብ አድርጌ ወደፊት እመለስበታለሁ።

በንጹሃን ዜጎች ላይ ዳግም ተመሳሳይ ወንጀል ላለመስራት በመጠንቀቅ፣ ስሜትንና ቁጣን በመግታት ለሶስት ወይም ከዛ በላይ ዓመታት ማንነታቸውን የተሰረቁ፣ ባህላቸውና ወጋቸውን የተነተቁ ሌላውን የማያስከፋ አሳማኝና ህግን የተከተለ ውሳኔ በአስቸኳይ እስከሚሰጥ ረገብ ማለትና የትህነግን ጥቂት ጁንታ ቀብር አፋጥኖ በአርማታ ማሸጉ ላይ ትኩረት ቢደረግ የሚመረጥ ሆኖ ይሰማኛል።

የትግራይ ህዝብ ትህነግን የመውደና የመጥላት ብቸኛው ወሳኝ ሃይል ነው። ትህነግ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት። ይህንን ሁሉ አባል አሸባሪ ብሎ መፈረጅ እንደ ፖለቲካ አያስኬድም።

Related stories   ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች

ሳዳም ሁሴን ሲሰቀል የባዝ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ እንዲበተን ሲደረግ የጦር መኮንኖች ተሰባስበው የአማኤሪካን መንግስት ወኪሎችን፣ የዘመቻው መሪዎችን፣ አግባብ ያላቸውን ዲፕሎማት የባዝ ፓርቲን መበተን ችግር ያመጣል። ሰፊ ቁጥር ያለውን ጦር ሲመራ የነበረ ፓርቲ መበተን ሰራዊቱና መሪዎቹን ወደ ሌላ ሃሳብ ይመራቸዋል ቢባል አሜሪካኖቹ በበረሃው ማዕበል ድል ሰክረው ነበርና ከሳዳም ስቅላት በሁዋላ ያሳሰባቸው ነገር ስላልነበር ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት።

ያ የተበተነ ሰራዊትና መሪዎቹ ኢራን ዛሬ ድረስ የያዘችውን ቅርጽና መከራ አከናነቧት። እናም በ10 ደቂቃ ስብሰባ ትህነግን አሸባሪ ማለት ፖለቲካው ወደ ምን ያመራል የሚለውን በሰከነ መንገድ ማሰብ ወይም ሁሌም እንደምለው ፓርቲ ቀንድ ነውና ለፓርቲው መተው ይበጃል። 2 ሚሊዮን በላይ የተመዛገበ ደጋፊ ያለው ፓርቲ አሸባሪ ሲባልና ሲፈረጅ የመቸረሻ ተስፋው ምን እንደሆነ በማሰብ ሰክነን ብናስብ ደግ ነው። አለያ 360 ዲግሪ ይዞርብንና በአዲሱ ቀመር መሰረት አንድ ለአስር አስልተን ሳንተኩስ በድል አድራጊነት ስንቧርቅ ያልቀበርነው ጁንታ እንዳይበላን።

ቀንድ ቀንድ ነው። ጭራም ጭራ ነው። ቀንድ የሚተገብረውን ጭራ አይችለውም። ቀንድ መሪ ነው። ጭራ ከሁዋላ ነው። ቀንድ ጭራን ይመራዋል። የጭራ በቀንድ መመራት ወይም ጭራ የቀንድ ኋላ መሆን ተፈጥሯዊ ነው። ፖለቲካም እንዲሁ ነው። ፓርቲ ቀንድ ነው። መሪ የቀንዱ ጫፍ ነው። ጫፉን ቀንድ ማድረግ የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ጨዋታው ደግሞ ህግ አለው። ህጉም የሚከበር ነው። በተከበረ ህግ የተደረግ ጨዋታን ውጤት መቀበል ደግሞ ቀንድ ጭራ እንዲሆን የገባው ቃል ነውና ሊያከብር ግድ ነው።

ሰርግና ሃዘን ልዩ ናቸው። ሰርግ ደግሶ እየበላ እየጠጣ ሙሾና አሽሙር የሚያወርድ ምን አልባትም ቀድሞ የሰከረ ወይም ሰርጉ ላይ ልዩ ስሜት የቋጠረ ብቻ ነው። አሁንም አገር ሳንካዋን ለመቅበር ሰርግ ላይ ባለችበት ወቅት፣ ገና ሙሽሮች ሳይገቡ በስካር መዘላበድ ሰርግ ሰርጎ ሃዘን እንደመቀመጥ ይቆጠራል። ከሁሉም በላይ የአገርን ሰንኮፍ ነቅሎ ለመቅበር አንድ ሆኖ የተነሳ ሕዝብ የተሰውበት ልጆቹ ደም ሳይጠግ ድግሱን ማበላሸት ከቀደመው ክህደት አይለይምና አንስብ። ሁሉንም ሰክነን እናካሂደው።

ሰብስቤ ካሱ

 

 

 

 

 

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0