“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጉዞ አብዓላ – የታጀበ ጀንበር ምስክርነት ሶስት

አብዓላ ከመቀሌ ከ30-50 ኪሎሜትሮች አካባቢ የምትርቅ አፋር ክልል ውስጥ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት፡፡ ከሽሬ እና ከ አዲግራት የመጡት የስራ ባልደረቦቻችን አልጋ በያዙበት ሆቴል ደላላ አግኝተው በአብዓላ በኩል አድርገን በመኪና መውጣት እንደምንችልና ሰዎችን የሚያመላልሱ መኪናዎች መኖራቸውን ብዙዎችም በዛ መስመር ወጥተው ሰመራ እንደገቡ የምንሰራበት ተቋም የድጋፍ ደብዳቤ ከፃፈልን ከትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመውጫ ፈቃድ አፅፍላችኋለሁ እንዳላቸው ነግረውን እኛም በጣም ተደስተን መስሪያቤታችንም ከአዲስ አበባ ለስራ የመጡ ናቸውና ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ድጋፍ ይደረግላቸው ብሎ ለ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ፅፎልን ከደላላው ጋር በመሆንም ሁለት የስራ ባልደረቦቻችንን ጉዳዩን እንዲያስጨርሱ ወደ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደው ባልተጠበቀ ሁኔታ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የይለፍ ወረቀት መስጠት ማቆሙን እና ማንም ሰው ወደፈለገበት ምንም አይነት ፈቃድ ሳያስፈልገው መሄድ እንደሚችል ነግሯቸው ይመለሳሉ፡፡
Image may contain: 1 person, outdoor and nature
ደላላው በጣም ያጣድፈናል ደጋግሞ ምንም ችግር አለመኖሩን እና መስሪያቤታችን የፃፈልን የድጋፍ ደብዳቤ በቂ እንደሆነ ብዙ ሰዎች ሰሞኑን እንኳን አብዓላ እንደገቡ ያስረዳናል፡፡ ከመቀሌ የመውጣት ፍላጎታችን በጣም ከፍተኛ ነበርና የደላላውን ሁኔታ ልንጠራጠረው አልቻልንም፡፡ ጆሯችን መስማት የሚፈልገው አባዓላ ትገባላችሁ ሚለውን ብቻ ነበር እሱም ደጋግሞ የሚነግረን ይሄን ነውና ምንም አልተጠራጠርነውም፡፡
አብዓላ የሚወስደን ሾፌር ወዲ መቀሌ በሚል መጠሪያ ሚታወቅ ነው ስንት እንደሆንንና የመስሪያ ቤታችንን የድጋፍ ደብዳቤ ከተመለከተ በኋላ በ 10 ሺ ብር አብዓላ እንደሚያደርሰን ይነግረናል፡፡ ከመቀሌ አብዓላ በሰላሙ ጊዜ የ 30 ብር መንገድ ነው፡፡ 20 ሺህ ብር ቢለንም ከዚህ ቦታ መውጣት እጅጉን ጓጉተናልና መከፈላችን የሚቀር አልነበረም፡፡ እኔና አንደኛው ባልደረባዬ 8 ሺህ ብር በቂው ነው ብለን 8 ሺህ ይበቃሀል እንለዋለን እሱም አያዋጣኝም ነዳጅ ተወዷል ብሎ ድርቅ አለ እንዴት በዚህ ሰዓት ዋጋ ትከራከራላችሁ ክፈሉ ያለንን ከፍለን መሄድ ነው እንጂ ብለው የተቆጡንም ነበሩ፡፡ በዚህ መሃል ወደ አዲስ አበባ እየሄድን መሆኑ የተመለከቱ አንድ አባት እባካችሁ ልጆቼ ከናንተ ጋር ልሂድ ብለው መማፀን ይጀምራሉ ከእኛ ጋር ቢሄዱ ምንም ችግር እንደሌለ የምንሰራበት መስሪያቤት የሁላችንንም ስም ጠቅሶ የፃፈልን ደብዳቤ እንዳለንና የእርሳቸው ስም እዚያ ላይ ባለመኖሩ የሚፈጠር ችግር ካለ ኃላፊነቱን እራሳቸው እንደሚወስዱ አስረድተናቸው ምንም ችግር የለም ብለው አመስግነውን ጋቢና ተቀመጡ፡፡
ደላላው እኚህን ሽማግሌ ደጋግሞ የአዲስ አበባ መታወቂያ እንደያዙና የወታደር መታወቂያ እንደሌላቸው ይጠይቃቸዋል፡፡ እሳቸውም መታወቂያቸውን አውጥተው ያሳዩታል አራዳ ክፍለ ከተማ በቃ ችግር የለም ምንም አታስቡ መታወቂያቸውን አይቻለሁ ለምን መሰላችሁ አፋሮች ከዚህ ፖሊስ ኮሚሽን የተፃፈውን የይለፍ ወረቀት መታወቂያቸው የትግራይ የሆኑትን ሰዎች ትግራይ የምን መንግስት አለ እያሉ ፊታቸው ላይ እየቀደዱ እየመለሷቸው ስለሆነ ነው እናንተ የአዲስ አበባ መታወቂ ስላላችሁ በቃ ምንም አይሏችሁም ትገባላችሁ እያለ ተስፋ ይመግበናል፡፡
በስተመጨረሻም በ 8 ሺህ ብር ተስማምተንና እቃጭንን አሳስረን እንግዳ ተቀባይዋን ተሰነባብተን ጉዞ ወደ አብዓላ፡፡
ከመቀሌ ከተማ ወጥተን 10 ያህል ኪሎሜትሮችን እንደተጓዝን ወደ ማይጨውና የሚወስደውን መንገድ ትተን ወደ ግራ ስንታጠፍ አንድ ፖሊስ በእጁ ቁም የሚል ምልክት ለሾፌሩ ያሳዋል ሾፌሩ ወዲያው አልቆመም ይሄኔ ፖሊሱ ክላሹን ማነጣጠር ጀመረ ሾፌሩ መኪናውን አቁሞ ፖሊሱን በእጁ ና የሚል ምልክት አሳይቶ ይጠራዋል ፖሊሱም ክላሹን ከትከሻው አኑሮ ጅንን ንጥር እያለ ይመጣል፡፡ ፖሊሱን ሳየው ማመን አልቻልኩም በጣም ለጋ ፂም ማብቀል እንኳን ያልጀመረ 14 ዓመት የማይሞላው ህፃን ነው በእርግጥ እኩዮቹ የሚሆኑ በሱ እድሜ የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላትንም በአይናችን አይተናል፡፡
ቀጥሎ በቁጥር አነስ ያሉ ቤቶች ያሉባት ከተማ ለመሆን እየጣረች ያለች ቦታ ስንደርስ ሁለተኛ ኬላ አጋጠመን፡፡ የፖሊሰ መለዮውን ከነ ኮፊያው ከአንገቱም እስጋርፕ የጠመጠመ ፖሊስ እንደተለመደው ጥብርር ኮራ እያለ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ሾፌሩን ይጠይቀዋል፡፡ ወዲ መቀሌም መስሪያቤታችን የፃፈልንን ደብዳቤ እያሳየ ፖሊስ ኮሚሽን የይለፍ ወረቀት መስጠት ከዛሬ ጀምሮ ማቆሙንና ማንም ማለፍ የፈለገ ማለፍ እንዲችል መወሰኑን ወጥሮ ይከራከራል፡፡ ፖሊሱ አይሆንም ማለፍ አይቻልም አለ፡፡ ፖሊሱን ቢለምነውም ምንም ሊሰማው አልቻለም ይባስ ብሎ ወንበር ከቤት አውጥቶ ፀሀይ መሞቅ ጀመረ፡፡
ከአንድ 40 ደቂቃ ጥበቃ በኋላ ወዲ መቀሌን (ሾፌራችንን) ከኋላ አስከትሎት ወደ ጓሮ ይወስደዋል፡፡ በቃ ግባልኝ እያለው ነው እንሄዳለን ብለን ተስፋ አደረግን ምን ሊለው እዛ እንደወሰደው ባናውቅም ሲመለሱ የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡ የፖሊስ ኮሚሽን የይለፍ ወረቀት የያዙ መኪናዎች ወረቀታቸውን እያሳዩ እያለፉ ነው እንደኛው ፖሊስ ኮሚሽን የይለፍ ወረቀት መስጠት አቁምያለሁ የፈለጋችሁበት ያለምንም ፈቃድ መሄድ ትችላላችሁ ያላቸው ደግሞ አታልፉም ተብለው ከኛ ኋላ ረድፋቸውን ይዘው ተደርድረዋል፡፡
Image may contain: one or more people, sky, outdoor and nature
የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን መምሪያ ሀላፊ እና ምክትሉ ናቸው የይለፍ ወረቀት መስጠት አቁመናል ያሉን ታድያ ለእነኚህ እንዴት ተሰጣቸው ደላላው ሸውዶናል እንዳንል ከደላላው ጋር ለነበሩት ባልደረቦቻችን ነው የይለፍ ወረቀት መስጠት ማቆማቸውን የነገሯቸው፡፡ በዚህ መሃል ብዛት ያላቸው የተባበሩት መንግስታት መኪኖች ሰራተኞቻቸውን ጭነው የተመድን አርማ እያውለበለቡ በክልሉ ልዩ ሀይል ታጅበው እያለፉ ነበር፡፡ በአገራችን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለመግባት የኬኒያን ወይ የሱዳንን ድንበር እንደምናቋርጥ አይነት መታገታችን በተቃራኒው የተመድ ሰራተኞች ታጅበው ሲያልፉ ስናይ ሁላችንም አዘንን፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋል ፖሊሱ ሾፌራችንን እለፍ ይለዋል እሱም ፊቱን አብርቶ ሂዱ ብሏል ብሎን ገና ሞተር ከማስነሳቱ ፖሊሱ ሀሳቡን ይቀይርና 1 ሰዓት ለሚጠጋ ጊዜ ካቆየን በኋላ የኔ የበላይ አለቃ ስላለ እሱ ከመጣ በኋላ ትሄዳላችሁ እስኪመጣ መኪናህን አዙርና ጠብቁት ብሎ ሌላ መርዶ ይነግረናል፡፡
ስልክ ስለማይሰራ አለቃው በስንት ሰዓት እንደሚመጣ አይታወቅም ያለን አማራጭ ይመጣል በሚል ተስፋ መጠበቅ ብቻ ነበር፡፡ ከ 1፡30 በላይ ከቆየን በኋላ አለቃው መጥቶ እንድናልፍ ተወሰነ፡፡
ከፊታችን የሚጠብቁን ሁለት የመጨረሻው ኬላዎች ላይ ምን እንደሚገጥመን ባናውቅም ይሄንን ኬላ በማለፋችን የተሰማን ደስታ ቀላል አልነበረም፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች ጉዞ በኋላ ጠመዝማዛውን የቁልቁለት መንገድ መውረድ ጀመርን፡፡ በስራ አጋጣሚ አካባቢውን ከዚህ ቀደም የሚያውቁት የስራ ባልደረቦቻችን ይሄን ተራራ እደወረድን አብዓላ ከተማን እንደምናገኘውና በጣም እንደቀረብን በጣታቸው እያሳዩን እዚህች ነች በቃ ብለው ያስረዱናል፡፡ ደስታም፣ ፍርሃትም እናልፍ ይሆን አናልፍ የሚል ጭንቀትም ብቻ ሁላችንም ዝብርቅርቅ ያለ ስሜትውስጥ ነን፡፡ ሾፌራችን ወዲ መቀሌ የመኪናውን ፍጥነት ገታ አደረገና ዞር ብሎ ይሄን ተራራ ሁለቴ እንደዞራችሁት አብዓላ ነው እኔ እዛ ከደረስኩኝ ታርጋው የትግራይ በመሆኑ ምክንያት መኪናውን ማውጣት ስለማልችል ተባበሩኝ፡፡ ገብቼ መውጣት የምችል ቢሆን ሰመራ የሚወስዳችሁን መኪና አገናኛችሁ ነበር እዚህች ቅርብ ነች ደርሳችኋል በእግራችሁ ቀጥ ብላችሁ መግባት ነው ብሎን እኛም እቃችንን አውርደን ሻንጣችንን እየገፋን ቁልቁለቱን ተያያዝነው፡፡
