እነዚህ ጩቤ፣ ክላሽንኮቭ እና ቀስት ይዘው ነበር ያላቸው ከ20 እስከ 30 የሚሆኑት ጥቃት አድራⶄች አካባቢውን ለቀው መሄዳቸውን በመግለጽ “ብዙም ጉዳት ያልደረሰብን ሰዎች እንደምንም ብለን ከአካባቢው አመለጥን”

ተከታዩ የቢቢሲ ዘገባ ነው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀ ተከታታይ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸ በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል።

በዚህም ሳቢያ የሚፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስን ያካተተ ኮማንድ ፖስት በስፍራው ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋል። ነገር ግን በአካባቢው ባሉ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ከአንድ ወር በፊት ከቡለን ወረዳ ወደ ቻግኒ ይጓዝ በነበረ የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው። በወቅቱ ከግድያው ካመለጡት ውስን ሰዎች መካከል የቡለን ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት በጥቃቱ ቆስሎ በሕይወት መትረፍ መቻሉን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወጣቱ ተኩሱ ሲከፈት ቆስሎ ሲወድቅ ሌሎች ሰዎች ተመትተው እላዩ ላይ በመውደቃቸው ገዳዮቹ እንደሞተ አስበው ሲሄዱ ከጥቃቱ ከተረፉ ሌሎች ሰዎች ጋር ወደ ጫካ በመግባት እንዳመለጠ ይገልጻል።

ከቡለን ወደ ቻግኒ ይጓዝ የነበረው ይህ ተሽከርካሪ፣ ዕለቱ የገበያ ቀን ስለነበር በርካታ ሰዎችን ጭኖ እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣቱ፣ ቂዶ የምትባል ሰፈር ሲደርሱ ጫካ ውስጥ ተደብቀው በነበሩ ታጣቂዎች ጥቃቱ ተፈጸመባቸው።

“ተኩስ ከፈቱብን፣ ከዚያም ሹፌሩ መኪናውን አቆመው። ሁሉም መጥተው ብዙዎቹን ተሳፋሪዎች ገደሏቸው። እኔ ላይ አስከሬን ተጭኖኝ ስለነበር ቆስዬ ለመትረፍ ቻልኩ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

እነዚህ ጩቤ፣ ክላሽንኮቭ እና ቀስት ይዘው ነበር ያላቸው ከ20 እስከ 30 የሚሆኑት ጥቃት አድራⶄች አካባቢውን ለቀው መሄዳቸውን በመግለጽ “ብዙም ጉዳት ያልደረሰብን ሰዎች እንደምንም ብለን ከአካባቢው አመለጥን” ብሏል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

የክልሉ ባለስልጣናት ይህን አይነቱን ተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን “አማጺያን፣ የህወሓት ተላላኪ እና ከኦነግ-ሸኔ ጋር ያበሩ” የሚሉ ጥቅል ስሞችን ይሰጧቸዋል። ነገር ግን እስካሁን ለእነዚህ ጥቃቶች በይፋ ወጥቶ ኃላፊነት የወሰደም ሆነ አላማውን የገለጸ አካል የለም።

ተደጋጋሚ ጥቃት በሚያጋጥመው በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ ተወልዶ ያደገው አሁንም እዚያው የሚኖረው አቶ አበበ (ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) በአካባቢው ከሌላ ቦታ መጥቶ ጥቃቱን የሚፈጽም “አማጺ የሚባል ቡድን የለም” ይላል።

ጨምሮም “አብረውን የሚኖሩ ፖሊሶች፣ ታጣቂዎችና የጥበቃ ሠራተኞች ናቸው ይህንን ጉዳት የሚያደርሱት” የሚለው አቶ አበበ በቅርቡ አንዝባ ጉና በሚበላው ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት እንደማሳያ ያነሳዋል።

“በወቅቱ ጥቃቱን አድርሰው ከተያዙት ሰዎች መካከል አንዱ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ሆኖ ተገኝቷል። ራሱም አምስት ሰዎች መግደሉንም አምኗል” በማለት የአካባቢው አመራር የግጭቱ ተሳታፊ መሆኑን ያስረዳል።

ባለፈው ሳምንት የአካባቢውን ጸጥታ ለመጠበቅ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ያለፉት አራት ወራት ሥራውን በገመገመበት ጊዜ በመተከል ዞን ለተከሰተው ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ 284 ታጣቂዎች መደምሰሳቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በአካባቢው በተከታታይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 66 በተለያየ አመራር ደረጃ ላይ በነበሩ ኃላፊዎች ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰዱ ተነግሯል።

አማጺ ቡድን የሚባል የለም የሚለው አቶ አበበ ግን “ኮማንድ ፖስቱ ራሱ የችግሩ አካል ነው” ይላል። በማስረጃነት የሚያቀርበው ደግሞ ጉብላክ ከተባለው ቦታ ላይ የተከሰተውን ጥቃት ነው።

መንገዱ ሽፍቶች እንዳሉና አስተማማኝ ስላልሆነ ወደዚያ እንደማይሄድ አሽከርካሪው ፈቃደኛ እንዳልነበረና የኮማንድ ፖስቱ አባላት በአጀብ እንደሚሸኟቸውና የተወሰነ መንገድ አብረዋቸው እንደተጓዙ አበበ ይናገራል።

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

“ነገር ግን በፓትሮል ሸኝተዋቸው የሆነ ቦታ ተመለሱ፤ እነሱ ከተመለሱበት ቦታ 300 ሜትር አለፍ ብሎ ደግሞ መኪናው በሽፍቶች እንዲቆም ተደርጎ በተሳፋሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል” ይላል።

ባለፈው ወደ ቻግኒ ሲጓዝ ጥቃት የደረሰበት ተሽከርካሪም ሹፌሩ አልሄድም ቢልም “አንተ ራስህ ችግር ፈጣሪ ነህ ተብሎ በወረዳው ፖሊስ ተገዶ ነው የሄደው” በማለትም ያክላል።

የአካባቢው አመራር ውስጥ ያሉና ሌሎች ሰዎች በነዋሪው መካከል ጥርጣሬና ስጋት የሚፈጥሩ ወሬዎችን በሚያሰራጩበት ወቅት ጥቃቶች እንደሚፈጸሙና እንደሚባባሱ አቶ አበበ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ክስተቶችን በማስታወስ ይናገራሉ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ በመተከል ዞን እየተፈጸሙ ካሉ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በአካባቢው ያሉ የመስዳደር አካላት ላይ ከነዋሪዎች የተሰነዘረውን ክስ በተመለከተ ቢቢሲ ምላሽ ለማግኘት አቶ መለሰ በየነ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊን ጠይቆ ነበር።

ኃላፊው በሰጡት ምላሽ “ማንኛውም አመራር በዚህ ቀውስ ውስጥ ተሳትፎ ካለው ጥያቄ የሚያነሱት ነዋሪዎች መረጃ ሰጥተውን እርምጃ እንወስዳለን። እስካሁንም እየወሰድን ነው” በማለት፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአመራርና በጸጥታ አካላት ላይ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት ፖለቲካዊ ርምጃና ለሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

በአንጻሩ ኮማንድ ፖስቱ ችግሩ ሲፈጠር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ያላቸውን 67 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፖሊስ አባላትን መያዙን አስታውቋል።

መስመር

በአካባቢው በሚፈጸሙ ጥቃቶች በሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ከመድረሱ ባሻገር በሺዎች የሚቆጠሩት ለመፈናቀል ተዳርገዋል። በዚህም በመተከል ዞን ቢያንስ 22 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የኮማንድ ፖስቱ ባለፈው ሳምንት ባደረገው ግምገማ ላይ ተገልጿል።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ መለሰ በየነ እንዳረረጋገጡት በርካታ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ “እነዚህን ተፈናቃዮች በክልሉ አደጋ መከላከልና በሰላም ሚንስትር አማካኝነት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው” በማለት በቀጣይም ወደቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳን ጠቅሶ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው በመተከል ዞን “ከጥፋት ቡድኑ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ማለታቸውን ተዘግቧል።

አቶ ጌታሁን ጨምረውም በዞኑ በተደጋጋሚ ከሚከሰቱ ጥቃቶች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት አላቸው በተባሉ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና የተለያዩ ግለሰቦች ላይ ፓለቲካዊና ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን መናገራቸውን ገልጿል።

ይህ ክስተት ያሳሰበው የቤኒሻንጉል ክልልን ብቻ ሳይሆን በተፈጸሙ ጥቃቶች ኢላማ ተደርገዋል ባላቸው የክልሉ ተወላጆች ሳቢያ የአማራ ክልልም የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥቃቶቹን ለማስቆምና የዜጎችን ደኅንንት እንዲያስጠብቁ ሲጠይቅ ቆይቷል።

በቅርቡ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ባወጧቸው መግለጫዎች ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የመተከል ዞን ውስጥ በታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ወራትን አስቆጥሮ፤ አሁንም ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰነውና በሰባት ወረዳዎች በተዋቀረው የመተከል ዞን የተለያዩ ብሔረሰቦች ይኖራሉ። በዋናነት የጉሙዝ፣ የሽናሻ፣ የአማራ፣ የአገው፣ የኦሮሞና የበርታ ብሔሮች ይገኙበታል።

በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማንነትን የለየና በተወሰኑት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ቢቢሲ ያናጋረቸው ነዋሪዎችና ከዚህ በፊት የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *