“Our true nationality is mankind.”H.G.

የመቃብር አፈሩን መልሶ ሳይጨርስ፣ የሚቀብረውን መርገምት ክርስትና እያነሳችሁ ህዝቡን አታሳቅቁት፡፡ (በድሉ ዋቅጅራ)

‹‹አልደራደርም የሚለው ቃል ውስጥ የአምባገነንነት ቡቃያ አለ፡፡›› ብዬ ነበር፡፡
‹‹መጀመሪያ ቃል ነበር!›› እንዲል መጽሀፉ አምባገነንነትም የሚጀምረው ከቃል ነው፡፡
አቶ አዲሱ አረጋ ስለፌደራላዊ አስተዳደር የጻፉትን ተመልከትኩት፡፡ እንዴት ከመከራ እንኳን መማር ያቅታል?
.
አቶ አዲሱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት የፌደራል አስተዳደር ስርአቶችን (አሃዳዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ህብረ ብሄራዊ) ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉ ሀይሎች እንዳሉ ይጠቅሱና የሚከተለውን ይላሉ፡፡
.
‹‹አሃዳዊ እና መልክኣ ምድር ፌዴራሊዝም የአስተዳደር ዘይቤዎች በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስኬዱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ሀይሎች በታሪክ ለነበሩት የብሄር ጭቆናዎች ዕዉቅና አይሰጡም፡፡ ብዝሃትን ለማስተናገድም ዝግጁነት የላቸዉም፡፡ ስለሆነም እነዚህን የአስተዳደር ዘይቤዎች ወስዶ ለመተግበር መሞከር ሀገራችንን ወደ አላስፈላጊ የግጭት አዙሪት ዉስጥ መክተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡››
.
ይህ የአምባገነንነት ቡቃያ ነው፡፡ ሀገርን የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣን የተናገሩት እንደሆነ ስናስብ ደግሞ፣ ቡቃያው ማበብና እምቡጥ መያዙን እንጠረጥራለን፡፡ አቶ አዲሱም ሆኑ ፓርቲያቸው፣ ብልጽግና አሁን ያለውን የፌደራሊዝም ስርአት ደግፈው ሀሳባቸው ማራመድ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የተቀሩትን ሁለት የፌደራሊዝም ስርአቶች፣ ‹‹ለመተግበር መሞከር ሀገራችንን ወደ አላስፈላጊ የግጭት አዙሪት ዉስጥ መክተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡›› ብሎ ማስፈራራትና ማስጠንቀቅ ምንድነው? ሀሳብ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያን ይቅርና ጠመንጃን ገንጥሎ እንደሚወጣ ከእሳቸው (አቶ አዲሱ) የተሸለ እማኝ ከየትስ ማቅረብ ይቻላል?
.
አቶ አዲሱ ከጠቀሱዋቸው ሶስት የፌደራሊዝም ስርአቶች መካከል ግጭት ውስጥ እንደሚከት በተግባር ሞክረን ያየነው እሳቸው መድህን ነው የሚሉትን ሆኖ ሳለ፣ ያልተሞከሩትን አጋጭ ብሎ መመደብና ባለሀሳቦቹን ማስፈራራት ምን የሚሉት ነው?
.
አቶ አዲሱ ያሰፈሩት የግል አስተያየታቸውን ወይም የፖራቲያቸውን ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሊያውቁት የሚገባው እያንዳንዱ ዜጋ፣ የትኛውም ፓርቲ ስለሀገሩ ያገባዋል፤ ሀሳቡን ማራመድ መብቱ ብቻ ሳይሆን ሀላፊነቱም ነው፡፡ የየትኛውም ብሄር አባል፣ እያንዳንዱ ዜጋ ስለ ሀገሩ መወያየት፣ ‹‹ይሻላል›› ያለውን መምረጥ አሁንም መብቱ ብቻ ሳይሆን ሀላፊነቱ ነው፡፡ ‹‹እኔ አውቅልሀለሁ›› መጨረሻው፣ ‹‹ያለ እኔ ሀገር አትኖርም፤ ትበታተናለች›› የሚል እቡይ ተአብዮ ነው፡፡ ዛሬ ያለመው የዚህ እቡይ ተአብዮ ቀብር ላይ ነው፡፡ በተለይ እናንተ መሪዎች መሪያችሁን ምሰሉ፡፡ የመቃብር አፈሩን መልሶ ሳይጨርስ፣ የሚቀብረውን መርገምት ክርስትና እያነሳችሁ ህዝቡን አታሳቁት፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0