ዘላለም ግዛው

አዲስ አበባ፦ ሱዳን የድንበር ውዝግቡን አስመልክቶ እየሄደችበት ያለው የተሳሳተ መንገድ በአባይና በሌላም ምክንያት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚፈልጉ አገራት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተገኝ ገብረእግዚአብሄር አስታወቁ

ፕሮፌሰር ተገኝ በወቅታዊው የኢትዮ-ሱዳን የድንበር አለመግባባት ዙሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፣ ሱዳን የድንበር ውዝግቡን አስመልክቶ እየሄደችበት ያለው መንገድ በአባይና በሌላም ምክንያት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚፈልጉ አገራት ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል። አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ የወሰዱት ይመስላል።

Related stories   “በአጣዬ እና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ኮማንድ ፖስቱ

አንዳንድ አገራት ኢትዮጵያ ከተበታተነች የህዳሴ ግድቡ ሊቆም ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፣ አላማቸውን ለማሳካትም ሀገሪቱ አለመረጋጋት ውስጥ የምትሆንበትን ጊዜ እንደሚመርጡ ገልጸዋል። አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታም እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወስደው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው ድርጊታቸው በግልጽ ያሳያል ብለዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ሰሜኑ አካባቢ ያለውን የጸጥታ አለመረጋጋት እንደምቹ ሁኔታና ጊዜ የተመለከቱት ይመስለኛል ያሉት ፕሮፌሰር ተገኝ፣ የድንበር ችግሩ ለረጅም ጊዜ በእዚህ ደረጃ ሳይነሳ ቀርቶ አሁን በተለየ መልኩ መነሳቱና ችግሩን ባልተገባ መልኩ ለመፍታት መሞከሩ ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

የህዳሴ ግድቡ ላይ ሱዳን ብዙ ጊዜ የሚያወላውል አቋም እንዳሳየች ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ ፤ አሁንም በግድቡ ላይ ያላትን አቋም በግልጽ ለይቶ ማወቅ እንደሚያስቸግር አመልክተዋል። ግብጾች ግን ግድቡ እንዳይሰራ፣ ግንባታው እንዲቆም፣ የግድቡ ግንባታ እንዲሰናከልና ግድቡ ውሃ እንዳይሞላ ብዙ ጥረት ማድረጋቸውንና ይሄንኑም በግልጽም መናገራቸውን አስታውሰዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *