ሁላችንም እንደምናስታውሰው የዛሬን አያድርገውና ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም ከሀገሪቱ ትልቅ የፖለቲካ ተቋማት አንዱን ፣ ማለትም የፌዴሬሽን ም/ቤትን ትመራ ነበር። የህወሃት ሰዎች ስልጣንሽን ለቀሽ ነይ ሲሉ ባዘዟት መሰረት የም/ቤቱን ስብሰባ ጠርታ ስታበቃ ልዑካኑ ወደ ሸገር ሲከትሙ እርሷ ወደ መቀሌ እብስ ብላለች። ህወሃት ኬርያ እግሯ መቀሌን ከመርገጡ ያዘጋጃቸውን አለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ተጠቅሞ ፕሮፖጋንዳውን ያቀልጠዋል ፣ ትልቅ ባለስልጣን ስልጣን ለቀቁ ሲሉ እነ አልጀዚራም ፣ ቢቢሲም ሮይተርስም ዘገቡ። ፈረንጅ እንዲህ አይነተን ሁነት 15 minutes fame ይለዋል።
የኬርያን ነገር ያስታወሰኝ አቶ ተቀዳ ተባባል የሚሰኙ የብልጽግና ፓርቲ አመራር ” ከሽመልስ አብዲሳ እና ታዬ ደንዳኣ ጋር ከምሰራ እንጨት ፈልጬ እኖራለሁ ” ሲሉ ስልጣን ለቀቁ ብለው አድናቂዎቻቸው ጭብጨባ ሲግቷቸው አንብቤ ነው። ችግሩ የእርሳቸውን ጉዳይ ገና አልጀዚራና ሮይተርስ ጆሮ አልደረሰም እነ ተቦርነ በየነ ብቻ ናቸው እስካሁን ያጀገኗቸው።
የኬርያም ይሁን አቶ ተቀዳ ስልጣን መልቀቅ ብዙ የሚያመሳስለው ጉዳይ አለ። ሁለቱም ህሊናቸው መርቷቸው ሳይሆን አድርጉ ተብለው ፣ የሆነን ወገን ለማስደሰት እግረ መንገድም ለመጀገን ያደረጉት ይመስለኛል ። ለዚህ ክርክሬ ዋንኛ መነሻ ይዘውት የነበረው የፒለቲካ ሀላፊነት የሚፈልጉትን ለውጥ ለማምጣት ብርቱ መሳሪያ instrument መሆኑ ነው። እርሱኑ ጠበቅ አድርጎ መታገል እንጂ ኩርፊያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ኩሊ ነው የሚያደርግህ። ከላይ እንዳልነው ለኬርያ ኢብራሂም ሁነኛ ተጽዕኖ መፍጠሪያ ቦታ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንጂ የትግራይ ሚዲያዎች አልነበሩም። ያ ከያዙት ስልጣን የሚመነጨው ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም መቀሌ ሴትዮዋ ሲገቡ አብሮ ሞቷል። አቶ ተቀዳም ነበረኝ ያሉትን ስልጣን ተጠቅመው ያልወደዷቸውን የፓርቲው ሀሳቦች ውስጥ ሆነው መታገል ይበጃቸው ነበር ፣ ያንን የለቀቁ ቀን ወደ አክቲቭዝሙ መንደር ነው የሚመጡት እርሱ ደግሞ በእነማን እንደተጨናነቀ የምናውቀው ነው።
ሁለተኛው የኬርያና አቶ ተቀባ መመሳሰል ‘ ዲዳነታቸው ‘ ነው። ሁለቱም ስልጣን ላይ ሳሉ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያውን ተጠቅመው ሀሳቦቻቸውን ለህዝብ ማቅረብ ሲችሉ በዝምታ ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲያበቁ እንጀግን የሚሉት ስልጣን ሊለቁ አስራ አንደኛው ሰአት ላይ ነው። የታዬ ደንደኣ ሀሳብ የጎረበጠው ተቀዳ በፌስቡክ ይሁን መደበኛ ሚዲያዎች ሀሳቡን ለማስተላለፍ ማን ቀፍድዶ ያዘው ? ያንን ወርቃማ ዕድል ሳትጠቀምበት ቀርተህ ስልጣንህን ካለቀቀክ በኃላ አንድ ሁለት የዩቱይብ ሚዲያዎች ላይ ተፍ ተፍ ብትል ነገርየው ከአንድ ሳምንት አጀብ አያልፍም ተጽዕኖ የመፍጠር አቅምም አብሮ ይሞታል።
ለማንኛውም አቶ ተቀባ ተባባል የሚባሉ ባለስልጣን ስልጣን ዕምቢዮ አሉ ተብለው ስማቸው ሲጀግን ፌቡ ላይ አንብበን ከላይ ያለውን ጥፈናል። ሰውየውም ኬርያ ኢብራሂምም ስልጣንን ተጠቅሞ የመታገል ስልትን አላወቁበትም ፣ ከኃላ ለሚሾፍሯቸው ሀይሎች ታዛዥነታቸውን ለማሳየት ብቻ ነው ከመርከቧ የዘለሉት ባይ ነኝ። አቶ ተቀባ ከታዬ ደንዳኣ ጋር ከምሰራ እንጨት እየፈለጥኩ ብኖር እመርጣለሁ ብለዋል ተብሏል ፣ የምትቀርቧቸው የእንጦጦን ደን መፍለጥ ውስጥ እንዳይገቡ ምከሯቸው – እርሱ ቦታ በሪፓብሊካን ምናምን ይጠበቃል ሲሉ ሰምቻለሁ !
Samson Michailovich ፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የባይደን አስተዳደር ፖሊሲ አምስተኛው ምሰሶ የኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የሚቀመጠዉን ቡድን መወሰንና የ 2021 ምርጫን ማዋደቅ (1ኛ ክፍል 2)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *