ክፍለዮሐንስ አንበርብር

ባህር ዳር፦ ምርጫ፤ ብሄራዊ ምክክር እና የዜጎች ደህንነት ማስጠበቅ ቀጣይ የመንግስት ዋነኛ ትኩረቶች ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ። “የተረጋጋች አገር በመፍጠር ማጽናት የሚቻለው የአንደኛው መብት ለሌላኛው ሸክም ሳይሆን የጋራ ስሜት አቃፊ ሆኖ ሲቀረጽ እንደሆነም ተገለጸ።

‹‹የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓትና ዴሞክራሲ ለህዝቦች መተሳሰብና አብሮነት›› በሚል መሪ ኃሳብ በባህር ዳር ከተማ ትናንት በተጀመረው ብሄራዊ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡትና በምስራቅ አፍሪካ የደህንነት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሳሚር ዩሱፍ እንዳሉት፣ ምርጫ፤ ብሄራዊ ምክክር እና የዜጎች ደህንነት ማስጠበቅ ቀጣይ የመንግስት ዋንኛ ትኩረቶች ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ቅቡልነት ያለው መንግስት ለመመስረትና ዘለቄታዊ ሥርዓት ለማስፈን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤት ሥራ እንዳለበት ያመለከቱት ዶክተር ሳሚር፣ የብሄር ክፍፍልና የተወሳሰበ ፖለቲካ የወቅቱ የአገሪቱ ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል።

ትኩረት ሰጥቶ የጋራ የሆኑና የሚያቀራርቡ ሃሳቦች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመልክተው፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተወሳሰበ ፖለቲካ መኖሩ እና ዴሞክራሲን በሚገባው ልክ ያለመለማመድ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

በአገሪቱ ሚዛነን የጠበቀ ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎች አለመኖርና የህዝብን ስሜት በሚገባ ማስተጋባትና ማሰማት አለመቻል፣ በመንግስት ላይ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንግድ ጫና ለመፍጠር አለመሞከር፣ ጠንካራ ሲቪክ ማህበራት አለመደራጀት፣ የአገራትን ነባራዊ ሁኔታ አለመረዳት ለአገራት አደጋ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ አውድ ላይ በሚገባ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ሌላኛው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በበኩላቸው፤ መድረኩ ከጎጥ፣ ክልልና አገር ያለፈ መሆኑን ጠቁመው፣ ቀጣናዊ እይታን ከግንዛቤ ያስገባና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ያልተረጋጋች ከሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ካለመረጋጋት ጋር ተነጥሎ አይታይም ያሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ ዴሞክራሲዊ ምርጫ ማካሄድ፣ የዜጎችን ደህንነት በሚገባ መጠበቅ ብሎም ጠንካራ አገር ፣ መንግስት ማስቀጠል ለሌሎቹ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ዋነኛ መሠረት እና እንደ አብነት የሚጠቀስ መሆኑንም መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ፋንታሁን ዋቄ ፤ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ፣ ብሄራዊ ምክክር ፍሬ እንዲያፈራ እና የዜጎች ደህንነት በሚገባ ትኩረት እንዲሰጠው ሀገር በቀል ፍትህና ዳኝነት ሥርዓቶች ብሎም ሃይማኖታዊ እሴቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መጠቀም እንደሚገባ አብራተዋል።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

ይሁንና በርካታ ምሳሌዎች ማጣቀሻቸው ሀገራዊ እሴት፣ እምነትና ባህል ሳይሆን ምዕራባውያን ፍልስፍና ላይ ብቻ ማተኮር ፋይዳ የለውም ያሉት አቶ ፋንታሁን ፣ ቀጣዩን ምርጫ ስኬታማ ለማድረግ፣ ብሄራዊ ምክክርና የዜጎች ደህንነት ለመጠበቅ ሁሉንም አማራጮች መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከአማራ ወጣቶች ማህበር የመጣው አያሌው ከቤ በበኩሉ ፣ የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል በጥሩ መደላድል እንዲወድቅ ከተፈለገ ሲቪክ ማህበራት በአደራጃጀት ሆነ በተግባር የተጠናከረ መሆን አለበት። እስካሁን በነበረው አሰራር ሲቪክ ማህበራት እንዲኖሩም እንዲጠፉም አይፈለጉም ነበር ብሏል።

ከሁሉም ፍላጎትና ማንነት በላይ ያለችው ኢትዮጵያ ናት ወጣት አያሌው፤ ለፍላጎትና ስሜት ምላሽ የሚገኘው ሀገር ሲኖር መሆኑን ማወቅ ይገባል። በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫም ለሚመጡት ምርጫዎች መሰረት የሚጥልና ለዴሞክራሲ ልምምድም እንዲኖረን የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንዲያገለግል ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክቷል። በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን ለመፍታትም ልበ ሰፊነትና የአስተሳሰብ ቀናነት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

“የተረጋጋች አገር በመፍጠር ማፅናት የሚቻለው የአንደኛው መብት ለሌላኛው ሸክም ሳይሆን የጋራ ስሜት አቃፊ ሆኖ ሲቀረጽ ነው። የአንዱ ፓርቲ ምልክት እና ዓርማ ለሌላው ህመም መሆን አይገባም። የአንዱ ስኬት ለሌላኛው እንደ ውድቀት መታየት የለበትም። መንግስት ብቻ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲመጣም መጠበቅ የአንዳንድ ፓርቲዎች፣ ማህበረሰብ አንቂዎችና ምሁራን ትልቁ ችግር ነው” ብሏል።

የሚቃረኑ እንጂ የሚዛመዱ ሃሳቦችን ማንሳት የፖለቲካ ውድቀት ተደርጎም እየተወሰደ ነው። ሃሳቦችም ፉክክራቸው ለዜጎችና አገር በሚጠቅም መንገድ እንጂ የግለሰቦችን አሊያም የጥቂት ቡድኖችን ልዕልና ለመገንባት የታሰበ መሆን እንደሌለበትም አመልክቷል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው ።

አዲስ ዘመን ጥር 08/2013

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *