መንግስት “ጁንታ” ብሎ እስኪሰይመው ድረስ ትግራይን ሲያስተዳድር የነበረው ትህነግ በትግራይ በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ከጥቅም ውጪ ማድረጉ ሲጠቆም ሰንብቷል። ዛሬ ኢትዮ ቴልኮም ይፋ እንዳደረገው ግን ትህነግ በቴሌኮም አገልግሎት ላይ ውድመት ሲያደርስ የሚያሳት ቪዲዮ ማስረጃ በማስደግፍ መሆኑንን አመልክቷል። 

ትህነግ የቴሌን ሲስተም ሰብሮ የሞባይል አገልገሎት ለመጀመር ሙከራ ማድረጉ፣ የመረጃ ዘረፋ ሰፊ ሙከራ ማድረጉ፣ እንዲሁም በትግራይ የስልክ ግንኙነት እንዳይኖር መስመሩን ከዋና ጣቢያዎቹ ማቋረጡን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል። ቢቢሲ እንደሚከተለው ዘግቦታል።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በክልሉ የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጡን እንዲሁም መጠነ ሰፊ የመረጃ መረብ ጥቃትና አገልግሎት የማስተጓጎል ሙከራዎችን ማምከኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት ከአንድ ወር በፊት ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ37 ደቂቃ ላይ በትግራይ ክልል አገልግሎት መቋረጡን አመልክተዋል።

ይህ ድርጅቱ ሰሜን ሪጅን በሚለው አካባቢ ለተከሰተውና እስካሁን በበርካታ አካባቢዎች እንደተቋረጠ ላለው አገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደምክንያት ያስቀመጡት “በመቀለ እና በሽሬ የሚገኙት ዋና ጣቢያዎች ያላቸው አማራጭ የመገናኛ መስመሮች በሙሉ በመቋረጣቸውና ከዋናው የኃይል ምንጭ የነበረው ኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ በመደረጉ” የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቴሌኮም አገለግሎት መቋረጥ በተጨማሪ በመንግሥት የኮምፒውተር ሥርዓቶችና ድረ ገጾች ላይ፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በቴሌኮም መሰረተ ልማቶችና ስርአቶች (ሲስተሞች) ላይ መጠነ ሰፊ የመረጃ መረብ ጥቃት ሙከራ መደረጉን ኢትዮ ቴሌኮም ይፋ አድርጓል።

በመቀለና ሽረ የሚገኙት ዋነኛ ማዕከላት ላይ የአገልግሎት መቋረጥ ከማጋጠሙ በፊት ችግር ሊያስከትል የሚችል ምንም አይነት መረጃ እንዳልነበረ እንዲሁም የኃይል መቋረጥ ካጋጠመመም በማዕከላቱ ያሉትም ጄኔሬተሮች ምንም ችግር እንዳልነበረባቸው የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሆን ተብሎ ኃይል እንዲቋረጥ መደረጉን ጠቁመዋል።

በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት በተከሰተበት ዕለት ከድርጅቱ ሠራተኞች ውጪ የሆኑ አካላት በሰሜን ሪጂን ውስጥ ወደሚገኙት የመቀለ እና የሽረ ዋነኛ ጣቢያዎች በመግባት አገልግሎት የማቋረጥ ድርጊት መፈጸማቸውን ከደኅንነት ካሜራዎች ላይ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተ ተገልጿል።

ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከደኅንነት ካሜራዎች ተገኙ ምስሎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በምስሉ ላይ ከኢትዮ ቴሌኮም ቅጥር ጊቢ ውጪ የመጡ የልዩ ኃይል አባላት ወደ ተቋሙ በመግባት የኃይል አቅርቦቱን አቋርጠው መውጣታቸውን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

በትግራይ ውስጥ የአገልግሎት መቋረጡ እንደተከሰተ በመላው አገሪቱ ባለው ኔትወርክ ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ ለመከላከል በኢትዮቴሌኮም አስፈላጊው ጥረት መደረጉንና ከፍተኛ መጠን ያላቸው የመረጃ መረብ ጥቃቶችን በአገሪቱ ቁልፍ ተቋማት ላይ ለማድረስ እንደተሞከረም ተነግሯል።

የአገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ የተከሰተውን ነገር በተመለከተ የተገኙ መረጃዎችን ምርመራ እያደረገ ለሚገኘው ለፌደራል ፖሊስ የተሰጠ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸው ምርመራው ሲጠናቀቅ ዝርዝር መረጃው በፖሊስ ይፋ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በመቀለ አካባቢ ከኢትዮ ቴሌኮም ዕውቅና ውጪ በሕገወጥ መልኩ ወደ ስርአቱ (ሲስተሙ) ለመግባት ሙከራ መደረጉንና የሞባይል ድምጽ አገልግሎት ለማስጀመር ሙከራዎች እንደተደረገ በመግለጽ በዚህም ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

“ከአንድ ወር በፊት አንስቶ በትግራይ ክልል በሚገኙ የኢትዮ ቴሌኮም ሁለት ዋነኛ ማዕከላት ላይ ሆን ተብሎ በተፈጸመ የኃይል መቋረጥ ምክንያት አገልግሎቶች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የስልክና የኢንትርኔት አገልግሎት አስካሁን እንደተቋረጠ ነው።” በማለትም ተናግረዋል

በዚህም መሰረት የቴሌኮም አገልግሎት ለማስጀመር ሰፊ ጥረቶች እየተከናወኑ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸው፤ በዚህም ጉዳት የደረሰባቸውን መስመሮችን በመጠገን፣ መልሶ በማቋቋምና አማራጭ ኃይል ምንጮችን በመጠቀም በዳንሻ፣ በተርካን፣ በሁመራ፣ በሽራሮ፣ በማይፀብሪና፣ ማይካድራ፣ በኮረም በከፊል የቴሌኮም አገልግሎት መጀመር እንደተቻለ ገልጸዋል።

ጨምረውም በአካባቢው የቴሌኮም አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር የኃይል አቅርቦት መቋረጥ፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረስ፣ ወደ ክልሉ የሰው ኃይል ለማሰማራት አዳጋች መሆን እና ሌሎችም ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን በትግራይ ክልል ለሳምንታት ተቋርጦ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር ድርጅቱ መጠነ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ለወራት የዘለቀው አለመግባባት ተካሮ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት በአገሪቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ በትግራይ ኃይሎች ጥቃት እንደተከፈተበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከተገለጸ በኋላ በክልሉ ውስጥ ለሳምንታት የዘለቀ ወታደራዊ ግጭት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ በአብዛኛው የትግራይ ክልል ውስጥ የኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት እስካሁን ድረስ እንደተቋረጠ ሲሆን በአንዳንድ የክልሉ ቦታዎች ግን ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በከፊል ወደ አገልግሎት መመለስ ጀምረዋል።


Share and Enjoy !

Shares
Related stories   እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እቅዷን ይፋ አደረገች፤ ዶክተር ዳንኤል የማይካድራን ጂኖሳይድ ዝም ማለቱ ክህደት ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *