አሁን ከሞቱትና ምስላቸው ልብን በሚነካ መልኩ ከሚሰራጨው  መካከል የአንደኛው ባለስልጣን  ልጅ ማታ ቲቪ ዜና ላይ ፖሊስ ሲደባደብ፣ ሲያባርርና ሲያሳድድ ድንገት ያሳያል። ዜናው የቀረበው ፖሊስ ህግን አስከብሯል በሚል ነበር።  ልጅ ግን ” ዴሞክራሲ ነው እያልቹህ ለምን እንደዚ ይሆናል ባባ” ብላ ሲቪክ ላይ የሚማሩትን አንስታ እንደሞገተችው ከዛሬ በግምት አስራ አምስት ዓመት በፊት አንድ ትልቅ የተከበሩ ሰው አጫውተውኝ ነበር።
የአገራችን ፖለቲካ እውቀቱ በጅምላ ፈርጅ በመሆኑ ከዛን ቀን ጀምሮ ወላጅንና ልጆችን ለይቶ ማየት እንደሚገባ አስባለሁ። እንደውም ለማንኛውም አስዛኝ ጉዳይ ወይም ሃሳብን ለመግለጽ የህጻናትን ምስል መጠቀም በህግ መገደብ ይኖርበታል ስል አምናለሁ። ህጉ ካለም ለምን ተግባራዊ አይደረግም ስል እጠይቃለሁ። ቤተሰብ አጠፋ ሲባል ልጆችን ሬክላም ማድረግ ልዩ መብት እስከመሆን ደርሷል። በዚህ ጉዳይ የሚከራከር ካለ መረጃም ማስረጃም አለ።
ይህንን ያነሳሁት አቶ ስዩምና አባይ ጸሃዬ ሌላውም ጭምር ጉድባ ውስጥ ሞተው የሚያሳይ ምስል በግል ተልኮልኝ በማየቴ የተነሳ ነው። የተላኩልኝ ምስሎች ፌስ ቡክ ላይ የተለጠፉ ናቸው። እናም የፌስ ቡክ ሰራዊት ይህንኑ ምስል እየተቀባበለ፣ የመሰለውን እየጻፈ አሻምቷል። ገና በድንብ ይራባል። እንደ ስጦታ የሳምንቱ ፍጻሜ ማብሰሪያ ይሆናል።
ፎቶዎቹን ለአፍታ ካየሁና ለአንድ ወዳጄ ከላኩኝ በሁዋላ ግን አመመኝ። የነዚህ ሰዎች ልጆች ይህን ምስል እንደሚያዩ ወዲያ አሰብኩና እነሱን ሆኜ ነገሩን ለካሁት። ስሜቱ እንዴት እንደሚከብድ ለመገመት አልተቸገርኩም። እንደ አባት ልጄን ባይነ ህሊናዬ ሳልኩት። ከባድ ሆነብኝ። ያለምንም ማጋነን ክፉኛ አዘንኩ።
መቼም ከሳይበር ሜዳ ላይ የማይጠፋ፣ የማይፋቅ፣ የጸጸት ማህደር መሆኑንን ስገነዘብ የሰዎቹ ቤተሰቦች ልቡና እንዴት ዕለት ዕለት እንዴት እንደሚጎዳ ለመረዳት ብዙ ምርምር አይጠይቅምና የሰው ልጅ ከ”ሰበር” ዜና በታች ሆኖ ማየቴ አሳዘነኝ።  አንዷ ይህንን ምስል የምታየው ልጅ ዛሬ ምን አልባት 25 ዓመት የሚሞላት ከላይ በመግቢያ ያነሳሁዋት ልጅ ናትና ቀሪ ህይወቷ እንዴት እንደሚጎዳ አሰላሁት።
እርግጥ ነው እጅግ በርካታ ጥፋት ተፈጽሟል። ከሁሉም በላይ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ግፍ እንዲህ እንደ አዛዦቹ ማየት አልተቻለም እንጂ ልብ የሚሰብር ነው። የደረሰባቸው፣ ያዩ፣ የነበሩና የተረፉ ግፉን ሲተርኩት ያንገፈግፋል። ሲኖ ትራክ የጭነት መኪና የሰው ልጅ ላይ እንደተነዳ መስማት ህሊናን ይፈታተናል። አስከሬን ላይ ሳይቀር የተፈጸመው አውሪያዊ ተግባር በምንም መልኩ ገድል አይባልምና  ይህን በፈጸሙት ላይ ቁጣ እንዲነድ ጠይቀናል። እዚህ ላይ የሚሰመርበት ጉዳይ ቢኖር እነዚህ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው እድሚያቸውን ያሳለፉ ጀግኖች  ም ልጆች አሉዋቸው።
በማይክድራ የሆነው ለማመን የሚከብድ ትርጉም የለሽ እብሪት ነው። የጭካኔ ማሳያ የመጨረሻ ምሳሌ ነው። ይህንን ሁሉ በግል አውግዣለሁ። ተቃውሜ ግዜ ሰጥቼ ሃሳቤን ገልጫለሁ። ይህ ከመሆኑ በፊትም ከግል ኑሮዬ ላይ ጊዜ ወስጄ አገር ተረጋግታ እንድትቀጥል የበኩሌን በጀት ተፈቅዶልኝ ሳይሆን ከራሴ መድቤ ጥረት አድርጌያለሁ። ልጄን ከማጫውትበት የተጣበበ ሰዓት ሰርቄ ያመንኩበትን ለዓመታት ስሰራ ቆይቻለሁ። ትህነግ ባለጌና አገር ለመምራት የማይችል ድርጅት እንደሆነ የገባኝ ቀደም ሲል በመሆኑ ታግየዋለሁ። ዋጋም ከፍያለሁ። እንዲወገዱ በምኞት ሳይሆን በተግባር ሰርቻለሁ።
ይህን ሁሉ ባደርጋና ስለ ሰዎቹ ብዙ መረጃ ብሰበስብም ዛሬ የሚሰራጩት ምስሎች ማየት ግን ደስታ ሊሰጠኝ አልቻለም። የስብሃት ነጋን ምስል ሳየው እርጅናውና ጉስቁልናው በመያዙ የተሰማኝን ደስታ አጎደለብኝ። የስዩምና የአባይ እንዲሁም ሌላው አንድ ላይ አስከሬናቸውን ባየሁ በቅጽበት ውስጥ ስሜቴ ተተራመሰብኝ። ይህንን ምስል ማሰራጨቱስ “ለምን አስፈለገ?” ስል ጠየኩ።
ተማሩ የሚባሉት የአገራችን ፖለቲከኞች መነጋገር አለመቻላቸው፣ ከመነጋገር ይልቅ ሴራ ላይ የተካኑና በሴራ የመጠቁ መሆናቸው እንደ አለመታደል ግማሽ ክፍለ ዘመን በመተላለቅ አሳልፈናል። ወደፊትም የሚቆም አይመስልም። የደም ስር ቁማርተኞች የእስካሁኑ ደም አልበቃ ብሏቸው አዲስ አጀንዳ እየቀረጹ ነው።
የዛሬ ትውልድ ከፊሉ የሴራ ፖለቲካ ከድጎማና ከበቂ የጥላቻ መርዝ ጋር እየተጋተ በማደጉ እንኳን ሊያዝን ሰቅሎ በድንጋይ እየወገረ ዚዲዮ የሚቀረጽ፣መግደል በቂ ስላልሆነ ገሎ ሆድ መተርተርን እንደ መዝናኛ የሚያይ፣ ነበሰ ጡርን የሚተረትር፣ ህጻናትን አስቀምጦ ፊትለፊት እያሳየ የሚያርድ፣ የወገኑንን ሃብት ዝም ብሎ የሚያወድም፣ በሄደበት ደም እየጠጣ የሚጨፍር፣ ዜጎችን በማፈናቀል የሚረካ፣ ክፋትና ስቃይ ልዩ ደስታ የሚሰጠው ሆኗል።
በእነዚህና ከላይ ባነሳሁዋቸው ጥቂት ማሳያዎች ብቻ ትውልድ ያገሸቡ የክፋት አለቆች ሊቀጡ ይገባል። እዚህ ላይ ጥያቄ የለም። ግና ከተቀጡ በሁዋላ ምስላቸውን ማራባቱ በግል አልስደሰተኝምና ሃሳቤን ልሰንዝር ብዬ ይህን ጽፌያለሁ። ቀሪውን ጊዜ ሰላም ያድርግልን እንጂ ቀጣዩ ፍትጊያ ” ኦሮሞ አማራን ሊያጠፋ ፐሮጀክት ነድፎ በቤኒሻንጉል በኩል ስራውን ጀምሯል” የሚል ታርጋ ተለጥፎ የተማረውም፣ ያልተማረውም ነዳጅ እየረጨ ነው። በተደጋጋሚ እንደተሞከረው ምስኪኑንን አማራ ከምስኪኑ ኦሮሞ ለማባላት ሩጫው ተጧጡፏል። ኦሮምውም ሆነ አማራው የተረጨበትን የክፋት ነዳጅ መጠን አልተቀጣጠለም።
በመቶ የሚቆጠር ሚዲያ፣ ማህበራዊ አውድ፣ በእልፍ ካድሬዎችና ቅልብ ኤጀንቶች አማካይነት ይህን ሕዝብ ለማጨፋጨፍ በድፍረት ካራ የሚስሉትን ” ዘወር በሉ” ከማለት ይልቅ ሌላ የሚበጅ ነገር ያለ አይመስለኝም። ዛሬ አገራችን ተወጥራ ባለችበት ወቅት አልነቃንም። ገና ምርጫ ሳይጀመር ምርጫውን በሃይማኖት ስም ለማተራመስ እቅድ እየተነደፈ ነው። ብቻ አምላክ ቀልብ እንዲሰጠን ከመለመን ሌላ የመለው የለም!!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *