የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የተመረቁ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት በማረጋገጥ የህዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ28ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎቹን በዛሬው እለት አስመርቋል።

በምርቃ መርሃ ግብሩ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እንደገለጹት፤ ተመራቂዎች ለአገራቸው ሰላምና ልማት በመስራት ህዝባቸውን ማገልገል አለባቸው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ቀጥለውና የተለያዩ ችግሮችን አልፈው በዛሬው እለት ለምረቃ በመብቃታቸውም ‘እንኳን ደስ ያላችሁ’ ብለዋል።

ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያካበቱትን እውቀት ሕዝባቸውን ለማገልገል እንዲጠቀሙበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በክልሉ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተማሪዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ላደረጉት አስተዋጽኦም ዶክተር ሙሉ አመስግነዋል።

በቀጣይም የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመሆን የከተማዋን ልማት እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

በዛሬው እለት ከተመረቁ ተማሪዎች አንድ የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ሲሆን የተቀሩት የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል 38 በመቶዎቹ ሴቶች ሲሆኑ የውጪ አገር ተመራቂ ተማሪዎችም እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎችም በውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው ለዚህ በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላም ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው በቅንነትና በታታሪነት አገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝም ታውቋል።

በምርቃ መርሃ ግብሩ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላት ታድመዋል።

(ኢዜአ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *