ኢትዮጵያዊ ስትሆን በፈተና አትደናጋጥም። በድል አትኩራራም። ለፍቅር ፣ ለተግባቦት ፣ ለአብሮነት እና ሠላም ቅድሚያ ትሰጣላህ። ሠላምን አጥብቀህ ትፈልጋለህ ሲባል ጦርነትን ትፈራለህ ማለት አለመሆኑን በተግባርህ ማሳየት ደግሞ ከአበው የወረስከውና ፈልገህ የሆንከው ሳይሆን በቃ ማንነትህ ነው።
እየጠሉ ለ27 ዓመታት የመሯት ሀገር ዜጎች ቆዳ ላይ ፣ ሲጋራ እየተረኮሱ በቃጠሎው ይዝነኑ ነበር። በውሃ መጠጫ ላስቲክ ከነውሃው ብልት ላይ ሲያንጠለጥሉ ፤ የሴት ማህፀን ውስጥ ባዕድ ነገር እየጨመሩ ሲያመክኑ ከሌላ ኘላኔት የመጡ ከፋሽስት ጣሊያን የበለጡ ጨካኝ በመሆናቸው እፍረት ሳይሆን ኩራት ይሰማቸው ነበር።
ጭካኔ መስፈርት ኖሮት የሚያሸልም ቢሆን ኖሮ ፣ እነዚህ ግፈኞች የአንደኝነት ሜዳሊያን ይቀናጁ ነበር። አትከፋፍሉን ፣ ፍትህ ይስፈን ፣ የዚች ጥቁር አፈር ዜጎች እስከሆንን ድረስ እኩልነታችን ይረጋገጥ ፤ ያሉ ወገኖች የተለያየ ስያሜ ባላቸው የገመድ አስተሳሰር ዘዴዎች ቃላት መግለፅ ከሚቻለው በላይ ተሰቃይተዋል ።
ሲጋራ ገመድና የታሸገ ውሀ መያዣ በጨለማው ዘመን ለተሰቃዩ ኢትዮጵያዊያን የተለየ የሚያም ትውስታ አላቸው። ለእነሱ ብቻ አይደለም ። በጨለማ በገዛ ወገናቸው ክህደት የተፈፀመባቸው የሰሜን ዕዝ አባላትም ቁስላቸውና ህመማቸው ተመሣሣይ ነው።
ጀግናን የሚያፈራው የሴት ልጅ ማህፀን ውስጥ ባዕድ ነገር የጨመሩ ፤ እጅ እግራቸው በገመድ ታስሮ የተረሸኑ እና በድናቸው የአሞራ ሲሳይ የሆነው ፣ አስክሬናቸው ላይ ነዳጅ ተርከፍክፎ የተቃጠሉ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ግን አይን ላጠፋ አይን አላሉም ፡፡
ፍቅር የገመዳቸው ፣ ህብር ያስዋባቸውና ህብር ያከበራቸው ጓዶቻቸው ላይ ይሄንን ግፍ የፈፀሙ የዘመን ነቃርሳዎች እጃቸው ላይ ሲወድቁ ምላሻቸው የተለየ ነበር።
እነሱ ወላጆችን በልጆቻቸው ፊት አሰቃይተዋል። ለልጅ የአባት አስከሬን እያሳዩ አልችል ብሎ ሲያለቅስ በሰደፍ መጥተው ከአፈር ደባልቀዋል።
እኛ ከእነሱ ጋር ሲንከራተቱ የተያዙ ልጆቻቸውን በአግባቡ ይዘን ወደሚያርፉበት ቦታ እንዲሸኙ ፣ የተጠሙት እንዲጠጡ ፣ የተራቡት እንዲመገቡ ፣ የደከሙት እንዲያርፉ አድርገናል። ምክንያቱም ፈሪሃ እግዝአብሔር ያለው ትልቅ የስነምግባር ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች ነንና ፡፡
ገመድ ፣ ሲጋራና የታሸገ ውሀ መያዣ ላስቲክ አጠቃቀሙ በኛ እና በእነሱ በእጅጉ የተለያየ ነው። የትልቋ ኢትዮጵያ ትንሹ ማሳያ የሆነው የኢፌዴሪ መከላካያ ሠራዊታችን ገመድን የተጠቀመው ፣ ቁንጮ አመራሮችን ከየተደበቁበት ሸለቆ እየጎተተ ለማውጣት ነው ፡፡
የሴራው ጠንሳሽ ፣ አበልፃጊና አስፈፃሚ ለሆኑት የታሸገ ውሀ ገዝቶ በመስጠት ከጥም ስቃይ ገላገላቸው። ይባስ ብሎ ሲጋራ ገዝቶ የሱስ ጥያቄያቸውን መለሰላቸው።
ከክብር ማማ ወርደህ ፤ የገነባኸውን እውነት የሚመስል ስብዕና ንደህ ፤ ከበረሃ ለብሰህ የወጣኸውን ሸበጥ ዳግም ለብሰህ እንደ ቀድሞው ከበሮ እየደለክ ፣ ኮሎኔል ማራኪን እየዘፈንክ ሳይሆን ፣ ፍርሃትህ የፈጠረውን የልብ ምትህን እያደመጥክ ፤ እጅህ በሰንሰለት ታስሮ ወደ መዲናዋ ፍትህ የምትመለሰው ኢትዮጵያዊ ማንነትህ ሲሸረሸር ፤ ዘርፈህና ገፈህ ብዙ ያለህ ቢመስልህም ስብዕና ተራቁቶ ባዶህን ስትቀር ነው።
ኢትዮጵያዊም ሆነ ባዕድ በዚች ሀገር ላይ ግፍ ሠርቶ ቆይቶ የማያፍር ፣ አንገቱን የማያቀረቅር እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው። የሚገርመው እና የሚያሳዝነው ጠላቶቿ ሁሌም ከታሪክ አይማሩም።
እኔ ግን እላለሁ ። የዚች የሰው ዘር መገኛ ፣ የጥቁሮች የነፃነት ተምሳሌት ፣ የራስ ፊደል ቋንቋ ባለቤት ፣ የቀደምት ስልጣኔና ባለታሪክ ፣ የተፈጥሮ ፀጋን አብዝቶ የቸራት ምድር ፣ ፍቅር የገመደው – ህብር ያደመቀው እንዲሁም ጠንካራ አንድነቱ ያከበረው የሀገር እና የህዝብ ወታደር አመራርም ሆነ አባል መሆን ያኮራል።
አቶ ስዩም ፣ አቶ አስመላሽ እና አቶ አባይ ፀሐይ የእጅ ስጡና በፍትህ አደባባይ ተዳኙ ጥያቄን አሻፈረኝ ብለው ባስከተሏቸው ጀሌዎች የማያሸንፉትን ጦርነት መርጠዋል ፡፡ በምርጫቸውም ወድቀዋል ፡፡ ውጤቱም ያየነውንና የሰማነውን ዓይነት ሆኗል።
ያ “ለሐጥዓን ምህረት ማድረግ የፈጣሪ ፋንታ ነው። የኛ ድርሻ እነሱን ወደ ፈጣሪ መላክ ነው።” ያለው ማን ነበር?
በአጠቃላይ ከዚህ ህዝብ በመወለድህ ፣ ጠላት ላንተ ባዘጋጀው ካራ የታሰረበትን ገመድ ትቆርጥበታለህ። በሲጋራው ፍም ሰውነትህን ቢጠብስም አንተ ሱሱን እንዲያስታግስበት ገዥተህ ትሰጠዋለህ ፡፡
ብልትህ ላይ ያንጠለጠለውን ኮዳ ውሀ ሞልተህ ታጠጣዋለህ ፡፡ ሁሉንም ለነፈገህ ያለህን ሁሉ በፍቅር ትለግሳለህ።
ጀግና እንጂ ጨካኝ አትሆንም። ትታገሳለህ እንጂ አትፈራም። ጠላት በአሳነህ ቁጥር ትገዝፋለህ። በነካህ ቁጥር ድል አድርገህ ለአንዴ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚተርፍ ትምህርት ትሰጠዋለህ። ለዚህ ደግሞ በኛና በጁንታው የነበረው የገመድ ፣ ሲጋራና የታሸገ ውሃ አጠቃቀም ሁነኛ ማሳያ ነው።
ከአገር መከላከያ ሰራዊት ፌስ ቡክ የተወሰደ
ሻምበል ፈይሳ ናኔቻ
ምስል Google image

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *