“አሁን ጊዜው የአዲስ ሃሳብና የአዲስ አስተዳደር ምሪት ነው። አዲሱ አስተዳደር ትግራይን ለመምራት ሳይሆን ሕዝብ በመረጠው እንዲተዳደር መንገድ በመጥረግ ታሪክ የሚሰራበት ወቅት ነው” ሲል ነዋሪነቱ በስዊዲን የሆነው ዘሮም ይናገራል። ዘሮም አዲሱ ጊዜያዊ አመራር የትህነግ አመራሮች ገደል የከተቱትን ዴሞክራሲ በማስፈን የትግራይን ህዝብ እምነትና ክብርን ሊያሳዩት እንደሚገባ ያምናል። ” ትግራይ በራች” የሚለው ከኤሌክትሪክ አልፎ በስርዓት ግንባታ ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባል።
ዘሮም ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ጥርጣሬያቸው ተገፎ ማየት ይወዳሉ። ቀደም ሲል የተረጨው ፕሮፓጋንዳ ስህተት እንደነበር በማሳየት ህዝቡ ልቡ እንዲረጋ መሰራት እንዳለበት በፊትለፊትም ባይሆን በጎንዮሽ ውይይት ያነሳሉ። ” ጦርነቱ ገና መቸ ተጀመረ” በሚል የሚሰማው ፉከራ እያንዘረዘራቸው የሚዝቱም ትንሽ አይደሉም።
ምንም ሆነ ምን ትህነግ እድሜው ያጠረው መከለከያ ላይ የተኮሰና እጅግ ሊታመን በማይችል ጭካኔ እርምጃ የወሰደ እለት መሆኑንን ግን የሚክድ የለም። ከዛም በላይ የትህነግ አመራር በአንድ በኩል ለዘመናት ጠላት አድርጎ የቀጠቀጠው አማራ፣ በአንድ ጫፍ ሊታረቅ የማይችል ቅርሾ ውስጥ የገቡት ሻዕቢያ እየለ እንዲህ ያለ እብደት ውስጥ መግባታቸው ፍጹም ድንቁርና እንደሆነ የሚናገሩ ” አሳፈሩን” እያሉ ይወቅሷቸዋል። እናም ድጋፉ አሁን በተከፋፈለ ደረጃ ወደ ወቀሳ እየዞረ ያለ ይመስላል።
ዘሮም እንደሚለው ይህን አጋጣሚ ወደ በሳል የፖለቲካ ጨዋታ በማዞር አዲስ አሳብና አዲስ መንገድ የሚጀመርበትን መንገድ ማፍጠን አግባብ እንደሆነ ይገልጻል። ትናንት የተሰማው ዜና የዚሁ አካል መሆኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ጉዞ በተመሳሳይ ለትግራይ አዲስ ትንሳኤ ትኩረት የተሰጠ መሆኑንን አመላካች ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ የሚሰሙ ቅሬታዎችና የተረኝነት እሳቤዎች ዛሬም ባይሆን አድሮ ቂም የሚያስቀምጡ እንዳይሆኑ ቢታሰብ መልካም እንደሆነ ያሳስባል። በጅምላ ባይሆንም ግለሰቦች ስህተት እየሰሩ ነውና እርምት ቢደረግ ይላል። የመቀሌን መብራት አስመልክቶ ፋና ይህንን ዘግቧል።