ፎቶ በማንሳት አብዮት ካላስነሳን ከሚሉት ባልደረቦቻችን አንደኛው ከኋላችን ሆኖ አንዴ ዙሩ ለማስታወሻ እያለን እኛም ዞረን ፈገግ እያልንና ሻንጣችንን እየጎተትን ፎቶ ያነሳናል፡፡ የመጀመሪያውን ዙር እንደተጠማዘዝን ፒካብ መኪና ከእኛ መሃል ላለችው ብቸኛዋ ሴት እንዴ በእግራችሁ በጣም እሩቅ እኮ ነው እስከ ኬላው እንኳን እናድርስሽ ብለው እቃዋን አስገብተውላት ይዘዋት ሄዱ፣ ባለፒካፑ በጣም እሩቅ እኮ ነው ያላት ነገር ግን ምንም አልጣመችኝም፡፡ ምን እየተፈጠረ እንዳለ ግራ ተጋባሁ ቦታውን እናውቀዋለን የሚሉን ከኛው ጋር ያሉት ባልደረቦቻችን ደርሰናል ይላሉ ሾፌራችንም ደርሳችኋል ብሎን ወደ መቀሌ ተመልሷል ይሄ ሰውዬ ደግሞ ይሄ ሁሉ መንገድ በእግራችሁ እሩቅ እኮ ነው እንዴት ይለናል? ሌሎች ዶልፊን መኪኖች ደግሞ ህዝብ ጭነው እያለፉ ነው እኛን ለምን አወረደን? እያልኩ ከራሴ ጋር እያወራሁ ነው በሠዓቱ ይሄን ጥርጣሬዬን ለማንም የመናገር ድፍረቱ አልነበረኝም ለራሴ እንኩዋን የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እያልኩ ነበር የምነግረው፡፡
የሰዓቱ መምሸት እንጂ መንገዱ የፈለገውን ያክል እሩቅ ቢሆን የእግር ጉዞው ያውም በሃስፋልት መንገድ ብዙም ከባድ አይሆንብንም ብቸኛዋ አብራን ያለች ሴት ባልደረባችን ደግሞ መኪና አግኝታለች እያልኩ ራሴን እንደተለመደው ተስፋን እመግበዋለሁ፡፡
ሁለተኛውን ዙር እንደዞርን ቅድም በክልሉ ልዩ ሀይል ታጅበው ሲያልፉ ያየናቸው የ ተ.መ.ድ መኪናዎች በግራ በኩል ተደርድረው ቆመዋል፡፡ በቀኝ በኩል ደግሞ የህዝብ ማመላለሻ መኪናዎች፣ የጭነት አይሱዙ እና የቤት መኪናዎች ተደርድረው ቆመዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መኪናዎች ተሰልፈው ስናይ ከመቅፅበት ተስፋችን እየመነመነ ፊታችንም እየጠወለገ መጣ እነሱ ማለፍ ያልቻሉትን እኛ ከቶ እንደምን ማለፍ ይቻለናል? አንዲት ቪትዝ መኪና እና ዶልፊን የህዝብ ማመላለሻ ኬላውን አልፈው ሲሄዱ ስናይ ሌላ ተስፋ በውስጣችን ይለመልም ጀመር፡፡ ኬላው ጋር ከቆሙት መኪናዎች ወርደው እዚም እዚያም የቆሙ ሰዎች በግራ እጃችን ቦርሳ አንጠልጥለንና በቀኝ እጃችን ሻንጣችንን እየጎተትን ከተራራው ላይ ስንወርድ መዳፋቸውን በአፋቸው ጭነው በአዘኔታ ይመለከቱናል፡፡
ከኬላው ደረስን፡፡ ሜዳ ላይ በትኗችሁ ተመለሰ? እንዴት ውረዱ ሲላችሁ ሜዳ ላይ እሺ ብላችሁ ትወርዱለታላችሁ? አውርዷቸው ነው? ሌላኛው ይጠይቃል ምን ላይ እኮ ነው ጥሏቸው የተመለሰው ምን አይነት ግፈኛ ነው በማርያም፡፡ ፀጉራችን ቆመ ፊታችን አመድ መሰለ መልስ ለመስጠት የሚበቃ ትንፋሽ አልነበረንም፣ በዛ ላይ ሰዓቱ እየመሸ ነው ተመለሱ ቢሉን በምን ልንመለስ ነው?፡፡ ሰውነቱ ደልደል ያለ ረዥም ወጣት የልዩሀይል አባል 1,000.00 ብር ነው የተቀበላችሁ በአዎንታ አንገታችንን ነቀነቅን ተበሳጨ እሺ ታርጋውንስ ይዛችኋል ለክፉም ለደጉም ብዬ መዝግቤው ነበርና አዎ ብዬ ቁጥሩን ተናገርኩ፡፡ አጠገቡ ላለው የልዩሀይል አባል ታርጋውን እንዲመዘግብ ነግሮት መኪናው ይያዛል የትም አያመልጥም እንዲህ እንዴት ይደረጋል? ለመሆኑ የት አደረስኳችሁ ብሎ ነው ያወረዳችሁ? አብዓላ እየተቅለሰለስን እንመልሳለን ሳቅ እያለ አብዓላ እኮ ገና 10 ኪሎሜትር ይቀራል እሩቅ እኮ ነው ይሄን ሁሉ መንገድ በእግራችሁ ሂዱ ብሎ ሜዳ ላይ አወረዳችሁ በዚ መከላከያ ምሽግ ይዟል በዛ የአፋር ልዩ ሀይል ሰፍሯል እንዴት ብላችሁ ነው የምታልፉት? ቋንቋ አትችሉ፣ ፊታችሁ እንኳን አፋር አይመስል በዚህ ምሽት እሺ ምን ልትሆኑ ነው? ሰራተኞች ናችሁ? አዎ ባንክ ነው የምንሰራው ንግድ ባንክ ነው? አይ የምንሰራበትን ባንክ ተናገርን መታወቂያችንም ለማውጣት ዳድቶናል፡፡ መታወቂያ በብዙ ቦታዎች ነገሮችን አቅልላልናለች፡፡ ፀጉረ ልውጥ በተባልንበት ሁሉ አድናናለች ምንም ነገር ስንጠየቅ ቀድመን መዥረጥ የምናደርገው እሷን ነው፡፡ መውጫስ ይዛችኋል? ወደ መሬት አቀርቅረን ባንኩ የፃፈልንን ወረቀት ይዘናል ፖሊስ ኮሚሽን ሄደን መውጫ ቀርቷል ያለመውጫ ማለፍ ይቻላል ብለውን ነው የመጣነው፡፡
ልዩ ሀይሉ ሁኔታችንን በደንብ ተረድቶታል ጭንቀታችን ገብቶታል መንገዱ ቢከፍትልን ሁላችንም 10ሩን ኪሎሜትር በምሽትም ቢሆን ብንሄድ ደስታችን ነው፡፡ ሂዱ ብላችሁ ያውም በዚህ ምሽት የትግራይ መንግስት ለስለላ የላካችሁ ነው የሚመስላቸው እናንተ ምንም የምታውቁት ነገር የለም ምንም በማታውቁት ነገር ቢገድሏችሁስ? ይኸው የ ተ.መ.ደ ሰዎች እንኳን ቆመው የሚቀይራቸው ሌላ መኪና ከዛ እስኪመጣላቸው እየጠበቁ ናቸው፡፡ ተረጋግታችሁ እዛው መቀሌ ባላችሁበት ብትሆኑ ነው የሚሻላችሁ አይዟችሁን እኔ ኮማንደር እገሌ እባላለሁ አትጨናነቁ እዚህ ፒካፕ መኪና አለ እኔ ወደ መቀሌ እሸኛችኋለሁ ገንዘባችሁም ይመልሳል ወይ ደግሞ የይለፍ ወረቀቱን አፅፋችሁ እዚህችው በነፃ መልሶ ያመጣችኋል ነገ 3 ሰዓት ፖሊስ ኮሚሽን ስለምመጣ እዛው አገኛችኋለሁ፡፡
በኮማንደሩ ደግነት ሁላችንም ተደመምን ከልባችንም አመሰገንነው የሱን ያክል የተረዳን ሰው ገጥሞን አያውቅም፡፡ የመስሪያቤታችን ሀላፊዎች እንኳን የእሱን ግማሽ ሊረዱን ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ኮማንደሩ በእድሜው ወጣት እንዳየነውም በጣም ቅን አሳቢ የሆነ ሰው ነው ይህ ኮማንደር የሚገኘው ድንበር ላይ ነው ምናልባትም በአብዓላ በኩል ጦርነቱ ሲጀመር ህይወቱ ያልፍ ይሆናል ጦርነት እንዲህ ያሉ ነገ አገራችንን ሊጠቅሙ የሚችሉ ቅን አሳቢ የሆኑ ሰዎችን የሚበላ አውዳሚ ነገር መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡ ተረጋግታችሁ እዚሁ ጠብቁኝ ብሎን ወደ ስራው ተመለሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ስንመጣ በእግራቸው ሲጓዙ ያየናቸው ሁለት ፖሊሶች ከኬላው የደረሱት፡፡ ሁለቱም ክላሽ አንግተዋል፡፡ የት ናችሁ ኮማንደሩ ይጠይቃቸዋል፡፡ መንገድ ተከፍቷል ተብሎ ልናልፍ ነው፡፡ ቆጣ ብሎ መታወቂያ? መታወቂያ አልያዝንም ሁለቱም ፖሊሶች መለሱ፡፡ በሚያስደንቅ ፍጥነት የሁለቱንም ፖሊሶች ክላሽ ካርታውን ከመቅፅበት ፈትቶ የያዙት ክላሽ ዱላ አድርጎባቸው ወደ ማረፊያ ተላኩ፡፡
በመጨረሻም ይህ ኮማንደር የይለፍ ወረቀት ባለመያዛቸው ምክያት ወደመጡበት መቀሌ እንዲመለሱ በተደረጉት መኪናዎች ያለምንም ክፍያ ሶስት ሶስት ሆነን በትርፍ እንዲጭኑን አድርጎ በምሽት ወደ መቀሌ ተመለስን፡፡ ወደ መቀሌ ስንመለስ ታድያ ስንወጣ ከገጠመን በላይ በየ ኬላውም ሆነ ምንም ኬላ በሌለበትም ኃይለኛ ፍተሻ ነበር የገጠመን፡፡ አንደኛው ፈታሽ ታድያ ላፕቶፕ ኮምፒውተር የያዛችሁ ወደኔ አምጡ አለ ከኋላችን የተቀመጡ ሁለት ተሳፋሪዎች ላፕቶፖቻቸውን ይሰጡታል አንደኛውን ላፕቶፕ ከፍቶ መብራቱን ካረጋገጠ በኋላ ላፕቶፑን እንደበራ ለባለቤቱ መመለስ ሲችል ለመዝጋት ኪቦርዱን ይፈትሻል የላፕቶፑን ጀርባ እያገላበጠ በባትሪ ያስሳል መከራውን ያያል ተሳፋሪው በምሬት ኸረ መሽቶብናል እያለ ያጉረመርም ጀመር ባለላፕቶፑ አትቸገር አጥፈህ ስጠኝ ችግር የለውም ይለዋል ፈታሹም እየሳቀ አጥፎ መለሰለት ሌላኛውን ላፕቶፕ በእጁ አልነካውም ውሰድ ውሰድ ብሎት እኛም ጉዟችንን ቀጠልን፡፡
መቀሌ እንደደረስን የተከዜ ግድብ ተመቷል በሚል ውዝግብ ለቀናት የጠፋው መብራት መጥቶ እንደ አጋጣሚ ብቻዋን ውር ውር ምትል ባጃጅ አግኝተን ቀን ወደ ተሰነባበትናቸውና ወደ ነበርንበት ማረፊያችን አመራን፡፡
እንዴት እንዲህ እንሸወዳለን? ከ ስምንት ሰው እንዴት አንድ ሰው እንኳን አይባንንም? እያልን ሁላችንም በገጠመን ነገር ተበሳጭተናል፡፡ ከንግዲህ የትም እግሬን አላነሳም የመጣውን እዚሁ እቀበላለሁ የሚሉ ሰዎችም በረከቱ፡፡
ከሁላችንም በጣም የመሄድ ፍላጎት የነበረው አንደኛው ባልደረባችን ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጠም የሁላችንም ፍላጎት በምንም አድርገን ከዚህ ክልል መውጣት ቢሆንም የእርሱ ጉጉት ከሁላችንም የተለየ ነበር፡፡ ኮማንደሩ ለነገ እንደቀጠረን ትዝ ሲለን እንዳየነውም ኮማንደሩ እንደሚረዳን እርግጠኞች ነንና የመጨረሻ እድል በ ኮማንደሩ በኩል መሞከር እንዳለብን ተስማማን።
ታድያ ቁርሳችንን እንኳን ሳንበላ ለ ሶስት ሰዓቱ ቀጠሮ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ሲል ፖሊስ ኮሚሽን በር ላይ ተሰይመናል፡፡ ትላንት የይለፍ ወረቀት ባለመያዛቸው ምክንያት አብረውን የተመለሱ ሌሎች ሰዎችም እንደኛው በጊዜ ፖሊስ ኮሚሽን ደርሰዋል፡፡ የፖሊስ ኮሚሽኑ ኃላፊን በድጋሚ አናግረውት ምንም ሊተባበራቸው ባለመቻሉ ምክንያት በእግራቸው አፋር ለመግባት እየተነጋገሩ ነው ከዚህ ውስጥ ወደ 4 የሚጠጉት ሴቶች ናቸው፡፡
ከጦርነቱ ባልተናነሰ ባንኮች በድንገት ስራ በማቆማቸው ምክንያት ህዝቡ ምንም ገንዘብ በእጁ ባለመያዙ የደረሰበት ጉዳት በቀላል የሚገመት አልነበረም፡፡ በእግራችን አብአላ ካልገባን ሲሉ ከነበሩት መሃል አንደኛው ከአባዓላ ስንመለስ ያለበትን ሁኔታ እንደነገረኝ ሚስቱና ሶስት ልጆቹ ያሉት አዲስ አበባ ሲሆን እሱ ለ አንድ ሳምንት ስራ ሽሬ መጥቷል ሽሬ ስራውን እንደጨረሰ ሽሬ ደርሼ መቀሌ ያለችውን እናቴን ሳላገኝ እንዴት እመለሳለሁ በማለት እናቱ ጋር ለ አንድ ቀን አድሮ በነጋታው ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ይወስናል ታድያ መቀሌ የገባበት ለሊት የጦርነቱ ጅማሬ ሆኖ መንገዶች ይዘጋሉ በረራ ይቋረጣል አዲስ አበባ ያለችው ባለቤቱ ስራ የሌላት በመሆኑ ምንም የገቢ ምንጭ የላትም እቤት ሶስት ልጆች አሉ በሳምንት ጊዜ ውስጥ እመለሳለሁ ብሎ በማሰቡ ለባለቤቱና ለልጆቹ ለቀለብ እንኳን የሚሆን ያስቀመጠላቸው ገንዘብ አልነበረም ከዚህ ገንዘብ እንዳይልክ ባንኮች ሁሉ ዝግ ናቸው፡፡ ተክዞ የኤርትራ ጦርነት ጊዜም እንዲሁ እንደቀልድ ነበር ቤተሰብ ለ 20 ዓመታት ተበታትኖ እንዲቀር የሆነው አሁን ጦርነቱ ምን ያክል ጊዜ እንደሚፈጅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ከትግራይ ክልል ፖሊስ መምሪያ ፊት ለፊት ቆመን ኮማንደሩን እየጠበቅነው ልዩሀይሎች ወዲህ ወዲያ ይራወጣሉ ግማሾቹ በመከላከያ ፒካፕ ተጭነው ይመጣሉ የተቀሩት ደግሞ ወደ ስምሪታቸው ተጭነው ይወሰዳሉ፡፡ ኮማንደሩን ከቀጠራችን በጣም ቀድመን ለረጅም ሰዓት ብንጠብቀውም ልናገኘው አልቻልንም በእርግጥ ኮማንደሩ ቢመጣም የተፃፈልን የድጋፍ ደብዳቤ የያዙት ባልደረቦቻችን ደብዳቤውን ይዘው በቀጠሯችን መሰረት አልተገኙም እስካረፉበት ሆቴል ሄደን ብናፈላልጋቸውም ምንም መልዕክት ሳያስቀምጡልን ለቁርስ እንደወጡ አልተመለሱም በዚህ ሁላችንም ክፉኛ ተበሳጭተናል፡፡
ጠብቀን ጠብቀን ሲደክመን የጉዞውን ነገር ሰርዘን ወደ አፄ ዮሀንስ ትምህርት ቤት አመራን በዚህ ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ ሰዎች ሰልፋቸውን ይዘው በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በኩል ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወዳሉ ቤተሰቦቻቸው ስልክ ለመደወል እየተመዘገቡ ናቸው፡፡ እኛም ወደ ቤተሰቦቻችን ለመደወል ሰልፋችንን ይዘናል ወደ ግንባር እየተመሙ ያሉ የትግራይ ልዩ ሀይሎች የትግራይን ባንዲራ ይዘው ክላሻቸውን አንግተውና ከራሳቸውም ፎጣ ጠምጥመው በኤፍኤስአር መኪናዎች በአይሱዙዎች እና በባሶች ተጭነው ህዝቡን እጃቸውን ከፍ አድርገው እናሸንፋለን እያሉ ምልክት እያሳዩ ይሰናበታሉ ስልክ ለመደወል የተሰለፈው ህዝብና መንገደኛው በጭብጨባና በጩኸት ከጎናችሁ ነን እያለ ይሸኛቸዋል፡፡
ሁላችንም ከመቀሌ ለመውጣት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ አዝነን እዚሁ ሆነን ፍፃሜውን እንይ ይሄም አንድ እድል ነው ብለን ነገር ግን ደግሞ ጦርነቱ እየተፋፋመ ሲመጣና ህወሀት ሽንፈት መቅመስ ሲጀምር በዚህ የሚቆጡና ንዴታቸውን መቆጣጠር የሚሳናቸው ጥቂትም ቢሆኑ የመቀሌ ነዋሪዎች መኖራቸው የሚቀር ባለመሆኑና ህወሀትም እንዲህ ያለ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለፖለቲካው መጠቀሚያ የሚያውል በመሆኑ ከመሀላችን አንድም ትግሪኛ መናገር የሚችል አለመኖሩ ተጨምሮበት ጉዳት እንዳይደርስብን የቻልነውን ያህል መጠንቀቅ እንቅስቃሴ አለማብዛት ከተወሰኑ ምግብ ቤቶች፣ ከአንድ የጀበና ቡና ከሚሸጥበትና ፑል ተጫውተን ማናውቅም ጭምር ምንም ጊዜ ማሳለፊያ አማራጭ ስላልነበረን መጫወት ጀምረን ነበርና ከአንድ ፑል መጫወቻ ቤት በስተቀር እንዳንሄድ ለደህንነታችን ጥሩ ስላልሆነ ወዴትም ሌላ ቦታ እንዳንንቀሳቀስ ተስማምተን ኑሯችንን በዚህ መልኩ መግፋት ጀመርን፡፡
እንዲህ ያለውን ኑሮ በጀመርን በሶስተኛው ቀን 5 ሌሎች ባልደረቦቻችን ከ ሽሬ እና አፅቢ ተነስተው መቀሌ የተቀላቀሉን ሲሆን ከ አስራስድስታችን አስራሶስታችን መቀሌ ተሰባስበናል ቀሪዎቹ ሁለቱ (አንድ ወንድ እና አንድ ሴት) አድዋ ሲሆኑ መውጫ መንገድ አግኝተው ወደ አዲስ አበባ ይመለሱ አይመለሱ ባሉበትም ምን ይሁኑ የምናውቀው ነገር የለም አንደኛው ደግሞ ሽሬ ከተላኩት ጋር የነበረ ቢሆንም ሽሬ የነበሩት ወደ መቀሌ ሲመጡ እሱ ቀደም ብሎም ሽሬ ውስጥ ለብቻው ይንቀሳቀስ ስለነበር እዚያው ሽሬ ቀርቷል፡፡ ይህ ልጅ የእኛን ቢሮ በቅርቡ የተቀላቀለና ሽሬንም ሆነ ትግራይን በአጠቃላይ ምናልባት የማያውቅና ለስራውም ለአገሩም አዲስ በመሆኑ ለብቻው መቅረቱ ቢያሳስበንም በፍላጎቱ መቅረቱን ስንሰማ የጦርነት ልዩ ፍቅር ያለው ይሆናልና መልካም ባህላዊ ጨዋታ ይሁንለት እግዚአብሄር ካለ ጦርነቱ ሲያበቃ እንገናኝ ይሆናል ብለን ተመኝተን ከዚያ ወዲህ ስለዚህ ልጅ አንስተን አናውቅም፡፡
በዚህ ወቅት ሁመራ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ውሎ ነበርና ከሽሬ የመጡ ባልደረቦቻችን ሽሬ ስላለው ነገር ሲነግሩን ከሁመራ ብዛት ያለው ህዝብ እናቶች ልጆቻቸውን አዝለው ወንዶች መሸከም የሚችሉትን ንብረት ተሸክመው ከብቶቻቸውን እየነዱና በእርሻ መኪናዎች እየተጓዙ ሽሬ መስፈራቸውንና ሽሬ በአንድ በኩል እጅግ ብዙ ቁጥር ባለው ጦርነቱን ሸሽቶ በተሰደደ ህዝብ ተጨናንቃ በሌላ በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የትግራይ ልዩሀይልና ሚሊሻ ተከማችቶባት ሚጎችና ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች በፍጥነት የሚርመሰመሱባት ሆናለች፡፡
ከዚህ ቀደም መንግስት ሽሬን ይዥያለሁ ብሎ ነበር ታድያ ይሄ ሁሉ የትግራይ ልዩሀይልና ሚሊሻ ከየት መጣ? ስንላቸው መንግስት ሽሬን ይዥያለሁ ሲል የሽሬ ህዝብ በሳቅ ከማለቅ ለጥቂት ነበር የተረፈው ዜናውን ስናይ እኛም ገርሞን ነበር፡፡ ጦርነት ስለሆነ መንግስት ለዚያ የሚሆነውን ስልት እየተጠቀመ ሊሆን እንደሚችል አስበን የነበረውም ሁኔታ በጣም አስፈርቶን ነው ወደ መቀሌ ለመምጣት የወሰንነው ነበር ያሉን፡፡
በስተመጨረሻም ሽሬ ላይ ለብቻው ቀርቶ የነበረው የስራ ባልደረባችን በእግሩ ከሽሬ ጎንደር ድረስ ተጉዞ ቀድሞን አዲስ አበባ መድረሱን ሰማን። በጣም የተባበረንና በማታ ሜዳ ላይ መመለሻ ሳይኖረን ተጥለን በነበረበት ሰዓት ያለውን ሁኔታ አስረድቶን ወደ መቀሌ እንድንመለስ የተባበረን ኮማንደር በህይወት መትረፉን ሰማን። ደስም አለን።
አድዋ ስለቀሩት ሁለት ባልደረቦቻችን እስከአሁኑ ደቂቃ ስላሉበት ሁኔታ የሰማሁት ነገር የለም። ፈጣሪ ባሉበት ይጠብቃቸው።
ሁለተኛ ዙር ጉዞ ወደ አብዓላ ይቀጥላል…
በመቀሌ የባንክ ባለሙያ የነበረው ታጀበ  ምስክርነት ሶስት

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0