የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር እስክንድር ነጋን ጨምሮ አምስት ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ተከሳሾቹ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ በተከሰተው ግርግር እጃቸው አለበት በመባሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በዚህ የክስ መዝገብ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም፣ አስካለ ደምሴና በዋስትና የተለቀቁት ጌትነት በቀለ ይገኙበታል። ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ሲካሔድ የነበረውን ምርመራ ሲከታተል የቆየ ሲሆን የአቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ለመጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ዛሬ እንዳስታወቀው የቀጠሮውን ቀን በማሳጠር ተከሳሾቹ ለዛሬ ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲቀርቡ ያደረገው ችሎቱ በሶስት ቦታ ተከፋፍሎ እንዲሰራና የነበረበት ጫና እንዲቀንስ በመደረጉ ነው
ፍርድ ቤቱ የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጾ የመጀመሪያውን የአቃቤ ሕግ ምስክር ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም መስማት እንደሚጀምር አሳውቋል።
ተከሳሾቹ በበኩላቸው ‘በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ እንድንችል አሁንም ምስክር ለመስማት የተያዘው የቀጠሮ ቀን ሊያጥር ይገባል’ ሲሉ ጠይቀዋል። ጉዳዩን የያዘው አቃቤ ሕግም ከምርጫ ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ነገር የለም፤ ፍርድ ቤቱ ለሶስት ወር ቀጥሮት የነበረውን ጉዳይ ሰብሮ በአንድ ወር ለማየት መወሰኑ መልካም ነው ሲል መከራከሩን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *